- Последний пост
- 6 июн.
- Последнее чтение
- 14 авг.
- Постов за неделю
- 0
- Всего постов
- 22
- Тип
- открытый
- Язык
- und
- В каталоге с
- 14 авг.
- 1/24сутки в ленте
- —
- 1/48двое суток
- —
- 1/72трое суток
- —
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
አላገባሁም:: የሆነ ብር ነበረኝ:: መኪና ላስቀድም ወይስ ቤት ልሥራበት? እንደየሰው እና አካባቢው ቢለያይም እኔ ግን መኪና ነው የማስቀድመው:: ወንድ ልጅ እግር እንጂ አገር የለውም እንደሚባለው ወንድ የትም ቢሄድ ጠፉን ሁላ እያቀና ሀገር ማድረግ ይችላል:: እግርህ ይቅደም:: በዚህ ዘመን ሞባይል የሌለው ጆሮ እንደሌለው ሁሉ ... መኪናም የሌለው እግር አለው ማለት አያስደፍርም:: እንደውም ልበጭርቅበትና ቅድሚያ የሚሸማተረው ሦስተኛው እግርህ ነው:: ቤት ተቀዳሚ ነገር መሆኑ አያጠያይቅም:: ለዚህኛው የኢኮኖሚ ሲስተም ቤት መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ደጋግመን አንስተነዋል:: ሆኖም ግን ያለ እግር ቤቱም ሴቱም አይሰሉም:: እግር (መኪና) የግድ ነው:: ዘንድሮ በመኪና እንኳ መፈጸም ያልተቻለ ሀጃ በቸርኬ ከባድ ነው:: ቴሌኮሙ ቢዘምንም የመኪና ሚና ገና ነው:: መኪና ማለት መለስተኛ ቢሮ ነው:: ስለዚህ መኪና ግዛ:: ተሯሯጥ:: አስሩጠው:: መኪናውን ለተፈጠረለት ዓላማ አውለው:: ንዳው:: አልኩህ እኮ ንዳው:: ፀሓይ የለ ውርጭ, ዝናብ የለ ጭጋግ, ሰርግ ይምጣ ለቅሶ, ምጥ ይምጣ ፍልጥ ... አያሳስብም:: ሩቅ የሚባል ሰፈር የለም:: ታዲያ መኪናህን የሴት መኪና እንዳታደርገው:: ስታጥብ እንዳትውል:: ገና ቤት አልገዛህም እኮ:: ሩጫ ላይ መኳኳል አለ እንዴ? ሩጥ ተባል:: ጎን ለጎን ሴት አታሯሩጥ:: በትእግስት ሠርተህ በመኪናው ላይ ቤቱ የመጣ ወቅት ሴቱ ያሳድዱሃል:: ናማ! ሴቶቹን አስተውለሃቸዋል? እንዴት እንደበለጡህ? ወጥረው ሠሩ:: ንብረት ያዙ:: ያንንም በጀነት ሰንጢ የተሠራ ነገር ያዙ:: የቀራቸው ፍቅር እና አፍቃሪ ባል ነው:: ካንተ ሌላ አይፈልጉም:: አንተም ወጥረህ ሥራ:: ወጥራ የሠራች እና የተማረችዋ ጋር ተወዳጅ:: የምትለዋወጡት ፍቅር ብቻ ነው:: መቼም አትሰለቻቹም:: መቼም አትዘጋጉም:: መሃል ሰፋሪዋን ግን አደራ:: ወይ ጥንቅቅ አድርጋ የተማረች:: ወይ በጣቷ የምትፈርም ትሁን:: ሳታገባ ኪሎሜትር የቆጠረችም ከbad ነች:: ስትጃጃል ያለፋትን ሁሉ ካንተ ትፈልጋለች:: እና መኪና የዝነጣ ግዛ አሉህ ደግሞ:: የሥራ ነው የተባልከው:: ቢዝነሱ በዝነጣ የሚመጣም ከሆነ መብትህ ነው:: ድሮ መኪና ብርቅ በነበረ ዘመን ጫማ ነበር የሚታየው:: ብድር ለማግኘት ወይም እቃ ለመሸጥ ጫማ ወሳኝ ነበር ነበር:: አሁን መኪና ነው:: ካንተ ጋር ቢዝነስ የሚሠራ ሰው መኪናህን እንጂ ቤትህን አያውቅም:: ቤትህን የሚያውቁት ባንኮች ናቸው:: ቤትህን ለባንክ ... መኪናህን ለማርኬቲንግ ዓላማ ብለህ ነው የምትገዛው:: Hasen Injamo
ከተማችንን ዞር ዞር ብለን እያየናት ነው። ስቴድየም አከባቢን አየነው። ሰፈሩ ጸዳ ብሏል። ያምራል፣ ግን ህይወት የለውም፤ ጭር ያለ ነው። እነዚያ የስቴድየም ዙሪያ ግርግሮች የት ጠፉ? ሱቆቹን ቃኘናቸው። ልብስ ቤት፣ ልብስ ቤት፣ እንደገናም ልብስ ቤት፣ ካፌ፣ ፋርማሲ፣ ምግብ ቤት፣ ጫማ ቤት፣ እንደገና ካፌ፣ ልብስ ቤት፣ ካፌ፣ ፋርማሲ፣ ... በቃ እነዚህ ይደጋገማሉ። አልፎ አልፎ መጽሐፍት መሸጫ ቤት ይታያል። አብሮን የነበረው ፈረንጅ ግሪልድ ናይል ፐርች መብላት ፈልጋለሁ ቢለን በየምግብ ቤቱ ብንገባ ናይል ፐርች የለም። ቡና፣ ኬክ፣ በርገር እና ሽሮ ነው የሞላው። ህያት ሬጀንሲ እንሂድ ብለን ተሻገርን። እዚያም ዛሬ ቡፌ ነው ብለውን ወጣን። ማዶ ካለችው የጥንት የጠዋቷ ፍላሚንጎ ሬስቶራንት ገባን። እዚያ የምንፈልገውን አግኝተን ወደ ቦሌ ተሻገርን። ቦሌ ላይ እግረኛው ይርመሰመሳል። ወንድ ሴት ይራመዳል። ወፍራም፣ ቀጭን፣ ባለቆንጆ ልብስ፣ ባለጂንስ ሁሉም በእግሩ ይሸከሸክዋል። ልዩነቱ ያለው ጫማ ላይ ነው። ጫማው የሰውየውን ዓቅምና ድካም ይናገራል። ጫማዎቹን ሳይ እሸቱ መለሰ "ጫማው ሲናገር" በሚል የሠራው የሰዋስተኔ ማስተማሪያ ኮሜዲ ትዝ አለኝ። ከሁሉ የገረመኝ ግን ከተማዋ የእግረኛ ሩጫ እና የካፌ ተቀማጭ እንጂ የሱቅ ተገበያይ አላየሁባትም። ቢዝነስ low እያለች ይመስላል። አዲሳባ የሆነ ማስተካከያ (Fine Tuning) ነገር ትፈልጋለች፤ Event አይታይባትም፣ ፍዝ ነች፣ የድሮው ግርግርና ጨዋታ አይታይም። ከተማዋ በየመንገዱ እና በየአደባባዮቿ Engaging Event ትፈልጋለች። አለዚያ እንደ ኢብን ባቱታ እግረኛ አሳሽ ብቻ ማየት ይሆናል። በዚህ ረገድ የሐረር ኮሪደር ድንቅ ነው፣ ቢዝነስ ይታይበታል። ፍዝዝ ብሎ ለውጥ የሌለውና ቁልቁል የሄደ የሚመስለው ደግሞ የድሬዳዋ ኮሪደር ነው። እሱን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። እናንተስ ስለኮሪደሩ በየቦታው ምን ታዘባችሁ?
ዋጋህ ስንት ነው? ዋጋህ በውሎህና በአስተሳሰብህ አድማስ ልክ ይወሰናል። ውሎና እሳቤህ አገርኛ ከሆነ ዋጋህም በአገሩ መገበያያ ገንዘብ ይገለጻል። ውሎና እሳቤህ ዓለም-አቀፋዊ ከሆነ ደግሞ ዋጋህ በዓለም-አቀፍ መገበያያ ገንዘብ ይገለጻል። ደሞዝ 10,000 ነው ስትባል 10,000 ምን? እንዳትል። ሰውየው ዓለም-አቀፍ ከሆነ ዶላር ማለቱ ነው፤ አገርኛ ከሆነ ግን ብር ማለቱ ነው። አንዳንዴ ግን ቀበልኛ ሰው ካጋጠመህ አሞሌ ጨው 😆 ማለቱም ይሆናል።
አንድ ቢሮ ለመግባት እየጠበቅሁ ነው። እንዲህ ያለ ክፍተት ሳገኝ ዘወትር እንደማደርገው ሞባይሌን አወጣሁና ሃሳቤን ማፍተልተል ጀመርኩ። መጣሁ ብዬ ወደ ኮሪደሩ ወጣሁና ደጁን ማየት ጀመርሁ። ሰዉ ይሮጣል፣ ይቸኩላል። ከሞላለት ይልቅ ያልሞላለት የበዛ ይመስላል። ሰው ግን ለምን ይቸኩላል? የህይወት ግርግር ምክንያቱ ምንድን ነው? የሀሳብ ሻማ ተለኮሰ። ማንም ይሁን ማን ጠዋት ተነስቶ የሚሮጠው ለመኖር፣ ለመባዛትና ለምርታማነት ነው። በቃ ሲጠቃለል የህይወት ሩጫ ይኸው ነው አለኝ ውስጤ። "አይደለም!" ካልህ መሟገቻ ነጥብህን ከነምክንያትህ ቁጭ አድርግና ነገሩን እየበለትን እናወራርደዋለን። ስነ-ፍጥረቱ ሁሉ ግን ለመኖርና ለመባዛት ሲል ከቤት ወጥቶ ከጠዋት እስከማታ ሲባዝንና ሲማስን አይገርምም? ሠራተኛ ንቧን እያት ጥዝዝዝ ብላ አበባ ትቀስማለች፣ ትመገባለች፣ ሌላውን ትመግባለች፣ ዘሯን ታስቀጥላለች። ድንጉላውስ? ንግስቲቱስ? የነሱ ሥራ ሌላ ነው። ድካም የለባቸውም። ፎቅ ላይ ሆኜ ሰዉ ሲርመሰመስ አየሁ። መኪናው ሽው እልም ይላል። አውሮፕላኑ ይበራል። ፓስተሩ ይሰብካል። ቄሱ በመቅደስ ይቀድሳሉ። ከመስጊድ አዛን ይሰማል። ተማሪዎች ይጫወታሉ። የዚህ ሁሉ ሩጫ ፋይዳና ግብ ምንድን ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። ያገኘሁት መልስ ቢኖር ሲጠቃለል #ተደስቶ_መኖር ነው። እና ደስታን መሻት (The Pursuit of Happiness) እንደ አሜሪካ ህገ-መንግስት በህገ-መንግስታችን ለምን አልገባም? ለምንስ አይገባም? ደስታን መሻትን ለማዘግየት ወይም ለመከላከል የቆሙ የሀገራችን ሰዎችና ተቋማት ምን እያሉን ነው? የመኖር ምክንያታችን ምን ሆነና ምን ይሁን ሊሉን ነው? አስቦ የሚኖረው ሰው ጥቂት ነው። ሌላው መሮጥና መሯሯጥ ውስጥ ነው። ልክ እንደ ህጻናት አባሮሽ ጨዋታ ያለ ቡረቃ ብቻ። ፎቁ ላይ ቆሜ ሴቶቹን አየሁ። ብዙ ሴቶች ሁለቱም እጃቸው ሥራ ይዟል። በአንድ እጅ ትከሻ ቦርሳ፣ በሌላው ጃንጥላ ይዘዋል። ሸክመ-ብዙ ናቸው። ቦርሳው ቢከፈት ቅባት፣ ሊፕስቲክ ትንሽ ብር እና ሞባይል ቢይዝ ነው። ለዚያ ተብሎ ከባድ ቦርሳ ይያዛል። ቦርሳው ጌጥ ነው፣ መወዳደሪያ ነው፣ ውበት ማጉሊያ ነው፣ ማማሪያ ነው። ዣንጥላውስ ቢሆን? መኪና እና ታክሲ ለሞላበት ከተማ 300 ሜትር መንገድ ለመራመድ ዣንጥላ መያዝ። ለምን? ሲባል መልኬን ፀሓይ እንዳይጎዳው ይባላል። መልክ ምን ያደርጋል? መልክማ መኖሪያ ነው፣ አበባ ነው፣ እንክብካቤ የሚሻ ግን በቀላሉ የሚረግፍ። አበባ ይጠራል፣ ይመግባል፣ ያኖራል፣ የመራባት ፍላጎትን ይቀሰቅሳል። ፎቁ ላይ ሆኜ ወንዱን አየሁ። ሁሉን ነገር በኪሱ ከትቷል። ኪሱ ውስጥ ምን አለ? ወረቀት፣ ስክሪፕቶ፣ ብር፣ ካርድ፣ ቁልፍ፣ መሣሪያ፣ ሞባይል አለው። ቅባት ለምን አይዝም? ለምን ዣንጥላ አይዝም? እሱ አበባ አይደለም፤ ንብ ነው፣ ወደ አበቦቹ ይሳባል። አበቦች መንቀሳቀስ ቢችሉ ብዬ አሰብኩ? አበቦቹ መንቀሳቀስ ቢችሉ ወደየትኛው ንብ ይሄዳሉ፣ ወደየትኛው አካባቢ፣ ወደየትኛው አበባ? አበባ ራሱ የሚያብበው እኮ ሌላ አበባ ፍለጋ ነው። የቆምኩበት ፎቅ ላይ ክራቫት አድርጎ የመጣውን ሰውዬ አየሁት። ሽክ ብሏል። በሀሳቤ ልብሱን ላጥ ላጥ አድርጌ እርቃኑን ቆሞ አሰብኩት። ቦርጩ፣ እስኪቱ፣ የብብቱ ጠጉር፣ የእግር ጥፍሮቹ እንዴት ይሆኑ ብዬ አሰብኩ። ለምን እንዲህ ሽፍንፍን ብሎ ልብስ ደራረበ? ምን ለመሸፈን? ምን ለመደበቅ? ምን መስሎ ለመታየት? ይሄ ሁሉ ልፋት ለመብላትና ለመራባት ነው እንዴ? ብዬ ሳቄ መጣ። ውጭ መቆም ሰልችቶኝ ወደ ቢሮው ውስጥ ገባሁና ሶፋው ላይ አረፍ አልኩ። ቢሮ ውስጥ ያለችውን ፀሓፊ አየኋት። ሽክ ብላለች። ሂዩማን ሄር አድርጋለች። ፊቷ በፋውንዴሽን ተሰርቷል። ቅጥያ ጥፍርና ሽፋል አላት። ውፍረቷን ሳይ ሆዷ በኩርሲ እንደተጠፈረ ገመትኩ። ስትራመድ ኋላዋ ይንቀጠቀጣል። ትርፍ ስፖንጅ ጨምራ ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ይሄ ሁሉ ግን ለምንድነው? ብዬ ስል አሁንም ሳቄ መጣ። "አለቃው ስለቆዩ መጠበቅህ ገርሞህ ነው ፈገግ ያልከው" አለችኝ። "እ እ እ አይ ሌላ ነገር አስታውሼ ነው" አልኳት። ያሰብኩትን አልነግራት ነገር ምን ተብሎ ይነገራል? አእምሯችን በIOT ተገናኝቶ ቢሆን ኖሮና ያሰብኩትን ብታውቅ ምን ትለኝ ነበር? አደራ እንዳትነግሯት። "በጣም ይቅርታ!" አለ አለቅየው። "የአዲሳባ መንገድ እኮ ለቀጠሮ አይመችም" አለና ቢሮ ገባ። እኔም ለመግባት ጥሪውን እየጠበቅሁ ነው። ይቅናኝ! ይሄ ሁሉ ፍጥረት ግን ሩጫው አይገርምም? ይህ ገርሟቸው ነው መሰል ባለቅኔው አብዬ መንግስቱ ምን አሉ? "ለምንድነው አልኩኝ ለምን ምክንያት? ይህ ዓለም መኖሩ አዱኛ ፍጥረት፣ ህጻን ልጅ ተወልዶ አርጅቶ ሊሞት፣ ......... " እያለ ግጥሙ በውስጤ ፈሰሰ።
እውቀት ካልተመሰጠረ ርካሽ ነው። የሁሉም የሆነ ነገር ውድ አይደለም፤ አያበላም፣ አያከብርም፣ አያስከብርም። ምስጢር ዋጋ ይጨምራል። ይህንን የተረዱ የውጭም የሀገርም ሰዎች ማመስጠርን ሲጠቀሙበት አስተውለሃል? እስኪ አንድ ሁለት ሦስት ነጥቦችን እናንሳ። አንዴ ህንድ አገር ሳለሁ የኮምፕዩተር ፕሮግራሚንግ ልማር ከፍዬ ትምህርት ቤት ገባሁ። C++ መማር ስንጀምር # include io stream < > እያሉ አደከሙን። በእጃችን በቀላሉ የምንሠራውን Fibonacci Series በኮድ ድብልቅልቅ አድርገው አደናቆሩን። ነገሩ ካልከበደ አይከብድማ! ዛሬ ሰዋስተኔ/AI ያለጣጣና ማካበድ የአንድ ድረ-ገጽ ማረፊያ ገጽ (Landing Page) ዱብ ስታደርግ ግርም ይለኛል። አየህ ድሮም ያከበደው ማመስጠር ነበር። ሀኪሞቹ ዶርሳል፣ ኖክቸርናል እያሉ በላቲን ቋንቋ የሚያወሩት እኮ ማመስጠራቸው ነው። መድሃኒት ጽፈውልህ እንኳ አታነበውም እኮ! እንዲያ ካልሆነ አለዚያ እውቀቱ ተራ ይሆናላ! አሁን ሰዋስተኔ ነገሩን በተንተን እያደረገችው ፒጅን ኢንግሊሽ እያደረገችው ነው። ጉድ እኮ ነው። ድሮ ድሮ ፒያኖ መጫወት ብትችልም የሞዛርትን ሙዚቃ መሞዘቅ አትችልም። ለምን? ሙዚቀኞቹ ሙዚቃን ለማመስጠር እነርሱ ለመግባቢያ የሚጠቀሙበት ኮድ አላቸው። እነርሱ ኖታ ይሉታል። ኖታ ካልተማርክ በቀር ቫዮሊን ይሁን ፒያኖ ብትችልም የሞዛርትን ሙዚቃ ኮድ አትፈታም። አካውንቲንግን በተራ ቋንቋ ቢነግሩህ አይከብድህም። ግን ተራ ነጋዴ እንዳይገባው አካውንታንቶቹ መስጠር መስጠርጠር ሲያደርጉት ዴቢት ክሬዲት፣ ጆርናል፣ ባላንስ ሺት ሲሉህ ጥግ ይዘህ እንደባይተዋር ቁልጭ ቁልጭ እያልህ ታዳምጣለህ። መሃንዲሶቹም መግባቢያቸውን ከቃል ይልቅ በስዕል አድርገው ያወሳስቡብሃል።በሶሊድ እና ሂድን ላይን፣ በተለያየ ቪው ስለው ሲሰጡህ አስተርጓሚ ትፈልጋለህ። በጣም ግራ ከገባህ ለራጅ አንባቢ ሁሉ ልታሳይ ትችላለህ። 😆 I am just kidding. የአየር መንገድ ሰዎች እንኳ አንተን እንዳይገባህ ABCDውን አልፋ፣ ብራቮ ... ያንኪ፣ ዙሉ እያሉ ያወሳስቡሃል። AB...YZ ቢሉ ምን ነበረበት። እኔ መከራዬን ዓይቼ ነው 8ኛ ክፍል ሆኜ ኮዱን የፈታሁት። አይዞህ አንተ ጥሩ ዘመን ላይ ነህ። ሰዋስተኔ ደርሳልሃለች። ወደ ቁም-ነገር እንሻገር። አየህ ይህንን የማመስጠር ዘዴና ጥቅም የተረዱ ፖለቲከኞች በቋንቋ ቢለያዩህ እንዳይገርምህ። ቋንቋ ኮድ ነው፣ ለተመረጡት መግባቢያ ነው፣ ያልተመረጡትን መለያ ነው። ቋንቋን ቶሎ እንዳይገባህ ካስፈለገ ደግሞ ፊደልና አጻጻፉን ማመስጠር አለብህ። የቁቤና የግእዝ ጉዳይ ተመሳሳይ ነው። ቁቤም ግእዝም ማመስጠሪያ ናቸው። አይደሉም እንዴ? ቋንቋው ሲመሰጠር የጥቂቶች ብቻ መጠቀሚያ ይሆናል። የተመሰጠረ ቋንቋ Crypto ነው፣ የስልጤ ቦኖ ነው። መፍትሔው Decipher ማድረግ ነው። አሊበደርቼ ! _ (ጣልያንኛው Arrivederci/አሪቨዴርቺ ነው)።
"የለም ሕልም አይደለም" እየሮጠ ወደ ቤቱ ገባ ። ጠንፌ ከልጇ ጋር ተኮራምታ ትንሰቀሰቃለች። በሩን በርግዶ ዘሎ ገባ። "ጠንፌ ጠንፌ"ብሎ ተጣራ። ቀና ብላ አየችው ። ፊቷ ንፍሮ ይመስላል። - እንሂድ ጠንፌ ። - የት? - ሀኪም ቤት ፤ የውሬሏ ሀኪም እጇ መድሃኒት ነው ብለሽ የለም ? - የለም ዋጋ የለውም ከንቱ ነው። - ለምን ዋጋ የለውም ? - ልጄን ከሞት አያድንም ። - እንዴት አወቅሽ ? - ያ ያገኘኸው አዋቂ ሰው አይድንም ብሎህ የለ ? - እሱን ተይው አያውቅም ። - ያውቃል ቱሉ ። ሰውየው ያውቃል። ቱሉ ደነገጠ በገዛ ገመዱ እንደተተበተበ ገባው። "ስሚ ጠንፌ በመጨረሻ ያለኝ እኮ ሃኪም ቤት ከሄደ ይድናል ነው።" አላት። "የውሬሏ ሀኪም ቤት -- የካዛንቺሷ ሀኪም ቤት" አለና ሀያ ብር አጠገብዋ አስቀመጠ፤ ቀና ብላ አየችው ። ለመጠየቅ ጊዜ የላት። ወደ ሃኪም ቤት ጠንፌና ቱሉ ልጁን ይዘው በረሩ። በሶስተኛው ቀን ሕፃኑ እንደልብ ይጠባ ጀመር ። ዳን ያለው መቼም አይሞትም ። ብቻ ከልጁ መዳን ጋር በቤቱ ፀጥታ ሰፈነ።እንደ ቀድሞው መነጋገር መጨዋወት ቀረ። ሁለቱም ተፈራሩ። ጠንፌ ባሏን ሰረቅ አድርጋ ታይና ቁና ትተነፍሳለች። ለመጠየቅ ትከጅልና መልሳ ጥያቄውን ትውጠዋለች። አንድ ማታ ከራት በኋላ ድፍረቷን ሁሉ ሰብስባ "ቱሉ" አለችው ። ድምፅዋ ፀጥታውን ሲሰብር ቤቱ የፈረሰ ያህል ሆነ፡፤ - ቱሉ - ምነው ጠንፌ ? - አንድ ነገር ልጠይቅህ ? - ምንድን ነበር ጠንፌ? - ሃያውን ብር ከየት አመጣኸው ቱሉ? ድንገት በሩ ተንኳኳና ተከስተ ገባ ። መሽቷል ፤ ሦስት ሰዓት ሊሆን ነው። - እንዴት አመሻችሁ ሕፃኑስ ደህና ዋለ? - ደህና ነው፣ አሁንማ ተሻለው። ምንም አይለውም። - ጥሩ ጥሩ ። እንኳን ተሻለው ጃል። እኛማ በቀደም ደንግጠን ። - አረፍ በል ጋሼ ተከስተ ! - የለም ልሂድ ፣ እቤት አልደረስኩም። ገና ከስብሰባ መውጣቴ ነው ። - ስብሰባ እሰከ አሁን የሚያቆይ? - አወን እባክህ ሰሞኑን እንድ ትዕዛዝ መጥቷል። - የምን ትዕዛዝ ? - ማኀበሩን አፍርሱ የሚል ። - ማኀበሩን ? ማን? የ .... የት ? .... እ ... እንዴት ? ማ ... ማን አባቱ ? - ከሚኒስተሩ ነው አሉ ። - አኮ ለምን ? - ሙሴ ጋሌብ ሠራተኛውን ስራ አስፈታ፤ አባለገ ብለው አመልክተው ነው ይባላል። ብቻ ገና ነው እስኪ እንሰማው የለ ? በሉ ደህና እደሩ እቸኩላለሁ። ተከስተ ፋብሪካው ውስጥ መካኒክ ነው ። ተከስተ የሠራተኛው ማኀበር ፀሐፊ ነው ። ተከስተ ማለፊያ ሰው ነው ። ተከስተ ከቱሉ ቤት ወጣ ። ቱሉ ከበራፉ ላይ ቆሞ በጭለማ ውስጥ የሚወዛወዘውን የተከስተን ቅርፅ ትኩር ብሎ ያየው ጀመር ። ከባሻገር ያዲስ አበባ የኤሌትሪክ ብርሃን እንደጧፍ ሲንቀለቀል ይታያል፤ ከላይ ከሰማይ ከዋክብት ይፍለቀለቃሉ ። እነርሱ እንደ ጧፍ ናቸው ይባላል። ከዚያ ዳር የቱሉ ሁለት ዓይኖች አለወትሮአቸው በሲቃ ተጎልጉለው እሳት የሚተፉ ይመስላሉ ከኋላው ደግሞ ጋዝ ያለቀባት የቱሉ ኩራዝ ብልጭ ድርግም ታላለች። ቱሉ ሁለት እጆቹን በኃይል ጨብጦ ስሩ እየተግተረተረ ፣ ጥርሶቹን ነክሶ ፤ ጡንቻው እስኪነፋፋ ካማጠ በኋላ፣ "ይቺ ማኀበር ነፍሴ ቆማ አትፈርስም" አለ። ቱሉ ፎርሳ! - ይህ ጽሁፍ በነሐሴ 1968 ዓ.ም. የመኢሶን ልሳን ናት ትባል በነበረችው ጎህ መጽሔት ላይ ወጥቶ የነበረ ልቦለድ ነው። በዚያ ጽሁፍ ላይ ደራሲው ስላልተገለጸ አይታወቅም ነበር። አሁን ግን ደራሲው ጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤል መሆኑን ፍንጭ አግኝተናል። ቱሉ ፎርሳ ከኢትዮጵያ ክላሲክ አጭር ልቦለዶች ቀዳሚው ሳይሆን አይቀርም። ቱሉ ፎርሳ ከታተመ በቀጣዩ ነሐሴ ወር 50 ዓመት ይሞላዋል። ይህንን አስመልክቶ እንዘክረው ይሆናል። ማን ያውቃል!
ቱሉ ብር ሊበደር ወደ ፋብሪካ ሄደ። በሽተኛ ሕፃን ፣ ምስኪን እናት እና እንባ በትንሿ ጎጆ ውስጥ ቀሩ። ቱሉ ጠዋት ተነስቶ ወደ ፋብሪካ ሄደ ። ፈቃድ ተቀበለ።በደንቡ መሠረት ፍቃድ የወሰደ ደመወዝ የለውም ። ቢሆንም መቼስ ምን ይደረጋል ? ልጅህ ሞቷል ና ቅበር ከመባል ልጄ ሞቷል ኑ አቃብሩኝ ማለት ይሻላል። ጠዋት ሠራተኞቹ ወደ ስራ ተሰማሩ ። "አንድ ሁለት ፎርሳ ፣ አንድ ሁለት ፎርሳ…… " እንዴት ያለ ዘፈን ነው? ሠራተኞች ጆንያውን ተሸክመው ይበራሉ። ጆንያ ተሸክሞ በዝግታ መራመድ እራስን መጉዳት ነው ። መሮጥ ነው የሚበጀው። ማን ዝግ ብሎ ? ያውስ ካቦው "ዳይ ፣ዳይ፣ ዳይ" ፣ ሲል መቼ ፋታ ይሰጣል። ቱሉ እንደ እንግዳ ሠራተኞቹን ቆሞ አስተዋላቸው። እንደ ጅል ተመለከታቸው። ጠጉራቸው ዱቄት ለብሷል። ግንባራቸው ዱቄት ተለቅልቋል። ልብሳቸው ዱቄት ተነስንሷል። ወደ አንገታቸው የሚንቆረቆረው ላብ ፊታቸው ላይ ትናንሽ ጅረቶች የሠሩ ይመስላሉ። ጫንቃቸው ጉብጥ ያለ ይመስላል።ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ ይላል። ሰዎች በጣም ይሠራሉ።ያም ሆኖ ጌታ ጋሌብ አስተያየት ሲሰጡ "አበሻ ሥራ አይወድም ፤ሰነፍ ነው ። ለዚህ ነው እንደኔ ዲታ የማይሆነው" ይላሉ። ሠራተኞቹ ለብዙ ዘመናት ሙሉ ቀን ሲሰሩ ነው የሚውሉት። ዲታ ግን አልሆኑም። ከቶውንም መናጢ ናቸው። ቀደም ብሎ ብድር የጠየቃቸው ሠራተኞች ሁሉ ሁለት ብር የላቸውም። አበበ እንዲያውም የሞፎ ዋጋ መክፈል አቅቶት ብድር ተከልክሏል። ከለላ ትላንት የጎማ ጫማውን ሸጦ ነው እራት የበላው። እርገጤ የቤት ኪራይ መክፈል ተስኖት ሊባረር ነው። ተክሌ የኮሾ ሲጋራ መግዣ ፍራንክ አጥቶ ያዛጋል።ሁሉም ምስኪን ነው። ሠራተኞች ብዙ ይሠራሉ። ብዙ ገንዘብ ግን አያገኙም።ማንን ይጠይቋል ? ማንን ይለምኗል ? ቱሉ በሙሉ ሠራተኞቹን በብድር ጥየቃ አዳርሶ ሳይሳካለት ቀረ። ማንም ገንዘብ የለውም። ገንዘብ ያላቸው ምናልባት የቢሮ ሠራተኞች ናቸው። እነርሱ ቢሮ ደግሞ "ያለ ሥራ መግባት ክልክል ነው።" የሚል መከልከያ አለ። ደግሞ ከቢሮ ቢሮ ሲንጦለጦል ጌታ ጋሊብ ቢያዩትስ? በካልቾ ብለው ከሥራ ወዲያውኑ ያባርሩታል። ቱሉ ከፋብሪካው አጥር ሲወጣ ችግሩን ለዘበኛው ለበቀለ አወያያቸው።አቶ በቀለ ምንም እንደሌላቸው ይልቁንም በሌት ዘበኝነት የብርድ መከላለያ አሮጌ ካፖርታቸውን ማስጣፊያ ገንዘብ በማጣት እትት ሲሉ እንደሚያድሩ አዋዩት። አልሆነም። ሁለት ብር ቢያገኝ ኖሮ ልጁ ይታከም ነበር። ሁለት ብር ቢኖር ኑሮ ምንናልባት ልጁ ይድን ነበር። የውሬሏ ሀኪም እጅዋ መድኃኒት መሆኑን ጠንፌ ነግራዋለች። ሁለት ብር ከየት ይመጣል። የለበሰው አሮጌ ቱታ ምንም ዋጋ አያወጣም። ከመኪና ጎማ ውዳቂ የተሠራው መጫሚያው ስሙኒም አይሸጥ። አቤት ድህነት ፤መልኩ ምንኛ አስቀያሚ ነው? ቱሉ ሰማይ ምድር ዞሮበት አውራ ጎዳናውን ተከትሎ ሲንገላወድ ከፀሐይ ቡና ቤት አጠገብ ደረሰ። ፀሐይ ቡና ቤት የወይዘሮ ፀሐይ ንብረት ነው። ከመንገዱ ዳር የተሰራ አምሮ የተሰራ ቤት ነው። መኝታ ክፍሎች አሉት። የአበባ መደብ አለው ። ምግብ ቤት አለው። ፀሐይ ቡና ቤት ተራ ሰው አይገባም። ሠራተኞች በውጭ ሲያልፉ የቤቱን ድርጅት ከማድነቅ በቀር ገብተው አያውቁም። ቱሉ ከፀሐይ ቡና ቤት ግቢ ሰተት ብሎ ገባ። ወደ ጓሮ ዞረ። አንድ ምግብ አቅራቢ ትኩር ብሎ አየው። "የኔ ወንድም ፤ ወይዘሮ ፀሐይ አሉ?" "አወን አሉ ። ማን ነው የፈለጋቸው?" "ተልኬ ነበር ብቅ ብታስደርግልኝ።" "ማን ነው የላክህ?" "የለም እዚህ ላይ ያሉ ዲታ ናቸው።" ምግብ አቅራቢው ገብቶ ወይዘሮ ፀሐይን ጠራቸው። ወይዘሮ ፀሐይ ቆንጆ ናቸው ይባላል፤ ወፍራም ናቸው። ጉንጫቸው ብርቱካን ይመስላል። ገና ብቅ ሲሉ ተንደርድሮ እግራቸው ስር ወደቀ። "በንብረትዎ ፤ በትዳርዎ ሲሉ ይለመኑኝና ሁለት ብር ያበድሩኝ። እንደው ደፈረኝ አይበሉና ሁለት ብር ስለነፍስ ብለው ልጄ ታሞብኛል ..." "ሂድ ወዲያ !!" አሉና እሜቴ ፈንጠር ብለው ቆሙ ። "የማንም ዕብድ መጫወቻ አደረገኝ እንዴ ! እከከከ ሌባ ቀጣፊ ሠርተህ አትበላም? እንዲህ ነችና ፀሐይ ..." እንደ ወፈፌነት አደረጋቸው ። ዘበኛው መጣና ፤ "ሰውዬ ቀስ ብለህ ውጣ ሳትደበደብ" አለው። ቱሉ ዓይኑ ረጠበ ። ቅልጥሙ ካደው። ይንቀጠቀጥ ጀመር ። እየተገላመጠ ከግቢው ወጣና ካጥሩ ስር ኩርትም አለ። ዘበኛው መጣ። - ስማ ሰውዬ ምን ሆነሃል ? - ፍርሃት ይዞኛል ። - ቤት የለህም ? - አለኝ ቤት ነው ? እ.... የኔ ቤት እ... - ሰክረሀል መሰል ቱሉ ደረቅ ሳቅ ያዘው ። ከቶውንም ይንፈቀፈቅ ገባ ። አፈፍ ብሎ ተነስቶ ቆመ። - ሃሃ ሃሃሃ እኔ ? እኮ እኔ ልስከር ? ቱሉ ሽቅብ ይሮጥ ጀመር ። እየሳቀ ። እንደ ሰከረ ሰው ለብቻው እየፈነደቀ ። ምን ይታወቃል ሰክሮ ይሆናል ? እየሮጠ ወደ ቤቱ ሄደ ። ከደጃፉ ቆመ። ፀጥ አለ። ለንቦጩን ጣለ ። ማልቀስ ቃጣው። ልጁ ሞቶ አላበቃም። እንደ ደህና ሰው ወደ ቤት ገባ። - ቀናህ ቱሉ ? - እ ምን አልሺኝ ? የት ? መቼ ? - ብሩን አገኘህ ? - አዎን - ጎሽ እንካ ልጁን ያዝልኝ ። ከማማ ወደሬ ቤት ጃንጥላ ተውሼ ልምጣ ፤ ፀሐዩ ግሮአል። - ካዛንችስ ሀኪም ቤት ልትሄጂ ? - አዎን - አይ አትሂጂ ጠንፌ ፤ ጠንፌ አትሂጂ ምንም ዋጋ የለውም ።እኔ እ..... አውቀዋለሁ።ዋጋ የለውም። - ምነው ? ለምን ዋጋ የለውም ? - አሁን ስመጣ አሁን እዛጋ እንትን አገኘኝ ። - ምን? - ይሄ ምንድነው ስሙ ? ት .... ትልቅ ሰው ።ጠጉሩ በ ..... በጣም ትልቅ። ትልቅ ትልቅ ቃልቻ አገኘሁ። ዋዋ ..... ዋና ባ .... ባሕታዊ መስቀል ሁሉ የያዘ ትልቅ አዋቂ አ ...... አዋቂ ። - ታዲያ ምን አለህ ? - አትድከም አለኝ። - አትድከም? - አ ...... አዎን ። ልጁ አ ...... አይ አይ ...... አይድንም አለኝ። ጠንፌ ከመሬቱ ላይ ልጅዋን እንደታቀፈች ሟሟች ። በክንድዋ የታቀፈችው ሕፃን ገለጥ አድርጋ ፊቱን አየችው ትኩሳት የጠበሰው ጨቅላ በትኩስ እንባ ቀቀለችው። ተንሰቀሰቀች። "ልጄ ወይኔ ልጄ" ብላ በተሸፈነ ድምፅ አለቀሰች። ቱሉ ቤቱን ጥሎ ወጣ ። ራቅ ብሎ ከምድሩ ላይ ቁጭ አለ። "ወይኔ ልጄ ልጄን በላሁ ።ነፍሴን በውሸት ሸጥኩ - ወይኔ ወይኔ" አለ። ይነደው ጀመር። ቱሉ ዋሽቶ አያውቅም አለዛሬ። አይሆንለትም። ያየውን አላየሁም ያለበት ጊዜ ነበር ። ሳያይ አየሁ ያለበት ጊዜ ግን አለ ዛሬ ...... ቱሉ እንባ አልወጣውም። አንጀቱ ግን ተንሰፈሰፈ ፤ ቁጭ ብሎ ወባ እንደያዘው ይንዘፈዘፍ ጀመር ። ስለኑሮው እያሰበ እራሱን ረገመ። - ቱሉ ፎርሳ ምነው ወደክ እንዴ ? - እእ ..... እኔ አወን ። የለም አለሁ ። - በል ተነስ እንካ ትንሽ ገንዘብ ። - ገንዘብ? ምንድነው እሱ ጋሼ ምትኩ ? ል ..... ልጄ ሞተ ? የእድር ገንዘብ ነው እንዴ ? - ምንድነው የምትለው ቱሉ ፎርሳ ? ትቃዣለህ ልበል ? እንካ ሃያ ብር የሠራተኛ ማህበር ብድር ነው። ወደ ፊት ትከፍላለህ። - ማ ... ማህ .... ማህበር ? የኛ ማህበር ? ለኔ ለ .... ለኔ ነው ሃያ ብር። - ኋላ ትፈርማለህ ። አሁን እቸኩላለሁ ። ወደ ፋብሪካ ልመለስ ነው ። ጠፍቼ ነው የመጧሁት ልሰጥህ ። ቱሉ ብቻውን ቀረ ። እሱና ሃያ ብሮቹ ። አንድ ቀይ፣ አንድ ቢጫ ፤ አምስት አረንጓዴ ብሮች - - - የሚሰራው ጠፋው ።ፊቱን ጠረገው ። ቆጠረው። "አልማለሁ ልበል" አለ ለራሱ እራሱን አርገፈገፈው።
#ቱሉ_ፎርሳ ቱሉ ፎርሳን ማን የማያውቅ አለ ? እናንተ አታውቁትም እንዴ ? ቱሉ ይሄ ማካሮኒ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራው እኮ ነው። ኦ ቱሉን ማን የማያውቅ አለ? ቱሉ ሠላሳ ዓመቱ ነው።ወይም ወደዚያ ግድም ነው። እና ቱሉ ቁመቱ ረጅም ነው። የቱሉ እጆች ትላልቅ ናቸው።የቱሉ ክንዶች ጠንካሮች ናቸው።የቱሉ መዳፎች ሸካራ ናቸው። ቱሉ ከማካሮኒ ፣ፓስታና ፓስቲኒ ፋብሪካ ውስጥ ወፍጮ ክፍል ነው የሚሠራው። ወፍጮ ክፍል ስድስት ዓመት ሠርቷል። የፋብሪካው ባለቤት ሙሴ ጋሌብ ናቸው። ጌታ ጋሌብ እዚች ሃገር (ይቺው የኛይቱ የምንላት) ሲገቡ ቤሳቤስቲን አልያዙም።እዚህ ከገቡ በኋላ ነው ይህንን ሁሉ ያፈሩት፣ ያንን ሁሉ ቪላ ሠርተው የሚያከራዩት፣ያንን ሁሉ ሱቅ የከፈቱት። ጌታ ጋሌብ የናጠጡ ዲታ ናቸው።አቤት ሠራተኛ ሲፈራቸው።ጌታ ጋሌብ ሽማግሌ ናቸው።አጭር ፣መላጣ ባርኔጣ የማይለያቸው፣ አማርኛ አቀላጥፈው የሚያውቁ ዕድላም ሰው ናቸው። ስለ አበሻ ሲናገሩ "አበሻ ሥራ አይወድም።አበሻ ሠነፍ ነው።ለዚህ ነው ሃብታም የማይሆነው - እንደኔ" ይላሉ። ቱሉ ፎርሳ በወር ሠላሳ አምስት ብር ያገኛል። ያ ደመወዝ ነው። ቱሉ ፎርሳ ሲሏችሁ ፎርሳ የአባቱ ስም እንዳይመስላችሁ። አይደለም። የወፍጮ ቤት ሥራ አታውቁትም እንዴ? ስንዴ በካሚዮን ይመጣል። ከካሚዮን ወደ መጋዘን ይጋዛል።ከመጋዘን ወደማንጠርጠሪያው የወንፊት ሞተር ቤት ይወስዳል። ከዚያ ይታጠባል። ከዚያ በሞተር ይደርቃል። ከስንት ጣጣ በኋላ ይፈጫል። ዱቄት በጆንያ እየታሰረ ወደ ቡኮ ክፍል ይተላለፍል።ይህንን ሁሉ የሚያደርገው የሰው ትከሻ ነው።ካሚዮን ሲመጣ ካቦው ሰው ይጠራል - እንዲያወርዱ፤ << አንድ ሁለት ፎርሳ …. >> ከመኪናው ላይ ኩንታሉን እየተሸከሙ ወደ መጋዘን ትንንንን….. እና በስራ ቱሉን የሚያህል የለም። ኩንታል ተሸክሞ ሲበር ጭብጥ ላባ የያዘም አይመስልም። ሁል ጊዜ በጩኸት "አንድ ሁለት ፎርሳ …. " ይወዳል ።ለዚህ ነው ቱሉ ፎርሳ ተብሎ የቀረው እንጂ ያባቱ ስም ሆኖ አይደለም። የቱሉ ሚስት ጠንፌ ነው የምትባለው። እንጀራ ለመግዛት ጉልት የሄደ ሁሉ ጠንፌን ያውቃል። መሽት ሲል ወደ ጉልት ብቅ ያለ ጠንፌና የእንጀራ ሰፌዷን ይለምዳል። መሸት ሲል የቀን ሠራተኞች ወደቤታቸው ይመጣሉ። እግረ መንገዳቸውን እንጀራ ይገዛሉ። ሲመሽ የእንጀራ ገበያ ይደራል። "እሲኪ እንጀራው?" ይላል ጠጋ ይልና። "ይኸው ወርቅ የመሰለ እንጀራ" ይባላል። "ጤፍ ነው ቅይጥ ይላል ላፉ።" "ንጹሕ የበቾ ጤፍ" ተብሎ ይነገረዋል። ጠንፌ ዘንድ ግን ብዙዎቹ እንዲያ ብለው አይጠይቁም። ብዙዎቹ ስለሚያቋት ዝም በለው ነው የሚገዟት አንዳንዴም ከተጠየቀች። "ጤፍ ነው ?" "ትንሽ ዘንጋዳም አለበት" የቀን ሠራተኞች ላፋቸው ነው የሚጠይቁት። ያገኙትን ነው የሚገዙት። የሚገርመው ነገር የቀን ሠራተኞቹ ወንደላጤዎች ናቸው።የቀን ሠራተኞቹ ወጥ አይሠሩም። የቀን ሠራተኞቹ ብዙ ሆነው በትንሽ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት።ታዲያ ለምን ዳቦ(ሞፎ) ገዝተው አይበሉም? ሞፎ ወጥ አያስፈልገውም። ሞፎ የወንደላጤ ምቹ ምግብ ነው። ግን የቀን ሠራተኞቹ እንጀራን ይመርጣሉ። ደርቅ እንጀራ ማላመጥ ደስ ይላቸዋል። ምንአልባት የቀድሞ ቤታቸውን ፣ የወትሮ ትዳራቸውን የሚያስታውሳቸው እየመሰላቸው ይሆናል። እንጀራ የወደፊቱ የተስፋ ምልክት እየመሰላቸው ይሆናል። ጠንፌ አንድ ሃያ አምስት ዓመት ይሆናታል። ጠንፌ ከሁለት ዓመት በፊት ቱሉ ፎርሳን አገባች። በፊትም ከአያቷ ጋር ስትኖር የመንደር እንጀራ ጋጋሪ ነበረች፤ እንጀራ መጋገር እንዴት ዓይነት ሥራ መሰላችሁ? አንዱ ቤት ሰላቢ ነች ይላሉ፣ ሌላ ቤት ማገዶ አይመክታትም ይላሉ፣ ሌላው ቤት እንጀራ ታወፍራለች ፣ ሌላው ቤት ታሳሳለች…….. ጣጣ ነው። በመጨረሻ አያቷ ሲሞቱ ጋግሮ ከማብላት ይልቅ (በሦስት ብር ተቀጥሮ ) ጋግሮ መሸጥ ይሻላል ብላ በነጋዴነት ተጠቃለለች፤ ከቱሉ ጋር የተዋወቁት በእንጀራ ደንበኝነት ነው። ሆሆይ!! ይሄ ደግሞ እራሱን የቻለ ታሪክ እኮ ነው። ታዲያ ጠንፌ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁ ደግሞ ጤና የለውም፤ እሷንም ጤና ነሳት እቴ። የእንጀራ ንግዱም አላዋጣ አለ። እንደ ዱሮ ርካሽ ዱቄት ፍለጋ መንከራተት አለ፣ ማገዶ ፍለጋ አገር ጥሎ መሄድ አለ።… እረ ስንቱ ። በዚህ ላይ ልጇ ጤና የለውም። ባሎች ሁሉ ሚስቶቻቸውን ይማታሉ። ባሎች ሁሉ ይሰክራሉ። ቱሉ ግን አይማታም፣ አይሰክርም፣ ከጠንፌ ምንም አይደብቅም። አምላኩ ጠንፌ ናት። ያለ ጠንፌ ምን ሕይወት አለውና! ጠንፌም ባሏን ትወዳለች ፣ ታከብራለች። "ጠንፌ!" "አቤት።" "ዛሬ ደመወዝ ተቀብዬ ከጓደኞቼ ጋር ጠላ ቤት ገብቼ ስልሳ ሳንተም አጠፋሁ።" "ደግ አረክ።" ጠንፌ ቀና ብላ አታየውም። ጠንፌ ለቱሉ ቱሉ ለጠንፌ የተፈጠሩ ይመስላሉ። ትሳሳለታለች። "ጠንፌ ዛሬ ደመወዝ ተቀበልኩና ስመጣ ሉካንዳ ቤት ገብቼ የሃምሳ ሳንቲም ሥጋ ገዛሁልሽ።" "ጥሩ አረክ።" "ከዚያ በፊት አማረኝና አንድ ብርሌ ጠጅ ጠጣሁ። ምነው ጠንፌ ከፋሽ እንዴ?" "እኔቴ።" ቱሉ ሚስቱን ትኩር ብሎም አያያትም። የምትሟማ ይመስለዋል። ይሳሳላታል። ታዲያ ልጁ እያደር ይታመም ጀመር። በተወለደ በአስር ወሩ የጠና ሕመም ታመመ።ይቃትት ጀመር። ያጣጥር ጀመር። "ሀኪም ቤት ውስጂው" ይላሉ ጎረቤቶቹ ። "የትኛው ሀኪም ይሻላል?" "አሮጌው አውሮፕላን ጣቢያ ያለው ጥሩ ነው።" "እሺ እስቲ" ትላለች ጠንፌ ። ለባሏ ግን አትነግረውም። ምን ብላ ትንገረው ? የቤት ኪራይ አስር አራት ብር ፣ የቤት ጣጣ ሌላውን ይወጣዋል። ምን ብላ ትንገረው ? እንጨቱ ውድ፣ እህሉ ውድ፣ የኩራዝ ጋዝ እንኳ ካቅሙ ዱሮ ሁለት ፍራንክ የሚሸጠው ዛሬ በአራትም ፍራንክ አይገኝም። ሁሉ ቀጥሏል። የረከሰ ቢኖር የሰው ነፍስ ነው።ታዲያ ምን ብላ ትንገረው ? ልጁ ጠናበት። የሰው አፍ ደግሞ አይጣል ነው። "በቅሎ ግዙ ግዙ ፤ አንድ ጨው ላይገዙ" ማለት ያ ነው። "ኸረ ባካችሁ ሀኪም ውስዱት ?" አሉ አንድ ቀን ማታ ሊጠይቁ የመጡ የመንደር አሮጊት። "የትኛው ይሻላል?" አለች ጠንፌ ። "የውሬሏ ጥሩ ናት ሲሉ ሰምቻለሁ።" "እንዲህ እንዳይመስልሽ ፣ አሁን የዛች የቀለሟ ልጅ ታማባት፣እንዲው በጠና ተይዛባት እዛ ሄዳ እንደው ባንድ መርፌ አዳነቻት። ደግሞ ዋጋው ትንሽ ነው።ሁለት ብር ከፍሎ ካርኔ መቁረጥ ነው..በቃ!።" ጠንፌ ልቧ ስንጥቅ አለ። የውሬሏ ሀኪም ሁለት ብር። ሲመሽ የታመመው ዕፃን ከቶውንም ጡት መሳብ ተሳነው። ያ የፈራችው ሊመጣ ነው። ወልዶ መቅበር ላይቀርላት ነው።አዬ ሰው መሆን። "ቱሉ?" "ምን አልሺኝ ጠንፌ ?" "ሁለት ብር አለህ?" "አይ አሁን? …… እንዴት ? እኔ ሁለት ብር ነው ያልሺኝ?" "አወን ሁለት ብር ለውሬሏ ሀኪም የሚከፈል።" "ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል?" "አዎን በጣም አሞታል። አታየውም ትኩሳቱን?" "እ ….. ይሁን…. ጠዋት እበደራለሁ፣ ግድ የለም ጠንፌ አታስቢ።" ሕፃኑ መቃተቱን ቀጠለ። ከቶውንም ማልቀስ እያቃተው ሄደ። ጠንፌ ለባሏ የሚበላውን ሰጠችውና ልጅዋን አቅፋ ቁጭ አለች። "እንብላ እንጂ ጠንፌ?" "እኔ ስበላ ነው የዋልኩት እባክህ። የሴት ነገር ስቀምስም ስበላም ጠገብኩ።" ቱሉ የቀረበለትን እንጀራ ፍርፋሪ በኩራዙ ብርሃን አስተዋለው። ትናንት ከፊቱ የተነሳው የሻገተ እንጀራ ነው።ጠንፌ ዋሽታለች። ጠንፌ ምንም አልቀመሰችም። ጠንፌ ጦሟን ልታድር ነው - ለሱ ብላ። ጠንፌ ልጇን ታቅፋ በዓይኗ እንቅልፍ ሳይዞር ነጋላት።
ከስዊድን፣ ከኖርዌይ፣ ከአይስላንድ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከፊንላንድ፣ ከዴንማርክ ሴቶች ጋር ግብዣ ተገባብዘህ ወንዱ "እኔ ልክፈል" ሲል ሴቶቹ ይቀየማሉ አሉ። የአንዳንዶቹ አገራት ሴቶች ቅድሚያ ለሴት ሲሉ ሌሎቹ Let's go Dutch (ሂሳብ የየግል ወይም ሂሳብ የጋራ) ይላሉ አሉ። የእነዚያ አገር ሴቶች፣ ወንዱ እኔ ልክፈል ብሎ ድርቅ ካለ፣ "ምን ለማለት ፈልጎ ነው? የበታች ሊያደርገኝ አስቦ ነው?" ብለው እስከመቀየም ይደርሳሉ አሉ። በእኛም ሀገር አልፎ አልፎ የሚታዩ እንደዚያ ዓይነት ፍንጮች አሉ። ይሄ መቼም ድንቅ ነው። እንደዚያ ሲያጋጥም ለሴቶቹ እድሉን መተው ነው። ነገር ግን ይህንን ያልተለማመዱ የኛ አገር ሴቶች ብዙ ናቸው። ሁሌም #ድንወ ይክፈል ብለው ዝም የሚሉ ብዙ ስላሉ፣ ለትምህርት ይሁን ለሌላ ወደ እነዚህ አገራት በብዛት ተልከው "ሂሳብ!" ሲባል "እጅ በኪስ" የሚባለውን ጨዋታ ተምረው ቢመጡ ለወጣት ወንዶቻችን ትልቅ እፎይታ ነው። እኩልነት በተግባር ይገለጽ! "ትውልድ ይዳን፣ በኛ ይብቃ!" ከሚለው ንቅናቄ 😆 ወጣቶች:- ለንቅናቄው አማካሪ ስትፈልጉ አለንላችሁ። 😀 _ አሁን እፉዬ ገላ:- "የቡና እርሻ ያለውን፣ ጌትዬዋ" ብትለኝ ጊዜ ትዝ ብሎኝ እኮ ነው። 😂😂😂 "እምቢ አላገናኝም አልኳታ!" እህእ! ሌሎቹስ? 😉
ትምህርት በዋነኛነት በ2 ምድብ ይከፈላል። 1ኛው ምድብ ስታንዳርድ የምትማርበትና ያንን ተከትለህ የምትሠራበትን መንገድ የሚያስተምር ነው። 2ኛው ምድብ ሰርስሮ ማሰብን (Critical Thinking) የሚያስተምር ምድብ ነው። ሁለቱም ምድብ 100% የሚባል ድንበር የላቸውም፤ ሁለቱም ከሌላኛው ምድብ ባህሪይ ጥቂት ጨለፍ ያደርጋሉ። የምድብ ብያኔው በአብዛኛው በሚያስተምሩት የትምህርት መንገድ አዝማሚያ ላይ ተመሥርቶ የተከፈለ ነው። ሁለቱም ግን አንድ የጋራ ጸባይ አላቸው። ሁለቱም ምድቦች የየራሳቸው ሞዴል እና ቲዮሪ አላቸው። የትኞቹ የትምህርት መስኮች የትኛው ምድብ ውስጥ የሚወድቁ ይመስላችኋል? 1ኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ብዙ አወዛጋቢ ነገር የላቸውም። ወይ ልክ ነህ አለዚያም ስህተት ነህ። እዚህ ምድብ ውስጥ ያሉትን መማር ሥራ ለማግኘት ይቀላል። እዚህ ምድብ ውስጥ አካውንቲንግ፣ ህግ፣ ህክምና፣ ምህንድስና፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ሂሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ፋርማሲ፣ ... ይካተታሉ። 2ኛው ምድብ ውስጥ ግን ልክ የሚባል ነገር ጥቂት ነው። ሁሌም ልኩ እንደሁኔታው የሚለያይ እና ከውጤት በኋላ የሚታወቅ ነው። እዚህ ምድብ ውስጥ ፖለቲካ፣ ሳይኮሎጂ፣ ሶሽዮሎጂ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ማኔጅመንት፣ ሊደርሺፕ፣ ... ይካተታሉ። ሁሌም ክርክር ያለው እዚህ ምድብ ውስጥ ነው። በዚህ ምድብ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን ከህይወት ልምድ በኋላ መማሩ ይጠቅማል። ገና በልጅነት ተምረህ አትረዳቸውም። የብዙዎች ችግር ያ ነው። ያው ምን ማለቴ እንደሆን ይገባችኋላ ብዬ አስባለሁ። ካልገባችሁም ብዙ አትጨነቁበት። #IYKYK እኔ እንዲህ ታየኝ። እናንተስ ምን ትላላችሁ?
<<ትላልቅዬ>> ባለሥልጣናት ነዳጅ በመጥፋቱ የሰጡዋቸው የመፍትሔ ዓይነቶች - ጠዋት ስንወጣና ማታ ስንመለስ ሰዎችን እየጫንን ብንሄድ ይላል አንዱ:: ጅብ ይጫነውና ለጠፋው ነዳጅ መፍትሔ ጠዋትና ማታ ሰው መጫን ነው እንዴ? ነዳጅ ለቢሮ እግረኛ ብቻ ነው እንዴ የሚውለው? ነዳጅ ቢትረፈረፍም ሊደረግ የሚችል ነገር ሊሆን ይችላል:: ይህ ሰውዬ ለአውሮፕላንም ለክሬንም ነው እንዴ ሊፍት የሚሰጠው? ወይስ የጠፋው የቪትዝ ቤንዚን ብቻ ነው? - ሌላው ደግሞ ሕዝቡ ዎክ መብላት መልመድ አለበት ይላል:: የሕዝባችን ዋነኛ መብል እኮ ዎክ ነው:: መገናኛና ሜክሲኮ የሚተራመሰው ምእመን ጀት ነው እንዴ የሚበላው? 80% ገበሬ እኮ ከእህል ጎን ለጎን በባዶ እግር ሻከር ያለ ዎክ አይደል እንዴ የሚበላው?እሺ አውሮፕላኑም ዎክ ያድርግ? ሲኖ ትራክ, ሚክሰር, ሎቤድ ዎክ ያድርጉ? - ሦስተኛው ባለሥልጣን ደግሞ በከፍት ብንጓጓዝ ጥሩ ነው:: አሕያ! ማለቴ ፈረስ, አሕያ አርማታ ያቡኩ? ተሳቢ ከነኮንቴይነሩ ይሳቡ? አውሮፕላን ይጫኑ? ፋብሪካ ያንቀሳቅሱ? ከእግረኝነት ያልወጣ ጭንቅ-ላት ሚዲያ ላይ ባይቀርብ, ባይጽፍ, ባይናገር ይሻላል:: ስንት ጉድ ይሠራሉ ብለህ ስትጠብቃቸው አሕያዋ ከተማ ውስጥ ስታጓጉዝ ልትጥለው በምትችለው ፋንዲያ ይከራከራሉ:: ዳይፐር ታስርላቸዋለህ:: የኒኩሊየር ኃይል, የኤሌክትሪክ መኪናና ማሽን ለመጠቀም ምን ያህል ግድብ መገደብ እንዳለብን, የኤሌክትሪክ መኪና ፋብሪካ የአፍሪካ ማሳለጫ ለመሆን መደረግ ያለባቸው ክተቶች ብለው ማውራት ሲገባቸው የፊንቴክ ሿሿዎች ወሬ አየሩን ያዘው:: ለማንም ሿሿ ሠሪ ብሩን የሚያወጣ ምእመን ካለ ዘርፉ በጣም ለም ነው ማለት ነው::
ዘመኑ የፍጥነት ነው! ፈጠን በል። ዝም ብሎ ተፍ ተፍ ማለት ብቻ አይሠራም። ፍጥነት ጨምርበት። ከተኛህ ሌላው ፈጣን ሰው ያንተን ቦታ ወስዶታል። ዘገምተኛ ሰው ኤኮሲስተሙን ሁሉ ይጎትተዋል። ይሄ የደጋ ሰው ባህሪይ ነው። በደጋ አገር ሁሉ ነገር ቀስ ያለ ነው። በደጋ አገር ጠዋቱ ራሱ ገና ፀሓይ ተሞቆ፣ ቡና ወይ አረቄ ተጠጥቶ ሥራ የሚጀመርበት አገር ነው። ቆላ ግን እንደዚያ አይደለም። ብድግ ካልህ ውልቅ ነው። ቁርስ ራሱ ውጭ ነው። ምግብ ቤት ውስጥ መሥራት አልተለመደም። ምክንያቱ ደግሞ አንድም ቤት ያሞቃል እንዲሁም የተሠራውም ቶሎ ይበላሻል። ቆላ አገር ቢዝነስ ያጧጡፋል። ሌላው ቢቀር ውሃ ይሸጣል። ጠዋት ውሃ የጠጣው ረፋድ ላይ እንደገና ውሃ ይፈልጋል። ቆላ ውስጥ ኑሮ ይፈጥናል። ቆላ ፍላጎት ይፈጥራል። Demand Create ያደርጋል። ለዚህ ነው ቆላማ ሀገራት ፈጥነው የሚያድጉት። ይሄ እንዲገባህ በረሃ አገር ሄደህ 3 ወራት ስትቆይ ይገባሃል። ቆላ ሀገር ውስጥ ሥራ በሽ በሽ ነው። ምግብ በየቀኑ መሠራት አለበት። እንደ ደጋ ሀገር እንጀራ አንዴ ጋግሮ 3 ቀን መጠበቅ የለም። ቆላ ውስጥ ልብስ ቶሎ ቶሎ መታጠብ አለበት። ልብስ በላብ ይቆሽሻላ! ሳሙና ቶሎ ቶሎ ይገዛል፣ ቡና ይጠጣል። Demand በሽ ነው፣ ሥራው ፈጣን ነው። አሁን የዓለም ሙቀት እየጨመረ ነው። በዚህ ምክንያት ትውልዱ እየፈጠነ ነው። ፈዘዝ ያለ ልጅ ካለህ ቆላ አገር ዘመድ ፈልገህ ላከው። ተገርቶ ጀት ሆኖ ይመጣልሃል። ነግርቻሎ! ፈጠን በል። አትንቀርፈፍ! ይህ አገር ግን ገራሚ ኖ! ፈጠንክ ብሎ ራዳር ይዞ ይቀጣሃል🤔 ቢሆንም ፍጠን! አንድ ቀን ወይ ቀጪው ይቀየራል ወይም ህጉ ይቀየራል።
ኤለን መስክ የዓለም ቁንጮ ሀብታም የሆነበት ምስጢር ምንድን ነው? መቼም ቴስላ ኩባንያ የሚሸጠው የመኪና ብዛት ነው አትሉኝም። ቴስላ በዓመት ስንት መኪና ይሸጣል? ከBYD የበለጠ ይሸጣል? ደግሞም በSpace X ኩባንያው ምክንያት ነው እንዳትሉኝ። በዚህ ኩባንያ ወደ ህዋ የሄደ ተሳፋሪ አለ? እሺ ሃይፐርሉፕ የተባለው ኩባንያስ ሥራ ጀምሯል? ኤለን መስክ እዚህ አገር ቢሆን ኖሮ ታስሮ የሀብቱ ምንጭ ይጣራልን ይባል ነበር። የኤለን መስክ አስተሳሰብ እና አኗኗር ከለመድነው (በእኛ ሀገር ከተለመደው) የሀብታም አኗኗር ይለያል። ኤለን መስክ በስሙ የተመዘገበ ቤት የለውም። ኤለን አሁን የሚኖርበት ቤት 47 ካሬ ሜትር ናት። ሂድ በለው! አትልም? ጉዱ ገና ነው። ተከተለኝ። ኤለን መስክ ከሀብቱ አንጻር ያለው ካሽ ትንሽ (0.25%) ነው። በእርግጥ ያ ራሱ ብዙ ነው፤ ጥቂት ቢሊየን ዶላሮች ነው። ለኤለን መስክ ግን ይህ አይበቃውም። የ800 ሚሊየን ብር ኩባንያ ኖሮህ አንድ ሲገል BYD የሚገዛ ጥሬ-ገንዘብ ባይኖርህ አስበው! እንደ ኤለን መስክ ያለ ሰው ካሽ ቸግሮት ብዙ ጊዜ ይበደራል ብትባሉ ምን ትላላችሁ? ይህ ሁሉ ዳር ዳርታ ምን ለማለት ነው? የኤለን መስክ ሀብት ያለው የኩባንያዎቹ የድርሻ ዋጋ ላይ ነው። የኩባንያዎቹ የድርሻ ዋጋ ደግሞ በአክሲዮን ገዢዎች እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ እምነት ከወረደ የኩባንያው አክሲዮን ዋጋም ሆነ የኤለን ሀብት ይወርዳል። ኩባንያ ላይ ያለ እምነት በተለያየ መንገድ ሊዋዥቅ ቢችልም የሰውየው ብራንድ እና ሌሎች ሰዎች ያላቸው አመለካከት ግን ከፍ ያሉ በመሆናቸው በኤለን መስክ የሀብት መጠን ላይ ጉልህ ድርሻ አላቸው። የኤለን መስክ ብራንድ ሁሌም በአዲስ ነገር ፈጠራ ላይ ነው። አዲስ ኢንቨስትመንት ሲያስብ የኩባንያ አክሲዮኑን አስይዞ ከባንኮች ይበደራል። ከዚህ ቀደም Starkink የተባለ ኩባንያ ፈጥሯል። ስታርሊንክ የሳተላይት ስብስቦችን አምጥቆ ለመንግስታት ያከራያል። አሁን ደግሞ አንድ መንደር ሊገነባ ነው። ኤለን መስክ ቤት ባይኖረውም፣ በቂ ካሽ ባይኖረውም "ሁዱ-ቁላ" ወይም "ቂጠ-ባዶ" የምትለው ዓይነት አይደለም። በስሙ ብቻ ቢሊዮኖች መበደር የሚችል፣ የትም ገብቶ መኖር የሚችል ነው። ይህ የአስተሳሰብ ውጤት ነው። እኛ ሀገር ቢሆን አንድ ሰው ትልልቅ ህንጻዎች ሳይኖረው፣ የጭነት ትራንስፖርት ድርጅት ሳይኖረው፣ ብዙ ማደያ ሳይኖረው፣ አካውንቱ ላይ በርካታ ሚሊዮኖች ሳይኖረው እንዴት ሀብታም ሊሆን ይችላል? ብለን ኡ ኡ ልንል እንችላለን። ኤለን መስክ የሚኖረው ግን አሜሪካ የሚባል ሀገር ውስጥ ነው። በአሜሪካ ሀሳብ ይታመናል፣ ሀሳብ ይሸጣል፣ ሀሳብ ሀብታም ያደርጋል። ለዚያ ነው America is the land of opportunities መባሏ። የእኛም ሀገር አስተሳሰብ አንድ ቀን እዚያ ደረጃ ላይ መድረሱ አይቀርም። የእኛ ሀገር ኤለን መስክ ግን ማን ይመስላችኋል? ለእኔ ወዳጄ Bejai Nerash Naiker ነው። እስኪ አስቡት ቢጃይ አክሲዮን ማህበር ቢመሠርት የቢሊየን ዶላር ኩባንያ አይፈጥርም? ቢጃይ የእኛን ሀገር የመጀመሪያውን #Unicorn እንዲፈጥር #ቻሌንጅ ሰጥቼዋለሁ። ተስማሚውን ጊዜና ሁሳብ ቁጭ ብለን እንመክርበታለን። እናንተስ ምን ትላላችሁ? ትልቅና ሀብታም ኩባንያ ሲኖረን ሀብታም አገር ይኖረናል። ያ ደግሞ ለሁሉም ይተርፋል። "ያ ረቢ ቶኩማፍ ኬኒ" ይላል የሐረር ሰው።
ምን እንደሚሻለን አላውቅም! ሴቶቹ ሁሉ ያማርራሉ። ከተማ ያደገችዋም፣ ከገጠር የመጣችዋም ሴት ታማርራለች። መኪና የምትነዳዋም፣ የሥራ ኃላፊዋም ታማርራለች። ገንዘብ የሞላትም፣ ባል የሌላትም ታማርራለች። አሳቢ ባል ያላትም፣ የፈታችዋም፣ ሲንግል ማም የሆነችዋም ታማርራለች። ይሄንን መረዳት በጣም ይከብዳል። የማታማርር ሴት ያየሁት እናቴን ብቻ ነው። ይሄኔ እሷም እኔ ሳልሰማት ታማርር ይሆናል። እሷ ሁሉን እችላለሁ ብላ ስለምታስብ ይሆናል የማታማርረው። የሚገርመው ሴቷ ልጄ እንኳ እንዲሁ ስጠይቃት ታማርራለች። ሁሉም የምሬታቸው ትኩረት አንድ ፍጥረት ላይ ነው - ወንድ! ሴቱ ሁላ ወንድን ያማርራል። ግን ደግሞ ወንድን ይፈልጋል፣ በአፉ ግን አልፈልግም ይላል። የተፈጥሮ ምስጢር እንዲያ ነው። ግን ደግሞ ሴትን መረዳት ቀላል ነው። ሴትን ለመረዳት መቼም እንደማትረዳት ማወቅ ነው። ሴትን አትከራከራት፣ እሺ በላት፣ ምችት ምችትችት እንዲላት አድርጋት፣ ድንገት ጥፋባት፣ ስትናፍቅህ ብቅ በልላት፣ አስተሳዝናት፣ ሲበርዳት ጃኬትህን ደርብላት፣ አድንቃት። ለሴት አድናቆት የየእለት ምግቧ ነው። አድናቆትን ያለስስት መግባት። ውብ ነሽ በላት! ጨረቃ፣ ፀሓይ፣ ኮከብ ነሽ በላት። ታድያ ተጠንቀቅ! በአንድ ጊዜ 2 ሴት አታድንቅ። ለየብቻ! እኔ ግን ችግር አለብኝ። የምሬን ካልሆነ ማስመሰል አልችልም። ሴትንም ይሁን ወንድን ካደነቅሁ የምሬን ነው! የምሬን! የምር! እናንተም ግን አታማርሩ። ሄዋን ግን አማርራ ታውቃለች?
አገር (#Country) ማለት ዳር ድንበር ያለው የጂኦግራፊ ክልል ነው። ህዝብ (#Nation/#People) ማለት ተመሳሳይ ባህል እና ማህበራዊ ስነ-ልቦና የሚጋሩ ሰዎች ናቸው። ልክ እንደ አይሁድ ህዝብ። ህዝብ አገር ሳይኖረው ተበታትኖ በተለያየ አገር እየኖረም በጋራ ስነ-ልቦና ተሳስሮ ይኖራል። የኩርድ ህዝብ እንደዚያ ነው። ዜጋ (#Citizen) ማለት የአንድ አገር ህጋዊ ነዋሪዎች ማለት ናቸው። ዜጋ ከህዝብ ይለያል። ዜጎች ዝርያቸውም፣ ስነ-ልቦናቸውም አንድ ባይሆንም በህግ የታወቁ ነዋሪዎች ናቸው። አሜሪካ ውስጥ እንደዚያ ያለ ብዙ ዜጋ አለ። ህዝብ በተለያየ የጂኦግራፊ ክልል ውስጥ ተበታትኖ የተለያየ ዜግነት ይዞ ሊኖር ይችላል። መንግስት (#State) ማለት የአገር አስተዳዳሪ ወይም የዜጎቿ ገዢ ነው። የህዝቡ ገዢ አይደለም። ከመንግስት አስተዳደር ውጪ ያለ ህዝብ ይኖራል። አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የቱ ጋ ነው? አሁን የኢትዮጵያ ዜጋ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚባል አለ? ካለ የትኛው ባህል፣ የትኛው ስነ-ልቦና፣ የትኛው ማስተሳሰሪያ ያለው ነው? የህዝብ ስነ-ልቦና የሚገነባም የሚዳከምም ነው። የኤርትራውያን የጋራ ስነ-ልቦና እዚሁ እያየነው ተገንብቷል። የአሰብ ወደብ ጥያቄ ሲነሳ ከጎንህ ያሉት ሁሉ ሲቆጡ ታያለህ። "ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን" የሚለውን የዋሸራ ቅኔ እንተወውና ኢብሳ ጉተማ ከ50 ዓመት በፊት በዩኒቨርሲቲ ውድድር ላይ በግጥም እንደጠየቀው "ማነው ኢትዮጵያዊው?" እንበል እስኪ? ኢብሳ ጉተማ ግን ከኦነግ ጋር መጥተው፣ የሽግግር መንግስት ውስጥ ገብተው፣ የትምህርት ሚንስትር ሆነው ነበር። ምን ሠርተው ሄዱ? አሁን የት ናቸው? በቃ የሚታወሱት በጥያቄያቸው ብቻ ነው ማለት ነው? ኢትዮጵያዊው ማነው? የኢትዮጵያን ፓስፖርት የያዘው ብቻ ነው? የመንግስት ደጋፊውና ተጠቃሚው ብቻ ነው? ዜግነቱን ቢቀይርም፣ ኢትዮጵያ ልቡ ውስጥ ያለችውና በገንዘቡም፣ በእውቀቱም፣ በሀሳቡም ኢትዮጵያን የሚያግዘውን ሁሉ ይጨምራል? ከመሃል አገርና ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በቋንቋ ባይግባባም ኢትዮጵያ በምትባለው የጂኦግራፊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ ናቸው? ብቻ ነገሩ ውስብስብ ነው። አንዳንድ ነገሮች ግን እንዲሁ ለነገ በይደር ትተናቸው ላይ ላዩን እያየን አብረን የምንኖራቸው ችግሮች ናቸው። ያ ሁላ ተመራማሪ እያለ ማን ይነግረን ይሆን? መታወቂያ የሌለው ኢትዮጵያዊ ልክ የአባልነት ምዝገባ ቁጥር ሳይኖረው እንደሚጨፍር ቲፎዞ ነው ተብሎ ፋይዳ እያወጣን ነው ያልከኝ ልጅ ግን ይሜ። 😂 እስኪ እያሰብንበት እንቆይ! ዜግነት ቀይራችሁ ክለብ መቀየር የከበዳችሁ ሰዎች ግን ምን ሆናችሁ ነው? ለምቾት ብላችሁ ዜግነት ከቀየራችሁ ለዋንጫ ደስታ ብላችሁ ክለብ ለምን አትቀይሩም? ይሄንን ሀሳብማ እመለስበታለሁ። የምን እንደዛገ ግራናጆ ነክሶ መቅረት ነው? እናብላላው እንጂ!
[The 1% Club] ∞ ∞ ∞ ∞ ጌታዬ - ሰሞኑን አዶናይ የተባለ የቲክቶክ ወጣት ለመከላከያ ሰራዊት ማነቃቂያ ሲሰጥ አይተህ ተሸማቀሀል፤ ከዛም አለፍ ብሎ "ከሰሜን የሚነሳው ቴዎድሮስ ነህ ይሉኛል" ብሎ እሱም እንደተከታዮቹ ዴሉዥን ውስጥ እየገባ መሆኑን አይተህ ፈገግ ብለሃል - ነጥብ አለህ። - ግን በዚህ መልኩ እየው እስኪ። - ሰግጥ በሚል Soundtrack ቪዲዮ የሚሰራውን ሰው ተመልከተው፤ የሰጡትን እና አድርግ የተባለውን ከማድረግ ወደኋላ የማይለው ሰፊው ህዝብ አካል ነው። - በእርግጥ ከአምባሳደር ዲና እስከ ቀሳውስት ይሄን Trend ተቀላቅለዋል . . . ነገርግን እንዲህ አይነቱን ሰው ካንተ ከራስህ ጋራስ አነፃፅረኸው ታውቃለህ ወይ? ተከተለኝ። ሠፊው ሕዝብ መሠረታዊ የባንክ አገልግሎት ለመጠቀም ማንበብ እና መፃፍ ስለማይችል፣ በባንክ አስተናጋጆች እየተረዳ ነው Financial Transaction የሚፈጽመው፣ አንተ Mobile Banking ትጠቀማለህ። ሠፊው ሕዝብ ማትሪክ አልፎ ዩንቨርሲቲ አልገባም፣ አንተ ገብተሃል። ሠፊው ሕዝብ መሃል ከተማ ውስጥ አይኖርም፣ አንተ ትኖራለህ። ሠፊው ሕዝብ Netflix ስሙንም ሰምቶ አያውቅም፣ አንተ Applicationኑ አለህ። ሠፊው ሕዝብ የዓለማችን ከባዱ የስለላ መፅሃፍ ዴርቶጋዳ ይመስለዋል፣ አንተ የ'የስንብት ቀለማት' ቴስት አለህ። ሠፊው ሕዝብ ሮፍናን ሰከላ የሚለው ዘፈኑ ላይ 'ሚኒሊክ ዛሬም ንጉስ ነው' የሚል ሐረግ ስላካተተ፣ ''ንጉሠ ነገሥት ሚኒሊክ በሕይወት አለ የለም'' እያለ ይከራከራል፣ አንተ ግን ሮፍናን ከ Universal Records የተዋዋለውን ውል አንብበህ analyze ማድረግ ትፈልጋለህ። - ሠፊው ሕዝብ አዲስ አበባን አይቷት አያውቅም፣ አንተ ዱባይን ታውቃታለህ። ሠፊው ሕዝብ ሹመኛ በሙሉ አዋቂ ይመስለዋል፣ አንተ ከአንድ ሚኒስትር የላቀ እውቀትም ብቃትም አለህ። ሠፊው ሕዝብ ቴሌቪዥን ከፍቶ፣ ''ጤናዎ በቤትዎ'' የሚል ፕሮግራም እየተከታተለ ስልክ ይደውልላቸዋል፣ አንተ ዴቭ ቻፔልን ትከታተላለህ። ሠፊው ሕዝብ በሸማቾች ዘይት ረክሶ ኑሮውን ለመቀየር ይጓጓል፣ አንተ Ai ተጠቅመህ ኑሮህን ለመቀየር ተዘጋጅተሃል። ሠፊው ሕዝብ ባቡጂን የአለማችን ታላቅ አክተር አድርጎ ይገምታል፣ ያንተ ቴስት እነጃክ ኒኮልሰን ናቸው። ሠፊው ሕዝብ 'ብሔሬ ስልጣን አገኘ፣ ብሔሬ ስልጣን አጣ' እያለ ይገ ዳደላል። አንተ የብሔር ጆተኒ ገብቶህ ትስቃለህ። - ሠፊው ሕዝብ አገር የተመሰቃቀለው አባቶች ቀድመው ስለተነበዩ ነው ብሎ ያምናል፣ አንተ ይሄ አገር አዘቅት የወረደው ቀሽምና ዘረኛ መንግስት ወጥ ሥርአት ዘርግቶ ማስተዳደር ስላቃተው እንደሆነ ታውቃለህ። ሠፊው ሕዝብ በYouTube የሚነገር ነገር በሙሉ እውነት ይመስለዋል፣ አንተ ደግሞ ስለ Monetization፣ ስለ Misinformation እና Disinformation ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ለሠፊው ሕዝብ ጂጂ ኪያ፣ ዮኒ ማኛ፣ ሞጣ ቀራኒዮ፣ ዘመዴ፣ ወዘተ. . . ተአማኒ የመረጃ ምንጮቹ ናቸው፣ ላንተ ደግሞ ጨለል ዳያስፖራ እንደሆኑና - ከማዝናናት ያለፈ እርባና እንደሌላቸው፤ ጉዳይ አስጩኸው እና ሴንሴሽናል ሆነው ቢዝነስ እንደሚሸቅሉበት ታውቃለህ። ስማ ስማ። ሃብት ላይኖርህ ይችላል፤ #ግን የነቃ የበቃ አእምሮ እና የሠላ ጭንቅላት አለህ። ቤት ንብረት ላትይዝ ትችላለህ፤ ነገ አኪር አጋጣሚ ብታገኝ የምትቀየርበትና የምትከብርበት አይዲያዎችና ኮኔክሽኖች አሉህ። አሁን አልበረገደልህ ይሆናል፤ ነገር ግን ከዘመኑ ጋራ ሊሄድ የሚችል አዋቂ፣ አንባቢ እና ነገሮችን በቶሎ የሚረዳ Flexible and Quick ተፈጥሮ አለህ። ዛሬ ከአገርህ ወጥተህ አታውቅ ይሆናል፣ ነገር ግን እዚሁ ሆነህ አለም ላይ ያለ ዋና ዋና Trend በደንብ ጠንቅቀህ ትከታተላለህ። እና። እና - አንተ እና ሠፊው ሕዝብ በምን መለኪያ ነው አንድ የምትሆኑት? ለሠፊው ሕዝብ የሚቀርብ ማጃጃያ Consumption አንተን ለምን ይሞቅሃል ይበርድሃል? #Remember: You Are The ONE PERCENT. አንተ እኮ ክሬሙ ነህ ለዚህ ሕዝብ። አራዳው ነህ። ኤሊቱ ነህ። ሮል ሞዴሉ ነህ። - መህዲ ሀሰንን እና አማንፖርን በሚሰማ ጆሮህ፣ ስቲቭ ጆብስን ባደነቀ ጭንቅላትህ፣ ሌክስ ፍሪድማን በሰማ ህሊናህ፣ ሻርክ ታንክ በተከታተለ ወኔህ፣ Ted Talkን አሳልሶ ባዳመጠ ብቃትህ፣ Forbus 400ን በሚያነብብ ማንነትህ እንዴት በአዶናይ እና ተከታዮቹ ቅር ትሰኛለህ? ደግሞ። ደግሞ ''እንደ ማኅበረሰብ ዘቅጠናል፣ ላሽቀናል'' የምትል አዲስ የኑዛዜ (Confession) ፈሊጥ መጥታልሃለች። ስህተት ነው። ከላሸቁ እነሱ ይላሽቁ። እኔና አንተ የለንበትም። #እኛ Belong አናደርግም ከላሻቂው ወገን። ዓለምም በPop Culture፣ በTabloid ወሬ እየደነዘዘ ነው። እኛ ደግሞ ከዓለም አቀፉ 99% ጋራ ውግንና የለንም። የለንማ! መቼም። ይሄ መቼም የማነቃቂያ ንግግር፣ ወይንም የማነሳሻ ክሊሼ ሳይሆን ጥሬ ሐቅ ነው። ስለአንተ ብቃት እና ስለ አቅምህ፣ ሰለ ቀጣይ የት መድረስ የምትችል ከባድ ሰው እንደሆንህ አስረግጬ እየነገርኩህ ነው። ከምሬንም ነው። - #ተውላቸው #አትውረድ #YouAreTheOnePercent #የእዮባ_ህልም_ትቀጥላለች
የልጆቻችንን ጊዜ አትጫወቱበት! ልጆች ቀኑን ሙሉ ትምህርት ቤት ውለው፣ ለዓመታት ተመላልሰው የረባ እውቀት ሳይዙ ጊዜያቸውን ይጨርሳሉ። ለዚህ ማረጋገጫው ብሔራዊ ፈተናን የሚያልፉት ጥቂት መሆናቸው ነው። ኮሌጅ የገቡትም ቢሆን ከጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና የትምህርት ዘርፎች በስተቀር ሌላው የጊዜ ብክነት እንጂ በቂ እውቀት እንደማያስጨብጥ የታየ ነው። ብዙ ምሩቃን ለሥራ ብቃት የላቸውም። እና የልጆቻችን ጊዜ በከንቱ ሲባክን እኛ ካልተቆጨን ማን ሊቆጭልን ነው። ልጆቹ ከዚህ አልፈው ሌላ አገር ስሄዱም የረባ ሥራ መያዝ አይችሉም። እዚህ ያገኙት ትምህርት ብቁ ተወዳዳሪ አላደረጋቸውም። የትምህርት ዓላማ ለዘመኑ ሥራና አኗኗር ብቁና ስምሙ የሆነ ሰው ማፍራት ነው። የአሁኑ ትምህርት አሰጣጥ የታለመው በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ለነበሩ ሥራዎች ነበር። እነዚያ ስራዎች ሰዓት ማክበርን፣ በትጋት መሥራትን፣ ለአለቃ መታዘዝን የሚፈልጉ ነበሩ። አሁን ዘመኑ ተቀይሯል። የትም ሠርተህ ውጤት አምጣ የሚባልበት ዘመን ነው። እንግዲያው ትምህርት ሚኒስቴር ልጆቹን ብቃት ያለው ተመራቂ የማያደርግ ካሬኩለም እንዲማሩ በማድረግ ጊዜ ከሚፈጅ፣ እንደሌላው ሚኒስቴር መ/ቤት ብቃት እና ጥራት መቆጣጠር ላይ ብቻ አትኩሮ ለምን አይሠራም? ፕሮሰስ ውስጥ ለምን ይገባል? ካሬኩለም ለምን ይወስናል? ሙሉ ቀንና 12 ዓመት እንዲፈጁ ለምን ያደርጋል? የቻለ፣ የፈጠነ እና የበረታ ለምን በ4 ዓመትስ አይጨርስም? ለትምህርት ጥራት ማረጋገጫው ብሔራዊ ፈተና ነው። ብሔራዊ ፈተናዎቹ በ8ኛ እና 10ኛ ላይ ከተደረጉ በቂ ነው። ዩኒቨርሲቲ በመግቢያ ፈተና ይቀበል። ትምህርት መማሩን ግን ሁሉም በተመቸው እና ባዋጣው መንገድ ይማር። የፈለገ በኦንላይን፣ የፈለገ በማታ፣ የፈለገ በቀን ተምሮ ይፈተን። በቀን ክፍል ለሚማር ተማሪ ትምህርት ቤት የመገኘት ግዴታው 4:00 ሰዓት ብቻ እንዲሆን ቢደነገግ ትምህርት ቤቱ በ2 ፈረቃ በማስተማር፣ የትምህርት ዋጋንም ቀንሶ የትምህርት ቤት ገቢንም ይጨምራል፣ የሥራ እድል ያስፋፋል፣ የትምህርት ቤት እጥረትን ይቀርፋል። ት/ሚ ለትምህርት ፈቃድ ለመስጠት ብቃት ያረጋግጥ፣ በመጨረሻው የምርቱን ውጤት በፈተና ያረጋግጥ። የትኛው ሆስፒታል ነው በጤና ሚ/ር እንዲህ አድርገህ አክም የሚባለው? የህክምናው አሰጣጥ ለተቋሙ የተተወ ነው። የትኛው ፋብሪካ ነው እንዲህ አድርገህ ካላመረትህ የሚባለው? እንዴትም ያምርት፣ የምርት ጥራቱ ግን ይፈተሻል። እናም የትምህርት ተቋሙ እንዴትም ያስተምር ውጤቱን መቆጣጠር እንጂ ት/ሚ አብሮ ፕሮሰሱ ላይ መግባት የለበትም። ያኔ ወላጅ እንዴትና የቱ ት/ቤት ልጁን ማስተማር እንዳለበት ይመርጣል። ትምህርት እንደ ሳሙና ተመሳሳይ ምርት እንዲያወጣ የሚፈለግበት ዘመን አልፏል። አሁን ላይ ልጆቻችንን ወይ እኛ አላስተማርን ወይ በትክክል አልተማሩ ለዘመኑ የማይመጥኑ እንዲሆኑ ተደርገው ጊዜያቸው ሲባክን ማየት ይበሽቃል። ግዴለም ት/ሚ ጥራት ቁጥጥርና ፈተናውን ይሥራ። ሌላውን ለባለቤቱ ተዉት። የትውልዱ ጊዜ አይባክን።
የንጋት ሰው ነኝ። ማለዳ መንቃት ቀኔን ብሩህ እና ሰፊ ያደርገዋል። በማለዳ ምን ትሠራላችሁ? የማለዳ ጊዜ ረብሻ የሌለበት ነው። አብዛኛው ሰው ማለዳ ላይ እንቅልፍ ላይ ነው። ማለዳ ለጸሎት፣ ለእንቅስቃሴ፣ ለንባብ፣ ለመጻፍ፣ ለማሰብም ጥሩ ጊዜ ነው። በማለዳ ላይ ግን ብዙ በማሰብ ጊዜ መውሰድ ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም። ማለዳ የተግባር መጀመሪያ ጊዜ ነው። ማለዳ ላይ ሀሳብ ወደ ተግባር የሚለወጥበት ጊዜ ነው። ማለዳ ኳስ በአንድ ማሳለፍ የሚፈልግበት ጊዜ ነው። የማለዳን ሀሳብ ሳይንዛዛ ወደመሬት አውርደው ወይ አባርረው። ማለዳ የዕለቱን ፕሮግራም ማጥሪያ ጊዜ ነው። የማለዳን ንፋስ ፊትህን አስመታውና ውሃህን እየተጎነጨህ በለስላሳ ዜማ ቀንህን ጀምር። አዲስ ቀን ስለሰጠን ጌታ ይባረክ።🙏 መልካም ማለዳ! Dawn is a Go-to-Action time. #Go2Action
ለልጆችህ ስለታክስ ለማስተማር ከፈለግህ ከብስኩታቸው ላይ ትንሽ ሰብረህ ቅመስባቸው። ያኔ ምንም አይሉህም። ስለኢትዮጵያ ታክስ ለማስተማር ግን ግማሹን ብስኩት ብላባቸውና ያኔ ምን እንደሚፈጠር ተመልከት። የአብራክህ ክፋይ ልጆችህ እንኳን ምን ቢወዱህ ግማሹን ብስኩት ብትበላባቸው ባይናገሩህ እንኳ ያለቅሳሉ ወይም ይቀየሙሃል ከባሰም ይጠሉሃል። ዋሸሁ እንዴ?
ቢዝነስ ማስተዳደር ፈተና እየሆነ ነው። Yes, it has become challenging to run your business with profit. "አይዞህ!" እያልኩ ላስተዛዝንህ አይደለም። ይልቅስ በብዙ ውጣ ወረዶችና የህግ ለውጦች ውስጥ እንዳለፈ ማኔጀር ወገብህን እንድታጠብቅ ልመክርህ ነው። When the going gets tough, the tough get going ይባል የለ? ጉዞው ሲከብድ፣ ከባዶቹ ብቻ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ ነው ነገሩ። "ዓላማን ማሳካት ክብድብድ ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር፣ ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር " ይላል የኛም ሀገር ሰው የኃይሉ ገብረዮሓንስን ግጥም ሞዲፋይ አድርጎ። እናም ከወትሮው በተለየ መንገድ አስብበት። የቻሌንጅ ዘመን ነው። የቢዝነስ ዓላማ የደንበኞችን ችግር በመፍታት ገቢ እና ትርፍ ማግኘት ነው። ለደንበኞችህ ጥቅም ከሌለህ ገቢ አታገኝም። ይህ የቢዝነስ ሀ ሁ ነው። የቢዝነስ አቡጊዳ ደግሞ ቢዝነስህን ትርፋማ አድርጎ መምራት ነው። የሽያጭ ገቢ ማግኘት ብቻውን ትርፋማ አያደርግም። ገቢህ ለትርፍ የሚያበቃ ገቢ ነው ወይ? ካልሆነ ልታስብበት የተገባ ነው። የግርድፍ ትርፍ መጠንህ ከ30% ካነሰ ልታስብበት የተገባ ነው። አሁን ላይ ያሉ አስተዳደራዊ ወጪዎች ከቀድሞው ይልቅ እየጨመሩ ነው። የባንክ ወለድ ጨምሯል። እሱም ብድር ከተገኘ ነው። የምትወስደው ብድር ወለድ ያዋጣል ወይ? ይህንን ማየት አለብህ። የመንግስት የገንዘብ ጥያቄ ጨምሯል። መንግስት ገና ሳታተርፍ በታሳቢ ታክስ ክፈለኝ ማለት ጀምሯል። ይሄ መቼም ገራሚ ጫና ነው። ልክም ተገቢም አይደለም። የሠራተኛ እና የሙያተኛ ክፍያ ጨምሯል። ይህ እንኳ በሠራተኛው ላይ አይፈረድም። ታድያ ከቀድሞው ይልቅ የአሁን ወጪዎች ከጨመሩ እንዴት ትርፋማ ትሆናለህ? "ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም፤ ለሚመጣው ይታሰብበታል እንጂ" እንዲሉ ትርፍህን ለመጨመር ጥሩ ማኔጅመንት እና አጋዥ አማካሪ ያስፈልግሃል። የቢዝነስ ሜዳው፣ መንገዱ፣ ዙሪያ ገባው Ecosystem ማጥ በማጥ ሆኗል። በድሮው አሠራር መጓዝ ከባድ ሆኗል። ካልነቃህ ገና ደግሞ ይከብዳል። ለቢዝነስህ ጉልበት የሚሰጥ ሬዶታ (ረዳት ማርሽ) ያስፈልግሃል። ብቻህን ተጋፍጠህ የምትችለው ዘመን አይደለም። በዚህ ዘመን ብክነቶችህን ልትቀንስና ብዙ ተጠቃሚዎች ጋ ልትደርስ አስፈላጊ ነው። የተዝናናው የቢዝነስ አሠራር ዘመን አልፏል። ንቃ! በዚህ ዘመን ትርፋማ ሆነህ እንዴት ትኖራለህ? 1. #ፍተሻ:- የውስጥ አሠራርህን ፈትሽ። የውስጥ አሠራርህ እንዴት ነው? ብክነት አለው? የብክነቱ ምንጮች ምንድን ናቸው? ስንት አስገብተህ ስንት ታወጣለህ? ከአንድ ኩንታል ዱቄት ስንት ዳቦ ይወጣል? ከአንድ ኩንታል ጤፍ ስንት እንጀራ ይወጣል? ተወዳዳሪህ 900 እንጀራ እያወጣ አንተ 600 ካወጣህ ተበልተሃል! የውስጥ ችግርህን ፈትሽ። ንቃ! 2. #አስተካክል:- ክፍተትህን አስተካክል። ጉድለትና ክፍተትህን አተካክል። ብክነትን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ክፍተትህን እንዴት እንደምትዘጋው እወቅ። ክፍተትን መዝጋት ቀላል አይደለም። ችግር ችግሩን በፈጠረው አእምሮ አይፈታም። ሌላ ፈቺ ይፈልጋል። እርዳታ ጠይቅ። አንዳንዱ ማስተካከያ ችግሩ ተፈትቶ ሲታይ ቀላል ይመስላል። ግን ቀላል ያደረገው የብዙ ዘመን ልምድ ይሆናልና ለልፋት ሳይሆን ለልምድ ዋጋ ስጥ። አንዳንዱ ማስተካከያ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋልና መጠበቅን ተለማመድ። አንተ ስለቸኮልህ በ6 ወር ልጅ አይወለድምና አትቸኩል። 3. #ተባበር:- አብረውህ ከሚሠሩት ጋር ተባበር። አንተ የያዝከው ሸክም ብዙ መሆኑን አስተውል። The more you invest, the less you become free. ብዙ ኢንቨስት ባደረግህ ቁጥር ነጻነትህ ይቀንሳል። ከሸቀጥ ነጋዴው ይልቅ የባለፋብሪካው ነጻነት ያነሰ ነው። ሌሎቹ ግድ ባይሰጣቸው አንተ ግን ግድ ሊሰጥህና ሌሎችን ልታግባባ ያስፈልግሃል። ብዙ ኢንቨስት አድርገህ ነጻነትህ እንዲጨምር ከፈለግህ ከሌሎች ጋር ተባበር። ከሠራተኞች፣ ከማኔጀሮች፣ ከአማካሪዎች፣ ከተቆጣጣሪዎች ጋር ተባብሮ ማሠራትን እወቅበት። 4. #ስርዓት :- ሲስተምና መዋቅር ዘርጋ። የምትፈልገው ቦታ ለመድረስ ግርግርና ተፍ ተፍ ማለት ብቻ ሳይሆን ሲስተምና መዋቅር ያስፈልግሃል። ሲስተም ከሌለህ የዛሬ ስኬት ነገ አይደገምም። እስኪ የሽያጭ ገቢህን ተመልከት። በየወሩ፣ በየሩብ ዓመቱ እያደገ ነው? ካልሆነ ችግር እየመጣ ነው። በጊዜ ንቃ! 5. #ኢንቨስት :- ለአዳዲስ ሀሳብና አሠራሮች ዋጋ ክፈል። ዘመኑ አዳዲስ አስተሳሰብ የሚፈልቅበትና አዳዲስ አሠራሮች የሚዘረጉበት ነው። AI እየናኘ ነው። ሮቦቶች እየመጡ ነው። አንተ ግን ያልፋል እያልክ በጥበቃ ላይ ነህ። አትሞኝ ንቃ! የድሮው እያለፈና እየተረሳ አዲሱ እየገነነ ነው። የድሮው ስልክ ላይመለስ ሄዷል። ሞባይል ደግሞ አዲስ ደረጃ ላይ ደርሷል። እናም ለአዳዲስ ሀሳቦችና አሠራሮች ጊዜህን፣ ትኩረትህንና ገንዘብህን ክፈል፣ ያውም በደንብ ክፈል። ከፍለህም ባገኘህ። 6. #ለውጥ :- ከለውጥ ጋር ተራመድ። የባንክ አሠራር ላይ ለውጥ አለ። ታክስ አሰባሰብ ላይ ለውጥ አለ። ውድድር ላይ ለውጥ አለ። የአስተዳደር ወጪ ላይ ለውጥ አለ። የደንበኞች አስተሳሰብ ላይ ለውጥ አለ። አንተስ ጋ ለውጥ አለ? ከሌለ Watch Out! ዙሪያህ ሲለወጥ አንተ ከቆምህ የአደጋ ቀለበት ውስጥ ነህ። ለዛሬው ይሄ ይበቃል። ዘመኑን መዋጀት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። በመጨረሻም 7. #ፍጠን :- አትቁም! ጊዜ አታባክን። አማራጮችን ፈትሽ። ተነጋገር፣ ተመካከር፣ ወስን። አንተ ካልወሰንክ ሌሎች ይወስኑብሃል። ፍጠን!