ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት [The Orthodox study bible]
Статистика✝️ ኑ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት ናትና በኦርቶዶክሳዊው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን እናጥና! ✝️ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ጀምረናል! ¶ ዘወትር ማክሰኞ እና ሐሙስ ይጠብቁን ¶ ለአስተያየትዎ በ @teklemaryam19 ይላኩ፡፡
- Последний пост
- 29 апр. 2025 г.
- Последнее чтение
- 15 авг.
- Постов за неделю
- 0
- Всего постов
- 20
- Тип
- открытый
- Язык
- ti
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- —
- 1/48двое суток
- —
- 1/72трое суток
- —
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።” ሮሜ 9፥13 የቀጠለ...👆👇👆👇 👉 የቃሉ ትርጓሜ ምንድነው ቢሉ አስቀድሞ እንደተናገረው “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው...” ሮሜ 8፥29-30 እንዲል የእግዚአብሔር ምርጫ ወሰን የለሽ በሆነው እውቀቱ ላይ የተመሰረተ ነው። እግዚአብሔር ያዕቆብን የወደደው የመረጠውና የጠራው ያዕቆብ ለእግዚአብሔር ፍቅር የሚቀበልና በጎ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ አስቀድሞ ስላወቀ ነው። ኤሳውንም ጠላው የተባለው እግዚአብሔርን ለመቃወምና በእርሱ ላይ ለማመጽ ልቡናውን እንደሚያነሳሳ አስቀድሞ ስለታወቀ ነው። 👉ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ክፍል በተረጎመበት አንቀጽ እንዲህ ይላል "ያዕቆብ የተወደደበትና ዔሳው የተጠላበት ምክንያት ምን ነበር? አንዱ አገልጋይ፣ ሌላኛው ደግሞ ተገልጋይ የሆነው ለምን ነበር? አንደኛው [ኤሳው] ክፉ፣ ያኛው [ያዕቆብ] ደግሞ ደግ ስለነበረ ነው።... ገና ሳይወለዱ እግዚአብሔር 'ታላቁ ለታናሹ ይገዛል' አለ። እግዚአብሔር እንደዚህ ያለው ለምን ነበር? እርሱ ደግ የሚሆነውንና ክፉ የሚሆነው ግብራቸው በጊዜው ጊዜ ተገልጦ እስከሚታይና እስከሚታወቅ ድረስ እንደ ሰው መጠበቅ አያስፈልገውምና፣ አስቀድሞም የትኛው ክፉ እንደሆነና የትኛው ደግሞ እንዳልሆነ ያውቀዋልና ስለዚህ ነው። ...ይህ ገና ሳይወለዱ መመረጣቸው፣ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አስቀድሞ የማወቁ ማሳያ ነው። "ምርጫው ነገሩ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ ከማወቁ [foreknowledge] የተነሳ የሆነ ነው። ገና ምን ዓይነት ሰዎች እንደሚሆኑ በጊዜ ሂደት ከመታወቁ አስቀድሞ የትኛው መልካም እንደሆነና የትኛው መልካም እንዳልሆነ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ ተናገረ። ስለዚህ ሕግንና ነቢያትን ማንበብህ፣ ለዚህን ያህል ረጅም ዘመን አገልጋይ መሆንህን አትንገረኝ ማለቱ ነው(አይሁድን):: ነፍስን መመርመር የሚያውቅበት እርሱ ለመዳን የሚገባው የትኛው እንደሆነ ያውቃልና። ስለዚህ ለምርጫው የማይመረመር መሆን ሕሊናህን አስገዛ። ትክክለኛ በሆነ ሁኔታ መሸለምና ዋጋ መስጠት የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነውና። ለምሳሌ እርሱ የሚመርጠው ለሰው በሚታየው ሁኔታ ቢሆን ኖሮ ከቅዱስ ማቴዎስ የተሻለ የሚመስሉ ስንቶች ነበሩ ይሆን? ሆኖም ያልተገለጡትን ነገሮች ሁሉ ጥርት አድርጎ የሚያውቃቸው እርሱ፣ የሕሊናን ዝንባሌና ትክክለኛ ማንነትና መመርመር የሚችለው እርሱ፣ በጭቃ ውስጥ የወደቀና የተዳፈነ ቢሆንም እንኳ ዕንቁውን ካለበት ለይቶ ያውቀዋል። ስለዚህም ሌሎችኝ ካለፈ በኋላ በእርሱ ውስጥ ባለው ውበት በመደሰቱ እርሱን [ማቴዎስን] መረጠው፣ በልዕልና በተወለደችው ነጻ ፈቃድ ላይ ከእርሱ የሆነውን ጸጋውን በመጨመር የተመሰገነች አደረጋት። ኃላፊና ጠፊ በሆኑት በዚህ ዓለም ጥበቦችና በሌሎች ጉዳዮች እንኳ መልካም የሆኑ ዳኞች በፊታቸው ከሚቀርብላቸው መካከል ሲመርጡ ያልተማሩ አላዋቂ ሰዎች በሚመርጡባቸው መሥፈርቶች ላይ ተመስርተው የሚመርጡ አይደለም፣ እነርሱ ከሚያውቋቸው ነጥቦች በመነሳት ይመዝናሉ ይመርጣሉ እንጂ፣ ከእነዚህ መስፈርቶቻቸው የተነሳም ያልተማሩ ሰዎች የሚያደንቁትንና የሚያመሰግኑትን እነርሱ ግን ይነቅፉታል፣ ችላም ይሉታል።....እንደዚሁም 'ያዕቆብን ወደድሁ ዔሳውን ጠላሁ ' ሲልም ይህን ያለው ፍትሐዊና ተገቢ በሆነ ሁኔታ መሆኑን አንተ የምታውቀው ከሆነ [ግብራቸው በተግባር ከተገለጠና ከታየ በኋላ] ውጤቱን አይተህ ነው፤ እርሱ ግን ከመሆኑ በፊት ግልጽ ባለ ሁኔታ ያውቀዋል። እግዚአብሔር የሚመለከተው የሚመረምረውና የሚመለከተው የሥራውን ሁኔታ ብቻ አይደለምና። ከዚህም ባሻገር ሰው የሚመርጠውን የምርጫውን ሐሳብ ልዕልናና የሕሊና ርትዓትም ነው እንጂ። ...[ትርጓሜ ሮሜ፣ ክፍለ ትምህርት 16:1፤ መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 2. ገጽ.381-383]
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።” ሮሜ 9፥13 👉 በሥጋ ከአብርሃም የተወለዱት [እስማኤልና የኬጡራ ልጆች] ሁሉ የአብርሃም ልጆች ተብለው እንዳልተጠሩ ይልቁኑ በተስፋው ቃል የተወለደው በይስሐቅ እንደተጠራ ከገለጸ በኋላ ከአንድ ማሕጸን ከተገኙት ያዕቆብና ኤሳው ምንም እንኳ የበኩር ሆኖ የተወለደው ኤሳው ቢሆንም የተመረጠው ታናሹ ያዕቆብ እንደሆነ ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተብሎ እንደተነገረ ይናገራል። 'ታላቅ' የተባሉ አይሁድ ናቸው። እግዚአብሔርን በማወቅ ከአሕዛብ ይቀድማሉና። አሕዛብ እርሱን [መሲሁን] በሃይማኖት ሲቀበሉት አይሁድ ግን ክደውታል። አሕዛብ ከእስራት ሲፈቱ አይሁድ ወደ ባርነት ወደቁ። ፊተኞች የነበሩት ኋለኞች ሆኑ። 👉 ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር እስራኤል የተባለ ያዕቆብን ለምን እንደመረጠው ማብራራት ካልተቻላቸው እግዚአብሔር ለዓለሙ ሁሉ ያለውን ሃሳብ እንዴት መመርመርና መረዳት ይችላሉ? ብሎ ሲጠይቅ ነው ይህን ያመጣው። ያዕቆብን ገና ሳይወለድ በእናቱ ማኅጸን ሳለ የወደደው እግዚአብሔር አሕዛብንም የመምረጥና የመውደድ ስልጣን አለው ሲል ነው። 👉 "ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ጠላሁ" የሚለው ቃል አስቀድሞ በነቢዩ ሚልኪያስ የተነገረ ቃል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ተጨማሪ አስረጂ አድርጎ ያቀርበዋች። “ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን፦ በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤” ሚል. 1፥2:: ይህ ቃል ይዘን እግዚአብሔር ያዳላል የሚል ትርጉም እንዳንሰጠው ደግሞ ሐዋርያው “እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም።” ሮሜ 9፥14 በማለት በእግዚአብሔር ዘንድ አመጻ አድልዖ የሌለ መሆኑን ይነግረናል። 👉 ቅዱስ ሄሬኔዎስ በእንተ መናፍቃን በተባለ መጽሐፉ አንዱን አስቀድሞ ለጥፋት ሌላውንም ለሽልማት እንዳልፈጠረ ሲናገር "...ነገር ግን አንዳንዶች በተፈጥሯቸው ክፉዎች ሌሎች ደግሞ መልካሞች ሆነው ተፈጥረው ቢሆኑ ኖሮ እነኚሆቹም መልካም ስለመሆናቸው ምስጋና የሚገባቸው አይሆኑም ነበር፤ ምክንያቱም እንደዚያው ሆነው ከጥንቱ የተፈጠሩ ናቸውና። እነዚያዎቹንም የሚያስወቅሳቸው አንዳች ምክንያት ባልኖረ ነበር፤ ምክንያቱም ከጥንቱ እንደዚያ ተደርገው የተፈጠሩ ናቸውና።" ይላል። ይቀጥላል...👆👇👆👇
መርገመ በለስ "...አዳም በገነት እርቃኑን ሆኖ በየትኛው ቅጠል ነበር እርቃኑን የሸፈነው? ይህች ቅጠል እንዴት እንደደረቀች አየህን?አዳም የሸፈነባት እርቃኑን የሸፈነባት አይደለችምን? ጌታ ኢየሱስ ወደ ለመለመችው የበለስ ዛፍ መጥቶ አዳም እርቃኑን የሸፈነባትን ቅጠል በቃሉ አደረቃት። አዳምን ድሃ ሆኖ ስላገኘው ንጹህ የሆነ የብርሃንንም ልብስ ሰጠው። ይሀውም ብርሃን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰራ ነው። የተጠመቃችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። የበለሱን ቅጠል አድርቆ የነፍሱን ድህነት ሰጠው..." [ ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅ - የሰኞ ጠዋት ግብረ ሕማማት ምንባብ]
እንደምን አመሻችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች? በቀጣዩ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አይኖረንም።መልካም ሰሙነ ሕማማት ይሁንልን።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው።” ሮሜ 9፥8 👉 ቅዱስ ጳውሎስ ከእስራኤል የተወለዱ እስራኤላውያን አይደሉም በማለት በእግዚአብሔር ተስፋ የተነገረለትን መዳንና ጸጋ ለመቀበል በዘር ለአይሁድ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን በመንፈሳዊ የሚደረግ [የሚተረጎም] እንደሆነ ይገልጻል። በሥጋ የአብርሃም ዘር ብቻ መሆን በቂ አይደለም በዘር አይሁድ ነገድ መሆን መዳንን ለማረጋገጥ በቂ እንዳልሆነ ይናገራል። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በአብርሃም ልጆች ይስሐቅና እስማኤል አድርጎ ይሞግታል። ይስሐቅና እስማኤል ሁለቱም የአብርሃም ልጅ ቢሆኑም የተመረጠው ግን ይስሐቅ ብቻ ነበር። ይስሐቅና እስማኤል ከተለያየ እናት የተወለዱ ናቸው። ከአንድ እናት በተወለዱት በያዕቆብና በ ዔሳው ደግሞ ይህን ነገር የበለጠ ግልጽ እየሆነ ይመጣል። እግዚአብሔር የበኩር ልጅ ከነበረው ዔሳው ይልቅ ታናሹ ያዕቆብን መርጧል። ሮሜ.9፥7-11:: "የተስፋው ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ" ማለቱን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተረጉም "ጳውሎስ የሚለን ይስሐቅ በተወለደበት መንገድ የተወለደ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ የአብርሃም ዘር ይባላል። ይስሐቅ በተፈጥሮ ሕግ በሥጋ ኃይል የተወለደ አይደለም ይልቁኑ በተስፋው ኃይል ተወለደ እንጂ።" ይላል። 👉 አንዱም ሊቅ "አብርሃም ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ሁኔታ በአምላክ ቸርነት አባት መሆን ችሏል። ጳውሎስ ይህን የሚለው እስማኤልም የአብርሃም ልጅ ሆኖ ሳለ ነው። ከዚህም በላይ እርሱ [እስማኤል] የበኩር ልጅ ነበር። ስለዚህ እናንተ አይሁድ ስለምን ትታበያላችሁ? እስማኤል ያልተቆጠረው የባርያ [ገረዲቲ] ልጅ ስለሆነ ነው ብላችሁ ብታስቡ ተሳስታችኋል። ቅዱስ መጽሐፍ ዘርን በአባት በኩል እንጂ በእናት አይቆጥርም። ቅዱሱ ሐዋርያ ለአብርሃም ከኬጡራ የተወለዱለትን ልጆች ጠቅሶ ነጻ ከሆነች ሴት የተወለዱ ቢሆንም ዘር ሆነው አለመቆጠራቸውን ማሳየት ይችል ነበር። ...እዚህ ላይ ጳውሎስ ሊያሳይ የፈለገው የአብርሃም ዘር ሁሉ በረከቱን እንዳልተቀበለ ነው። ሌሎቹን ልጆቹን ትቶ ከልጆቹ አንዱ ብቻ [ይስሐቅ] ነው ይህን በረከት የተቀበለው።" በማለት የሥጋ ልጆች የተባሉት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳልሆኑ ያስተምራል። 👉 አንዱም ሊቅ "ጳውሎስ ለዚህ ምሳሌ ሆኖ የቀረበችው ሳራ ብቻ ሳትሆን የይስሐቅ ሚስት ርብቃም ሊመጣ ላለው የእግዚአብሔር ሥራ ምሳሌ [ጥላ] ሆና ቀርባለች። ይስሐቅ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ያዕቆብና ኤሳው የሁለት ሕዝቦች የሕዝብና የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። ...ያዕቆብ የሕዝብ ምሳሌ የሆነው ኤሳውም የአሕዛብ ምሳሌ የሆነው በሥጋ ዘሩ ስለሆኑ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው ግንኙነት የተነሳ ነው። ያዕቆብ የተመሰገነው ከርሱ በሥጋ የሚወለዱት ዘሮቹ ሁሉ የርሱ ልጆች ተብለው መጠራት የተገባቸው ስለሆኑ አይደለም። ኤሳውም የተጠላው ከርሱ በሥጋ የተወለዱት ዘሮቹ ስለተረገሙ [ፍርድ ስላለባቸው] አይደለም። አባቱን አታልሎ የነበረው ያዕቆብ የማያምኑ ልጆች ነበሩት ኤሳውም ደግሞ በእግዚአብሔር የተወደዱ የሚያምኑ ልጆች አሉት። የያዕቆብ ልጆች ሆነው የማያምኑ ብዙ እንዳሉ ጥርጥር የሌለበት ጉዳይ ነው። አይሁድ ሁሉ አማኝም ሆነ የማያምን ዘራቸው ከርሱ ይመዘዛል። የኤሳው ዘር ሆነው መልካምና እምነት የነበራቸው እንደ ኢዮብ ያሉ አሉ። ከአብርሃም አምስት ትውልድ የሚርቅ የኤሳው ዘር ነበር።" ይላል።
የቀጠለ...👆👇👆👇 👉 አይሁዳውያን በአባቶቻቸው በኩል ስለተቀበሉት ብዙ በረከቶችና ከእግዚአብሔርም ስለተሰጣቸው ተስፋ ራሳቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሆኑ ያምናሉ። እግዚአብሔር የሰጠውን ቃልኪዳን [ተስፋ] ለዘላለሙ የማይሻር ነውም ይላሉ። የተነገረው የእግዚአብሔር ቃልም (ቃልኪዳኑ)እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የገባውን ቃልኪዳን ያመለክታል። “የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” ዘፍ. 12፥3 ፤ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ...” ዘጸ. 19፥5 የሚሉት ናቸው። 👉 ቅዱስ ጳውሎስም "የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም" በማለት የሰጠውን ተስፋ የሚሽር የተናገረውን ተስፋ የሚያስቀር አምላክ እንዳልሆነ አጽንዖት ከሰጠ በኋላ አይሁድ የእግዚአብሔርን ቃል መረዳታቸው ላይ እንደሆነ ያስረዳል። እግዚአብሔር "እስራኤል" ብሎ ተስፋ ሲሰጣቸው ለእውነተኛው መንፈሳዊው እሥራኤል [እስራኤል ዘነፍስ] እንጂ ምንም ዓይነት ግብር ቢኖራቸው ቃልኪዳኑን የማይነጠቁ የተወሰኑ ነገዶችን የሚመለከት እንዳልሆነ ያስረዳል። ለዚህም አስረጂ አድርጎ ይስሐቅን ያዕቆብን እያነሳ ይሞግታል። 👉 ሐዋርያው የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል [ተስፋ] ባይሻርም የአይሁዳውያን የተሳሳተ ትርጓሜ [እኛ የእስራኤል ዘሮች ነን] ብለው ማስተማራቸውን ነው የሚቃወመው። ለዚህም ነው 'ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤላውያን አይደሉም' ብሎ የሚጽፈው። ይህንንም አገላለጽ አስቀድሞ በሮሜ ምዕራፍ 2 ጠቅሶታል እንዲህ ሲል:-“በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤” ሮሜ 2፥28:: ይስሐቅ የተወለደው በተስፋው ቃል ነው። በእድሜው ከሸመገለው አብርሃም ምውት ማሕጸን ከነበራት ሳራ የተወለደው ይስሐቅ እንደ ተፈጥሮ ሕግ የተወለደ አልነበረም [መውለድ በማይቻልበት ጊዜ በእግዚአብሔር ተስፋ ተወልዷል] በተስፋው ቃል በእግዚአብሔር ቃል እንጂ። እኛም ክርስቲያኖች [እስራኤል ዘነፍስ] በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት የተወለድን ነን። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚያስተምረው በመጠመቂያው ገንዳ በእግዚአብሔር ቃል እንወለዳለን።ስንጠመቅም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሐዲስ ሆነን በዳግም ልደት እንወለዳለን። ይህ በተፈጥሮ ኃይል የሚደረግ ሳይሆን በእግዚአብሔር የተስፋው ቃል ኃይል ይፈጸማል እንጂ። [ዮሐ.3:3፤ ኤፌ.5:26]። ይስሐቅ እንደሚወለድ አስቀድሞ ተነግሮ እንደተፈጸመ። የእኛም ልደት ከዘመናት በፊት አስቀድሞ በነቢያት የተነገረ [ሆሴ.2:1] በኋላም የተፈጸመ ነው።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖“ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም። እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፥” ሮሜ 9፥6 👉 ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ.9:4-5 ላይ አይሁዳውያን ስለተሰጣቸው በረከቶች ይዘረዝራል። ክርስቶስን ባለመቀበላቸው የተወሰደባቸውን የአይሁድ ተመራጭነት ይናገራል። ለእስራኤል ሕዝብ ተመራጭነት ምልክት ናቸው ብለው ሐዋርያው ያቀረባቸው:- 1. እስራኤል መሆናቸውን- ይሀውም አባታቸው ያዕቆብ በህልሙ ሲታገል ከቆየ በኋላ ካልባረከኝ አልለቅቅህም በማለቱ እስራኤል የሚል ስም ሰጥቶ ባርኮታል:: ስለዚህ እስራኤል ለሚለው ቃል ያዕቆብ የተባረከበት ስም በመሆኑ ለተመራጭነታቸው አንዱ መንገድ ነው። ዘፍ.32:24-28 2.የእግዚአብሔር ልጅነታቸው- ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቶ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ልጁ አድርጎታል። ዘጸ.4:22-23:: እንዲል። ሆሴ.11:1 3.ክብር የተገለጸላቸው መሆኑ -በሲና ተራራ የነበረውና በኋላም በምድረ በዳ አብሯቸው የተጓዘው የእግዚአብሔር ክብር ማለት ነው። ይህም ክብር በታቦቱ የሳጥን መክደኛ ላይ ሆኖ በየጊዜው በመካከላቸው ምልክትን አሳይቷል። ይህም የእግዚአብሔር ክብር ወደ ባቢሎን እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ አልተለያቸውም:: ሕዝ10:4&18:: 4. ቃልኪዳን:- ይህን እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃልኪዳን ነው። ዘፍ.12:1-3:: 5. ሕጉ የተሰጣቸው መሆኑ :- በሲና ተራራ ላይ ሕገ እግዚአብሔር የተሰጠው ለእስራኤል ሕዝብ ነው። ዘጸ.19:40:: 6. አምልኮተ እግዚአብሔር- በመጀመርያ በምስክሩ ድንኳን ኋላም በሰሎሞን ቤተመቅደስ ይከናወን የነበረው የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥነ ስርዓት የተሰጠው ለእስራኤል ሕዝብ ነው። ዘጸ.19:40፤ 1ኛ ነገ 8:9:: 7ኛ. ተስፋ :- በብሉይ ዘመን ብዙ ተስፋ ተሰጥቷቸው ነበር። ዘፍ.35:12፤ ዘጸ.3:15-17:: 8ኛ.አባቶች- እንደ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ያሉ የእምነት አባቶች የነበሩዋቸው በመሆኑ የእነዚያ አባትነት ለበረከት እንደሚያበቃቸው ያምኑ ነበር። 9ኛ. ክርስቶስ በሥጋ የመጣው ከእነርሱ ነው። 👉 ስለዚህ የአይሁድ ሕዝብ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንደ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ የመሳሰሉ ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆኑ አባቶች ስለነበሩባቸው ከመካከላቸውም ብዙ ደጋጎች ስለነበሩ እግዚአብሔር ለነዚያ ደጋግ አባቶች የገባውን ቃልኪዳን ለመፈጸም መረጣቸው እንጂ ከሌሎች ወገኖች ለይቶ በማድላት የመረጣቸው አይደለም። ይህንንም በተብራራ በዘዳ.7:6-12 ላይ "ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና። ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ።" ዘዳ.7:6-8። ይቀጥላል...👆👇👆👇
ከ 60 በላይ ጥያቄዎችና ማብራርያ ትምህርቶች የተካተቱበት የማርቆስ ወንጌል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በዚህ ቻነል 130 ገጽ በሚሆን Pdf በመጽሐፍ መልክ ከለቀቅነው እንደ ቀልድ 5 ዓመት ሆነው። የማርቆስን ወንጌል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን እንዴት አገኛችሁት?
የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና።” ሮሜ 9፥3 👉 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ ኅዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት አለብኝ በማለት በሥጋ ወንድሞቹ ስለሚሆኑ አይሁድ አለማመን ያለውን የልቡና ኃዘን ይናገራል። አይሁድ ለእነርሱ ጠላትነት አለበት ብለው ይከስሱት ነበርና። በዚህም የተነሳ ኅዘንና ጭንቀት እንዳለበት ይናገራል። ይህም ንግግሩ እውነተኛ ስለመሆኑ ሦስት ምስክሮችን ያቀርባል። ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስና ሕሊናውን ምስክር አድርጎ ያቀርባል። ቅዱስ ጳውሎስ እንደ አባቱ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ከራሱ ድኅነት የአይሁድን ድኅነት ሲናፍቅ እንመለከታለን። በምዕራፍ 8 ላይ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየኝ የሚችል አንዳች ኃይል የለም ብሎናል አሁን ደግሞ በሥጋ ወገኖቹ ወንድሞቹ ስለሚሆኑ አይሁድ ሲል ከክርስቶስ ተለይቶ የተረገመ እንዲሆን ይለምናል። በዚህም አገላለጽ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው የሚችል አንዳች እንደሌለ ተናግሮ በመቀጠል ከክርስቶስ ተለይቼ የተረገምኩ እንድሆን እጸልይ ነበር ማለቱ አይሁድ ተመልሰው በክርስቶስ እንዲያምኑ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየናል። ይህ ማለት አይሁድ በክርስቶስ እንዲያምኑ የጳውሎስ ከክርስቶስ መለየት አስፈልጎ ሳይሆን ርሱ ውድ በሚለው አንዳች ኃይል ከርሱ ሊለየኝ አይችልም ባለው በክርስቶስ ፍቅር ምሳሌ በመስጠት ስለእነርሱ መስዋዕት ለመሆን ያለውን ዝግጁነት ሲያሳይ ነው። 👉 የጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር መሆን ማመን አይሁድ በክርስቶስ እንዳያምኑ የሚያደርግ የማሰናከያ ድንጋይ ሆኖ አይደለም። ይልቁኑ ውድ በሚለው አንዳች ኃይል ሊለየኝ አይችልም ያለውን እንኳ አይሁድ ሚድኑ ከሆነ እኔ የተለየሁ ብሆን እመርጣለሁ የሚል የመስዋዕትነትን ፍቅር የሚያመለክት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደ አባቱ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ለአይሁድ ካለው ቅንዓት የተነሳ ከሕዝቡ ኃጢአት የተነሳ ያደረገው የፍቅር መገለጫ ነው። ሁለቱም ተለይተው የተረገሙ ይሆኑ ዘንድ ጸልየዋል። “አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ።” ዘጸ 32፥32 እንዲል። 👉 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ቃል ሲተረጉም እንዲህ ይላል። "ጳውሎስ ሆይ ምን እያልኸን ነው? መንግሥተ ሰማይ ገሃነም የሚታየው የማይታየው ሌላ ዓለም እንኳ ሊለየኝ አይችልም ካልኸው ከምትወደው ከክርስቶስ ተቆርጠህ መለየት ትፈልጋለህን? በርሱ መረገም ትሻለህን? ምን ተፈጥሮ ነው? አንተ ተለውጠህ ነውን የቀደመ ፍቅርህን አውጥተህ ጣልኸውን? አይደለም ጳውሎስ ይመልሳል። ከዚህ በተቃራኒው ለእርሱ ያለኝን ፍቅር የበለጠ አጠነከርኹት እንጂ።" አንድ የእስክንድርያ ሊቅ የክርስቶስን የቤዛነት የማዳን ሥራ ጳውሎስ ራሱን የተረገመ ከማለቱ ጋር አነጻጽሮ ሲያቀርብ እንዲህ ይላል "በእግዚአብሔር ምሳሌ ያለ እርሱ ራሱን ባዶ ካደረገና የባርያውን መልክ ከያዘ ስለ እኛ እርግማን ከሆነ [ገላ.3:13] ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ወንድሞቹ [አይሁድ] ሲል ራሱን የተረገመ እንዲሆን መለመኑ ምን ያስደንቃል? ክርስቶስ ለባሮቹ ርግማን ከሆነ[ሆነ ከተባለ] የእርሱ አገልጋይ ከሆኑት አንዱ [ጳውሎስ] ስለ ወንድሞቹ ርግማን ቢሆን ምን ያስደንቃል?" ይላል።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ መጽደቅ መዳን እንደሚገኝ በቀደሙት ምዕራፎች አብራርቶ ጽፏል። ጽድቅ በክርስቶስ የሚገኝ ከሆነ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ትቷቸዋል የሚል እንዳይኖር እግዚአብሔር ሕዝቡን የተወ እንዳልሆነ ከምዕራፍ 9-11 ባሉት ክፍሎች እያብራራ ይጽፋል:: ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ምዕራፉ 👉 አስቀድሞ የርሱ ወገን ስለሆኑት አይሁድ ያለውን ጭንቀት [ሮሜ.9:1-5] 👉 እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች እነማን እንደሆኑ [ሮሜ.9:6-29] -የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች እንጂ በሥጋ የተወለዱት እንዳልሆኑ፤ - የእግዚአብሔር የምህረቱ ዕቃዎች እንደሆኑ እኚህ ከአይሁድም ከአሕዛብም እንደሆኑ 👉 የእግዚአብሔር ምርጫ መሠረቱ እምነቱ መሆኑን በመግለጽ ያስተምራል። [ሮሜ.9:30-33]
አንብባችሁ ጥያቄ የምትልኩበት የመወያያ Group link ነው 👇👇👇 https://t.me/+VrUcJE_9FV8xZDY0
በቀጣይ ምዕራፍ ዘጠኝን እንጀምራለን። ምዕራፍ ዘጠኝን አንብቡና ስታነቡ ጥያቄ ያስነሳባችሁን ክፍል በመላክ ተሳተፉ።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥” — ሮሜ 8፥38 👉 ቅዱስ ጳውሎስ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየው አንዳች ኃይል እንደሌለ እየዘረዘረ ይገልጻል። "መላእክትም ቢሆኑ" ሲል ቅዱሳን መላእክት ለማለት የተጠቀሰ አይደለም። ቅዱሳን መላእክትማ ወደ እግዚአብሔር እኛን ለማቅረብ የሚተጉ በምልጃቸው በረድኤታቸው የሚያግዙን ናቸው። “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ዕብ. 1፥14 እንዲል ቅዱሳን መላእክት እንድንድን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን የሚረዱን ናቸው። 👉 መላእክት ለምን ተባለ ካልን በመጽሐፍ ቅዱስ መልአክ የሚለው ቃል ለቅዱሳን መላእክት ብቻ ሳይሆን ለሰይጣንና መልዕክተኞቹ እንዲሁም ለምድር ሹማምንት አለቆች የተሰጠ ስም ነው። በራዕየ ዮሐንስ የተጠቀሱት የቤተክርቲያን መላእክት “በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ..." ራእይ 2፥1 እያለ ሲጽፈልን የቤተ ክርስቲያን አለቆች አስተዳዳሪዎችን የሚያመለክት ነው። ከጌታ ሥር ለመማር የመጣው የአይሁድ አለቃ ኒቆዲሞስ በዮሐ.3:1 ላይ "ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤" የሚለውን ግዕዙ "ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወመልአኮሙ ለአይሁድ" ይለዋል። መልአክ ማለት መናፍስትን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን አለቃ ሹም ገዢ ማለትም ጭምር ስለሆነ። ከዚህ በተጨማሪ “ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና። 1ኛ ቆሮ. 4፥9 ሲል የምድር ሹማምንት ገዦች ማለቱ ነው ክርስቲያኖች በምድር ገዦች መከራ ይደርስባቸው ነበርና። "ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ ..." ቆላ.2:18 የመላእክት አምልኮ ማለቱ የጸሐፍት የፈሪሳውያን የአይሁድ አለቆችን አምልኮ ማለቱ ነው። 👉 ከዚህ በተጨማሪ የረቂቃኑ የአጋንንት ፈተና ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል የሚያስተምር እንደሆነ ይናገራል። አንዱ ሊቅ ይህን ሲተረጉም "ሞት ያለው ነፍስን ከእግዚአብሔር ፍቅር የምትለየዋን ሞት ነው ሕይወት የሚለውም ከእግዚአብሔር ፍቅር እኛን ለመለየት የሚታገለንን የኃጢአት ሕይወትን ነው። መላእክትና አለቆች የሚላቸውም ሰይጣንና መላእክቱን እንደሆነ ይጠቁማል...ሰይጣንና መልእክተኞቹ ከእግዚአብሔር ፍቅር እኛን ለመለየት ይተጋሉ ፍቅረ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ሥር የሰደደ ከሆነ በእኛ ላይ ሊያይሉብን አይቻላቸውም።" በማለት መላእክት የተባሉት ሰይጣንና መላዕክቱን እንደሆነ ይገልጻል። ሊቁ አውግሥጢኖስም "አንድን ምዕመን ከእግዚአብሔር ሊለየው የሚቻለው የለም። በሞት የሚያስፈራረው ቢሆን በክርስቶስ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ሆኖ ይኖራልና። ምድራዊ ሕይወትን የሚሰጥም ቢሆን ክርስቶስ [የሚበልጠውን] ዘላለማዊ ሕይወት ሰጥቶናልና። መልአክም ሊለየን አይቻለውም “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።” ገላ.1:8 ተብሏልና።...በማለት መልአክ የተባሉ አጋንንት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩን እንደማይችሉ ይጠቅሳል።
በቀጣይ የሮሜ መልዕክት ምዕራፍ 9ን ስለምንጀምር የሮሜ መልዕክት ምዕራፍ 9ን ሙሉ አንብባችሁ በንባብ ጊዜ ጥያቄ የፈጠረባችሁን ሃሳቦች ጥቅሶች በአስተያየት መስጫው ሥር እንድትልኩ እጠይቃለሁ።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 9 በቀጣይ እንቀጥላለን... በተከፈተው የመወያያ (Discussion] ላይ የሮሜ መልዕክት ምዕራፍ 9ን አንብባችሁ በንባብ ጊዜ ጥያቄ ያስነሳባችሁን ጥቅሶች በመጻፍ እንድትሳተፉ ይሁን። በአስተያየት መስጫው ውስጥም እስካሁን ስላለው ጥናት አስተያየታችሁን ጻፉልን።
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች የ ሮሜ.8:34 ማብራርያ የቀጠለ... [የመጨረሻ ክፍል] 👉 በግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ ሮሜ.8:34 እንዲህ ይነበባል:- "ለእመ ለሊሁ ያጸድቅ መኑ ዘይኴንን ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ ወተንሥአ እምውታን ወሀሎ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ወይትዋቀሥ በእንቲኣነ" ይለዋል። አንድምታችንም "ወይትዋቀስ በእንቲኣነ" የሚለውን ሲተረጉም "ስለ እኛ ይከራከራል። መከራከርስ የለም። ስለ እኛ በዕለተ ዓርብ ባደረገው ተልእኮ ፍጹም ዋጋችንን የምናገኝ ስለሆነ በማለት ይተረጉማል። ቀጥሎም "በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን" 1ኛ ዮሐ.2:1 የሚለውን የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ቃል ሊቃውንቱ ይጠቅሱታል። 👉ኦሪገን የተባለ የእስክንድርያ ሊቅ ሮሜ.8:34ን በተረጎመበት ክፍል "ሐዋርያው "የጠራቸውን ማን ይከስሳቸዋል?" አላለም "የመረጣቸውን" እንጂ ካልተመረጥክ በሁሉ ነገር በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኘህ ካልሆንክ በቀር ከሳሽ ሊኖርህ አይችልም። ክፉ ነገር ቢኖርብህ ክፉ ሥራህም የሚከስስህ ቢሆን ጠበቃ ምን ሊረዳህ ይችላል?... ኢየሱስ እርሱ እውነት ስለሆነ እውነት ደግሞ በሐሰት ስለ አንተ ሊመሰክር አይችልም። ጠበቃም አንተን የሚረዳህ በክፉው ከሳሽህ ክሶች እንዳትሸበር አስቀድሞ በጥምቀት የታጠበልህ የቀደሙት ኃጢአቶችህ በአንተ ላይ ክስ ሆነው እንዳይቆጠርብህ ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ዳግመኛ ብትበድል ይህንንም በንስሐ እንባ ባታጥበው በአንተ ላይ ክስ ያመጣ ዘንድ ለከሳሽህ የክስ ማስረጃዎችን እያቀበልከው ነው። ክርስቶስ ስለ እኛ የሚማልድ ቢሆንም ኢየሱስ ጨለማውን ብርሃን መራራውንም ብሎ ጣፋጭ አይጠራውም።... እርሱ መስዋዕት እንደሆነው ሁሉ ካህንም ነው በባርያ መልክ እንደሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር ምሳሌም ነው። እርሱ ጠበቃ [Advocate] ፈራጅም ነው። " በማለት "የሚማልደው" የተባለው ሊቃውንቱ በአንድምታችን እንደገለጹት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጠበቃ ከመባል ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ይተረጉማል። 👉 ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በመጀመርያይቱ መልዕክቱ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” 1ኛ ዮሐንስ 2፥1 በማለት እንደጻፈልን መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃ [Advocate] ብሎታል። ይሀውም ለተከሳሽ ቆሞ ከሳሽን የሚያሳፍር የሚፈርድም ጭምርን የሚያመለክት ቃል ነው። ጠበቃ ለተከሳሽ ቆሞ ከሳሽን እንደሚያሳፍር ዘወትር ስለኃጢአት እኛን የሚከሰን ጠላት ዲያብሎስ የሚያሳፍር ነውና "ጠበቃ" ብሎታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ ዮሐንስ ላይ “ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።” ራእ. 12፥10 በማለት ከሳሽ የተባለ ዲያብሎስ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ “እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።”ራእ. 12፥11 በማለት ከበጉ ደም የተነሳ ድል እንደነሱት ያመለክተናል። በጌታችን ሞት ድል የሚነሱ ሆነዋልና እንደተባለ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ድል የሚነሳ የሚሸነፍ ነውና። 👉 “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” 1ኛ ዮሐ. 1፥7። እንደተባለው የጌታችን የቆረሰው ሥጋ ያፈሰሰው ደሙ በዕለተ አርብ ያቀረበው መስዋዕት ጋር አንድ ነውና ሥርየተ ኃጢአትን የሚያሰጥ ከሳሽ ዲያብሎስንም የሚያሳፍር ነው። ጌታችን “ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤” ዮሐንስ 14፥30 እንዳለ የዚህ ዓለም ገዢ የሆነ ዲያብሎስ እኛንስ ለመክሰስ ምክንያት ያገኝብን ይሆን? በኃጢአት ወድቀን ከሳሻችንን ድል የምንነሳበት ፍጹም ሥርየተ ኃጢአት የምንቀበልበት ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙን እየተቀበልን ይሆን? ይህ ሁላችንም ለራሳችን የምንመልሰው ጥያቄ ይሁን። ማጠቃለያ:-" እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?" በማለት አነዋወራችን ከእግዚአብሔር ጋር ከሆነ የሚከሰን ኃጢአት ሰይጣን እንደሌለብን ስለ እኛ የሚከራከር የተባለ የወንድሞች ከሳሽን የሚያሳፍር በዕለተ አርብ ባደረገው ተልዕኮ የቆረሰውን ሥጋ ያፈሰሰው ደሙ የኃጢአትና የዲያብሎስን ክስ የሚያጠፋ እንደሆነ የሚገልጽ ምንባብ ነው። ከሳሽ ዲያብሎስን የምናሳፍርበት በፈቃደ ሥጋ ላይ ኃይል ምናገኝበት ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቀው በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ነው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የመሰከሩት እውነት ይህ ነው።
ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት [The Orthodox study bible] pinned «እንደምን ሰነበታችሁ የቻናላችን ተከታታዮች ወንድሞችና እህቶች ለረዥም ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ስለተቋረጠው ጥናታችን ይቅርታ እየጠየቅሁ የተቋረጠውን የሮሜ መልዕክት ጥናት በቀጣይ ሳምንት ካቆምንበት እንቀጥላለን። ቀሪዎቹን ምዕራፎች ከ ምዕራፍ 9 ጀምራችሁ በምታነቡበት ጊዜ ጥያቄ ያስነሳባችሁን ጥቅሶች በውስጥ መስመር እንድትልኩ እጠይቃለሁ። አምላከ ቅዱስ ጳውሎስ የጀመርነውን በሰላም እንዲያስፈጽመን ጸልዩ።»
የቀጠለ...👆👇👆👇 👉 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ቃል ሲተረጉም የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የፍቅሩን ጽናት የሚገልጥ ቃል እንጂ ወልድ ከአብ በክብር አንሶ የሚለምን ማለት እንዳልሆነ አጽንዖት ይሰጣል። “ስለ እኛ የሞተው፣ ከሙታንም የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ስለ እኛ የሚማልደው እርሱ ክርስቶስ ነው” አለ። አሁን ያለው በቀደመ ክብሩ (በእግዚአብሔር ቀኝ ቢሆንም እንኳ ስለ እኛ ማሰብን፣ ለእኛ የሚያስፈልገውን ማድረግን አልተወም፣ አላቋረጠምና። ስለ እኛ መሞት ብቻ ከዚህ በኋላ ይበቃኛል፣ ከእንግዲህ ወዲያስ በቃኝ አላሰኘውምና። አንድ ሰው እርሱ የሚቻለውን ማደረጉ ብቻ ሳይሆን ሌላውን ስለዚያ ሰው መጠየቁም የታላቅ ፍቅር መገለጫ ነውና። “ስለ እኛ ይማልዳል” ሲል ሊገልጽ የፈለገው (የሚገልጸው) ሐሳብ ይህ ነውና። እንዲህ በሰዎች ልማድ እና ወደ ታች ዝቅ ወዳለ ደረጃ ወርዶ እስከ መግለጽ የደረሰው ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማስረዳት ነው። “ለገዛ ልጁ ያልራራለት” የሚሉትን ቃላትም እንደዚሁ ባለ ሁኔታ የማንረዳቸውና የማንወስዳቸው ከሆነ እጅግ በጣም ብዙ ስህተቶች ላይ እንወድቃለንና። ለመግለጽ የፈለገው ዓላማው ይህ ማለትም የክርስቶስ ፍቅር መሆኑን ትረዳ ዘንድ መጀመሪያ “በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” ካለ በኋላ ቀጥሎ “ስለ እኛ የሚማልደው" አለ። ይህም የአብና የወልድን የክብራቸውን አንድነትና እኩልነት ካሳየ በኋላ፣ ለእኛ የሚያደርገው መግቦት የማነስ አለመሆኑን ለማስረዳት “ስለ እኛ የሚማልደው” አለ። እርሱ ራሱ ሕይወት ነውና! የመልካም ነገሮች ሁሉ መገኛ ምንጭ ነውና! ከአብ ጋር በሁሉ ነገር እኩል ነውና! ሙታንን ለማንሣትም ቢሆን፣ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ለማድረግ እኩል ከሃሊ ነውና! (ዮሐ.5፡ 19:21:36) ታዲያ እንዲህ ከአብ ጋር በከሃሊነትና በሥልጣን አንድ የሆነ እርሱ እኛን ለመርዳት ማላጅ መሆን እንዴት ያስፈልገዋል? እንዴት እርሱ አማላጅ ይሆናል? እንዴት ይማልዳል ይባላል? የተፈረደባቸውንና የተኮነኑትን ነጻ ያወጣቸውና ያዳናቸው እርሱ፣ ከሞት ፍርድና ከኩነኔ ነጻ ያወጣና ያዳነ እርሱ፣ ጻድቃንና ልጆች ያደረጋቸው እና እጅግ ከፍ ወዳለ ክብር ያወጣቸው እርሱ፣ ይህን ሁሉ ከፈጸመና ካከናወነ በኋላ፣ ባሕርያችንን በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ካስቀመጠው በኋላ፣ በጣም ቀላል ስለሆኑት ነገሮች ማላጅ መሆን እንዴት ያስፈልገዋል? ሲዖልን በሥልጣኑ የበዘበዘ፣ ሞትን በኃይሉ የሻረ፣ ልጅነትንና ትንሣኤን የሰጠ፣ ባሕርያችንን ከራሱ ባሕርይ ጋር አዋሕዶ በሰማያት በንጉሡ ዙፋን ላይ ያስቀመጠው እርሱ፣ ስለ ጥቃቅን ነገሮች ለምን ለማኝ ማላጅ ይሆናል? ስለዚህ ምልጃን የጠቀሰበት ምክንያት እርሱ ለእኛ ያለውን የፍቅሩን ጥልቀትና ብርታት ፍቅሩ እስከ ምን ድረስ የሚዘልቅ ወሰን የለሽ መሆኑን ለመግለጽ እንጂ ሌላ ምክንያት እንዳልሆነ ተረዳ። አብም ሰዎች ከእርሱ ጋር ይታረቁ ዘንድ እንደሚማልድ ሆኖ ለእኛ ተገልጾልናልና፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን" ተብሏልና። 2 ቆሮ. 5፡20 እንግዲህ እግዚአብሔር ቢማልድም፣ ሰዎች ደግሞ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ቢሆኑም፣ በዚህ አገላለጽ ምክንያት ለእግዚአብሔር ክብር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ልንረዳው አይገባንም። ሆኖም ከዚህ ሁሉ ለእኛ ከተነገረን የምንሰበስበው አንድ መሠረታዊ ነገር ብቻ ነው፤ እርሱም እርሱ ለእኛ ያለውን የፍቅሩን ጽናትና ጥልቅነት ነው። መንፈስ ቅዱስም ስለ እኛ በማይነገር መቃተት የሚማልድልን ከሆነ፣ ክርስቶስም ስለ እኛ የሞተልንና የሚማልድልን ከሆነ፣ አብም ስለ አንተ አንድ ልጁን ያልራራለት ከሆነ፣ እና የመረጠህና ያጸደቀህ ከሆነ፣ ታዲያ ምን የምትፈራው ነገር አለህ? ወይስ ይህን በመሰለ ልዩና ገናና የአባት ፍቅር ውስጥ እየዋኘህ ያለህ አንተ፣ ይህን ያህል ትኩረትና ዋጋ የተሰጠህ አንተ፣ የሚያስፈራህ ምን ነገር ይኖራል ይሆን? " ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ትርጓሜ መልእክተ ሮሜ [መድሎተ ጽድቅ ቅጽ.3] ገጸ ንባብ ይዘን እንዳንጠፋ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። ይህ ዓይነት አገላለጽ በብሉይ ኪዳንም እናገኘዋለን። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት "ተከራከርልኝ ፍረድልኝ የሚበድሉኝን በድላቸው" በማለት በተለያዩ ቦታዎች ጽፎ እናነባለን። ለአብነት ያህል:- “አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።” መዝ. 35፥1 [Plead my cause O LORD that strive with me] “ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፤ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።” መዝ. 119፥154 [Plead my cause, and deliver me:quicken me according to thy word] “አቤቱ፥ ፍረድልኝ፥ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር፤ ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ።” መዝ. 43፥1[Judge me, O God, and plead my cause against ungodly nation] 👉 በእንግሊዝኛው "Plead my cause" የሚለው ቃል "to defend, advocate for or seek justice on some ones behalf" ስለ አንድ ሰው ብሎ መከራከር ጥብቅና መቆምን ያመለክታል። Plead ማለት የቃሉ ትርጉም "መለመን" ማለት ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለተከሳሽ ቆሞ ከሳሽን የሚያሳፍር ፈራጅ አምላክ መሆኑን ያስረዳል። በነዚህ ንባባት እግዚአብሔርን ተከራከርልኝ ፍረድልኝ እያለ የምልጃ በሚመስሉ ቃላት ቢጠቀስም አምላክን አማላጅ የሚከራከር እንደማንለው ሁሉ "የሚማልድ" ተብሎ ስለተጻፈም ከአብ በክብር አንሶ የሚለምን ማለት እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባናል። ይቀጥላል...👆👇👆👇
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 📖 “የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” ሮሜ 8፥34 👉 ከላይ ባለው ክፍል ሮሜ.8:26 "መንፈስ ቅዱስ በማይናገር መቃተት ይማልድልናል" ሲል የመንፈስ ቅዱስ ረዳትነትን ለመግለጽ እንጂ መንፈስ ቅዱስን አማላጅ ከአብና ከወልድ በክብር አንሶ የሚያማልድ እንዳልሆነ ከተገነዘብን በዚህም ክፍል የቃሉን ትርጉም በተገቢው መንገድ መረዳት ይኖርብናል። 👉 የሚያጸድቅና የሚኮንን( ፍርድን የሚሰጥ) አንድ እርሱ ክርስቶስ ከሆነ በተመሳሳይ ምህረትን የሚለምን አማላጅ ብለን እንጠራው ዘንድ አይገባም። ቅዱስ ጳውሎስ “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።” 1ኛ ቆሮ.1:25 ብሎ ሲጽፍልን ቃል በቃል ተጽፏል ብለን ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ሞኝነት ድካም አለበት ብለን እንደማንረዳው ሁሉ "ስለ እኛ የሚማልድ" ተብሎ ስለተጻፈ አማላጅ ነው ብሎ መረዳትም ከእውነት መንገድ መውጣት ነው። እንዲህ ያሉ ገጸ ንባቦች በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ይገኛሉ ትርጓሜው ምስጢሩ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ከስህተት ያድነናል። ✝ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ዓለም ሳለን መከራ እንዳለብን ከተናገረ በኋላ እኛ ከመከራው ለመሳተፍ ዓቅምና ችሎታ አለን ወይ? በፈተናው ብንወድቅስ ከክብሩ ተለይተን ልንቀር ነው ወይ? ፈተናውን ማለፍ አቅቶን ወድቀን ላለመቅረታችን ዋስትናችን ምንድን ነው? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ከዚህም በመቀጠል የገለጻቸው ነገሮች ለዚህ መጽናኛና ማበረታቻ የሚሆኑንን ብሎም ዋስትና የሚሰጡንን ነገሮች ነው። እነዚህም 1ኛ. ከመከራው በኋላ የሚገኘው ክብር አሁን ከምንቀበለው መከራ ጋር የማይመጣጠን ልዩና ታላቅ መሆኑን [ሮሜ.8:18] 2ኛ. ይህ ሊገለጥ ያለው ክብር የክብሩ ተሳታፊና ባለቤት የሆነው ሰው ብቻ ሳይሆን ከክብሩ በቀጥታ የማይሳተፉት ሌሎች ፍጥረታት እንኳ የሚናፍቁት መሆኑን [ሮሜ.8:19-25] 3ኛ. መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን የሚያግዘንና አብሮን የሚሠራ መሆኑ [ሮሜ.8:26-27] 4ኛ. ምንም ነገር ቢመጣብን እግዚአብሔር እንዲያ እንዲሆን የሚፈቅደው ለእኛ ጥቅም ብቻ እንደሆነ ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሚደረግ [ሮሜ.8:28] 5ኛ. እግዚአብሔር በእኛ ላይ ዳኛችን ብቻ ሳይሆን አባታችንም ጠበቃችንም ልክ እንደ ራሱ እኛን ሆኖ የሚያየን ነው። ከ ቁጥር 31-34 ድረስ የሚያብራራው ሐሳብ ይህን ነው። ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ፣ አንድያ ልጁን ስለ እኛ አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሶ የወደደን እስከሆነ ድረስ፣ የሚያጸድቀውና የሚኮንነው (የሚፈርደው) እርሱ ራሱ እግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ፣ ዲያብሎስ ከሚያመጣው ፈተና እና በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚያቀርበው ክስ የተነሣ አንፈራም ማለቱ ነው ብፁፅና ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ። ሰይጣን እኛን በእግዚአብሔር ፊት ሊከስ ቢሞክር፣ ጌታችን የእኛ ዳኛ ብቻ ሳይሆን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የዋጀንና የገዛን ውድ ልጆቹና አካሎቹ ስለሆንን የሰይጣንን ክስ ውድቅ ያደርግበታል እንጂ ለመፍረድ የሚቀመጥ ፈራጅ ብቻ ሳይሆን ልጆቹ፣ አካላቶቹ በመሆናችን የእኛ ክስ አይቀበለውም ማለቱ ነው። ..."የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው” አለ። ይህም ማለት ዳኛው እርሱ እኛን ጻድቃን ያለን ከሆነ፣ ያውም እግዚአብሔርን የመሰለ ዳኛ እንዲህ ያለን ከሆነ፣ ከሳሹን ማን ይሰማዋል? ስለዚህ ፈተናዎችን መፍራትም ሆነ የሰይጣንን ክስ መፍራት የለብንም።...ስለሆነም በቆረሰው ሥጋው ባፈሰሰው ደሙ አምነን በጥምቀት ልጆቹ ሆነን ሥጋውንና ደሙን በልተን አካላቱ የሆንነውን እኛን፣ ከዚያ በኋላም ከእርሱ ጋር አብረን ስንሠራ በመንገድ ላይ በሚገጥሙን በተለያዩ ድቀቶች ንስሐ ገብተን የኃጢአታችን ማስተሥረያ የሆነውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የተቀበልን እኛን እንደ ባዕድ ሰው እንዲሁ ዝም ብሎ አሳልፎ አይሰጠንም። እኛ እርሱን ስለሆንን ዲያብሎስን ያሳፍረዋል እንጂ አይሰማውም። ስለዚህም በዓቅማችን ከክርስቶስ መከራ በምንሳተፈው ሱታፌ በሚገጥሙን ነገሮች ወድቀን ዲያብሎስ ከስሶ ከክርስቶስ ከክብሩ ከመሳተፍ ውጭ እንሆናለን ብላችሁ አትፍሩ፤ ምክንያቱም ይህ ሁሉ ሕያው የሆነ ማጽናኛና ማበረታቻ አለንና ማለቱ ነው። [Excerpts from መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 3] ይቀጥላል...👆👇👆👇
እንደምን አመሻችሁ? ከይቅርታ ጋር የዛሬውን ጥናት ወደ ነገ በማዘዋወር በነገው እለት የምንለጥፍ ይሆናል።