tgindex
✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

✞ ፀሐየ ጽድቅ ✞

Статистика

👉ፀሐየ ጽድቅ የሕይወት መብራት የጽድቅ ብርሃን በዚህ channel ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ ትምህርቶች እና መዝሙሮች እንዲሁም ቅዱሳንን እንዘክራለን ስለቅዱሳን እንማማራለን ዕለታዊ ዜና ቤተ-ክርስቲያ ስንክሳር ግጻዌ ጥያቄና መልስ እንዲሁም በየእለቱ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈስን የሚያለመልሙ ጽሁፎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን፡፡ ቻናሉን ይቀላቀሉ @Tsehaye_Tsidk ሼር ያርጉ!!

Последний пост
13 авг.
Последнее чтение
13 авг.
Постов за неделю
3
Всего постов
27
Тип
открытый
Язык
ti
В каталоге с
13 авг.
Подписчики
1 498
−1 за 5 дн.
Сутки
−2
−0,13%
Неделя
 
Месяц
 
Просмотров на пост
158
27 постов
Вовлечённость
10,5%
к подписчикам
Постов в день
0,4
всего 27
Упоминаний
1
каналов
Охват размещения
оценка
1/24сутки в ленте
76
1/48двое суток
87
1/72трое суток
93

Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.

Посты

  • ነሐሴ 7 ጽንሰታ ለማርያም ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንስቷንና ልደቷን በእርሷም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው። ይህ ጻድቅም ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር የእስራኤል ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቃልሉት ነበርና ። እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር ። ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉ ስለትን ተሳሉ። የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ በላዩ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት አሸለበ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት እንዲህም አለው ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለሙ ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎችም ዐይነ ልቡ ናቸው በእርሷ የሚበራላችውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች። በነቃ ጊዜም ወደ ቤቱ ሒዶ ለሚስቱ ለቅድስት ሐና ነገራት ራእይዋን እውነት እንደሆነች አመኑዋት ከዚህም በኋላ ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን የከበረች ሐና ፀነሰች ለዓለም ሁሉ መመኪያ የሆነች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የአምላክ እናት እመቤታችንን ማርያምን ወለደቻት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ኢያቄምና ሐና ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። (ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ) ~ @Tsehaye_Tsidk

  • የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ (ማብራሪያ) ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡ ፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡   ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡ ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_14.html?m=1 ~ @Tsehaye_Tsidk

  • https://youtu.be/QhsNpy_nY04

  • የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ (ማብራሪያ) ለምስጋና ሦስተኛ፣ ለፍጥረት አራተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ዕለት ከወትሮ ይልቅ መላእክትን አስከትላ እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ከባረከችው በኋላም ምስጋናዋን “ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ…” ብሎ ይጀምራል፡፡ ፩. ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ ሰማይ ዳግሚት ዲበ ምድር - ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ ሆይ! በሦስቱ ሰማያት (በኢዮር፣ በራማ፣ በኤረር) ያሉ መላእክት ንዕድ ነሽ፤ ክብርት ነሽ ይላሉ፡፡ ማርያም የምሥራቅ ደጅ ናት፤ ከእርሷ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ተኝቷልና፡፡ ማርያም ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት፡፡ በሠርግ ቤት የመርዓዊና የመርዓት (የሙሽራና የሙሽሪት) ተዋሕዶ ይደረግበታል፡፡ በእመቤታችንም እንደ መርዓዊና እንደ መርዓት ተዋሕዶ፤ ትስብእትና መለኮት አንድ ኹነዋልና፡፡ በሠርግ አዝማደ መርዓዊና አዝማደ መርዓት አንድ እንዲኾኑባት በእመቤታችንም ምክንያት ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኹነዋልና እመቤታችን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት /ኤፌ.፪፡፲፭/፡፡ አባ ሕርያቆስ “አስተንፈሰ ወአጼነወ ወኢረከበ ዘከማኪ፤ ወሠምረ መዓዛ ዚኣኪ ወአፍቀረ ሥነኪ ወፈነወ ኀቤኪ ወልዶ ዘያፈቅር” እንዲል /ቅዳ.ማር.ቁ.፳፬/ አብ ከሰማይ ኾኖ አየ፤ ነገር ግን እንዳንች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ሰዶ ካንቺ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ ከሌለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት (ክብርት) በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ እዚህ ጋር አንዳንድ ወገኖች የሚያነሡትን ጥያቄ መልሰን እንለፍ፡፡ “ልመናስ ከዚያ በኋላ ስንኳን በሷ (ከበቁ በኋላ) በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ” ስለተባለ ምሥጢሩን ሳይረዱ “ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ አያማልዱም” ለማለት የሚጠቅሱት ወገኖች አሉ፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት በ፲፫ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ጻድቃን ይረክቡ ኵሎ በአሐቲ ተምኔቶሙ በአሐቲ ስእለት - ጻድቃን አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን ኹሉ ያገኛሉ” እንዳለው /ቁ.፻፶፱/ ቅዱሳኑ በአጸደ ሥጋ ሳሉ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ “በስምሽ/ህ ለታረዙ ያለበሰ፣ ሕሙማንን የጐበኘ፣ ዝክርሽ/ህን የዘከረ…” እያለ በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በስማቸው የዘከረ፣ በስማቸው ሕሙማንን የጐበኘ፣ የመጸወተ እንደሚምርላቸው የሚያስረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፣ ዓለምን ዳግም በንፍር ውሃ የማያጠፋትና በየዕለቱ ቀስተ ደመናን የምንመለከተው ፡- “ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ኹሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይኾንም” ብሎ /ዘፍ.፱፡፲፩/ ለኖኅ አንድ ጊዜ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት እንጂ ኖኅ በየዕለቱ እንዲህ ስለሚለምን አይደለም፡፡ “አይለምንም” ሲባል ግን ክብሩን፣ ልዕልናውን፣ መንፈሳዊ ብቃቱን የሚያስረዳ እንጂ ማማለድ አይችልም ለማለት አይደለም፡፡ እንደውም ይህ ኃይለ ቃል ከማማለድ በላይ የኾነ ክብር እንደተሰጣቸው የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ለምኖ በየጊዜው የሚሹትን ማግኘት፤ ዕለት ዕለት እየለመኑ የሚሹትን ከማግኘት በላይ ልዕልናን፣ ክብርን፣ መንፈሳዊ ብቃትን ያሳያልና፡፡ አሁን ቅዱሳንን አማልዱን ስንላቸው አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ደጋግሞ እንደገለጸው ቃል ኪዳናችሁን አሳስቡልን ስንል ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፻፷፬-፻፸፩ ይመልከቱ/፡፡ ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_13.html?m=1 ~ @Tsehaye_Tsidk

  • የሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ማብራሪያ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው #“ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡ ፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡ #ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪ. ዘፍ ፫፥፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡ አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣ ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Genesis/፡፡ #ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡ አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡ ዳግመኛም #በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ እንዲህ አድርገህ በድለሃል ብሎ የመሰከረብህ ሳይኖር ይህን ያህል በፍርሐት መናጥ ከወዴት አገኘህ?” ይላል /Daily Readings of St. John Chrysostom/፡፡ #ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ሆይ! ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ #“ቅድስት” ማለቱ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡ ይኸውም፡- · ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እሷ ግን የዕንቆራው #ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ “ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በሕሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ - ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን (በሕሊናዋም በሥጋዋም) ከድንግልናዋ አልተለወጠችም” /ሃይ.አበ.፶፫፡፳፪/ እንዲል ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና፡፡ · #ጽንዕትም አለ፡፡ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፤ ኋላ ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ ጊዜ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (ወትረ ድንግል) ናትና፡፡ · #ክብርትም አለ፡፡ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን ወለዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ ወልዳልናለች ብለን ነውና፡፡ · #ልዩም አለ፡፡ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች፤ በድንግልናም እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የወለደች፤ እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ሱራፌልም በፍርሐት በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኮት ጌታን ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በዠርባዋ ያዘለች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡ #“ለምኚልን” ሲልም ልክ በዚህ ምድር እንደነበረው ዓይነት ልመና ከዚያ በኋላ ኖሮባት አይደለም፡፡ ስንኳን በሷና በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ፡፡ ይኸውም በቃል ኪዳኗ ማለት ነው፡፡ አንድም በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ማዘከር (ማሳሰብ) አለና፡፡ #“ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለው ቅዱስ ኤፍሬም የተናገረው አይደለም፡፡ “ታድያ ይህን የጨመረው ማን ነው?” በሚለው ላይም ኹለት ዓይነት አመለካከለት አለ፡፡ “ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መከፈያ ተናግሮታል” የሚሉ አሉ፤ “የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል” የሚሉም አሉ፡፡ ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_11.html?m=1 ~ @Tsehaye_Tsidk

  • https://youtu.be/km5ekgo6wG4

  • #የእሑድ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ (ማብራሪያ) በዚህ ዕለት እመቤታችን ከወትሮው ይልቅ ቀደም ብላ መጥታለች፡፡ “ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ዕለታት፤ ወውዳሲያቲሃኒ የዓብያ እምኵሉ ውዳሴያት - ከዕለታት ኹሉ ይህቺ ዕለት ታላቅ ናት፤ ከውዳሲያቱም ኹሉ የዚች ዕለት ውዳሴ ታላቅ ነው” አለችውና ባረከችው፡፡ እርሱም በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት ማለትም፡- በመሶበ ወርቅ፣ በተቅዋመ ወርቅ፣ በማዕጠንተ ወርቅ፣ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል፡፡ ፩. ንዕድ ክብርት ሆይ! ከሴቶች ተለይተሽ የሥላሴ ባለሟል ተባልሽ፡፡ ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ፣ ቅዱሳን ኪሩቤል የተሣሉብሽ፣ ቅዱሳን ካህናት የሚያመሰግኑሽ ኹለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ሕግ የተጻፈባት ጽላት ያለብሽ የምትባዪ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፴፪፡፲፭-፲፱/፡፡ ኪዳንም ያልኹት በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ (በግብር አምላካዊ የተገኙ) ዐሥሩ ቃላት ናቸው፡፡ ዐሥርቱ ቃላትን በጽላቱ ጽፎ እንዳኖረ ኹሉ ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔርም በአፃብዐ መንፈስ ቅዱስ (ያለ ወንድ ዘር፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ) በማኅፀንሽ እንዲቀረጽ ኾኗልና የሙሴ ጽላት አንቺ ነሽ /ቅዳ.ማር. ቁ.፴፫/፡፡ ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብም በነገረ ማርያም መጽሐፉ፡- “… ወማኅፀናሰ ለማርያም ድንግል በክልኤ ይትሜሰል በጽላት ዘተጽሕፈ ውስቴታ ዐሠርተ ቃላት፡፡ ወዐሠርተ ቃላት ቀዳሜ ስሙ ለወልዳ ውእቱ ዘውእቱ የውጣ ዘተሰምየ በኈልቄ ዐሠርተ ቃላት - … በኹለት ወገን ድንግል የምትኾን የማርያም ማኅፀንስ ዐሥሩ ቃላት በውስጧ በተጻፈ ጽላት ይመሰላል፡፡ ዐሥሩ ቃላትም የልጇ የኢየሱስ ክርስቶስ የመዠመርያ ስሙ ነው፤ ያውም የውጣ በዐሥሩ ቃላት የተጠራ ነው” ብሏል /ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን፣ ክፍል ፩፣ ገጽ ፻፳፰፣ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ/፡፡   ከአንቺ ሳይለወጥ ሰው ኾነን፡፡ ለኦሪት ሳይኾን ለወንጌል ሊቀ ካህናት ኾነን፡፡ ለምድረ ርስት ሳይኾን ለመንግሥተ ሰማያት አስታራቂ ኾነን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፤ እርሱም የበደላችን ስርየት ነው” እንዲል በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የኤፌሶንን መልእት በተረጐመበት በአንደኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኘነው ሥርየተ ኃጢአት በርግጥ ታላቅ ነው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በልጁ ደም መኾኑ ግን ከምንም በላይ ታላቅ ነው” በማለት የእግዚአብሔር ከኅሊናት የሚያልፈውን የማዳን ምሥጢር (ፍቅር) በመደነቅ ተናግሯል፡፡ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን ካዳነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡                                                             ፪. ኹል ጊዜ ንጽሕት የምትኾኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ስለዚህ ነገር ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ሰውን ከሚወድ ሰው ከሚወደው ከርሱ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ኹል ጊዜ ዓይነ ልቦናችንን ወዳንቺ እንሰቅላለን፡፡ ሸምሸር ሰጢን ከሚባል ከማይነቅዝ (በአምልኮተ ጣዖት ከማይለወጥ) እንጨት የተቀረጸ በአፍአ በውስጥ በወርቅ የተለበጠ ታቦት አካላዊ ቃልን ይመስልልናል /ዘጸ.፳፭፡፱-፳/፡፡ ይህ ንጹሕ የሚኾን፣ መለወጥ የሌለበት እርሱ ባለመለወጡ አለመለወጧን ነገራት፤ ከአብ ዕሪና ባለመለየቱም አለማለየቷን ነገራት (አምላክ ወሰብእ ኾኖ እርሷም እም ወድንግል መኾኗን ነገራት)፡፡ ከጥበብ በሚበልጥ ጥበብም ዘር ምክንያት ሳይኾነው እንደ እኛ ሰው ኾነ፡፡ አበው፡- “ዓለሙን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ ሰው ኾኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል” የሚሉትም ስለዚሁ ነው፡፡ አደፍ ጉድፍ ሳያገኝሽ መለኮቱን አዋሕዶ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ መለኮቱን አዋሕዶ ሰው ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ ፫.  እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፤ ሙሴ የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሙሴ አንቺ ነሽ፡፡ አንድም እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፣ ሰሎሞን የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሰሎሞን አንቺ ነሽ፡፡ ጌታ በማኅፀንሽ ያደረብሽ አማናዊቷ መቅደስ አንቺ ነሽ፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው አካላዊ ቃል በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን ኾነ፡፡ ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ ፬. መና ያለብሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፲፮፡፴፫-፴፬/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ከሰማይ የወረደና ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀንሽ የተሸከምሽው ነው፡፡ እርሱም “አበዊክሙሰ መና በልዑ በገዳም ወሞቱ - አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም” እንዳለው ያይደለ፤ ይልቁንም ለሰው ኹሉ ሕይወት የሚያድል ኅብስት ነው /ዮሐ.፮፡፶/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ላይ፡- “አስተማሰልናኪ ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት በመሶበ ወርቅ ዘውስቴታ ኅብስተ ሕይወት ዘወረደ እምሰማያት ወሃቤ ሕይወት ለኵሉ ዘየአምን ኪያሁ ወይበልዕ እምኔሁ በአሚን ወበልብ ሥሙር ምስለ እለ በየማኑ - የተለየሽና ደግ የኾንሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ሆይ! የሕይወት ኅብስት ባለበት በወርቅ መሶብ መሰልንሽ፡፡ የሕይወት ኅብስትም በቀኙ ካሉ ጻድቃን ጋር እርሱን ለሚያምን በሃይማኖትና ፈቃደኛ በኾነ ልብ ከእርሱ ለሚበላም ኹሉ ሕይወትን የሚሰጥ ከሰማይ የወረደ ነው” ብሏል /ቁ.፯/፡፡ ዳግመኛም አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫ፡- ኦ መሶብ ቤተልሔማዊት ዘወለደቶ ለኅብስተ ሰማይ ዘኢያብቌልዎ ዝናማት ወዘኢሐፀንዎ አየራት - ዝናማት ያላበቀሉትን አየራት ያላሳደጉትን የሰማዩን እንጀራ የወለድሽው ቤተ ልሔማዊት መሶብ ሆይ” በማለት መስክሯል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ከአባቶች አንዱም፡- “ድንግል ሆይ! በእውነቱ አንቺ ከታላላቅ ይልቅ ታላቅ ነሽ፡፡ ማኅደረ ቃለ አብ ሆይ! አንቺን ሊተካከል የሚችል ታላቅ ማን ነው? ድንግል ሆይ! ከየትኛው ፍጥረት ጋር አወዳድርሻለሁ? አንቺ ቀድሞ በወርቅ ካጌጠችው የሕጉ ታቦት ይልቅ በንጽሕና ያጌጥሽ ታላቅ ነሽ! እውነተኛውን መና የተሸከምሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ፡፡ መና የተባለውም መለኮት የተዋሐደው ሥጋው ነው” ብሏል፡፡ ኅብስተ ሕይወት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ፭. ብርሃንነት ያለውን ፋና የተሸከምሽ የወርቅ ተቅዋም (መቅረዝ) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡ ይኸውም ፋና ለሰው ኹሉ ዕውቀትን የሚገልጽ ብርሃን ነው፡፡ ጥንት ከሌለው ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፡፡ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው ነው፡፡ ሰውም በመኾኑም በድንቁርና በቀቢጸ ተስፋ ለምንኖር ለኛ አበራልን (ዕውቀትን ገልጸልን)፡፡ በጥበቡ ባደረገው ሥጋዌ እግረ ልቡናችንን ወደ ሕገ ወንጌል ጎዳና አቀናልን /ኢሳ.፱፡፩-፪፣ ማቴ.፬፡፲፬-፲፮/፡፡ ታላቁ የዜማ አባት ሊቁ ቅዱስ ያሬድም፡- “አንቲ ውእቱ ተቅዋም ዘወርቅ ዘኢገብራ እደ ኬንያ ዘሰብእ… - የብልሐተኛ እጅ ያልሠራት በውስጧም መብራት የሚያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ፤ ራሱ የአብ ብርሃን ያበራባታል እንጂ፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወደ አንቺ መጥቶ አደረ፡፡ አምላክነቱም በዓለም ኹሉ አበራ፡፡ ጨለማን

  • የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ  (ማብራሪያ) ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡   አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ሊንኩን ተጭነው ሙሉውን ያንብቡ https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_16.html?m=1 ~ @Tsehaye_Tsidk

  • እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ማዳን በወደደ ጊዜ የመጣው በድንግል ማርያም በኩል ነው። እንግዲህ መድኀኒት የሆነው ጌታ በእርሷ በኩል ከመጣ መድኀኒት ፈላጊ የሆነ ሰው እርሷን ደጅ መጥናቱ ምን ይደንቃል? ኦ ድንግል ሰአሊ በእንቲኣነ።      Via Simur Alamirew ~ @Tsehaye_Tsidk

  • የዓርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ (ማብራሪያ) ይህ ዕለት ለምስጋና አምስተኛ ለፍጥረት ስድስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ደናግልን አስከትላ መጥታለች፡፡ ፩. ከሴቶች ተለይተሸ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ሌለብሽ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ቤዴ የተባለ ተርጓሜ መጻሕፍት ይህን አንቀጽ ሲተረጉመው፡- “የመጀመርያው የሰው ልጆች ስሕተት ከዲያብሎስ በእባብ አማካኝነት ወደ ሴት ተላከ፡፡ ሴቲቱም በትዕቢት መንፈስ ወደቀች፡፡ ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ መጣና የመጀመርያዎቹ ወላጆቻችንን አታለላቸው፡፡ ኢመዋቲው ጸጋቸውን ገፈፈው፡፡ ስለኾነም ሞት በሴት ምክንያት ገብቷልና መድኃኒትም በሴት ምክንያት ይገባ ዘንድ ይገባው ነበር፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ አታለላት፡፡ ለሰውም ኹሉ የሞትን ጣዕም አቀመሰችው፡፡ ሌላይቱ ሔዋን ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከ መልአክ የዓለም መድኃኒት የኾነው ክርስቶስን አስገኘች” በማለት እመቤታችን ከሴቶች ኹሉ የመለየቷን ምሥጢር በጥልቀት አስተምሯል፡፡ የማኅፀንሽም ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍሰ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ የሚላን ሊቀ ጳጳስ የነበረውና አምብሮስ የተባለው ሊቅ ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “እመቤታችን አመነች እንጂ አልተጠራጠረችም፤ በመኾኑም የእምነቷን ፍሬ አገኘች፡፡ “ወብጽዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃለ ዘነገሩኪ እም ኀበ እግዚአብሔር - ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ነገር እንዲደረግ የምታምኚ አንቺ ንዕድ ክብርት ነሽ” እንዲል /ሉቃ.፩፡፵፭/፡፡ እናንተ ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገርዋችሁን ነገር እንዲደረግ የምታምኑም ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የሚያምኑ ነፍሳት አካላዊ ቃልን ይፀንሱታል፤ በግብራቸውም ይወልዱታል (ይገልጡታል)፡፡ እንግዲያውስ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርጉት ዘንድ እመቤታችንን ምሰልዋት፡፡ በፈጣሪያችሁ በመድኃኒታችሁ አምናችሁ ደስ ይላችሁ ዘንድ የእመቤታችንን ልቡና ገንዘብ አድርጉ /ሉቃ.፩፡፵፮-፵፯/፡፡ ምንም እንኳን ጌታችንን በሰውነቱ የምትወልደው (የወለደችው) እመቤታችን ብቻ ብትኾንም በእምነት በኵል ግን የኹሉም አማንያን ፍሬ ነውና” በማለት ይመክረናል፡፡ አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ! የጽድቅ ፀሐይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካንቺ ተወልዶም /ሚል.፬፡፪/ በክንፈ ረድኤቱ (በሥልጣኑ) አቀረበን፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ ወጣን፡፡ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ውሉደ እግዚአብሔር ተባልን፡፡ ከምንም በላይ ግን ከኀጢአት ቀንበር ተላቅቀን በሐዲስ ተፈጥሮ ተፈጠርን፡፡ ሥርየተ ኀጢአትን ሰጠን፡፡ ከርኩሰት ኹሉ አነጻን፡፡ ከጸጋው የተነሣ ደቂቀ አዳም የነበርን መላእክት አደረገን፡፡ መላእክቱም ለእኛ በተደረገው ነገር ሐሴት አደረጉ፡፡ ወዮ! ገና ሰዎች ሳለን መላእክት መኾናችን እንደምን ይረቃል እንደምን ይደንቃል? ይህ ኹሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው” /Fr. Tadros Malaty, On the Book of Isaiah 40:31/፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ከፈጠረን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ፪. አምላክን የወልድሽ እመቤታችን ሆይ! ፀሐይ ዘኢየዐርብ (የማይጠልቅ ፀሐይ) የተባለው የብርሃን ክርስቶስ እናቱ ነሽና በአፍኣ በውሰጥ በሥጋ በነፍስ አንቺን ብቻሽን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ልዑላን ከሚባሉ መላእክት አንቺ ትበልጫለሽ፤ ትሑታን ከሚባሉ ከደቂቀ አዳምም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከኀሊናት ኹሉ በላይ ነሽ (ኅሊና የአንቺን ክብር ተናግሮ መጨረስ አይቻለውም)፡፡ ክብርሽን ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው? አንቺንስ የሚመስል ማነው? ሊቁ አባ ሕርያቆስም፡- “ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩ ጥልቅነት ይዋኝ ዘንድ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል” ይላል /ቅዳ.ማር.ቁ.፹፬/፡፡ መላእክት ያከብሩሻል፤ ያገኑሻልም፡፡ ሱራፌልም ያመሰግኑሻል፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ አድሯልና፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ፤ ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለኛ ሰጥቶ ካባቱ ጋራ አስታረቀን፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በ “በእንተ ልደት” ድርሳኑ ላይ፡- “ስለዚህ ሥጋዬን ተዋሐደ! ወንጌልን ሲያስተምር እሰማው ዘንድ ሥጋዬን በተዋሕዶ ገንዘቡ አደረገው! ሥጋዬን ወስዶም መንፈሱን ሰጠኝ፡፡ ሰጠሁ፤ ተቀበልኩም። የእኔን ወስዶ የራሱን ስለ ሰጠኝም ሕይወትን ገንዘብ አደረግሁ፡፡ እኔን ለመቀደስ ሥጋዬን ተዋሐደ፤ የሚያድነኝ መንፈስ ቅዱስንም ሰጠኝ” ብሏል፡፡ ክብር የክብር ክብር ካለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡ ፫. ድንግል ሆይ! የደናግል ኹሉ መመኪያቸው አንቺ ነሽ፡፡ ከእናንተ መካከል “መመኪያነቷ እንዴት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ፩ኛ) ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ወበከመ አውፅአ ብእሲ ብእሲተ ዘእንበለ ብእሲት ከማሁ አውፅአት ብእሲት ብእሴ ዘእንበለ ብእሲ ወሀሎ ዕዳ ላዕለ ትዝምደ አንስት፤ ወበእንተዝ ኮነት ፈዳዪተ ዕዳሃ ለሔዋን - ለወንዶች የሚከፈል ዕዳ በሴቶች ላይ ነበረ፤ ያለ እናት ሔዋን ተገኝታ ነበርና፡፡ ስለዚህም የሔዋንን ብድራት ለአዳም ትከፍለው ዘንድ ድንግል ያለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) ክርስቶስን ወለደችው፡፡ አዳም ያለ እናት ሔዋንን ስላስገኘ እንዳይመካ ድንግል ያለ አባት ክርስቶስን ወለደችው፡፡ ድንቅ በሚኾን አንድነት ይህ አንድ የፍጥረት እኩልነት ይታወቅ ዘንድ” /ሃይ.አበ.፷፮፡፳፱/፤ ፪ኛ) ቀድሞ ወንዶች ሴቶችን በእናንተ ምክንያት ከገነት ወጣን እያሉ ርስት አያካፍሏቸውም ነበር፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ብእሲ ወብእሲት አሐደ እሙንቱ በክርስቶስ - ወንድም ሴትም የለም፤ ኹላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ብሎ እስኪያስተምር ድረስ /ገላ.፫፡፳፰/ በሔዋን ምክንያት ከገነት ብትወጡ በእመቤታችን ምክንያት ገነት መንግሥተ ሰማያት ገብታችሁ የለምን?ብለው የሚመኩ ኹነዋልና፤ ፫ኛ) ደግሞ ለደናግላን አስበ ድንግልናቸውን (የድንግልናቸውን ዋጋ) ስለምታሰጣቸው ሊቁ “ምክሆን ለደናግል” ብሏታል፡፡ ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ https://mekrez.blogspot.com/2013/08/blog-post_1585.html?m=1 ~ @Tsehaye_Tsidk

  • ጾመ ፍልሰታ በነገረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በዓመጽ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጥቶታል፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሠውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልነጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ እርሱም ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት” ሲሉት “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?” አላቸው፡፡  በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠጸ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ኹሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ሥጋዋን እንዲሰጣቸው በጠየቁበት በዚሁ ወቅት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ቢይዙ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ  አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል /ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡ ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፭ ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል /ፍት.ነገ.አን.፲፭/፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)” ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)” እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡ በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመጸነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለተዋሕዶ በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ በተጨማሪም ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ በረከት እና ምሕረትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንቀበልበት ጾም ያድርግልን!!

  • እንኳን ለፆመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ ➡️ ሕጻኑም ➡️ ወጣቱም ➡️ ወንዱም ➡️ ሴቱም ➡️ ዕድሜው የገፍውም ➡️ ሁሉም በፍቅር የሚጾሟት ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት የሚታፈስባት ➡️ ፍቅረ እግዚአብሔር በሰዎች ልቦና የሚሰለጥንባት ➡️ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚያይልባት ➡️ የንስሐና የምህረት ጾም ፆመ ፍልሰታ መጣች። ➡️ በዓለም ያሉ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅደስት ቤተ ክርስቲያን ያሉ ወደ ገዳማት የሚገሰግሱባት....ፆመ ፍልሰታ መጣች።" "ድንግል ሆይ ትንሳኤሽን ያሳየን" ለሐገራችን ኢትዮጵያም ፍጹም ሰላምን ከልጅሽ ዘንድ ለምኝልን! እንኳን አደረሳችሁ. . .🙏❤️ ~ @Tsehaye_Tsidk

  • “መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ" በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ፣ አሜን ! #Ethiopia | በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በሙሉ! የሰውን ወገን ለማዳን የልጁ ማደሪያ ትሆን ዘንድ ድንግል ማርያምን የመረጠ መፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ማርያም ኣደረሰን…

  • “መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ" በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ፣ አሜን ! #Ethiopia | በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በሙሉ! የሰውን ወገን ለማዳን የልጁ ማደሪያ ትሆን ዘንድ ድንግል ማርያምን የመረጠ መፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ማርያም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ! “ወእመሰ ታፈቅሩኒ ዕቀቡ ትእዛዝየ፡- ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ" (ዮሐ.14፥15)፤ ፍቅር የሕያዋን ኣካላት ረቂቅ መገናኛ ነው፣ ሕያዋን ኣካላት በውጫዊው ግዙፍ ኣካላቸው በተወሰኑ ጊዜያትና ቦታ ይገናኛሉ ፤ ስለ ጋራ ጉዳያቸውም በጋራ ይመክራሉ፤ ይበልጥም ይቀራረባሉ፡፡ ይሁንና የሕያዋን ኣካላት ግንኙነት በኣካል በጊዜና በቦታ ብቻ የተወሰነ ኣይደለም፣ በፍቅረ መንፈስ ተገናኝተውም ይግባባሉ፣ ከኣካላዊ ግንኙነት በላይ የበለጠም ይኸው ፍቅረ መንፈስ ነው፤ ከዚህ ኣንጻር እግዚአብሔርንም ማግኘት የምንችለው በዚሁ ፍቅረ መንፈስ ሆነን በእምነት ዓይን ነው! ይህም በመሆኑ ሓዋርያው ቅዱስ ዮሓንስ በመልእክቱ “በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔርይኖራል፣ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል" በማለት ያስተምረናል፣ (1ዮሐ. 4፥16) ይህም ማለት ከሱ ጋር በፍቅር ስንገናኝ፤ እሱም በኛ፣ እኛም በእሱ የመኖሩ ኩነት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! ጌታችን “አፍቅሮ ለእግዚአብሔር ኣምላክከ፤- አምላክህን እግዚአብሔርን ውደደው" በማለት በፍጹም ልባችን እንድንወደው፣ እንደዚሁም ራሳችንን በምንወድበት መጠን እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ማዘዙን እናውቃለን፤ የመውደዳችን መለኪያ ሚዛንና መገለጫ ምልክትም ትእዛዙን ማክበርና መጠበቅ እንደሆነ “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት ኣስተምሮናል ከዚህ ኣኳያ ጌታን መውደድ ማለት ትእዛዙን በመጠበቅ የሚገለጽ ግዙፍ ነገር እንጂ ምናባዊና የማይታይ ድብብቆሽ ነገር ኣይደለም ማለት ነው፣ ጌታችንን የመውደድ ነገር ትእዛዙን በመጠበቅ የሚገለጽ ከሆነ ትእዛዙ ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ኣስፈላጊ ይሆናል፤ ትእዛዙን በጥቅል ስናይ እግዚአብሔርንና ባልንጀራን በመውደድ እንደሚጠቃለል ራሱ ጌታችን ኣስገንዝቦናል፣ በተለይም በባልንጀራችን ላይ የምንከተለው መውደድ ከላይ እንደተገለጸው “እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ" ተብለ በግልጽ ተቀምጦኣል፤ የሰው ባልንጀራ እነማን ናቸው? በሕይወት ያሉት ናቸው? ወይስ የሞቱት? ወገን ዘመድ? ወይስ የሰው ወገን በሙሉ የሚለውንም ማወቅ ኣስፈላጊ ነው፡፡ ጌታችን ነገሩን በዚህ ደረጃ ለያይቶ ኣላስቀመጠም፣ ለምን? ቢባል ባልንጀራ ማለት የተወሰነን የማኅበረ ሰብ ወገን የሚያሳይ ሳይሆን መላውን የሰው ወገን የሚገልጽ በመሆኑ፤ እንደዚሁም የሞቱም ሆኑ ያለነው ሁላችን በእሱ ፊት ሕያዋንና እርስ በእርሳችን ባልንጀሮች በመሆናችን ነው፤ በመሆኑም መዋደዳችንም ሆነ መከባበራችን በሕይወተ ሥጋ ሳለን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ እስከ በሌለው ዕድሜ በመሆኑ ጌታችን በጊዜ በቦታና በከፊል ለይቶ ኣላስቀመጠም፡፡ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት ! ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ለ፲፭ ቀናት የምንጾመው የጾመ ማርያም መነሻ ምክንያቱ የእግዚአብሔርትእዛዝና ፍቅር ነው፣ እግዚአብሔር ሰውን በኣጠቃላይ በተለይም ደግሞ እንደፈቃዱ የኖሩ ቅዱሳንን እንድናከብርኣዞናል ክቅዱሳን ፍጥረታት መካክል ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም የመጀመሪያውን ደረጃ ትይዛለች፤ ይህም በመሆኑ ከፍጥረት ወገን ከሏ ክብር የሚደርስ ባለመኖሩ ከሁሉም ኣብልጠን እናክብራታለን፤ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ደረጃ የድንግል ማርያምን ክብር ስትገልጽ ክእግዚአብሔርና ለባስያነ እግዚአብሔር ክሆኑ ቀደምት ኣበው ተምራ ነው! በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ዕውቁ ቅዱስና ዓለም ዓቀፋዊው አባት ቅዱስ ኤፍሬም የድንግል ማርያምን ክብር! ቅድስና እና ልዕልና ሲናገር “ይእቲ ተዓቢ እምኪሩቤል፡ ወትፈደፍድ እምሱራፌል፣ እስመ ኮነት ታቦተ ለአሓዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ- እሷ ከኪሩቤል ትበልጣለች! ከሱራፌልም ትልቃለች፣ ከቅድስት ሥላሴ ኣንዱ ለሆነው ታቦት ወይም ማደሪያ ሆናለችና" በማለት አስተምሮናል፡፡ በመሆኑም ለስሟ መታሰቢያ በሆነው በዚህ ጾም ድንግል ማርያምን በዚህ ደረጃ ስናክብርትእዛዙን እንጠብቃለን፤ ትእዛዙን በመጠበቃችን ደግሞ እሱን መውደዳችንን እናረጋግጣለን ! እኛ ድንግል ማርያምን እንድንወዳት "እናታችሁ'' ብሎ እንዳዘዘ፣ እሷም ልትወደን “ልጆችዅ ተብላ ታዛለችና ስለኛ ትጸልያለች፡፡ በጸሎቷም ከመከራ ትታደገናለች፤ በኣጠቃላይ በእግዚአብሔር' በቅዱሳንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት በዚህ ትእዛዝና ፍቅር በትዕይንተ ዓለም ባለች ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የተሳሰረ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባዔ የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጣሎትን በማስታረቅ፤ የታመሙትንና የታስሩትን በመጠየቅ፤ ቅዱስ ቍርባንን በመቀበልና ለኃጢኣታችን የንሥሐ ሥርየትን በመለመን ሱባዔውን ልናሳልፍ ይገባል፡፡ በመጨረሻም በሀገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከባድ ስጋት የሆነው የፍጥረት ኣውዳሚ ጦርነትን በመለኮታዊ ጥበቡና ሥልጣኑ እንዲያስቆምልን በቅን ልቡና፤ በትሑት ሰብእና ሆነን እግዚአብሔርን በዚህ ሱባዔ እንድንጠይቀው ኣደራ ጭምር ኣባታዊ መልክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤ የተባረከና የተቀደስ ጾም ያድርግልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ! ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ አሜን! አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ ~ @Tsehaye_Tsidk

  • "በፈተና ጊዜ፥ ደካማው ሰው "እንደዚህ የደረሰብኝ'ኮ" እያለ የሚያመካኝበት ሌላ ሰውን ይፈልጋል፤ ብርቱው ሰው ግን በፈተናው ይጸና ዘንድ እግዚአብሔርን ይፈልጋል፡፡"         ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ~ @Tsehaye_Tsidk

  • በጸሎት ኃይል የሚያምን አንድ ጽኑዕ ክርስቲያን ነበር፡፡ ይህም ክርስቲያን ጥሪት የሌለው ደሃ፣ የሚበላ የሚቸግረው ረሃብተኛ፣ ልብሱ በላዩ ላይ አልቆ የታረዘ ምስኪን ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በጸሎት ሕይወቱ የነበረውን ትጋት በቅርበት ያውቅ የነበረው አንድ ወዳጁ እየተቆጣ 'ቢያንስ ለረሃብህ ማስታገሻ ቁራሽ ዳቦ እንኳን ማሰጠት ካልቻለ የአንተ ጸሎት ፋይዳው ምንድር ነው? ይቅርብህ በቃ! ፈጣሪህ አይሰማህም ማለት ነው' ሲል ተስፋ በሚያስቆርጥ ቃል ተናገረው፡፡ ያም ምስኪን ክርስቲያን እንዲህ ሲል መለሰለት፦ 'እግዚአብሔርማ አልረሳኝም። ለአንዱ ሰው ከዕለት እንጀራው የበለጠ አትርፎ በመስጠት ለእኔ እንዲያካፍለኝ መልእክተኛ አድርጎት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን አደራ የተቀበለው ሰው ዘነጋኝ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሳይሆን አድራሹ ሰው ረስቶኛል!' መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን "የዕለት እንጀራችንን ስጠን" የሚለው ጸሎት ለመነኮሳት ሲሆን "ለዕለት"፣ በዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሲሆን ደግሞ "ለዓመት" የሚሆን እንጀራ ስጠን ማለት ነው። ታዲያ ለምን አንዳንዶች ከዓመት የሚተርፍ ብዙ እንጀራ ሲያገኙ፣ ሌሎች ደግሞ ለዕለት እንኳን የሚሆን ቁራሽ ያጣሉ ? መቼም 'ለሰው ፊት የማያዳላ' እግዚአብሔር "አድልዎ ቢኖርበት ነው" ብለን የድፍረት ቃል በእርሱ ላይ አንናገርም። (ሐዋ 10፥34) ይህ የሆነው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት አትርፈው ያገኙ ሰዎች ምንም የሌላቸውን እንዲረዱ እና መግቦት የባሕርይው የሆነውን አምላካቸውን በጸጋ እንዲመስሉት ነው። በዚሁም ላይ በፈጠራቸው ሰዎች መካከል ያለውን የመተዛዘንና የፍቅር ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ነው፡፡ 'የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ' ብለን የለመንነው አምላክ ከዓመት እንጀራችን በላይ አትርፎ የሚሰጠን፣ የሚበቃንን ያህል ተመግበን በቀረው ለሌሎች አድራሽ መልእክተኞች እንድንሆን ነው። ስለዚህ ይህን የተጣለብንን አምላካዊ አደራ ባለመወጣት ድሆችን አንበድል፤ ተማርረው ከፈጣሪያቸውም ጋር እንዲጣሉ አናድርጋቸው። (ዲያቆን አቤል ካሳሁን) ~ @Tsehaye_Tsidk

  • "ጌታ ሆይ እርሻውን አቃጥለህ ሰብሉን ብትባርክ ምን ይጠቅማል? ዛፉንስ ቆርጠህ ቅርንጫፉን ብትባርክ ምን ይረባል? እናቴ እርሻ ናት እኔ ሰብል ነኝ:: እናቴ ዛፍ ናት እኔ ቅርንጫፍ ነኝ:: እባክህን እናቴ ብትክድ እኔ ባምን ምን ይጠቅማል:: ጌታ ሆይ የእናቴን ልብ በሃይማኖት አጽናልኝ" (ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ስለ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ የጸለየው ጸሎት) ቅዱስ ቂርቆስ ሆይ አንተ ሕፃን ሆነህ ትልቅ ነበርክ:: ትልቅ ሆነን ሕፃን የሆንን እኛን በምልጃህ አስበን! "የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል" መዝ 19፥7 (#ከዲያቆን_ሄኖክ_ኃይሌ_የተወሰደ)

  • ቅድስት ኢየሉጣን አላዊው ንጉሥ እስክንድሮስ "ስምሽ ማን ይባላል?" ባላት ጊዜ "#ክርስቲያን እባላለሁ፤ መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ኢየሉጣ ይባላል" አለችው። ልጇም ቅዱስ ቂርቆስም ተመሳሳይ ጥያቄ በተጠየቀ ጊዜ "ከማይደፈርስ ከንጹህ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ #ክርስቲያን ይባላል፤ መዋቲ ስሜን ከፈለግክ ግን ቂርቆስ ይባላል" አለ። እኛም ሕያው ስማችንን በገቢር መስክረን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ አምላከ ኢየሉጣ ወቂርቆስ ይርዳን!!

  • ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት #Ethiopia | ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ወቅታዊ ጉዳዮች በማስመልከት አባታዊ መልእክት አስተላለፉ ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንደሚከተለው ነው፦ መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! "ገባሬ ሣህል እግዚአብሔር፥ ወይፈትህ ለኩሉ ግፉዓን፦ እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል።" (መዝሙር ፻፪፥፮) ከሁሉ በማስቀደም በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የምትኖሩ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችንን ሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ለሚከበረው፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ በእምነታቸው የጸኑትን ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን በመከራቸው መካከል እየተራዳ የእሳቱን ነበልባል እንደክረምት ውኃ ላቀዘቀዘበት፤ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የታመኑትንም እስከ ሰማዕትነት ፍጻሜ ድረስ የሚያጸና መሆኑን ለምንዘክርበት ታላቅ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የወንጌልን ብርሃን በማብራት፣ የሰላምን መንገድ በማስተማር፣ ፍትሕን በማጽናት፣ የተጨነቁትንም በማጽናናት፣ ሕዝብንና ሀገርን እየደገፈች የኖረች ናት። በዚህ ቅዱስ ተልእኮ ውስጥም መናንያን መነኮሳት እና መነኮሳይያት ዓለምንና ከዓለም የሚገኘውን ጊዜያዊ ክብር፣ ጥቅም፣ ምቾትና የመሳሰሉትን በፈቃዳቸው ትተው፤ በየገዳማቱ በበአታቸው በጾም፣ በጸሎት ተወስነው፤ ሕይወታቸውን በትሕትና ለእግዚአብሔር በመስጠት፤ ስለ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ሀገር፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ሰላምና ስለ ዓለም ደኅንነት በመዓልትና በሌሊት የሚጸልዩ የምድራችን በረከቶች ናቸው። መስቀልን በተሸከሙ፣ ጸሎትን መከታ ባደረጉ፣ ለፍጥረት ሁሉ ምሕረትን በሚለምኑ፣ ራሳቸውን ለመከላከልም ምንም ዓይነት ቁሳዊ ዝግጅት በሌላቸው በእነዚህ መናንያን ላይ እጅን ማንሣት በእግዚአብሔር ዘንድ የተከለከለ፣ በታሪክ ፊትም የሚያሳፍር ድርጊት ነው። የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦረና ወረዳ በግዮን አባይ ገዳመ አስቄጥስ ቅድስት አርሴማ፣ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ቂርቆስ የአባቶችና የእናቶች አንድነት ገዳም ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓመተ ምሕረት በተፈጸመው ጥቃት የመናንያን መነኮሳይያት ሕይወት በግፍ መጥፋቱን፤ በርካቶች መቁሰላቸውን፤ በገዳሙና በንዋየ ቅድሳቱ ውድመት መድረሱን ከሀገረ ስብከቱ መግለጫ በከፍተኛ ሐዘን የሰማን ሲሆን፤ በተመሳሳይም በዚሁ ዕለት በሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት የአምልኮ ሥፍራ በኃይል መፍረሱና በምእመናን ላይ ጥቃት መድረሱ የሚያሳዝንና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው የተወገዘ ተግባር ነው። በመሆኑም የጸሎት፣ የትምህርት፣ የሰላምና የመንፈሳዊ እሴት ማዕከል የሆኑትን ገዳማት መጠበቅ የአንድ ሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ክብርን፣ የሕግ የበላይነትንና የሀገር ሰላምን የማስጠበቅ ሓላፊነት ያላቸው በየደረጃው የሚገኙ ባለሥልጣናትና የሕግ አስከባሪ አካላት ጭምር እንደመሆኑ አሰቃቂ ጥቃት የፈጸሙት ተጠያቂዎች ለፍትሕ እንዲቀርቡ፤ ሌሎች ገዳማትና አድባራት ደኅንነታቸው እንዲጠበቅልን፤ ለተጎዱትም ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግልን ዛሬም አበክረን እንጠይቃለን ። በመጨረሻም ሕዝበ ክርስቲያንና መላው ኢትዮጵያውያን የጥቃት ሰለባ ከሆኑት ወገኖች ጋር በመንፈሳዊም ሆነ በሰብአዊ ድጋፍ አብራችሁ እንድትቆሙ ከአደራ ጭምር እያሳሰብን፤ በጽድቅ የሚፈርደው እግዚአብሔር አምላካችን ለተበደሉት ፍትሕን፣ ለቆሰሉት ፈውስን፣ በግፍ ሕይወታቸውን ለተነጠቁት ዕረፍተ ነፍስን፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ፍጹም ሰላምን ይስጥልን እያልን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን። እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን። አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሐምሌ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ © የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ~ @Tsehaye_Tsidk

  • без подписи