ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት
Статистика''ኦርቶዶክስ ክርስቶስ ያሰባት ፣ ሐዋርያት የሰበኳት ፣ አባቶች የጠበቋት'' ቅዱስ አትናቴዎስ https://youtube.com/@orthodoxy_life?si=jhBnTj5VmIcmXlLb
- Последний пост
- 7 апр.
- Последнее чтение
- 13 авг.
- Постов за неделю
- 0
- Всего постов
- 20
- Тип
- открытый
- Язык
- und
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- —
- 1/48двое суток
- —
- 1/72трое суток
- —
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
በሰሙነ ህማማት ወቅት የምንሰማቸው እንግዳ ቃላትና ትርጉማቸው በግብረ ሕማማት ውስጥ በግዕዝም ሆነ በኋላ በአማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የእብራይስጥ፣ የቅብጥና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ። የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፦ #ኪራላይሶን፦ ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ < ኪርዬ ኤሌይሶን> ነው። #ኪሪያ ማለት እግዝእትነ / እመቤታችን" ማለት ሲሆን "ኪርዬ" ማለት ደግሞ "እግዚኦ / ጌታ ሆይ / አቤቱ" ማለት ነዉ፡፡ "ኤሌይሶን" ማለት ደግሞ "ማረን / ይቅር በለን" ማለት ነዉ ፡፡ ትርጉሙም "አቤቱ ማረን" ማለት ነዉ፡፡ "ኪራላይሶን" የምንለዉ በተለምዶ ነዉ፡፡ ይኸዉም "ኪርዬ" ከሚለዉ "ዬ" ኤሌይሶን" ከሚለዉ ደግሞ "ኤ" በመሳሳባቸዉ በአማርኛ "ያ"ን ፈጥረዉ ነዉ፡፡ #ናይናን፦ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ "መሐረነ፤ማረን" ማለት ነው። #እብኖዲ ፦ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ "አምላክ" ማለት ነው። "እብኖዲ ናይናን" ሲልም " አምላክ ሆይ ማረን" ማለቱ ነው። #ታኦስ ፦ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ "ጌታ፣አምላክ" ማለት ነው። #ማስያስ ፦ የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ "መሲህ" ማለት ነው። #ትስቡጣ ፦ "ዴስፓታ" ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም "ደግ ገዥ" ማለት ነው። #አምነስቲቲ_ሙኪርያቱ_አንቲ_ፋሲልያሱ፦ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ "ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግስትከ- አቤቱ በመንግስትህ አስበኝ" ማለት ነው። #አምነስቲቲ_ሙዓግያ_አንቲ_ፋሲልያሱ፦ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ " ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግስትከ -ቅዱስ ሆይ በመንግስትህ አስበን" ማለት ነው። #አምነስቲቲ_ሙዳሱጣ_አንቲ_ፋሲልያሱ፦ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ " ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግስትከ -የሁሉ በላይ የሆንክ ሆይ በመንግስትህ አስበን " ማለት ነው።
"አንተ ብቻ ቃል ተናገር" ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ። ማቴዎስ 8: 5-13
ከማር የሚጣፍጥ፣ ከሽቶ የሚወደድ ስም፤ ኢየሱስ! በዚህ ዓለም ላይ እንደ ኢየሱስ ስም ያለ ጣፋጭና ኃያል ስም የለም። ይህ ስም የነፍስ መድኃኒት፣ የልብ ሰላም ነው! ምድራዊ ማር ምላስን ብቻ ያጣፍጣል፤ "ኢየሱስ" የሚለው ስም ግን መራራውን ሕይወታችንን ወደ ጣፋጭነት ይለውጣል። በኀዘን ለተሰበረ ልብ ብርታትን፣ ለደከመች ነፍስ ኃይልን ይሰጣል። ምድራዊ ሽቶ መዓዛው ውሎ ያድራል፤ የጌታ ስም ግን ለዘላለም የማይጠፋ፣ የኃጢአትን ሽታ አስወግዶ ቅድስናን የሚያለብስ የሕይወት መዓዛ ነው። ሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ሳትጠራው ውላ አታድርም "ስምህ የሚጣፍጠው ኢየሱስ" ትለዋለች። ዛሬ ደግሞ በትንቢቱ መሠረት በቤተ መቅደስ "ኢየሱስ" ተብሎ የተጠራበት ዕለት ነው ዕፍረት ዘተሰውጠ ስምከ/ ስምህ እንደሚፈስ ሽቱ ነው መኃ 1÷3 መ/ር ብርሃኑ ተክለያሬድ
ተፈትኖ መማር “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።” ሉቃ. 22 ፡ 32 ። ጌታችን ለጴጥሮስ የተናገረው ድንቅ ተስፋ ነው ። ጴጥሮስ እንደሚወድቅ ጌታ ተናግሯል ። እምነቱ እንዳይጠፋ ግን ጌታ አሰበው ። ከጌታ ጋር እሞታለሁ የሚለው እምነቱ ቢጠፋ ፣ የጠፋውን ልጁን ጌታ ይቀበላል የሚለው እምነት እንዳይጠፋ አገዘው ። በእሳትና በስለት ፊት ለጌታችን ታማኝ መሆን ሊያቅተን ይችላል ፣ ከአንድ ወታደር ፣ ከአንድ ታማኝ ሎሌ አንሰን ልንገኝ እንችላለን ። እግዚአብሔር እኔን አይቀበለኝም የሚል አስተሳሰብ ግን ከባድ ነው ። መውደቅ ቢያቅት የጌታ እጅ እንዲያነሣን እጅን መዘርጋት ግን ተገቢ ነው ። የጴጥሮስ የድፍረት እምነቱ ቢጠፋም የመመለስ እምነቱ ግን አልጠፋም ። ለሰዎች እንዲጸኑ ለምነን ቢያቅታቸው ፣ ለመመለስ ግን ልቡን እንዲያገኙት መጸለይ አለብን ። ዛሬ የወደቀ ሰው የሁልጊዜ ውዳቂ አይደለም ፣ በመሠረቱ የሚወድቅ የቆመ ፣ የተራመደና ከፍ ያለ ቦታ የተቀመጠ ነው ። የወደቁ ሰዎች ሁሉ ትላንት ሌላውን የሚደግፉ ፣ ወደ ዓላማቸው የሚገሰግሱ ፣ በክብር ላይ የነበሩ ናቸው ። የወደቁ ሰዎች ትልቅ ፈተናቸው እግዚአብሔር እንደሚምራቸው እምነት ማጣትና ማፈር ነው ። ሰይጣን በሐፍረት ይዋጋቸዋል ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሚል ትልቅ እንቅፋትም ይይዛቸዋል ። እነዚህን ሰዎች ማበረታታት ለእነርሱም መጸለይ ይገባል ። የወደቀን የሚረዳ መውደቅን ያወቀ ነው ። ጌታችን ለጴጥሮስ “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ።” ሉቃ. 22 ፡ 32 ። ጴጥሮስ እንደሚመለስ ፣ ውድቀት በትንሣኤ እንደሚለወጥ ጌታ ነገረው ። ሰዎች የምናይላቸውን ከፍታ ይወርሳሉ ። የሚሄዱትም ወደ ተናገርንላቸው ተስፋ ነው ። በሰዎች ላይ ያለን እምነት አንድ ቀን ራእያቸው ይሆናል ። ቃል ያነሣል ፣ ቃል ይጥላል ። ሰዎች አሁን ያሉበትን ውድቀት ሳይሆን ነገ ላይ የሚኖራቸውን ከፍታ ማየት አስፈላጊ ነው ። ሰው በቆመበት ቦታ አይኖርምና ። ብዙ እልፍ የምናደርጋቸው ሰዎች አሉ ። የቆመ ሰው የማቆም አቅም አለው ። እልፍ ስናደርጋቸው እልፍ ነገር ይሰጡናል ። ሰው ባዶ ሊሆን አይችልም ፣ ወይ ያሳርፈናል ፣ ወይ ያስጨንቀናል ። በሰዎች ላይ የምናፈሰው መዋዕለ ንዋይ መልሶ ለራሳችን ነው ። ጌታችን ከጴጥሮስ ውድቀት ባሻገር እንደሚመለስና ለብዙዎች መጽናናትና መጽናት ምክንያት እንደሚሆን ተናገረ ። ውድቀት ይህን የማስገኘት አቅም ስላለው ሳይሆን እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ ስለሚያስተምር ነው ። የወደቀ ሰው ይህም ያልፋል ብሎ መምከር ይችላል ። የወደቀ ሰው የሌላውን ቍስል መረዳትና ስሜትን መካፈል ይችላል ። የወደቀ ሰው የወደቀን መርዳት ይችላል ። ብዙ ሰው አቅም አለው ፣ ስሜታዊ እርዳታ ስናደርግለት ከእኛ የተሻለ ብርታቱን ማውጣት ይችላል ። ሰዎች የሚገነዘባቸው ሰው ይፈልጋሉ ፣ የሚፈርድባቸውንና ሊገባው የማይችለውን ሰው ይሸሻሉ ። የሚገነዘባቸውን ሰው ይፈልጋሉ ። ሕመምን ከታመመ ጋር ማውራት የስሜት ደጋፊ ማግኘት ነው ። ጴጥሮስ የወደቀው በጠማማነት አይደለም ። አንዳንድ ሰው ማፍቀር ፈልጎ ራሱን በጥላቻ ውስጥ ያገኘዋል ። ኳስ በጣም የሚወዱ ግን መጫወት የማይችሉ ብዙ ሰዎች አሉ ። ጴጥሮስ ጌታን በጣም ማስደሰት የሚፈልግ ግን ያልቻለ ሰው ነው ። ጌታም በተግባሩ ሳይሆን በመሻቱ ተቀበለው ። ሜዳው ላይ ሲደርሱ ነገሮች እንዳሰብናቸው ቀላል ላይሆኑ ይችላሉ ። ለማፍቀር ወጥቶ የሚሰበረው ፣ የሚያዝነው ፣ ራሱንና ያፈቀረውን የሚጎዳው የገጠመውን ነገር ማስተዳደር አለመቻሉ ነው ። ሲዋደዱ መጣላትም እንዳለ አስቦ መዘጋጀት መልካም ነው ። ጥንቃቄ ጥርጣሬ አይደለም ። የሰዎችን መሻታቸውን መገንዘብ ብንችል በተግባራቸው ብቻ አንገመግማቸውም ። ለእኛ ያላቸው አስተሳሰብ ምን እንደሆነ በማሰብ በመሻታቸው ተግባራቸውን ይቅር ማለት አለብን ። አንዳንዶች ጥሩ ፊት ያሳዩናል ፣ ጥሩ ቃል ይናገሩናል ፣ ልባቸው ግን ጩቤ ነው ። ከጀርባችንም ጦር የሚሰብቁ ፣ አድማ የሚፈጥሩ ናቸው ። ሌሎችንም የምንርቃቸው ለራሳቸው አልሆኑምና ለእኔም አይሆኑም ብለን ነው ፣ ይህም መታሰብ አለበት ። ጴጥሮስ የወደቀው ከመጠን በላይ በራሱ በመደገፉ ነው ። በራስ መደገፍ በትልቁ ጸሎትን ያስረሳል ። የሚጸልይ ሰው ሲገጥመንም እንደ ሰነፍና እንደ ፈሪ እንድናየው ያደርገናል ። ትምክሕት መዘናጋትን ያመጣል ። በዚያ ጉዳይ ላይ ዝግጅት ስለማይኖረው በራሱ የሚመካ ሰው ቶሎ ይወድቃል ። ትምክሕት የጸሎት ጠላት ነው ። መጸለይ ባቆምንበት ጉዳይ የምንወድቀው ጠላት በመዘናጋታችን ስለሚያገኘን ነው ። ትምክሕት ፈራጅ ያደርጋል ፣ ሌሎች አይረቡም እንድንል ያደርጋል ። ብዙ ጊዜ የሚታመሙ ረጅም ዘመን ይኖራሉ ። ከበሽታው ጋር ይላመዳሉ ፣ ይጠነቀቃሉ ። ታሞ የማያውቅ ግን ጥንቃቄ ስለሌለው የተጎዳ ቀን መቋቋም ይከብደዋል ። አልወድቅም ብሎ የሚያስብም ድንገት ሊወድቅ ይችላል ። በሕይወት ውስጥ ተፈትኖ ማለፍ ዓላማው የሚፈተኑትን ለማጽናናት ነው ። እግዚአብሔር በዚያ ፈተና ውስጥ ያሳለፈን ባለፍንበት መንገድ ለሚያልፉት ውኃ እንድናቀብል ነው ። ፈተናችንን መማሪያና ማስተማሪያ ካደረግነው ያ ጊዜ አልባከነም ። መምህር አስተምሮ ይፈትናል ፣ ሕይወት ግን ፈትና ታስተምራለች ይባላል ። ዲ.አ.መ ታኅሣሥ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.
አንድ ቀን አለ ለዘመናት የጠበቅነው ወረፋ የሚደርስበት ፣ ስማችን ተጠርቶ የምንሸለምበት ፣ አደባባዩን የምንወርስበት ፣ ጥላቻን በፍቅር የምንለውጥበት ፣ ርግማኑ ቀርቶ ምርቃት የሚዘንብበት አንድ ቀን አለ ። ስህተታችን የሚታረምበት ፣ ውድቀታችን በትንሣኤ የሚለወጥበት ፣ ቀና ብለን የምንሄድበት ፣ በሕሊናችን ፊት ነጻነት የምናገኝበት ፣ ተስፋ ለቆረጡብን ተስፋ የምንሆንበት አንድ ቀን አለ ። የገፉን የሚያፍሩበት ፣ ስድብ የተለማመዱብን ምን ሆኜ ነበር? የሚሉበት ፣ የከሰሱን የሚመሰክሩበት ፣ ሞታችንን የተመኙ ዕድሜ ይስጣችሁ ብለው የሚመርቁበት አንድ ቀን አለ ። ያልተረዳናቸውን ሰዎች የምንረዳበት ፣ ስህተት የመሰለን እውቀታቸውን የምናከብርበት ፣ የእነርሱ መኖር ለእኛ በጣም የሚያስፈልግበት ፣ የወዳጅን ዋጋ የምናውቅበት አንድ ቀን አለ ። ያለፋን ኑሮ የሚሸነፍበት ፣ የተጫነን ደመና የሚገፈፍበት ፣ ሞት ሞት ያሰኘን ትግል ገለል የሚልበት ፣ የተሰናበትነውን ፍቅር ሰላምታ ሰጥተን የምንጀምርበት አንድ ቀን አለ ። ያስተማሩንን የምናመሰግንበት ፣ ያሳደጉንን የምናኮራበት ፣ ልጅነታችንን ያልናቁትን የምናከብርበት ፣ ልጄ ላሉን ልጅ የምንሆንበት አንድ ቀን አለ ። እንደ ኒቆዲሞስ በጨለማ ተምረን በገሀድ የምንሸኝበት ፣ ፍርሃታችንን የምንታዘብበት ፣ ከሰፈር ፍርድ የምንወጣበት ፣ የሰውን ሰውነቱን አቃለን ተስፋ ቢስ ባደረግንበት የምንጸጸትበት አንድ ቀን አለ ። ረሀባችን ዳርቻ ፣ ጥማታችን ድንበር የሚያገኝበት ፣ የሰው ያለህ እንዳላልን በሰው የምንከበብበት አንድ ቀን አለ ። ትዕግሥቱን ቸል ብለን ፣ ቃሉን ተጋፍተን ፣ ፍርድ እንደሌለ ራሳችንን አሞኝተን የተጓዝንበት መንገድ የሚቀጣበት አንድ ቀን አለ ። የተሰጠንን መብት ያባከንበት ፣ በረከታችንን ያድፋፋንበት ፣ ሥራችንን ያቃለልንበት ምርጫ የሚዳኝበት አንድ ቀን አለ ። በፈረድንበት ፍርድ የምንገኝበት ፣ “የወረወርሁት አንካሴ መልሶ ለራሴ” ብለን እያለቀስን የምንማርበት አንድ ቀን አለ ። የሚወዱንን መለየት አቅቶን የሚጠሉንን ለማሳመን የሮጥንበት ፣ የወደድነውን አጥተን የጠላነውን የምንቀላውጥበት አንድ ቀን አለ ። የማይሞቱ መስለውን ያሳዘናቸው ወላጆቻችን ፣ ሲፈልጉን የራቅናቸው ወዳጆቻችን ምነው ዛሬ ባገኘኋቸው ብለን የምናጣበት አንድ ቀን አለ ። ተባብረን ምስኪኑን ያጠቃንበት ፣ አድማው ፈርሶ እርስ በርስ የምንበላላበት አንድ ቀን አለ ። ሥልጣን አገኘሁ ብለን ደጉን የገፋንበት ፣ አውርቶ አደሮችን ያከበርንበት እንደ ሥዕል የሚመጣበት ፣ እየተገረፍን የምንማርበት አንድ ቀን አለ ። በቁመናቸው ያልሰማናቸውን ፣ ጥበባቸውን ጋርደው ያለፉትን ፣ ምነው ባልተማርሁ ብለው የተጸጸቱትን አዋቂዎች መቃብራቸውን ይቅርታ የምንጠይቅበት አንድ ቀን አለ ። ወገን ለይተን ያሳደድናቸውን ፣ ዘረኛ ሆነን ያፈረስናቸውን ፣ ሕፃናትን ሳይቀር የጠላንበትን ያንን ክፉ አእምሮአችንን የምንወቅስበት አንድ ቀን አለ ። የማንሞት መስሎን የገደልንበትን ፣ የማናጣ መስሎን የቀማንበትን ፣ የማንዋረድ መስሎን ያዋረድንበትን ፣ የማያልፍ መስሎን ሰባሪ ቃል የተናገርንበትን በእጥፍ የምንሸከምበት አንድ ቀን አለ ። ትዕግሥተኛው አምላክ ፈራጅ ነው ፣ ፈራጁም መሐሪ ነው ። አልገባ ያለን እውቀት እንደ ቀትር በነፍሳችን ላይ የሚበራበት ፣ የተሰወረ ጥበብ ገንዘባችን የሚሆንበት ፣ መጋረጃው ተቀዶ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት አንድ ቀን አለ ። ፈርተን እንዳላነጋን በዕረፍት የምንተኛበት ፣ ተሸማቀን እንዳልተሰማራን በእምነት የምንወጣበት ፣ እንዳላቀረቀርን ቀና የምንልበት አንድ ቀን አለ ። እግዚአብሔር እኛን የሚጎበኝበት ፣ ከተራብንበት ቤት የምንጠግብበት ፣ የተሸከሙንን የምንሸከምበት ፣ ያከበሩንን የምናከብርበት ፣ የዋሉልንን የምናደንቅበት አንድ ቀን አለ ። ቀን የእግዚአብሔር ባሪያ ነው ። ቀኑን ለእኛ የሚያስገዛበት ፣ ያለፉ ወራቶች የሚካሱበት አንድ ቀን አለ ። ሃምሳ ዓመት ዘርተን ያላጨድነውን በሃምሳ ደቂቃ የምናጭድበት ፣ እግዚአብሔር ሲዋጋ በዝማሬ የምንቆምበት አንድ ቀን አለ ። እንደ ሰው የምንቆጠርበት ፣ ተሸልመን በጸጋው የምንከብርበት አንድ ቀን አለ ። እዚች ቀን ለመድረስ አንደበታችንን እንጠብቅ ። ይህችን ቀን ለማየት ከፈለግን የነቢዩን ምክር እንስማ፡- “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው ? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ ? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ ። ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም ።” (መዝ. 33 ፡ 12-14) ። ዲ.አ.መ ታኅሣሥ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. https://t.me/orthodoxy_life
አንድ ጊዜ አንድ ጎብኚ (ቱሪስት) የአንድን መመነኵሴ በኣት ተመልክቶ፡-“የቤት ዕቃዎችህ የት አሉ?” ሲል ጠየቀው፡፡ መነኵሴውም ለቱሪስቱ መልሶ፡- “የአንተ የት አሉ?” አለው፡፡ ቱሪስቱ በዚህ ጊዜ፦እዚህ እኔ ቱሪስት ብቻ ነኝ አለው፡፡ መነኵሴውም መልሶ፡- “እኔም እንዲሁ ነኝ” አለው፡፡ሆኖም የቅዱሳን አንድ ጥሪት ክርስቶስ በመሆኑ እንዲህ ተብሎ የተገለጸ ነው፡፡ “አምላክ ያደረበት አሞንዮስ ለቅዱሳን አንድ ጥሪት አላቸው ብሎ የተናገረው ፀሐይ ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ። "ኦ መነኮስ ሕይወትከሰ ዘበአማን እግዚአብሔር ዉእቱ "
የቅዱስ አንብሮስ የንስሐ ጸሎት "ቁስሌን የሚፈውስልኝ ጌታ ኢየሱስ ሆይ አንተን ብቻ እከተላለሁ ፡፡ በአንተ ካለው የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ይለየኛል? መከራ ፣ ጭንቀት ወይስ ረሃብ? በምስማር እንደ ተያዘ እኔ በፍቅር ሰንሰለቶችህ ታስሬአለሁ። ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ኃጢአቶቼ በበረታው ጎራዴህ ከእኔ ቁረጥ ፡፡ በፍቅርህ እስራት ጠብቀኝ በእኔ ውስጥ ያለውን የተበላሸውን ነገሬ አስወግድ ፡፡ በፍጥነት ወደ እኔ ና የበዛውን ፣ የተሰወረውንና የደበቀውን መከራዬን ፍጻሜ አበጅለት ፡፡ አንተ የቆሸሸውን በውስጤ ያለውን አፅዳ፡፡ በኃጢአቶቻችሁ ውስጥ ሰካራም ሀሳቦችን የምታወጡ ፤ እናንተ ምድራዊ ሰዎች ሆይ ስሙኝ ፈዋሼን አጊንቻለሁ ፡፡ እርሱ በሰማያት ተቀምጧል በፈውሱ ምድርን ሞልቷል። እርሱ ብቻ ህመሜን ሊፈውስ የሚችለው። እሱ ብቻ ነው። እርሱ ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰወረውን የሚያውቅ ፣ የልቤን ሀዘን ፣ የነፍሴን ፍርሃት ሊያስወግድ የሚችል። ክርስቶስ ጸጋ ነው ፣ ክርስቶስ ሕይወት ነው ፣ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው! አሜን" ትርጉም፡ ብስራት ገብርኤል [ምንጭ ፦ A Prayer of Repentance and Conviction by St. Ambrose of Milan]
ያሻግራል “ውኃ ሲጠራ ተሻገር ፣ ዳኛ ሲገኝ ተናገር” በኖኅ ዘመን እግዚአብሔር ምድርን ይቅር እንዳላት ምልክቱ የውኃው መጕደል ነበር ። ውኃ ሲጎድል መርከብ ማረፊያ ፣ እግርም መርገጫ አገኘ ። ላዳነው አምላክ ኖኅ መሥዋዕትን አሳረገ ። እንደ ውኃ ወዳጅ የለም ፣ ውኃ ጥፋት ሲሆን ግን መላሽ የለውም ። ደጎችን እንዳናከፋ መጠንቀቅ ይገባናል ። በምድር ላይ እጅግ ክፉ የሚሆኑት ደግነታቸውን ያስጣልናቸው ሰዎች ናቸው ። አረመኔ ነገሥታት ፣ ጨካኝ ሰዎች ሁሉ የቀደመ ጠባያቸው ብቻ ሳይሆን ጠባይ የሰጠናቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። “ቸር ሲያጠቁት ቢስ ይሆናል” ይባላል ። ያጠቃናቸው ደጎች ፣ ለራስህም አስብ ያላልናቸው ቸሮች የከፉ ቀን የበላነውን ያስተፉናል ። የአፍቃሪ ሰው ቍጣ ከፍ የሚለው ለመውደድ የተጠቀመውን ኃይል ለጥላቻ ስለሚጠቀመው ነው ። አፍቃሪ ሁሉ አፍቃሪ ፣ ቸርም አዛኝ ይፈልጋሉ ። ይህ የተፈጥሮ ፍላጎት ነው ። እግዚአብሔርም ፍቅር ነውና የሚወዱትን ይፈልጋል ። ምላሽ የማይፈልግ ግዑዝ ብቻ ነው ። የውኃን ጥፋት ለማየት በዘመናችን ያየነው የሱናሚ አደጋ አስረጅ ነው ። በቅጽበት ስፍራዎች ተገለባብጠዋል ፣ ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል ። የብስ ላይ የነበሩ መኪናዎች ባሕር ገቡ ፣ ባሕር ላይ የነበሩ መርከቦች መሬት ላይ ረገጡ ። እሳት እንኳ ጊዜ ይሰጣል ፣ ውኃ ግን በቅጽበት ብዙ ጥፋት ያስከትላል ። ውኃ መንገደኛ ነው ። ተሰባስቦ ሲጓዝ በመንገዱ ፊት የሚቆመውን አይወድም ። ጠራርጎ ይወስደዋል ። የውኃ ዕድሜ አጭር ነው ። ትንሽ መታገሥ አለመቻል ግን ጥፋቱ ከፍ ያለ ነው ። የሰውም ቍጣ ለጊዜው ነው ፣ ትንሽ መታገሥ ፣ በመልካም ቃላት ማብረድ የሚቻል ነው ። ከዚያ በኋላ ተጸጽቶ ይክሰናል ፣ ከጥፋት አዳንከኝ ብሎ ያመሰግነናል ። ውኃ ሲጎድል እየጠራ ይመጣል ። ውኃን መሻገር ጠርቶ ወለሉ ሲታይ ነው ። በልጅነታችን ወላጆቻችን እጆቻችንን ይዘው ይሄዳሉ ። ይበልጥ የሚይዙን የመኪና መንገድ መሻሪያ ላይ ነው ። ያን ጊዜ እጆቻችንን ልቅም አድርገው ይይዛሉ ። መያዝ ብቻ ሳይሆን አጥብቀው ይይዙናል ። በዓይኖቻቸውም ግራና ቀኙን ያዩልናል ። እኛ የሚረብሸን እጃችንን መያዛቸው ነው ። የእኛ ባልሆነ መንገድ ፣ በወንዙ መሐል እንዳለን አናውቅም ። አንዳንድ ጊዜ መኪናው እየተቃረበ ከመጣ ተሸክመው ያወጡናል ። የሚያሻግር አባት አለን ። እርሱም እግዚአብሔር ይባላል ። እጆቻችንን ይዞ ያሻግረናል ። ከዓይነ ሞት በዓይኖቹ ይከላከልልናል ። እጆቻችንን ስለያዘን ከፍቶን ይሆናል ። ይህ የሚገባን ስንበስል ፣ በሃይማኖት ስናድግ ነው ። እግዚአብሔር እንድንተርፍ አድርጎ ይዞናል ። ዛሬ ፍላጎቶቻችን ሁሉ ቢሟሉ እንሞት ነበር ። እግዚአብሔር በኖኅ ላይ በርን እንደ ዘጋበት ፣ እኛም በመክፈት እንደ ባረከን በመዝጋትም ይባርከናል ። ቀኖቹ ክፉ ቢሆኑ ፣ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ችግሮችም ቢዘንቡ እግዚአብሔር ግን እጆቻችንን በእጆቹ ይዞ ያሻግረናል ። መያዛችን ላያስደስተን ይችላል ። ስለማናውቅ እግዚአብሔር በእውቀቱ ያድነናል ። ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ጥቂት እንደ በረረ ደብረ ዘይት ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላን ያመለጠው ተሳፋሪ እጅግ ተበሳጭቷል ። ጥቂት ቆይቶ ግን በዘመኑ ሁሉ የሚተርፍ የምስጋና ርእስ አግኝቷል ። ውኃ ሲጎድል ፣ ውኃ ሲጠራ መሻገር መልካም ነው ። ጥቂት ትዕግሥት ማጣት ዘላቂውን ሕይወት ያበላሻል ። ለመናገር ደውለን ስልኩ ስላልሠራ ቆይተን እግዚአብሔርን አመስግነናል ። ንግግር እንጂ ዝምታ ብዙ ጊዜ አያጸጽትም ። እነዚህ ቀኖች አስቸጋሪ ናቸው ። በክፍለ ዘመን የማይሰሙ መዓቶች በወራት ውስጥ ይሰማሉ ። ሁሉም ሰው ነገር ገብቶታል ፣ ጉዳይ ተሰጥቶታል ። የምድር ገዥዎች የሰው ማረፍ እየረበሻቸው ዜጎቻቸውን በብዙ ማስጨነቅ ይዘዋል ። ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ እስክንደናገር ፋታ አሳጥቶታል ። በዚህ ጊዜ ትዕግሥትን መለመን ሀብት ከመለመን በላይ ነው ። ከመጣውም ከሚመጣውም መዓት አሻግረኝ እያሉ መጸለይ የብልህ መገለጫ ነው ። በወፈፌ ዘመን ጠቢብ ሁኑ ! መናገርም ዳኛ ሲገኝ ነው ። አድር ባይ በበዛበት ፣ የዘመን ተለጣፊ በበረከተበት ፣ ተመሳስሎ መኖር ሥልጣኔ በመሰለበት ፣ ሰው ከሰውነቱ መንደሩን ባመለከበት ዘመን መናገር ጥቅም የለውም ። የምናገረው ውጤት ያመጣል ወይ ( ብለን ለክተን መናገር በጊዜ አቅም እንዳንጨርስ ያደርገናል ። ስናገር ይቀለኛል እያለን ይበልጥ እንቀጣጠላለን ። ባልበላ ሆዳችን ከበሉ ጋር መነጋገር ራስን ማድከም ነው ። “ይሁና ሰው ሲገኝ እናወራዋለና” ይሉ ነበር ወላጆቻችን ። መልስ አለኝ ምላሽ ግን አልሰጥም ብሏል ሰውዬው ። ዳኝነት ፣ የቅን ፍርድ እንኳን ከዓለም ከቤተ እግዚአብሔርም እየጠፋ ነው ። እንደ አራዊት በገዳይነት ያሸነፈ የበላይ የሚሆንበት መንገድ ላይ ነን። ሊቃውንት እውቀታቸውን ሽምጥጥ አድርገው ክደው ሰው የሚፈልገውን እያቀረቡ ነው ። እውነት እየተከሰሰች ውሸት በነጻ እየተለቀቀች ነው ። መሃይምነት ጊዜ አግኝታ ሰውን ሃይማኖተኛ እያሰኘች ነው ። ዳኛ የለም ። ለነፍሱ ፣ ለዘላለም መግቢያው ብሎ እውነትን እውነት የሚል እየጠፋ ነው ። የሃይማኖት ልብስ እንጂ የሃይማኖት ልብ የለንም ። መናገር ማባከን ነው ብለው አዋቂዎች ዱዳ ሆነዋል ። ትዕግሥት ፣ ጊዜውን ያየ ዝምታ ያስፈልጋል ። ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር እንደሚያሻግር ማመን ልብን ይደግፋል ። በሞት ጥላ መካከል በደኅንነት ልጆቹን የሚመራ ጌታ ዛሬም በሥራ ላይ ነው። ያቺ መልካም እጁ ዛሬ ትዋሰን ! አሜን ። ዲ.አ.መ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም.
ትዝብት ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ፣ ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው ፣ ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ ፣ ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ፣ ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ ። ዛሬን ያስረሳኛል የምንለው የዓመት ልቅሶ ይዞ ይመጣል ። ለአንድ ብር ችግር መቶ ብር ይከፈላል ። ችግሩ የታወቀ ነው ፣ መፍትሔው ችግር ሲሆን ግን ግራ የሚያጋባ ነው ። ለመዝናናት በሄዱበት አዝነው መመለስ ፣ ለማስደሰት ሞክሮ ሰውን ማሳዘን በሕይወት ጉዞ ውስጥ ተደጋጋሚ ነው ። ችግሮችን ለመርሳት ከመሞከር መፍትሔውን መፈለግ ጊዜና አቅምን ይቆጥባል ፣ ችግርን በችግር ለማጥራት መነሣሣት ወደ ኀዘን ሸለቆ መውረድን ያስከትላል ። በእኔ የሚሆነው በሁሉ የሚሆን ነው ። የሆነውም ሲሆን የነበረ ፣ ወደፊትም የሚሆን ነው ብሎ መቀበል ብርታት ይሰጣል ። እኛ የምንቀጥለው እንጂ እኛ የምንጀምረው ደስታም ኀዘንም የለም ። ሺህዎች ባለፉበት የሕይወት መንገድ ላይ ሺህ ትምህርት ተቀምጧል ። ታሪክን ማንበብ የሚጠቅመው አዲስ ነገር በዓለም ላይ እንደሌለ ለመረዳት ነው ። ሦስት ትምህርቶች ለማንኛውም ነገር ይጠቅማሉ ይባላል፡- ሂሣብ ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ ማወቅ ። ታሪክን ማወቅ የዛሬው ችግር ዛሬ እንዳልጀመረ ያሳየናል ። ትላንት ያለፉት ምን መፍትሔ ተጠቀሙ የሚለውንም ያስገነዝበናል ። ብቻ ለደስታ የምንሞክረው ነገር በመጨረሻ የሚቀረው በራስ መናደዱ ሊሆን ይችላል ። ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ። የጠላ መጨረሻ ጠላ አይሆንም ። የአቋራጭ ደስታ መጨረሻውም ደስታ ሊሆን አይችልም ። ደስታ በፊት በር እንጂ በጓሮ በር ገብታ አታውቅም ። ከከበሩ ሰዎች ጋር መዋል ፣ የከበረ ሰው ወዳጅና አጫዋች መሆን የራሱ መነቃቃት አለው ። የትልቅ ሰው ወዳጅነት አእምሮንም አካልንም ይቆጣጠራል ። የሌለንን ትልቅነት ያገኘን ስለሚመስለን ዕድላችን ያመልጠናል ። ከትልቅ ጋር ቢያዩን ይፈሩናል እንጂ አያግዙንም ። አማልደን ይሉናል እንጂ ወዳጅ አይሆኑንም ። መሰላል የሚወጣበት እንጂ የሚኖርበት ወዳጅ የለውም ። ድልድይ ይሻገሩበታል እንጂ ማንም አያስበውም ። ቶሎ ለማምለጥ ይጣጣሩበታል ። የድልድዩ ስም የሚነሣው ፣ በዜና የሚነገረው የተሰበረ ዕለት ነው ። ትልቅነትና የትልልቆች ወዳጅነት የስብራት ቀኑ በጉጉት የሚጠበቅ ነው ። ትንሽነት የሚሰማቸው ሰዎች በትልልቆች ውርደት በደስታ ይፈነጫሉ ። ትልቅነት ቢያዝዝ እንጂ መራመድ አይችልም ። ትልቅ የሆነው ራስ እግር እያጣ ያሰበውን ሳይፈጽም ዘመኑ ይቋጫል ። የንጉሥ መጠጥ ነው የሚባለውም ጠጅ መጨረሻ ላይ አምቡላ ሆኖ ይጣላል ። “ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው” እንዳሉት ነው ። የትልልቆች ወዳጅ የሆኑ ዘመን ይከዳቸዋል ። ትልቁ ሰው እልፍ ሲል እጅ እንዳልተነሡ ሰላም የሚላቸው ያጣሉ ፣ የአንድ ምስኪን ክብር ያጣሉ ። የምንጋደልበት ፣ በአምሮት የምንሰቃይበት ፣ ስርቆት ውስጥ የሚከተን ያ ፍላጎት መደምደሚያው የማይረባ ይሆናል ። ያሸነፍነው ሰው አንድ ቀን ሊያሸንፈን ይመጣል ። እኛ በአሸናፊነታችን ደስ ሲለን እርሱ ግን ማደጉን ለመለካት በእግር ኮቴአችን ላይ እግሩን ሲለካ ነበር ። “የናቁት ያደርጋል ዕራቁት” እንዲሉ የተኛው ውሻ እኛ ላይ ሊነሣሣ ፣ ሞኙ ብልጥ ሊሆን ይፈልጋል ። በዓለም ላይ ያለው ጠብ ሁሉ መነሻው ፍቅር ነው ። ዛሬ አፋፍ ላይ ደርሶ የምናየው የኢትዮጵያና የኤርትራ እሰጥ አገባ መነሻው ያሸለመ ፍቅር ነው ። በአንድ አፍንጫ ካልተነፈስን ፣ በአንድ መቀመጫ ካልተቀመጥን ያልንበት ነገር ሁሉ የማይሰበር አጥንት የሚሆንበት ጊዜ አያሌ ነው ። የምናኝከው ሥጋ መጨረሻው አጥንት ነው ፣ አጥንቱን ከተጫወቱበት ፣ ጊዜ ይህንንም ያሳያል ካሉበት ትምህርት አለው ። ሰው ሲቸግረው ይበደራል ፣ ባለጠጋን ባለጠጋ ያደረገው ከሥራ በላይ ብድር ነው ። የብድር ጥቅሙ ሲሠሩበት ፣ በጊዜው ሲመልሱት ነው ። ከግለሰብም ከተቋምም እንደገና ለመበደር የሚያስብ ሰው ፈጥኖ መመለስን ፣ ሳይጠየቅ መስጠትን ማወቅ አለበት ። ቀስ ቀስ እያሉ ዕዳም ይቃለላል ። የረዳንን መርዳት ፣ ያገዘንን ማገዝ አይቀርም ። የምንኖረው ብድር ለመመለስም ነውና ። በዚህ ዓለም ላይ ራስን እንደ መታዘብ ያለ ብርቱ ነገር የለም ። በርግጥ ራስንም ከታዘብን ሕሊና ጥሎን አልሄደም ማለት ነው ። ትዝብት ወደን ስንጠላ ፣ አብደን ስንሰክን ፣ ልሙትላችሁ ብለን ካልገደልሁ ስንል ለራሳችን የምንሰጠው አነስተኛ ዋጋ ነው ። ሰዎችን እንታዘባለን ። አንቱ ብለውን አንተ ሲሉን ፣ ወንበር እንዳልመረጡልን ወንበር ሲያነሡብን ፣ አፈር ልብላልህ እንዳላሉ አፈር ሲያበሉን እንታዘባለን ። ሰላም ለማለት እንኳ ጉዳይ ካልገጠማቸው የማይፈልጉንን ሰዎች ስናስብ እንታዘባለን ። ብልጠት ቶሎ ይታወቃልና ለትዝብት ይዳርጋል ፣ ሰዎች ሳይነግሩን የሚሸሹን ሲታዘቡን ነው ። መታዘብ ግን ስስ ሕመም ነውና ቆይቶ ሊጥለን ፣ ብቸኛ ሊያደርገን ይችላል ። ትላንት እንሞትለታለን ይሉለት የነበረውን ሃይማኖትና ርእዮት የጣሉ ሰዎችን ስናይ ፣ ዝምታ ሳለ ወደ መርገም የገቡትን ስንሰማ እንታዘባለን ። ሊያልፍ ቀን የማያልፍ ንግግር የተናገሩ ተሸማቀው ይኖራሉ ። ሁሉም ነገር ሊረሳ ይችላል ። ትዝብት ግን አይረሳምና ከሚያስተዛዝብ ግብር እንራቅ ። ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ፣ ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው ፣ ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ ፣ ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ፣ ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ ። ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ዲ.አ.መ
እውነተኛው የወይን ግንድ አዳም የሰው ልጆች መነሻ ነው ። አዳም የሰው ዘር ግንድ ነው ። የሰው ልጅ ጉዞ የጀመረው በእርሱ የቀጠለውም ከእርሱ አብራክ በተገኙት ልጆች ነው ። ሔዋንም የተገኘችው ከአዳም ነው ። አዳም የመጀመሪያው አባት ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋ እናት የሔዋን እናትዋ ነው ። አዳም በኃጢአት በወደቀ ጊዜ ብልየት ወይም እርጅና አገኘው ። ኃጢአት ያስረጃል ፣ የማሰብን አቅም ፣ የመናገርን ብቃት ፣ የመሥራትን ችሎታ ያሳጣል ። በኃጢአት ብልየት ውስጥ ያለ ጽድቅን በነበር ክፋትን በአሁን ያወራል ። አዳም እውነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደ ውሸት ቆጥሮ ሐሰት የሆነውን የዲያብሎስን ቃል እንደ እውነት ተቀበለ ። በዚህ ምክንያት ሐሰተኛ ሆነ ። ሲፈጠር እውነተኛ ግንድ እንዲሆን ነበር ፣ አሁን ሐሰተኛ ግንድ ሆነ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ዳግማዊ አዳም ተብሎ ነው ። እርሱ ርስት አስመላሽ ፣ ጠላትን ተበቃይ ነው ። ራሱ እውነት ስለሆነ እውነተኛው የወይን ግንድ ነኝ አለ ። ሐሰተኛው የወይን ግንድ መራራ ፍሬ እንድናፈራ ምክንያት ሆነ ። እውነተኛው የወይን ግንድ ግን ጣፋጩን የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት አስቻለን ። ግንዱ አዳም ሞቶ ስለነበር ቅርንጫፎቹ የሰው ልጆችም በሞት ተይዘው ነበር ። በክርስቶስ ስናምን ከአሮጌው አዳም ግንድ ተነጥለን በአዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ሕይወቱንም እንካፈላለን ። አዳም ልጆችን ለሞት ወለደ ፣ ክርስቶስ ግን በዳግም ልደት ምእመናንን ለሕይወት ወለደ ። የበደለው ቃየን ቢሆን ኖሮ እኛ እንተርፍ ነበር ። የበደለው ግን ግንድ የሆነው አዳም ነውና መትረፍ አልቻልንም ። ከምንጩ የደፈረሰ አይጠራምና ሁላችንም በዚህ ዕዳ ተያዝን ። ክርስቶስም ማሻሻያ በማድረግ ፣ አሮጌውን ግንድ በማከም ሳይሆን ሌላ ግንድ በመሆን መጣ ፣ በዚህም ፍጹም ድኅነትን አገኘን ። በአዳም ውስጥ የጽድቅ ምኞት እንጂ ፍሬው አልነበረንም ፣ በክርስቶስ ግን ለሰማይ የምንኖርበትን አቅም አገኘን ። ገበሬው ወይኑን ሁልጊዜ ይገዝረዋል ። ከገበሬው እጅም ስለት አይጠፋም ። እውነተኛው የወይን ግንድ ክርስቶስ ሲሆን ገበሬው እግዚአብሔር አብ ነው ተብሏል (ዮሐ. 15፡1)። እግዚአብሔር አብም ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል ። ልጁ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ። ስለትና ወይን አይለያዩም ፣ ክርስቶስና መስቀልም ለአንድ ቀን ተለያይተው አልታዩም ። ወደ ምድር መውረድ ፣ ከድሀ መወለድ ፣ በበረት መገኘት ፣ በግብጽ መሰደድ ፣ በሰው ሁሉ መጠላት ፣ ቤት አልባ መሆን ፣ የድህነት ኑሮ ፣ በባሪያ እጅ መጠመቅ፣ በሐሰት መከሰስ ፣ በመስቀል ላይ መዋል ፣ በተውሶ መቃብር መቀበር ፣ የሐዋርያት ስደት…. ይህ ሁሉ የመስቀል አካል ነው ። ወይን ስለት ካላገኘው አያፈራም ፣ ክርስቶስም መከራ ባይቀበል ኖሮ እኛን ማትረፍ አይችልም ነበር ። የመስቀሉ ትርፎች እኛ ነን ! አዳም እውነተኛነትን አጣ ። በዚህ ምክንያት በምድር ላይ የውሸት ኑሮ ተጀመረ ። አዳም የምድር ገዥና ትልቁ ንጉሥ ነው ። ውሸት በእርሱ ስለ ተገኘ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምድር መሪዎች የውሸት አውራ ሠራተኛ ሆኑ ። እውነት የላችሁም ያላቸውንም ባላቸው አቅም የሚያጠፉ ሆነው ተገኙ ። እውነት በነገሥታት ጥቃት ውስጥ ያለማቋረጥ ታልፋለች ። በዛሬው ዓለም ፖለቲካ ተብሎ ሲጠራ ትርጉሙን ውሸት ብሎ ሰው ሁሉ እስኪያስብ ድረስ የአስተዳደር ክብር ወድቋል ። በምድር ላይ ከቤተ መንግሥት እስከ ድሀዋ ጎጆ እውነተኛ ኑሮ እየጠፋ ነው ፣ ብቁ መሪዎች ተደርገው የሚታሰቡም ሕዝብን ማታለል የቻሉት ናቸው ። በወርቅ በአልማዝ ተንቆጥቁጦ የሚወጣው ቆንጆ ውስጡ የተበላሸ ነው ። የራሱ መጨነቅ ሳይደንቀው መጨነቁን ሰው እንዳያውቅበት በብልጭልጭ ይሸፍነዋል ። ብዙ ሕዝብ የሚከተላቸው ዘፋኝና ተዋንያን ሰውን ሲያስደስቱ ራሳቸው ግን ኀዘነተኛ ናቸው ። የውሸት ሳቅ እንዳደከማቸው ይታወቃል ። ባደጉ ከተሞች የቀነጨሩ ሰዎች አሉ ። ባማረ ቤት የሚኖሩ ብዙዎቹ የፈራረሱ ናቸው ። ሕንፃውን አቁሞ ትዳሩ የተበተነበት ፣ ልጆቹ የወደቁበት አያሌ ነው ። ሰዎች በተቃራኒው መኖር ከጀመሩ ቆይተዋል ፣ እንደሚወዱን ሲናገሩ እየጠሉን ሊሆን ይችላል ፣ የጠሉን ሲመስለን ደግሞ በጣም እየወደዱን ነው ። ሰው አድራሻ የለሽ ፣ በቃሉ የማይያዝ ከሆነ ሰንብቷል ። ይህ ሁሉ ከሐሰተኛው ግንድ የተወረሰ ጠባይ ነው ። የሚያሳዝነው የውሸት ኖረን የእውነት መሞታችን ነው ። ወይን ከሌሎቹ ተክሎች ልዩ የሚያደርገው ሕይወቱ ያለው ግንዱ ላይ ነው ። ቅጠሉ በጣም ቢያምርም በቅጠሉ ላይ ሕይወት የለም ፤ ፍሬው በጣም ቢያምርና ቢጣፍጥም ሕይወት በእርሱ ላይ ስለሌለ ወስደን ብንተክለው አይበቅልም ። የወይን ግንድ የቅርንጫፉና የፍሬው የሕይወት መገኛ ነው ። ከግንዱ የተለየ ወይን ይከስማል ። ክርስቶስ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው ። ምእመናን ቅርንጫፍ ናቸው ። ከእርሱ ተለይተው መኖር አይችሉም ። በራሳቸው ጉልበት ክርስትናን መፈጸም አይችሉም ። አንዳንድ ተክሎች በፍሬአቸው ይበቅላሉ ፣ ሌሎችም በቅርንጫፋቸው ሊበቅሉ ይችላሉ ። ወይን ግን ግንዱ ላይ ሕይወት ስላለ ያለ ግንዱ አይበቅልም ። ያለ ግንዱ ያለ ክርስቶስ ማመንም ፣ ማፍራትም አንችልም ። በፍሬው ግንዱ ይታወቃል ፣ በአማንያን ኑሮም ክርስቶስ ይሰበካል ። ከቤተሰቡ በሚመጣው ነገር የሚሰጋ ሰው ብዙ ነው ። ባለሙያዎች ጋ ስንሄድ በቤተሰባችሁ እንዲህ ዓይነት በሽታ ነበረ ወይ ብለው ይጠይቃሉ ። ቤተሰባቸው በሥልጣን ያሳለፈ ከሆነ ብዙዎች አገር ለቀው ይሰደዳሉ ። አገር የገዙ ሰዎች ለልጆቻቸው አገር እንኳ ማውረስ አይችሉም ። በቤተሰባቸው ባዕድ አምልኮ ያዩ የነበሩ ሰዎች በሚገጥማቸው አለመሳካት ሁሉ ያንን ያስባሉ ። ምናልባት ቤተሰባቸው የሚከተለው ሃይማኖት ከዚያ አላስጣላቸውም ብለው ስለሚያስቡም ለመሸሽ ብለው ሃይማኖት ይቀይራሉ ። ስጋቱ ከፍተኛ ነው ። በክርስቶስ ስናምን ግን እንኳን ከቤተሰብ ከአዳም ግንድነት ተነቅለን በሐዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ስለዚህ በዘርማንዘር የሚመጣው ዕዳ ሊያገኘን ፣ ክፉም ሊይዘን አይችልም ። ጦርነቱ አብቅቷል ፣ ጠላትም ተሸንፏል ፣ ነገር ግን አሁን በጦርነት ውስጥ እንዳሉ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። በክርስቶስ ያመነ የቤተሰብ ጣጣ ሊይዘው አይችልም ። ከዚህ በኋላ ለማፍራት ዕድልና አቅም አለውና በጽድቅ መኖር ይገባዋል ። እውነተኛው የወይን ግንድ አንተ አንተ ክርስቶስ ነህ ። ከእገሌ ተወለድሁ ፣ ዘራችን ከእነ እስክንድር ይመዘዛል ፣ ከነ ቄሣር ይገናኛል ማለት ሐሰት ነው ። እነዚህ ሁሉ የሞትን ሥልጣን ማሸነፍ አቅቷቸው ወድቀዋል ። ታላቅ ቢባሉም ሎቶሪ ወጥቶላቸው ነው ። ታላቅነታቸውን ሲነጠቁም ፍርድ ቤት ቆመው አልተከራከሩም ። የእነርሱ አይደለምና ፀሐዩ ሲጠልቅ አንሰው ወደ ዋሻ ገቡ ። በባሕርይህ ባለሥልጣን ፣ ጌትነት ገንዘብህ የሆነ አንተ ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ ። የእገሌ ዘር ነኝ ማለት ለኩራት እንጂ ለጥጋብ አይሆንም ። በአያቱ ድሀ ያልነበረ ባለጠጋ ፣ በአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ የለም ። ሁሉ ሐሰት ነው ፣ አንተ ብቻ እውነት ነህ ። ጌታ ሆይ የውሸት እየኖርን የእውነት መደሰት እንፈልጋለንና እባክህ ከተኛንበት ቀስቅሰን ! ዲ.አ.መ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም.
ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት “እኔ ክርስቲያን ነኝ” በኢትዮጵያ ፣ በቢዛንታየን ፣ በካቶሊክና በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት የታወቁና ክብር የሚሰጣቸው ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣ በዚህ ቀን ይታሰባሉ ፤ እነዚህ የ4ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ አርአያ ተደርገው ይወሰዳሉ ። ሕፃኑ ቂርቆስም ሠለስቱ ደቂቅን/ሦስቱን ወጣቶች የሚያስታውስ ሐዲስ ሰማዕት ነው ። ቅድስት ኢየሉጣ እግዚአብሔርን በመፍራት የኖረች ሴት ናት ። እግዚአብሔርን መፍራትዋ ከሰማይ ክብርን ሲያስገኝላት በምድር ግን ስደትን አምጥቶባታል ። እርስዋም ዋጋን ከምድር ሳትጠብቅ ከሞቀው ኑሮዋ ከሮም ከተማ ተሰደደች ። በስሜ ትሰደዳላችሁ ያለው ጌታ ቃሉ በእርስዋና በቤተሰብዋ ላይ ሲፈጸም በማየትዋ ዕድለኛ ነኝ ብላ ተደሰተች ። የቅዱሳን ደስታቸው መንገዱ አልጋ ባልጋ መሆኑ ሳይሆን ቃሉ በኑሮአቸው ተዳሳሽ ሲሆን በማየት የሚገኝ ነው ። ሰው ገድለው በሚሸሹበት ዓለም ስለ ክርስቶስ ስደተኛ መሆን ትልቅ ሐሤትን የሚሞላባቸው እውነት ነው ። ስለ እኔ ትሰደዳላችሁ ያለው ጌታ ቃሉ እውነት የሚሆነው በክርስቲያንነት ሲሰደዱ ብቻ ነው ። ስደት ከተማችንን አገራችንን ልቀቁ የሚል የክፋት አዋጅ ነው ። ጌታ ክርስቶስ ፣ ቤት ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚለቁለት ፣ አገርን ቢከስሩም አሁንም ትልቅ ማትረፊያ የሆነ ንጉሥ ነው ። እርሱ ክርስቶስ ቤትና የቤት ራስ ፣ አገርና ንጉሥ ነው ። በምድር ላይ ተመላልሶ ያስተማረን ምቾትን ሳይሆን ትግልን ነው ። ደግሞም ሰው በበሽታ ተበጣጥሶ በሚሞትበት ዓለም ስለ እርሱ ሰማዕት መሆን ቅዱሳን ሁሉ ሲለምኑት የኖሩት ዕድል ነው ። ቅድስት ኢየሉጣ በተሰደደችበት አገርም መኖር አልቻለችም ። ክርስቲያንነትዋ ሊደበቅ አልቻለም ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትምና ። ጴጥሮስን ከቃሉ የተነሣ የክርስቶስ ወገን ነህ እንዳሉት ኢየሉጣንም እንዲሁ አወቅዋት ። ወደ አገረ ገዥው አምጥተው ለጣዖት እንድትሰግድ ቢጠይቋት ዓይን እያለው ለማያይ ፣ ጆሮ እያለው ለማይሰማ አልሰግድም ። የዚህን እውነት የሦስት ዓመቱ ልጄ ቂርቆስ ይንገርህ ብላ አመለከተች ። ቅድስት ኢየሉጣ ለመሰደድ የሚበቃ ቆራጥ የክርስትና አቋም ነበራት ። በገዥዎች ፊትም ለመመስከር የምታምነውን ክርስቶስ የምታውቅ ሴት ነበረች ። ደግሞም ልጅዋን ገና በሕፃንነቱ ስለ ክርስቶስ ጌትነት እየነገረች ያሳደገች ናት ። ከዚህች ቅድስት እናት የምንማረው ብዙ ነገር አለ ። ልጆችን ገና በሕፃንነት ስለ ክርስቶስ ፍቅር እያስተማሩ ማሳደግን ነው ። ልጆች ከተማሩ በኋላ ወደ ኋላ ብንል እንኳ መልሰው ያበረቱናል ። ቅዱስ ቂርቆስ እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን “አትፍሪ” እያለ ሲያበረታታት ነበር ። ልጆቻችንን ፣ ደቀ መዛሙርትን ማስተማር በደከመን ጊዜ የሚያበረታታ ለማግኘትም ነው ። በዕለተ ሆሳዕና በአፈ ሕፃናት የከበረው ጌታ በቅዱስ ቂርቆስም አንደበት ጌትነቱ ተመሰከረ ። የሰሙት ሁሉ የዕድሜውን ለጋነትና የሚናገረውን እውነት ማጨባበጥ አልቻሉም ። ቅዱስ ቂርቆስ የሚታወቅበት ንግግሩ “እኔ ክርስቲያን ነኝ” የሚለው ነው ። ክርስቲያንነት በተራራም በሸለቆም ፣ በከፍታም በዝቅታም የሚሸፈን አይደለም ። ባላፈረብን ክርስቶስ ማፈር አይገባም ። እኛ ወደ ኋላ ብንል እግዚአብሔር ሕፃናትን ያስነሣል ። ልጆቻችንን ለክርስቶስ መኖርን ብቻ ሳይሆን መሞትንም ልናስተምራቸው ያስፈልጋል ። ክርስትና ከሰማዕትነት የተለየ አይደለምና ። ቅዱስ ቂርቆስም በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ወንጌልን ሰበከ ። የሰሙት ሁሉ አመኑ ። ብርሃናዊ ፊቱንና የሕይወት ቃሉን ሰምተው “በእውነት ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው ሰገዱ ። አገረ ገዥውም አንዲትን ሴት አስክዳለሁ ብሎ ሕዝቡን ሁሉ ከሰረ ። የሮማ ባለሥልጣናት ቄሣሮችንና ጣዖታትን የሚያስመለኩ እንቢ ያለውንም የሚሠዉ ነበሩ ። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ቂርቆስ በጥር 15 ቀን ሰማዕትነትን ሲቀበል በማግሥቱ ጥር 16 ቀን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም ሰማዕትነትን ተቀብላለች ። ሕፃኑ እናቱን በሰማዕትነት ቀደመ ። ሕፃናት በፍቅረ ኢየሱስ ካደጉ በሰማዕትነት ይቀድሙናል ። ዛሬ ላሉት ሕፃናት የምንጨነቀው ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው ወይስ የፈረንጅ ቋንቋ እንዲያውቁ ነው ? ቅዱስ ቂርቆስን ስናስብ የሕፃናት አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሊበረታታ እንደሚገባው ነው ። በሕፃንነቱ የገባ እስከ ማታ ይቆያል ። ብንወድም ባንወድም ነገ የዛሬዎቹ ሕፃናት ናት ። ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ሕፃናትን ማስተማር ለሰማዕትነትም ማዘጋጀት ይገባታል ። ክርስቶስ የምንኖርለት ብቻ ሳይሆን የምንሞትለትም ነው ። በዓለ ሰማዕታት የሚዘጋጀው በረከት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ምእመናን የሰማዕትነት ልብ ይዘው ዛሬ ገንዘብን ፣ ነገ ሰይፍን እንዲንቁ ለማድረግ ነው ። ዛሬም ሰማዕትነት በደጅ ደርሶ እያንኳኳ ነው ። ብዙዎች ቀድመውናል ። የማይቀረውን ሞት ለክርስቶስ ሰጥተው ባለ አክሊል ሆነዋል ። ቀጣይ ዘመንም ለቤተ ክርስቲያን ሜዳ ሳይሆን አቀበት ነውና ምእመናን ጣዕመ ዓለምን በመናቅ ፣ ለሰማዕትነት ክብር በመዘጋጀት ሊኖሩ ያስፈልጋል ። በቤዛነት የጀመረው ክርስትና በሰማዕትነት ይቀጥላል ። የምንሰደደው አገራችን በምድር ስላልሆነ ነው ። የማንከበረው ሰው ያለ አገሩ ስለማይከብር ነው ። ዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖችን የሚያፋቅር ነው ፣ የምቾት ዘመን የሚያጣላ ነው ። በተገፋን ቍጥር ወደ ክርስቶስ እንቀርባለን ። በተገፋን ቍጥር ወደ ሰማይ እናድጋለን ። እሳቱ አፈሩን ይበላዋል ፣ ወርቁን ያወጣዋል ! ለሕፃናት ገና ከአራስ ቤት ጀምሮ ፍቅረ ኢየሱስን እየነገርን ካሳደግን የማያሳፍሩን ፣ እኛን የሚያበረታቱን ቆራጥ አማንያን ይሆናሉ ። ሰማዕታት ሁሉ ሰማዕት የሆኑት ስለ ክርስቶስ በመመስከር ነው ። ሰማዕት ማለት ትርጉሙ ምስክር ማለት ነው ። በቃልም በጽናትም የመሰከሩ ሰማዕታት ተብለው ይጠራሉ ። እኛስ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ፣ ብሎም ስለ እርሱ መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን ? ስለ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉ ስማቸው በወርቅ ቀለም ተጽፎ ይኖራል ። የዘመን አቧራ ሊሸፍናቸው በፍጹም አይችልም ። ለዚህም ይህ ቀን ምስክር ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ የተደረገውን አትረሳም ! ከሰማዕቱ ከቅዱስ ቂርቆስ ረድኤት በረከት ያሳድርብን ! ዲ.አ.መ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም.
"እውነተኛ ክርስቲያን አባቱ ክርስቶስን ይመስላል፡፡ ይሰደዳል እንጂ አያሳድድም፡፡ ይሰደባል እንጂ አይሳደብም፡፡ የጠፉትን ፍለጋ ይደክማል እንጂ ይባስ ብሎ አይገፈትርም፡፡ በወንድሙ ውድቀት ያለቅሳል እንጂ አይደሰትም፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን አባቱ ሌላ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና በጊዜውም ያለ ጊዜውም ሊሆን ይገባል፡፡ ባገኘን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ባጣንም ጊዜ፤ ባለጤና በሆንን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በታመምንም ጊዜ፤ ሲሳካልን ብቻ ሳይሆን ባልተሳካልንም ጊዜ ማመስገን መለማመድ አለብን፡፡ የምስጋናችን ምንጭ የሁኔታዎች መለዋወጥ ሳይሆን ስለ አምላካችን ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ ስንለማመድ በክብር ላይ ክብር ይጨመርልናል፤ እንደ አባታችን ኢዮብ የዲያብሎስን አፍ እንዘጋለን፡፡ ተአምራትን ማድረግ ትፈልጋላችሁን?” እንኪያስ "በዘፈን የደነቆረን ጀሮ መዝሙር እንዲሰማ አድርጉት፡፡ ሴትን በመመኘት የታወረው ዐይን ፈጣሪውን እንዲያይ አድርጉት፡፡ በስርቆት የሰለለ እጅ በምጽዋት እንዲዘረጋ አድርጉት፡፡ ወደ ኃጢአት ቤት በመሄድ ሽባ የሆነውን እግር ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲሮጥ አድርጉት፡፡ ሐሜትን በማውራት ዲዳ የሆነውን ከንፈር መልካም ንግግርን እንዲናገር አድርጉት፡፡ ከተአምራት ሁሉ የበለጠ ተአምር ይሄ ነው፡፡" ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
+ ሌላ መንገድ + ሰብአ ሰገል ወደ ሄሮድስ ሔደው ስለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ጠየቁ:: ከዚያም በኮከብ ተመርተው ወደ ክርስቶስ ደረሱ:: ሔደውም ሰገዱለት:: እጅ መንሻም አቀረቡ:: ከዚያ በኋላ ግን "ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ" ማቴ. 2:12 ይህ መልእክት የተነገራቸው ስለ ሁለት ነገር ነው:: የመጀመሪያው ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ስለሚፈልግ ለሄሮድስ መረጃ እንዳይሠጡ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ እየመሰከሩ የመጡበትን መንገድ ትተው አየነው እያሉ በሌላ መንገድ እንዲመሰክሩና የሕፃኑ ንጉሥ ዝና እንዲሰፋ ወንጌል እንዲስፋፋ ነበር:: መልአኩ ወደ ሄሮድስ አትመለሱ አለ እንጂ "ሄሮድስ ሊገድለው ነው" አላላቸውም:: ምክንያቱም ይህን ዜና ቢሰሙ ጦር ይዘው የመጡ ነገሥታት ናቸውና "እኛ እያለን እስቲ ይሞክረን" ብለው ውጊያ ሊያነሡ ይችሉ ነበር:: የሰላም አለቃ የተባለው ህፃኑ ክርስቶስም የውጊያ መነሻ ይሆን ነበር:: ክርስቶስ ግን የምትዋጋለት ሳይሆን የሚዋጋልህ አልፎም የሚወጋልህ አምላክ ነው:: በዚህ መሠረት ሰብአ ሰገል "ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ" ወዳጄ ክርስቶስን ሳታገኝ በፊት ሄሮድስ ጋር ብትሔድ ችግር የለውም:: ክርስቶስን ካገኘህ በኋላ ግን ወደ ሄሮድስ መመለስ ኪሳራ ነው:: እንደ ሰብአ ሰገል ለጌታ እጅ መንሻ አቅርበህ ፣ ዘምረህ ፣ የከንፈር መሥዋዕት አቅርበህ ነፍስህ መድኃኒትዋን አግኝታ ከተደሰተች በኋላ ሕይወት እንዴት ይቀጥላል? ወደ ሄሮድስ ልትመለስ ይሆን? እንዳታደርገው! ሄሮድስ ጋር ያለው ኃጢአት ነው:: ሄሮድስ ጋር ያለው ክፋት ነው:: እመነኝ እንደ ሰብአ ሰገል ጌታህን ካገኘህ ወዲህ ወደ ሄሮድስ አትመለስ! ወዴት ልሒድ ካልከኝ መልሱ እዚያው ላይ አለ :- "በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሔዱ" እስቲ ሌላ መንገድ ሞክር! ትናንት ያልኖርክበትን ዓይነት ኑሮ ፣ ትናንት ያልሞከርከው የንስሐ መንገድ እስቲ ዛሬ ሒድበት! ሌላ መንገድ አልነግርህም "መንገድም ሕይወትም እውነትም እኔ ነኝ" ያለህ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እርሱ ነው:: በእኔ ኑሩ እንዳለ በእርሱ ኑር:: አደራ ወደ ሄሮድስ እንዳትመለስ! ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ጥር 2 2017
አንኳን ለ2017 ዓ ም ለጌታችን፣ ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረስዎ! “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱለሰብእ፤ በሰማያት ምስጋና ተደረገ በምድርም እርቅ ተወጠነ ‹‹ሰላም ሆነ፡፡›› (ሉቃ. ፪፥፲፬) በዚህ ዓለም ላይ የሰው ልጆች ነጻነትን ፣ ምድርም ሰላምን ይፈልጋሉ ፤ የምድር ገዥዎች አነዚህን ጸጋዎች እናመጣለ አያሉ ተስፋ የሚሰጡ ቢሆንም በተግባር ማረጋገጥ ስላልቻሱ የሰው ልጆች በሕሊና እስር፣ ምድርም በሁከት አያለፉ ነው ። አኛ ግን አውነተኛውን ነጻነት አርሱም ለአግዚአብሔር ክብር መኖርን ፤ አውነተኛውን ሰላም ከራስ ጋር መስማማትን አናገኝ ዘንድ በዳዊት ከተማ መድኅን ክርስቶስ ተወልዶልናል። መልካም በዓለ ልደት ይሆንልዎ ዘጓድ ምኞታችንን ስገልጽ በአክብሮት ነው! በክርስቶስ ፍቅር!
"ክብርና ሥልጣን፥ ሀብትና ንብረት፥ በዚህ ዓለም ላይ የምናገኛቸው ብልጽግናዎች ኹሉ ጸንተው የሚኖሩ አይደሉም። ኹሉም ከወራጅ ውኃ በፈጠነ ፍጥነት የሚያልፉ ናቸው እንጂ ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ዘላለማዊ የለም። የሙጥኝ ብሎ ሊልዛቸው የሚሞክር ሰው እንኳን በፍጹም ሊያቆያቸው አይችልም፤ የሚቀረው ባዶውን ነው። መንፈሳዊ ነገሮች ግን እንደዚህ አይደሉም፤ የዚህ ተቃራኒ ናቸው እንጂ፦ እንደ ጽኑ ዐለት የማይንቀሳቀሱ ናቸው፤ ሕልፈት ውላጤ የለባቸውም። ታዲያ ጸንቶ የሚኖረውን እጠፋ እጠፋ በሚለው፥ የማይነቃነቀውን በሚንገዳገደው፥ ዘላለማዊውን በጊዜያዊው ፥ የማያልፈውን በሚያልፈው ፥ ዘላለማዊ ደስታ የሚሰጠውን ዘላለማዊ ስቃይ በሚሰጠው መቀየራችን እንደ ምን ያለ ሞኝነት ነው?" ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
"የማርን ጥፍጥና ማርን ቀምሶ ለማያውቅ ሰው በመቅመስ እንጂ በቃላት ማስተማር እንደማይቻል ሁሉ የእግዚአብሔርን መልካምነት በቃላት በጠራ መልኩ ማስተማር አይቻልም። ራሣችን ወደ እግዚአብሔር መልካምነት ዘልቀን መግባት ይኖርብናል እንጂ።" ቅዱስ ባስልዮስ
አንዳንዴ በዙሪያዬ የማየው ነገር ልቤን ሲያናውጠው፥ ከመጽሐፍ ቅዱሴ በተጨማሪ መልሼ መላልሼ የማነባቸው መጻሕፍት አሉ። ከጥንቶቹም ከአሁኖቹም፤ ከጥንቶቹ መካከል፥ የቅዱስ አትናቴዎስ በእንተ ሥጋዌ፥ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ አምስቱ የነገረ መለኮት ድርሳናት፥ አረጋዊ መንፈሳዊና ማር ይስሐቅ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሕይወቴም የአገልግሎቴ መሪም ነው ሁሉም መጻሕፍቱ አነጋጋሪዎቼ ናቸው። ከእነዚህ ጋር አብሬ የምደምረው፥ የቅዱስ አውግስጢኖስ ኑዛዜ ( The Confessions of St. Augustine) ነው። መጽሐፉ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ታላቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው፤ ሁል ጊዜ ራሴን እንድመለከትበትና የእግዚአብሔርን ታላቅነት የእኔን ታናሽነት እንዳይ ያደርገኛል። በነገረ መለኮት ብቻ ሳይሆን፥ በሥነ ጽሑፍ ዓለም ታዋቂ የሆነው የመጀመሪያው መክፈቻ ምዕራፉን እንዲህ ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፤ ( ትርጉሙ የመጀመሪያ ረቂቅ ስለሆነ ግድፈት አይጠፋውምና ዓይናማዎቹ መሻሻል ያለበትን በኮሜንት መስጫ ላይ አስቀምጡት። ) ጌታ ሆይ፥ አንተ አምሳያ የሌለህ ነህ፤ በመሆኑም ለአንተ የምናቀርበው ውዳሴ ከሰብእናችን ከፍ ያለ ነው። ኃይልህ ድንቅ ነው፤ ጥበብህ ወሰን የለውም። እኛ ዝቅተኛ ፍጥረቶችህ አንተን እናመሰግን ዘንድ ተነሳሳን። የሰው ልጅ ምንድነው? የፍጥረትህ ቅንጣት ንጥረ ነገር አይደለምን? እያንዳንዱ ሰው በውስጡ የሚመጣውን ሞት ምልክት ተሸክሞአል። ሟችነቱ የሰውን ኃጢአተኝነት ይመሰክራል። ትዕቢተኛውን እንደምትገሥጸው ለሁሉም ያውጃል። ነገር ግን ዝቅተኛ ብንሆንም፥ የፍጥረትህ ቅንጣት ንጥረ ነገር ብንሆንም፥ የሰው ልጆች አንተን ለማመስገን እንሻለን። አንተን በማመስገን የሚገኘውን ሐሴት በውስጣችን ትቀሰቅሳለህ። አንተ ለራስህ ሠራኸን፤ በአንተ ዘንድ የዕረፍት ሥፍራውን እስከሚያገኝ ድረስ ልባችን ዕረፍት የለሽ ነው። ጌታ ሆይ! ከእነዚህ ሁለት ነገሮች የትኛው መጀመሪያ እንደሚመጣ እናውቅ ዘንድ ስጠን። አንተን ከማመስገናችን በፊት አንተን መጥራት አለብን? ወይስ አንተን ከማወቃችን በፊት አንተን መጥራት አለብን? አንተን መጀመሪያ ሳያውቅ፥ አንተን መጥራት የሚችል ማነው? አንተን የማያውቅ፥ አንተ ማን እንደ ሆንኽ የተሳሳተ አሳብ ይዞ ሊመጣ ይችላልና። ከዚያ ይልቅ፥ አንተን እናውቅህ ዘንድ አንተን እንጥራን? “ የማያምኑትን እንዴት ይጠራሉ? ሳይሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” ስለዚህ እርሱን የሚሹ እንደሚያመሰግኑት፥ እርሱን የሚፈልጉት እንደሚያገኙትና እርሱን የሚያገኙት እንደሚያመሰግኑት እናውቃለን። ጌታ ሆይ፥ አንተን በመጥራት አንተን እሻለሁ፤ አንተን በእውነት እንዳውቅህ በመታመን እጠራሃለሁ፤አንተ ተሰብከሃልና። እምነቴ፥ ጌታ ሆይ፥ አንተን ይጠራሃል፤ አንተ በመጀመሪያ የሰጠኸኝ እምነት። በዚያ እምነት በልጅህ ሰው መሆን በሰባኪው አገልግሎት ሕይወትን እፍ ብለህብኛል። ጌታ ካልሆነ ጌታ ማንነው? የእኛ አምላክ ካልሆነ በቀር አምላክ ማነው? ከፍ ያለው መልካሙኃያሉሁሉን ቻዩ መሐሪ ደግሞ ጻድቅ ሥውር ነገር ግን ለሁሉ የቀረበ እጅግ ውብ ደግሞ ብርቱ ቋሚ ነገር ግን የማያቋርጥ። አንተ አትለወጥም ነገር ግን ሁሉን ትለውጣለህ። አንተ አዲስ አይደለህም፤ ነገር ግን አታረጅም። አንተ ሁሉን አዲስ ታደርጋለህ፤ ነገር ግን ትዕቢተኞችን መቅረቡን ሳያውቁ በሽምግልና ድል ታደርጋቸዋለህ። አንተ ሁሌ ትሠራለህ፤ ነገር ግን ሁሌ በዕረፍት ነህ። አንተ አሁንም ትሰበስባለህ፤ ነገር ግን አንዳች አልጎደለህም። አንተ ሁሉ ያለህ ስትሆን፥ አሁንም ትደግፋለህ፥ ትሞላለህ፥ ትስፋፋለህ፤ አሁንም ትፈጥራለህ፥ ትመግባለህ፥ ታጎለምሳለህ፤ አሁንም ትፈልጋለህ። አንተ ሳትናፍቅ ታፈቅራለህ፤ ሳታማርር ትቀናለህ፤ ራስህን ሳትገስጽ ጸጸታችንን ትጋራለህ፤ ባህርይ ሳይነዋወጽ ቁጣህን ትገልጣለህ። ሌሎች ሁሉ ያቀዱትን መፈጸም ሲያቅታቸው፥ ያንተ ዕቅድ ግን አይለወጥም። ያገኘኸውን ነገር ግን ፈጽሞ ያላጣኸውን ትቀበላለህ። በዕጦት አይደለህም ነገር ግን ባገኘኸው ሐሴት ታደርጋለህ። አትመኝም ነገር ግን ገንዘብ ታደርግ ዘንድ እጅግ ዋጋ ትከፍላለህ። ነገር ግን ያንተ ያልሆነ ነገር ያለው ማነው? ምንም ሳይኖርብህ ዕዳ ትከፍላለህ፤ እዳህን በመክፈልህ ግን አንዳችም አይጎድልብህም። የእኔ አምላክ፥ የእኔ ሕይወት፥ የእኔ ቅዱስ ደስታ፥ አሁን ያልኩት ምንድነው? ስለ አንተ ሲናገር፥ ሟች የሆነ ሰው ምን ማለት ይችላል? ነገር ግን ወዮ ለማይናገረው፤ ዝምታ አስደናቂ ንግግር ነውና። ኦ በአንተ አርፍ ዘንድ፥ ኦ አንተ በልቤ እንድትገባ እና ልቤ በደስታ ይሰክር ዘንድ፤ የሚያስጨንቀውን ሁሉ እንድረሳውና ብቸኛው የእኔ መልካም አንተን እንድቀርብህ፤ አንተ ለእኔ ምንድነህ? ርኅራኄህን በእኔ አድርግና እንዴት እንደምገልጠው አስተምረኝ። የእኔን ፍቅርና ትኩረት የፈለግህ፥ ካልሰጠሁህ በታላቅ መከራ ልትቀጣኝ የፈለግህ? እኔ ለአንተ ምንድነኝ? እኔ አንተን ባልወድህ ቀላል መከራ አይደለምና፤ ኦ ጌታዬ አምላኬ አንተ ለእኔ ምን እንደሆንህ፥ ምሕረትህ በእኔ ላይ ይሁንና ንገረኝ፤ ለነፍሴ፥ “እኔ የአንቺ ደኅንነት ነኝ” በላት። ትሰማ ዘንድ፥ አሰምተህ ተናገራት። እነሆ፥ ጌታ ሆይ፥ ልቤ በአንተ ፊት ተገልጦ ተቀምጦአል። የልቤን ጆሮ ክፈትና ለነፍሴ “ እኔ የአንቺ ደኅንነት ነኝ” በላት። አንተ ከተናገርህ በኋላ፥ አንተን እንድይዝህ ፍቀድልኝ። ፊትህን ከእኔ አትሠውር፤ ሞቼ እንዳልቀር እንድሞት አድርገኝ፤ ፊትህን ብቻ እንዳየው ፍቀድልኝ፡ አሜን ቀሲስ መላኩ ተረፈ
የሰው አሳብ "በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል።" (ምሳሌ ፲፱ : ፳፩) አንዳንድ ጊዜ ልባችን የሚፈነዳ እስኪመስለን በአሳብ እንወጠራለን ፣ ሌላ ጊዜ ቀልባችን እንዳይከዳን እንሰጋለን። ጭልጥ ብለን በአሳብ እንጠፋለን፣ አለህ አለሽ ሲሉን ምንተ ህፍረታችንን አለሁ እንላለን። ከሰዎች ጋር እያወራን ካለንበት ጊዜ የሌለንበት ጊዜ ይበዛል፤ በአካል ተቀምጠን በአሳብ እንጠፋለን ። የሚገርመው ነገር ያንን ሁሉ መንገድ የነዳነው፣ ያንን ሁሉ ዜብራ የተሻገርነው በፍጹም ከአእምሮአችን ውጭ ሆነን ነው። ስንተኛ የሚጠብቀን ጌታ ስንጓዝም ይጠብቀን ነበር። ግን ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምንድነው? ሕይወትን እኛ እንደ ጀመርናት በራሳችን አቅም የምንለካት ለምንድነው? የእኛ ከመጠን በላይ መንቃት አጠገባችን ያሉት እንዲተኙ ፣ አሳብ የለሽ ሆነው እንዲኖሩ ምክንያት አልሆነም ወይ? ሁሉንም ነገር ማስተካከል እችላለሁ ብለን እንዴት አሰብን? ሁሉንም ሩጫ ያሳካ፣ በሁሉ ሙሉ የሆነ ሰው እናውቃለን ወይ? ቤተሰቦቻችንስ የራሳቸውን ሸክም መሸከም የለባቸውም ወይ? ታናሽ ሆነን እንደ ታላቅ እናስባለን። ወላጆች ልጅ ሲሆኑብን ወላጅ ካልሆንኩ እንላለን። ደግሞስ እግዚአብሔር ሁሉን እያየው ከሆነ ፍትሕ ጠፋ ብለን መጨነቃችን ምን ይጠቅማል? ለቀኑ ብልሃት እንዳለው ረስተን ፣ ሲያመጣው ከመቻያው ጋር መሆኑን ዘንግተን መዋተታችን ለምን አይበቃም? ችግርን መቀነስ እንጂ ማጥፋት እንደማንችል ለምን ረሳን? የድርሻችንን መወጣት እንጂ መረበሽ ጥቅም እንደሌለው ዛሬም አላመንም። የሆኑ ነገሮችን እንዳልሆኑ መመኘት ምን ይፈይዳል? የአቅማችንን ከጣርን ፈንታው የጌታ መሆኑን ለምን አንቀበልም? በልባችን ብዙ አሳብ አለ። አንዱን ጨረስኩት ስንል ሌላው ይተካል። ችግር ካለቀማ ምድር ገነት ሆኗል ማለት ነው። የሚጠሉን ሰዎች ይረብሹናል። ከሚሸነግሉን ሰዎች የተሻሉ መሆናቸውን ገና አላወቅንም። ምቀኞች ባይኖሩ ጠንቃቃ አንሆንም ነበር። ጠላቶችን መውደድ ያለብን ዕድሜአችን እንዲረዝም ስለሚያደርጉት ነው። ምንም በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ያሉት ዝማሬ ላይ ሳይሆን መጠጥ ላይ ነው። ሰው ችግር ከሌለበት ችግር ይፈጥራል። ምኞታችን እጅግ ብዙ ነው። ዓለም ለእነ እገሌ ብታልፍም እኛ ጋ ላታልፋ የመጣች ይመስለናል። አንድን ነገር እስክንጨብጠው ያለን ጥረት ብዙ ነው። ከጨበጥነው በኋላ ትርጉም እናጣለን። ሁሉም ነገራችን የችኩላ ነው፣ ለማግባትም ለመፍታትም ፈጣን ነን። በአንድ ጊዜ ሁለት ትምህርት፣ ሁለት ሥራ ፣ ሁለት ሃይማኖት ማራመድ እንፈልጋለን። ሁሉም ነገር ሰልችቶን ደግሞ አስቀምጠነው እንሄዳለን። ዕቅድ በዕቅድ እንሆናለን። ከማማከር በራስ መወሰንን እንደ ጀግንነት እንቆጥረዋለን። እንደሚኖር ብንሠራም እንደሚሞት መዘጋጀት አለብን። የሞቱትን ስናስብ ከሞታቸው ዕቅዳቸው ያስለቅሳል። አዎ እኛ እውነትም ውሸትም ነን። እውነቱ አለሁ እያልን ነው፣ ውሸቱ ደግሞ ላንኖር እንችላለን። ለቀጠሮ የማንበቃ፣ እገሌ ይሞታል ብለን እያስታመምን እኛ ልንቀድም የምንችል ፣ እርግጠኛ ባልሆነ ሕይወት ውስጥ ያለን ነን። እርግጡ እግዚአብሔርና የዘላለም ሕይወት ብቻ ነው፡፡ "እርሱ እኮ ልጅ ነው" ስለሚሉን ልጅ አይደለንም። ልጅ አይሞትም ያለው ማን ነው? የማንንም ውድቀት መመኘት አያስፈልገንም ፣ ማንንም ለመበቀል መኖር አያሻንም። ለዕለት የሚበቃ ካለን ማመስገን አለብን። ስለ ታመምን አንሞትም ፤ ጤነኛ ስለሆንን ምንም አይነካንም ማለት አይደለም። ሕፃን ልጅ ወላጆቹ ወደሚያውቁት መንገድ ስለሚጓዝ አይሰጋም። ላመሉ የት ነው? ብሎ ይጠይቃል ፣ ቢነግሩትም አይገባውም ፤ በወላጆቹ እውቀት ያርፋል። እኛም እንደ አማኙ ሕፃን አንተ ታውቃለህ ብለን ማረፍ አለብን። አታስቡ አልተባልንም ፣ አትጨነቁ ተብለናል። ኩንታል አሳባችን በሙሉ ግን አይፈጸምም። በአሳባችን ላይ እርሱ ሲያስብበት ብቻ ይሆናል። ትራፊኩ እጁን ወደ ላይ አንሥቶ ቁሙ ሲል መኪናውም ሾፌሩም ይቆማሉ ። የእግዚአብሔር ሥልጣንም የሰዎችን አሳብ፣ ሥልጣንና ኃይል ያስቆማል። ለምንድነው ያስቆምከኝ ብለን ትራፊኩን አንጠይቅም። ለእኛ ደኅንነት ያስቆመንን አምላክ ለምን ? አንለውም። ብቻ ብዙ ብናስብም የሚጸናው ምክረ ሥላሴ ነው! አምላኬ ሆይ፣ አንተ ያልከው ይሁን። ዛሬ እንኳ ሁሉን ላንተ ልተውልህ! ሁሉን መተው ቢያቅተኝ ነገን እንኳ ላንተ ልተውልህ። ረጅም አስቤ ባጭር የምቀር ነኝ። ልቤ ከፍ ከፍ ያለበትን አሳብ ወዲያው ወርዶ አገኘዋለሁ። ማን ያድነዋል? ሲሉኝ ባንተ ድኜአለሁ፣ እውቀትህ አሳልፎኝ በእውቀቴ እደገፋለሁ። የእኔም የሰዎችም አሳብ ወጥመድ ነው ። ያንተ አሳብ ግን መንገድ ነው። አዎ አንተ ያልከው ይሁን። ሁሉን ላንተ መተውን፣ በእምነት ማደርን አለማምደኝ። ማጉረምረምን፣ ተስፋ ቢስነትን አሸንፍልኝ። ንቀትን እንድታገሥ እርዳኝ። ቢልልኝ እዚህ እደርስ ነበር ማለትን ከእኔ አርቅ። ያልከው ይሁን ። በሰጠኸኝ ነገር አስደስተኝ ። አሜን! ዲ.አ.መ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም.
የተቆራረሰ ልብ ያላቸው በሌላቸው ጨከኑ፣ አግኝተው ካልሰጡ ከቶ መቼ ሊሰጡ ነው ? ደግሞም የማይሰጥ ድሀ ማነው ? ለድሀ ጥሩ ቃል መናገር እርሱም ምጽዋት ነው። የአፍ ጮማ መቁረጥ በድU መሳለቅ፣ በእግዚአብሔር ማፌዝ ነው ። የማይቀበል ሁሉ ያለው ባለጠጋ ማነው? ገንዘብ ሰጥቶ ከድሀ ደስታ ይቀበላል። ድሀ ማለት ምንም የማይሰጥ ማለት አይደለም፤ ባለጠጋ ማለትም ምንም የማይቀበል ማለት አይደለም። ለመስጠት ሀብተ ሥጋ ፣ ሀብተ ነፍስ ያስፈልጋል። ለመስጠት በሕይወት መኖር ያስፈልጋል። የማይሰጡ እጆች ዛሬ በሰይጣን ተገንዘዋል፡ ነገ በፈትል ይገነዛሉ። መስጠትም ዕድል ነው። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የበለጠ ደስተኛ ነው። ወገን የጨከነባቸው ልባቸው ይቆራረሳል። በበረሃ በውኃ ጥማት እንደ ተሰነጣጠቀ መሬት ይሆናሉ። ያዘኑብን ደስታችንን ይዘውብናል። የእኛን ስንሰጣቸው የእነርሱን ሊሰጡን ተዘጋጅተው የሚጠብቁን አሉ። እኔ ነኝ ማለት የማይችሉ፣ ራሳቸው ፍሬኑ እንደ ተበጠሰ መኪና አልቆም ያላቸው፣ ጽድቅን እያዩ ኃጢአትን የሚግጡ፣ ሁልጊዜ እየማሉና ራሳቸውን እየገዘቱ በቆሻሻው ስፍራ የሚገኙ ልባቸው የተቆራረሰ ነው። ራስን ማጣት፣ የሚፈልጉትን አለማወቅ፣ በመንፈሳዊ ድንዛዜ መኖር፣ በእግዚአብሔር ቤት ሆኖ ከእግዚአብሔር መለየት፤ በፍቅር ቤት በቂም ፣ በጸሎት ቤት በትዝብት መኖር ያደከመው ልቦቹ የተቆራረሱ ናቸው ። ሳይናገር ብልሃት የሚፈልግ ሞኝ፣ የልቤን ለምን አላወቁልኝም? ብሎ የሚጣላ ምስኪን ልቦቹ የተቆራረሱ ናቸው ። በግብጽና በከነዓን መካከል የሚኖር የሕይወት ጥጋብ፣ የነፍስ እርካታ የለውም። መርዛማ አሳቦች ይበክሉታል። ማኩረፍ ዘመዱ፣ ዝምታ አገሩ ይሆናል። ሰዎች አስረድተናቸውም ከተረዱን ዕድለኛ ነን። ሰው የሰውን ችግር ለመረዳት ራስ ወዳድነቱ መሰናክል ይሆንበታል። የሚጮኸው ከራሱ አንጻር ነው ። ከተማ ቢፈርስ ግድ የለውም፣ አጥሩ ሲነካ ግን ያመዋል። ሚሊዮን ሲረግፍ ሰምቶ እንዳልሰማ ያልፋል፣ ልጁ ሲያተኩሰው ግን ሆድ ይብሰዋል። መናገር የማይችሉ፣ በውስጣቸው በማጉረምረም የሚሰቃዩ ልባቸው የተቆራረሰ ነው። ፍቅርን ሰጥተው ጥላቻን ያተረፉ የመሰላቸው፣ ልቤን ሰጥቼ ቀልባቸውን እንኳ አልሰጡኝም ብለው የሚያስቡ የተቆራረሰ ልብ ይዘዋል። ይህ ስንጥቅጥቅ የመንፈስ ቅዱስ ዘይት ካልሆነ ምንም ሊያረጥበው አይችልም። የተቆራረሱ ልቦች ሰባራ አንገት፣ ስንኩል ጉልበት ይፈጥራሉ። ጥላቻ ሰባኪ አላት፣ ጥላቻ ሠራዊት አላት፣ ጥላቻ ደቀ መዝሙር አላት። በጥላቻ የተወጉ ሰዎች የማይጣሉት ሰው የለም። የበደላቸውንና ያልበደላቸውን መለየት አይችሉም። እንዴት የቆመ ሰው ከሞተ ሰው ጋር ይጣላል? በጥላቻ የተመረዙ የጅምላ ፍረጃ፣ የጅምላ ፍጅት ያውጃሉ። ሰዎች ስለ ተመረዘው ቃላቸው፣ ስለሚገድል ፍላፃቸው ይጠሏቸዋል። በውስጣቸው የሚያሳልፉትን ስቃይ ግን ማንም አይረዳላቸውም። ካልታመመ የሚያሳምም፣ ባልታወከ የሚያውክ ማንም የለም። ለሰው ሁሉ ቅን አመለካከት የሌላቸው የተቆራረሱ ልቦችን ይዘዋል። የተቆረሰ ልብ ለሌላው የሚያዝን ነውና ያረካል፣ የተቆራረሰ ልብ ግን በጥማት ምድረ በዳ የሚያልፍ ነው። የተቆራረሱ ልቦች በራስ ሥራ ከማፈር የተነሣ ፣ ራስን ይቅር ካለማለት ይከሰታሉ። የተቆራረሰ ልብ ከሰዎች ብዙ ጠብቆ ጥቂት ባለመቀበል ይከሰታል። የጀመርኩት ሁሉ አይሳካም ፣ የተሳካው ዕድሜ የለውም ብሎ የሚያስብ ሰው የተቆራረሰ ልብ ይይዘዋል። ያን ጊዜ በደመና ውኃ ይጠማዋል። ሆዱን ባሕር ባሕር ይለዋል ። ሆደ ባሻነት ያስለቅሰዋል። የቆሙትን ትቶ የሞቱትን እያስታወሰ ያዝናል። የተቆራረሰ ልብ መኖሪያውን ከመቃብር ሥፍራ ያደርጋል። የእኔ ነገር የሚል ልቅሶ ያስጀምራል። ሰውም እግዚአብሔርም ትተውኛል የሚል ሹክሹክታ ያመጣል። የተቆራረሰ ልብ የሚድነው በንስሐ ፣ በእምነት ፣ መለኮትን ብቻ ተስፋ በማድረግ ነው ። አዎ ነገሥታት የመኖሪያ ፈቃድ ይስጡ ይሆናል ፣ የመኖር ፈቃድ የሚሰጥ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው። አንተ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር እኖራለሁ በል! "መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤" ዘዳ. 33፥27 ዲ.አ.መ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም.
አዳምጣለሁ (2) ይቅር በለኝ አዳምጣለሁ ። የሰዎችን ፊት ዓይኔ አትኩሮ ያያል ። ጠንቋይ መዳፍን ሲያነብ ፣ እኔ ፊት እያነበብሁ ራሴን አሰቃያለሁ ። ዛሬ ፊታቸው ጠቆረ ፣ ምን አስበው ነው? እላለሁ ። የምታኖረኝን ትቼ የማያኖሩኝን እፈራለሁ ። መኖሬ በሰው ፍቅር ላይ የተመሠረተ ይመስለኛል ። ዓለሙ ሁሉ ቢያድም አንተ ካልፈቀድህ ማንስ ይነካኛል ? ጌታ ሆይ የሰዎችን የድምፃቸውን መጠን በጆሮዬ እለካለሁ ። ሰላምታቸው ቀዘቀዘ ደግሞ ምን ሊሉኝ ነው ? እላለሁ ። ስሜቴ ከፍና ዝቅ ይላል ። ቋሚ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ደስታዬን መሥርቼ ስወጣና ስወርድ እውላለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። አንተ በእውነት ስትወደኝ ምንም አይመስለኝም ፣ ሰዎች በሽንገላ ሲያፈቅሩኝ ልቤ ይዘላል ። ቀድሞም ያልወደዱኝ ሲጠሉኝ ግራ ይገባኛል ። የሰው ፍቅር ከሞት አያድንም ፣ “ወዶኛልና አዳነኝ” የተባለልህን አንተን ፣ የነፍስ አብነቴን ችላ ብያለሁና ይቅር በለኝ ። የእግር ኮቴዎች ምን ይዘው መጡ ? የሚል ጥርጣሬ ፣ የስልክ ጥሪዎች ምን ሊሉኝ ነው ? የሚል ስጋት ይጥልብኛል ። ትላንት ሰላም ያሉኝ እንዲህ ብለው ነው ፣ ዛሬ ደግሞ ይህን ቃል ቀነሱ እያልሁ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በብሉይ በሐዲስ ፣ በእውነት ምስክሮች የጸናውን ፣ አንተ ለእኔ ያለህን በጎ አሳብ አቃልያለሁና ይቅር በለኝ ። አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። ስሜን ሲያቆላምጡ ደስ ይለኛል ፣ ውለታ መስሎኝ ካልከፈልሁ ያሰኘኛል ። ለስም አጠራሬ የምከፍል ብቸኛ ሰው የሆንሁ ይመስለኛል ። በሙሉ ስሜ ሲጠሩኝ ደግሞ ደስታዬ እንደ ካባ ወደ ኋላ ይወድቃል ። ሰዎች ሥራቸውን ስለ ሠሩ ከማመስገን በላይ ለእኔ ልዩ ውለታ ያደረጉልኝ መስሎ ያሳቅቀኛል ። ቁመናዬ በነፋስ ሽውታ ይነቃነቃል ፣ ቆዳዬ ትንሽ ሲነካ የሚቆስል ስስ ሆኗል ። እንኳን ችግር መጥቶ ፣ ሊመጣ ነው እያለ ይርዳል ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አንተን ሳይሆን ወደዚህ ዓለም ያላመጡኝን ፣ ከዚህ ዓለም የማይወስዱኝን ፤ እንደ እኔ ፈሪ የሆኑትን አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ሰዎች ቃላቸውን ሲያጥፉ ፣ የትላንት ንግግራቸው ከዛሬው ሲዘባረቅ አዳምጣለሁ ፣ ለምን ? ብዬ በቀጭን መርፌ ነፍሴን እወጋጋታለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ሰዎች ለሌላው ሰው መርዛም ዱለታ ሲዶልቱ ፣ እኔን ባይነኩኝም አዳምጣለሁ ። ሲያሙ ቆይተው ፣ ያሙት ሲመጣ አቅፈው ሲስሙት እታመማለሁ ። ወላጅ ቀብረው በሠልስቱ ስለ ውርስ ሲያወሩ አዳምጣለሁ ፣ ስለዚህ እደቅቃለሁ ። በአካሌ ላይ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ገና ሞት እያለ መታመምን እፈራለሁ ። በመገናኛ ብዙኃኑ ስለ በሽታ ሲወራ እኔ እንደ ታመመ ሰው እንቅስቃሴ ማድረግ እጀምራለሁ ። አዎ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ትንሣኤና ሕይወት መሆንህን አምናለሁ እያልሁ በሽታን እሰጋለሁ ። ጠቢብ አልቻለም ሲባል በጆሮዬ የምሰማው እግዚአብሔር አልቻለም ብዬ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። እያንዳንዱን ቃል አጠራለሁ ፣ እንዲህ ያለው እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው እያልሁ አሰላስላለሁ ። እኔ እንደ ልቤ እየተናገርሁ ሰዎች ግን ችሎት ላይ ቆሞ እንደሚናገር ሰው በሰቀቀን እንዲያወሩኝ አደርጋለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አሰቡትም አደረጉትም ፣ ተናገሩትም ዝም አሉትም ያው ነው ብዬ አረፋ መትቼ ፣ በሺህ አባዝቼ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በሁለት ጆሮ እየሰሙ ከሰው ጋር መኖር እንደማይቻል ባውቅም ፣ በትዕግሥት ማጣት የካብኩትን ብንድም አሁንም አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ምን ይሉኛልን ፈርቼ ሥራዬን ፣ ሐሜትን ተሳቅቄ ራእዬን ትቻለሁና ይቅር በለኝ ! ልጆቼ ስለ እኔ ያላቸውን የፍቅር ሙቀት አዳምጣለሁ ። “ብሞትስ ምን ትላላችሁ” ብዬ የቅኝት ፍተሻ አደርጋለሁ ፣ ገና ሳልሞት አላለቀሱም ብዬ ተስፋ እቆርጣለሁ ። ማዳመጥ አስክሮኝ ብሶትን እወልዳለሁ ። ከሰው ጋር በጨዋታ በሳቅ ውዬ ፣ ወደ ቤቴ ስመለስ የተናገርኩትን ሌሊት ሙሉ ከልሼ አዳምጣለሁ ። አስቀይሜ ቢሆንስ ብዬ እሰጋለሁ ፣ ደስታዬን ሳበላሽ አድራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስልክ ደውዬ በመጀመሪያው ጥሪ ካልተነሣ አዳምጣለሁ ። የመጀመሪያው ጥሪ በእኔ ትርጉም ፍቅር ነው እላለሁ ፣ ሦስተኛው ጥሪ ላይ ካልተነሣ ስላልፈለጉ ነው እላለሁ ። ደስታዬን ጨቁኜ ለራሴ አለቅሳለሁ ። ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ኀዘን ውስጥ እገባለሁ ። ሰዎቹን ሳገኛቸው ያን ጊዜ ስልክ ያላነሣሁት ታስሬ ፣ ታምሜ ነበር ሲሉኝ በራሴ አፍራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስብከት ስሰማ አዳምጣለሁ ፣ ሰባኪውን ካወቅሁት የእኔን ምሥጢር እያወጣ ነው ብዬ ቃልህን ለመስማት እንኳ እፈተናለሁ ። እኔን ሊናገር ፈልጎ ነው እያልኩ አደባባይህን ፣ የንስሐ ድምፅን እጋፋለሁ ። አዳምጣለሁና እባክህ ይቅር በለኝ ። ሰዎች የትዳር ውድቀታቸውን ሲናገሩ የእኔም ጉድ ባልሰማው ነው እንጂ ይህን ይመስላል እያልሁ ቤቴን አውካለሁ ። ኑሮዬን አፈርሳለሁ ። ለእልህ ስላደረግሁት አልቆጭም ። ጉልበቴ በማይረባ ነገር ያልቃል ። ቃልህ ተተርጉሞ እንኳ አይገባኝም ፣ የሰዎችን ነጠላ ቃል ግን ተርጕሜ እጣላለሁ ። ትላንት የሰማሁት ቃልህን ረስቼዋለሁ ፣ የሃያ ዓመት ቂም ግን በውስጤ ሕያው ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ደግ ቃል ቶሎ አይገባኝም ። ትምህርትም ጎበዝ አይደለሁም ። ክፉ ቃል ግን ያለ አስተማሪ ይገባኛል ፣ ፈነካክቼ - አብጠርጥሬ እጋተዋለሁ ። አቤቱ ያን ጊዜ መተንተን ይሆናል ፣ የማይጠቅም መተንተን ነው ፤ ያን ጊዜ ሁሉም ነገር ብልጭ ይልልኛል ፣ የማይጠቅም ብርሃን ነው ። ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል ፣ የማይጠቅም ልቅሶ ነው ። ማዘንስ ሰዎች ስለበደሉኝ ሳይሆን ሊያስቀይሙህ የማይገባውን አንተን በማሳዘኔ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ። ተፈጸመ ዲ.አ.መ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም.