AY Bible Club Channel
Статистика“ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”” — ኢሳይያስ 40፥8
- Последний пост
- 14 авг.
- Последнее чтение
- 15 авг.
- Постов за неделю
- 5
- Всего постов
- 22
- Тип
- открытый
- Язык
- und
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- 264
- 1/48двое суток
- 302
- 1/72трое суток
- 326
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
እግዚአብሔርን በማወቅ ============================ 📖“በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።” — ኢሳይያስ 11፥9 በህይወቴ ውስጥ ስላወኳቸው ሰዎች የማልፀፀትባቸው ወገኖች አሉ። እነርሱን ማወቄ እጅግ ጠቅሞኛል። አሁን ላለውም ማንነቴ የተወሰነ ድርሻ አላቸው። በተቃራኒው ደግሞ "ምነው እነዚህን ሰዎች ባላወኳቸው" ያልኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። እውቀት ትልቅ የሆነ ኃይል አለው። ለዚህ ነው የእውቀታችን መሰረት ሊፈተሽ የሚገባው። ማወቅ እንዲሁ ዝም ብሎ መረጃ ከመሰብሰብ በእጅጉ ይለያል። እንኪያስ ከሆነ ግን ያወቅነው የመሰለን ነገር ያጠፋናል። ከላይ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው ብዙ ነገር አውቀን በውሳኔያችን የተፀፀትንባቸው ጊዜያቶች ይኖሩ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ነገርን በማወቃችን ከቶ ልባችን ዝቅ አይልም። እርሱም "እግዚአብሔርን ማወቅ" ነው። እስኪ መለስ ብለን ራሳችንን እንጠይቀው። እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ወይስ ስለ እግዚአብሔር እናውቃለን? በሁለቱ መካከል ትልቅ የሆነ ልዩነት መኖሩን ልብ ይሏል። ወገኖቼ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀና ግላዊ የሆነ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ስለ እርሱ በሰሚ ሰሚ ማወቅ ሳይሆን መንፈሱን ተጠማጥመን ራሱን እንዲገልጥልን ልንቃትት ያሻናል። የተለወጠ ህይወት መኖር የምንችለው ከእርሱ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ህብረት ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።” (ኢሳ 11፥9) አምናለሁ ይህ በቅርቡ ተፈፃሚ እንደ 'ሚሆን። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ አንተን በግሌ ማወቅና ፍቅርህን በሙላት ማስተዋል እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
🎉 ሰላም ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች 🎉 ሳምንታዊው የጥያቄና መልስ ውድድር ለ39ኛ ዙር ዛሬ ማታ 2:30 ላይ የሚቀጥል ይሆናል። በጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የጊዜው የቴሌግራም ቻናል ቤተሰብ መሆንዎ እንዳይረሳ። https://t.me/giziew7 ሁላችሁም በጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ተሳታፊዎች እንድትሆኑ ከወዲሁ እንጋብዛችኋለን። ተባረኩ!! ————————— YouTube | Telegram | Facebook | Instagram
ፃዲቅና ታማኝ ============================ 📖“የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።” — ኢሳይያስ 11፥5 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕፀፅ አልባ የሆነ ፃዲቅ ነው። የምድር ላይም ቆይታው ኃጢአትን ድል በመንሳት የተጠናቀቀ ነበር። ለታማኝነቱ ከቶ ወደር የለውም። እርሱ ትላንት፣ ዛሬና ነገ ሁሌም ለልጆቹ ታማኝ አምላክ ነው። እነዚህን ሁለት የክርስቶስ ባህሪያት ኢሳይያስ “የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።” (ኢሳ 11፥5) በማለት ስዕላዊ በሆነ መልኩ ሲገልጠው እንመለከታለን። አንደኛ፣ ጽድቅ በፅድቅ መንገድ ያላለፈ አካል ስለ ፅድቅ ሊያወራ አይችልም። ተከታዮቹንም ሊያፀድቅ አይነሳም። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ፃዲቅ በመሆኑ በኃጢአት ምክንያት ፅድቃቸው የመርገም ጨርቅ ለሆነባቸው መላ ሰብዓዊን የፅድቅ አድራጊና ፈፃሚ ሆኖ መጣ። በእርሱ በተደረገውም ቤዛነትና የመስቀል ላይ ስራ ፀደቅን። “...ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።” (1ኛ ቆሮ 6፥11) ሁለተኛ፣ ታማኝነት እርሱ ፃዲቅ ብቻ ሳይሆን ታማኝም አምላክ ነው። የተናገረውን ይረሳ፣ ቃል የገባውንም ያጥፍ ዘንድ ከቶ ሰው አይደለም። ታማኝነቱ ራሱን እስከ መስጠት አድርሶታል። ታዲያ ይህን በማስተዋል ታማኝ ለሆነልን ጌታ ታማኞች ልንሆን ያስፈልጋል። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ጽድቅን የተጎናፀፍክና ታማኝነትን የደረብክ ፈላጊዬ ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ እኔም ከአንተ ዘንድ የቀረበልኝን ፅድቅ በመቀበል ለአንተ ዘውትር ታማኝ መሆን እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
የእግዚአብሔር መንፈስ ============================ 📖“የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” — ኢሳይያስ 11፥2 መፅሐፍ ቅዱስ ነገሮች እንዲሁ በአጋጣሚ የሚሆንበትን ታሪክ መዝግቦልን አናገኝም። የሆነው ሁሉ የሆነው፣ እንዲሁም ሊሆን ያለው በእግዚአብሔር ሀሳብ ነው። ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ለመግለጥ ትንቢት አንደኛውና ዋነኛው መሳሪያ ሆኖ እናገኘዋለን። የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ስጋ ለብሶ ወደ ምድር መምጣት እንዲሁ የሆነ ነገር ሳይሆን የታሰበበት ጉዳይ ነበር። ይህን ለመግለጥ መረጃ ከሚሆኑን ክፍሎች መካከል አንዱ “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል።” (ኢሳ 11፥1) የሚለው ተጠቃሽ ነው። ቀጠል አድርጎም ስለ ባህሪው ይናገራል። “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤” (ቁ 2፣3) “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።” (ፊል 2፥5) ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ስፍራዎች እንድንሆን ያስፈልጋል። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥበብ ለጎደለው ጥበብን፣ ማስተዋልን ላጣ ማስተዋልን፣ አቅጣጫን ለሚፈልግ ምክርን፣ አቅመ ቢሶ ለሆነ ኃይልን፣ መገንዘብ ለከበደው እውቀትን፣ እንደ ቃሉ ለመኖር ደግሞ የሚያግዘን ታላቅ ስጦታ ነው። በዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ስንሞላ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ሀሴት እናደርጋለን። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ህይወቴ እንዲሁ በአጋጣሚ የሚመራ ሳይሆን በአንተ ሀሳብ መሆኑን እንድረዳ ስላስተማርከኝ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ” በሆነው ስጦታ ትሞላኝ ዘንድ እማፀንሃለሁ። አሜን።
ያለቀ የተቈረጠ ============================ 📖“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።” — ኢሳይያስ 10፥23 በአሦር ላይ የሚሆነውን የእግዚአብሔር ፍርድ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ አስር ያስቃኘናል። የአሦር ንጉስ በልቡ ካለው ትዕቢትና ንቀት የተነሳ በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ሲያላግጥ እንመለከታለን። “እርሱ እንዲህ ብሎአልና፦ አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፥ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፥ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤” (ኢሳ 10፥13) ነገር ግን ፍፃሜው የተሸላለመ እንደማይሆን ዝቅ ብለን ስናነብ እናገኛለን። “ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል። የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ቅዱስም እንደ ነበልባል ይሆናል፤ እሾሁንና ኵርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል ይበላውማል።” (ቁ 16-17) ልብ በኩራት ሲወጠር መጨረሻው መልካም አይሆንም። በፈጠረን አምላክ ላይ ጀርባችንን እንድንሰጥ ከማድረጉም በተጨማሪ ራስ ተኮሮች እንሆናለን። ይህም ወደ ለየለት የጥፋት ግዳና ይወስደናል። ሉሲፈር ሰይጣን የሆነው "እኔ፣ እኔ፣ እኔ" ማለት በጀመረ ጊዜ እንደነበር ልብ ይሏል። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።” (ቁ 23) ይህ ተስፋ የተነገረው ከእስራኤል ዘር ለተረፉት ነበር። እርሱ "የወሰነውን" ጥፋት እንደ 'ሚያመጣና አሦራውያንን ከቶ እንዳይፈሯቸው አበረታታቸው። የክፋት አለቃ የሆነውና በኃጢአት ጠምዝዞ ወደ ራሱ ሊስበን ሌት ተቀን የሚለፋው ጠላት "የተወሰነው" ጥፋት በእርሱ ላይ ተፈፃሚ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ታዲያ ያለው ሰዓት ጥቂት መሆኑን አውቆ እንደ ተራበ አንበሳ ሊውጠን አፉን አሞጥሙጦ ዙሪያችን ያደባል። ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ነውና ከቶ አያገኘንም። ይህም ትልቅ እምነትና ድፍረት ይሆነናል። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ሁሌም ለልጆችህ የምትጠነቀቅ መልካም አባት ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ጠላትን የማሸንፍበትን ፀጋና ኃይል ሙላብኝ በማለት እፀልያለሁ። አሜን።
ክፍል አምስት፣ አባትና ሰላም ============================ 📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” — ኢሳይያስ 9፥6 የጨለማ ህይወታችንን የሚገፍልን አምላክ "የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።" አባትነትን ከሰላም ጋር አዋህዶ በመያዝ ወደ ኤደን የምናደርገውን ጉዟችንን በብርሃን ይመራናል። አንደኛ፣ የዘላለም አባት አባት መከታ ነው። የቤቱ ዋልታና ማገር ያለው በእርሱ ነው። ስጋ ደግሞ ሟች በመሆኑ አባት ከአጠገብ ሲታጣ ብዙ ነገር ይጎድላል። በሰማይ ያለው አምላክ አባትነቱ ዘላለማዊ በመሆኑ ከቶ አናጣውም። ሁሌም ቅርብ ነው። እንዲህም በማለት የከበረውን ተስፋ ሰጠን፦ “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።” (ዮሐ 14፥18) ሁለተኛ፣ የሰላም አለቃ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ "የዘላለም አባት" ብቻ ሳይሆን "የሰላም አለቃ" ጭምር ነው። እርሱን ወደ ህይወታችን ስናስገባ የምናገኘው ሰላም ወደር የለውም። የተቅበዘበዘች ነፍስ እረፍትን ታገኛለች። ምን አልባት ዛሬ ሰላምን በማጣት እየባዘንን ያለን ሰዎች እንኖር ይሆናል። ወደዚህ "የሰላም አለቃ" ትመጡ ዘንድ በፍቅር አድማችኃለሁ። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” (ዮሐ 14፥27) በማለት ቃል ገብቷልና። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ አባቴና ሰላሜ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ዘላለሜን ከፊትህ እንዳልታጣ በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
🎉 ሰላም ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች 🎉 ሳምንታዊው የጥያቄና መልስ ውድድር ለ38ኛ ዙር ዛሬ ማታ 2:30 ላይ የሚቀጥል ይሆናል። በጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የጊዜው የቴሌግራም ቻናል ቤተሰብ መሆንዎ እንዳይረሳ። https://t.me/giziew7 ሁላችሁም በጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ተሳታፊዎች እንድትሆኑ ከወዲሁ እንጋብዛችኋለን። ተባረኩ!! ————————— YouTube | Telegram | Facebook | Instagram
ክፍል አራት፣ ድንቅ መካር ኃያል ============================ 📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” — ኢሳይያስ 9፥6 መጠሪያ ስሜን እወደዋለሁ። አባቴ እንዳወጣልኝ ሳስብ ደግሞ ይበልጥ ደስ ይለኛል። በስሜ አንድም ቀን አፍሬም ሆነ ተሸማቅቄ አላውቅም። ምንም እንኳን በዚህ ዘመን ስም ማንነትን የመግለጥ እንብዛም አቅም ባይኖረውም በቀደመው ጊዜ ግን ጥልቅ ትርጉም ነበረው። ከጨለማ ስፍራ በማላቀቅ በብርሃን የሚያራምደን ጌታ ስሙ "ድንቅ መካርና ኃያል" በመባል ቀርቦ እናነባለን። የክርስቶስ ስም እንዲሁ እንደሌሎች ስሞች አይደለም። ስሙ ከስሞች ሁሉ ይለያል። በስሙ ደዌያን ተፈውሰዋል፣ አንካሶች ዘለዋል፣ ዲዳዎች ሰምተዋል፣ ሞት ተሸንፏል። አዎ፣ ስሙ ድንቅና ኃያል ነው። ድንቅ የሆነን ነገር ማድረግ ይችላል። ለሰው ሁሉ ያቃተ ጉዳይ በስሙ ሲመጣ ቀሊል ይሆናል። ተራራን የመዳን ኃይል ያለው ስሙ ዛሬም ገዝፈው የታዩን ነገሮች ሁሉ ደልዳላ ሜዳ ያደርጋቸዋል። 🛐ፀሎት፣ አምላኬ ሆይ፣ በሕይወቴ ድንቅ የሆነውን ነገር ስለምታደርግ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ለኃያሉ ስምህ ደግሞ ክብርን መስጠት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
ክፍል ሶስት፣ አለቃ ============================ 📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” — ኢሳይያስ 9፥6 የተወለደው ሕፃን ስጦታ ብቻ ሳይሆን አለቃም ጭምር ነው። አለቃ የሚያዘው ሁሉ የሚደረግለት ስልጣን አለው። ያሻውንና ልክ የመሰለውን ነገር ቢከውን ከልካይ የለውም። አለቃ ነውና። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አለቃ ሆኖ ግን የባሪያን መልክ ያዘ። የከፍታን ስፍራ በፈቃዱ በመልቀቅ የከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ። ሁሉን ማድረግ ሲቻለው ግን እኛን ለማዳን ሲል በሸላቾቹ ፊት ዝም አለ። ፍቅር አለቃነትን አስትቶ አገልጋይ ያደርጋል። ይህም በገሃድ ተንፀባርቋል። አምላክ ሰው በመሆን የዓለምን ህዝብ ሁሉ ይቤዥ ዘንድ በመስቀል ላይ ራቁቱን ተንጠለጠለ። 🛐ፀሎት፣ አምላኬ ሆይ፣ እኔን ከፍ ለማድረግ አንተ ስንቴ ዝቅ አልክ። አባት ሆይ፣ አለቃነትን አስትቶ አገልጋይ ለሚያደርገው ፍቅር መገዛት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
ክፍል ሁለት፣ ተሰጥቶናል ============================ 📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” — ኢሳይያስ 9፥6 በጨለማ ይኖር የነበረ ህዝብ ብርሃን እንደ ወጣለት በትላንትናው ቀን ጥናታችን ተመልክተናል። ቀጠል አድርገን ደግሞ የዚህን ብርሃን ማንነት በሚቀጥሉት ጊዜያቶች አብረን እናያለን። በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ዘጠኝ ቁጥር ስድስት ላይ ከተገለፁት ነገሮች “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” የሚለው አንዱ ነው። ይህ ትልቅ የሆነን ትምህርት ያስተምረናል። ከጨለማ ስፍራ በራሳችን መውጣት የማንችል በመሆኑ እጃችንን ይዞ ወደ ብርሃን የሚያወጣን ተሰጠን። ድነት ስጦታ እንጂ ስራ አይደለም። ዋናው የብርሃን ምንጭ እስከተቋረጠ ድረስ የፈለገ ብንጥርና ብንለፋ ጨለማችንን ማብራት አንችልም። ለዚህ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” (ዮሐ 15፥5) በማለት የሚናገረው። የእየሱስ መወለድ ስጦታችን ሆነልን። ይህን ሊተካከለው የሚችል ዋጋ ባለመኖሩ እንዲሁ በነፃ ተሰጠን። ስለዚህ ይህን በመረዳትና የተደረገልንን ነገር በማስተዋል ለተሰጠን ጌታ ተሰጥተን እንኑር። 🛐ፀሎት፣ አምላኬ ሆይ፣ ስጦታዬ ነህ። ከወርቅና ከዕንቁ የማስበልጥህ ውድ ንብረቴ ነህ። ተመስገን። አቤቱ፣ እኔም ደግሞ ራሴን ለአንተ ህያው ቅዱስ መስዋዕት አድርጌ መስጠት እፈልጋለሁና ተረከበኝ። አሜን።
ክፍል አንድ፣ ብርሃን አየን ============================ 📖“በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” — ኢሳይያስ 9፥2 በማልፈልገውና ለእኔ እንግዳ በሆነ ሁኔታ አስቤው የማላውቀውን የትምህርት መስክ ስማር ራሴን ጅማ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አገኘሁት። ያ ወቅት ለእኔ እጅግ ከባድ ነበር። ለዘመናት የገነባሁት ነገር ከመቅፅበት የፈረሰ መሰለኝ። ዕልሜን በመጠራጠር ጭልጥ ብዬ ቅዠት ውስጥ የገባሁ እንደ ሆነ ተሰማኝ። ሁሉም ነገር ጨለመብኝ። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኔ ያለው ዓላማ የተሻለ ነበር። ምንም እንኳን ይህንን በሰዓቱ መረዳት ባልችልም ጣፋጭ ፍሬን ሲመግበኝ "ለምን?!" ባልኩበት አንደበቴ "ተመስገን!" አልኩኝ። የጨለሙብኝ የመሰሉ ነገሮች በሙሉ በእርሱ በብርሃን ተተኩልኝ። ይህቺ ምድር ሊታይ በማይችል ድቅድቅ ጨለማ ተውጣ ነበር። ምንም ተስፋ የሌለበት በሚያስብል ሁኔታ "ዝቅ" አለች። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን አሰበ። ይህንም አንድያ ልጁን ጨለማ ለዋጣት ዓለም በመስጠት ሕዝቡን በብርሃን በማራመድ ገለጠ። “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” (ኢሳ 9፥2) ሕይወት ያለ ክርስቶስ ጨለማ ነው። አንዳች የብርሃን ፍንጣቂ የሌለውን ማንነት በማላበስ የኋሊት ቁልቁለት ያስኬዳል። ይህም ጥፋትን በማስከተል ዘላለማዊ ሞት ውስጥ ይጨምረናል። ስለዚህ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።” (ዮሐ 12፥46) ወዳለን ጌታ በእምነት እንቅረብ። እርሱም ያድነናል። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ እንዲሁ በጨለማ ስላልተውከኝ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ብርሃን የሆንከውን አንተን በመከተል በሕይወቴ ብርሃን ይፈነጥቅ ዘንድ በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ============================ 📖“ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም።” — ኢሳይያስ 8፥20 ይህ ዘመን በእጅጉ ያስፈራኛል። የዲጂታሉ አብዮት መፈንዳቱ ሰው ሁሉ በቀላሉ የፈለገውን መልዕክት እንዲያስተላልፍ አድርጎታል። "አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል" የሚለው ቢሂል ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ገጣሚ ነው። በየሚዲያው የሚታየው ነገር ልብን ያደማል። ወንጌል ተሸቃቅጦና ተደበላልቆ "አስተማሪዎች" ነን ብለው ራሳቸውን በሰየሙ ሰዎች ይለፈፋል። የንሰሃ ጥሪ ከማቅረብ ይልቅ መበሻሸቂያ መንገድ ሆኗል። በዕይታ መጠን በሚገኝ ገንዘብ ዕይታቸው ታውሮ ቃሉን ቆመሩበት። እየሱስን ደብቀው እነርሱ ደምቀው ለመታየት ታተሩ። አዎይ ዘመን ... የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ሁሉ እውነተኛ አገልጋይ አይደለም። "እየሱስ እየሱስ" እያለ የጮኸ ሁሉ የመንጋ ጠባቂ አለመሆኑን ልብ ይሏል። ይልቁን የበግ ለምድ የለበሰና ሌሎችን የሚያጠፋ ተኩላ ነው። “ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም።” (ኢሳ 8፥20) 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ወንጌልን ሳልሸቃቅጥ ካንተ የተቀበልኩትን እውነት ለሌሎች ማድረስ እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
ሕጉን አትም ============================ 📖“ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም።” — ኢሳይያስ 8፥16 የእግዚአብሔር ሕግ የባህሪው መገለጫ ነው። እንዲሁ በደፈናው አድርግና አታድርግ የሚል ጭፍን መርህ ሳይሆን ግልጥ መሪ ነው። “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” (መዝ 119፥105) የእግዚአብሔር ሕግ ጨለማን በብርሃን እየገለጠ ወደ ሕይወት ሁሉ ይመራል። ታዲያ ይህ ሕግ በእያንዳንዱ እርምጃችን ላይ ሊገለጥ ይገባል። ጧትም ሆነ ማታ ዘውትር በቃሉ ልንመራ ያስፈልጋል። መፅሐፉም ይህን ያፀናልናል። “ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳ 6፥7) የታተመ ነገር ሊጠፋ ካለመቻሉ በተጨማሪ የአታሚውን አካል በውስጡ ይይዛል። “ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም።” (ኢሳ 8፥16) በማለት የሚናገረው ቅዱስ ቃል፣ በእግዚአብሔር ሕግ መታተም የእርሱ አባትነትን፣ የእኛን ደግም ልጅነትን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህም በዚህ ምድር ላይ ብቻችንን እንዳልተተውን ጉልህ ማረጋገጫ ነው። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ መንገዴን ትመራኝ ዘንድ ሕግህን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ሕግህን ደግሞ ታትምብኝ ዘንድ እፀልያለሁ። አሜን።
አማኑኤል ============================ 📖“ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” — ኢሳይያስ 7፥14 እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ አምላክ ነው። እርሱ የተናገረውን ይረሳና ይተው ዘንድ ሰው አይደለም። የሰጠውን ተስፋ በጊዜውና በወቅቱ ይፈፅማል። የሰው ልጆችን ለመቤዠት ከዘመናት በፊት የሰጠውን ተስፋ በኢሳይያስ መፅሐፍ ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን። “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” (ኢሳ 7፥14) የጨለመው ዓለም በልጁ ይበራ ዘንድ ቃሉን ሰጠ። ይህም ፅኑ ቃል ኪዳን ፍፃሜውን አገኘ። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐ 1፥14) እግዚአብሔር ለህይወታችን የተናገረው ነገር ይኖራል። ታዲያ ከጊዜው መርዘም የተነሳ ምን አልባት ተስፋ ወደ መቁረጥ ስሜት እየገባን ሊሆን ይችላል። ይህ ቃል ዛሬ ለአንተ፣ ለአንቺ፣ ለእኔና ለእኛ ነው። እነሆ በፈቀደው ጊዜ በጆሯችን ሹክ ያለን ህልማችን ዕውን ይሆናል። አማኑኤል፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው። አሜን። ይህ ነው የሚያረጋጋን የከበረ እውነታ። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ላትፈፅምና ላታደርግ ቃል አትገባምና አንተን በትዕግስት መጠበቅ እንድችል አስተምረኝ። አሜን።
እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ ============================ 📖“የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።” — ኢሳይያስ 6፥8 በህይወቴ ትልቅ ስፍራ ካላቸው ሰዎች መካከል ፓ/ር መልዓክ አለማየሁ አንዱ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ሆኖ በሚልካቸው መልዕክቶች ተፅናንቻለሁ፤ በርትቻለሁም። ጥልቅ ወደ ሆነ የመፅሐፍ ቁዱስ ንባብና የመንፈስ ቅዱስን ረሃብ እንድመራ ረድተውኛል። በእግዚአብሔር ሀሳብ ከፓ/ር መልዓክ ጋር በአካል የተወሰኑ ጊዜያቶችን እንዳሳልፍ ሆነ። እነዛ ቀናቶች ለህይወቴ የሚጠቅሙኝን ነገሮችን በትንሹም ቢሆን የቀሰምኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። ከእርሱ ጋር በነበረኝ ቆይታ ካነሳዋቸው ጥያቄዎች መካከል "እንዴት አገልጋይ ልትሆን ቻልክ?" የሚለው አንዱ ነበር። እርሱም እግዚአብሔር አምላክ እንዴት እንደጠራውና እንደመራው አጫወተኝ። ዛሬ ላይ ፓ/ር መልዓክ ለብዙዎች በረከት ነው። ከእርሱ ህይወት አንድ ጉልህ የሆነን ነገር ተምሬያለሁ። አገልግሎት ጥሪ እንጂ ጥበብ አይደለም። እግዚአብሔር እንድናገለግለው ሲፈልግ ራሱን ታምኖ በፍቅር ይጠራናል። እንዴት እንደምናገለግል፣ ለምን እንደምናገለግል፣ የት እንደምናገለግል ሁሉንም ነገር ራሱ ይገልጥልናል። ይህን የከበረ ስጦታ እንዲሁ ሳንጠራ በራሳችን ጥበብ የምናደርገው የዓለም ተልዕኮ አይደለም። እግዚአብሔር ለአገልግሎት ሲጠራን በየትኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ ልንሆን እንችላለን። ለዚህ የተገደበ ስፍራ የለውም። ጳውሎስ ለአገልግሎት ሲጠራ የእግዚአብሔርን ህዝቦች ለማሳደድ እየገሰሰ በነበረበት ጊዜ በደማስቆ ነበር። ጴጥሮስም የመጋቢነት ሚና ሲሰጠው በባህር ላይ ሆኖ አሳ በሚያጠምድበት ጊዜ ነበር። ኢሳይያስ የተጠራበትንም የአጠራር ሁኔታ እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። “የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።” (ኢሳ 6፥8) ወገኖቼ፣ ዛሬም እግዚአብሔር በአንድም ሆነ በሌላ ለአገልግሎቱ ይጠራናል። “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት የከበረውን ጥሪ ያቀርባል። መቼና እንዴት ልንጠራ እንደምንችል አናውቅም። እርሱ ሲጠራን የሚሰማ፣ ሰምቶ ደግሞ ምላሽ የሚሰጥ ህይወት ሊኖረን ይገባል። “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤” (ማቴ 9፥37) ስለዚህ ለወንጌል ስራ ታጥቀን እንነሳ። “እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ” በማለትም የምስራቹን ለዓለም ሁሉ እናዳርስ። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ብቁ ያልሆኑትን ጠርተህ ማብቃትና የከበረን ስራ መስራት የምታውቅበት አንተ ብቻ ነህና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። አቤቱ፣ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ስትጣራ “እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ” ማለት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ============================ 📖“ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።” — ኢሳይያስ 6፥1 እግዚአብሔር ሕፀፅ አልባ አምላክ ነው። እንከንም ሆነ ስህተት በእርሱ ዘንድ ስፍራ የላቸውም። በብርሃናት የደመቀ ገናና ነው። የክብሩ ፀዳል አቻ አይገኝለትም። ሁሉን ማድረግ የሚችል ኤልሻዳይ ነውና የሚሳነው አንዳች ነገር የለም። የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ ከፍ ብሎ በዙፋኑ ላይ አለ። መላ ዩኒቨርስን በፍቅርና በፍትህ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ያስተዳድራል። “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።” (ኢሳ 6፥1) ከክብሩ የተነሳ መላዕክት እንኳን በፊቱ ሲቀርቡ ራሳቸውን በመሸሸግ እንደ ሆነ ቃሉ ይናገራል። “ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።” (ቁ 2) ባለ ቅኔው እንዲህ በማለት ይጠይቃል፦ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤” (መዝ 113፥5) አዎ፣ እርሱ የነገስታት ንጉስ፣ የጌቶች ጌታ፣ የኃያላን ሁሉ ኃያል ነው። እንዲህ ከፍ ያለው አምላክ ግን ዝቅ ያሉትን ሰብዓዊያን ሲተው አንመለከትም። ባለ መዝሙሩ ይቀጥላል፦ “በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤” (መዝ 113፥6-8) ገናናው አምላክ የጎደለን መሙላት፣ የጠፋን መመለስ፣ የታመመን መፈወስ፣ ያዘነን ማፅናናት፣ የተራበን ማጥገብ፣ የተጠማን ማርካት፣ የተቅበዘበዘን ማሳረፍ፣ የወደቀን ማንሳት ያውቅበታል። ታዲያ ይህን ስናስታውል እኛም እንዲህ በማለት እናውጃለን፦ “አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።” (መዝ 108፥5) 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ከፍ ባለ ዙፋንህ ላይ ያለህ ቸሩ ጌታ፣ "አባቴ" ብዬ እንድጠራህ ስለፈቀድክልኝ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ የክብርህ ፀዳል ደግሞ በህይወቴ ያበራ ዘንድ እናፍቃለሁ። አሜን።
ቅዳሜ ከሰዓት ሌላ ቀጠሮ እንዳይዙ! 261 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሕፃናትና በታዳጊዎች አንደበት በቃል ሊቀርቡ፤ * ሐምሌ 18፣ ከ 8፡30 ጀምሮ * በወመዘክር ቅጥር ግቢ * በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ አዳራሽ ተቀጥሯል። በዕለቱም በጥንታዊ የብራና ጥቅልል ላይ በጥንቃቄ ከመከ'ተብ ጀምሮ አሁን በዘመናችን ስማርት ስልኮች ላይ በቀላሉ እስከመገኘት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈበት የብዙ ዘመናት ታሪክ በረዳት ፕሮፌሰር መስፍን ማንደፍሮ አማካኝነት ትንታኔ ይሰጥበታል። መግቢያ በነጻ ነውና ኪስዎን አንድም ሳይዳብሱ ጊዜዎትን ብቻ አመቻችተው ከወዳጆችዎ ጋር በመምጣት ይህንን መልካም ዕድል ይጠቀሙ! ©️ፍኖተ ብራና አገልግሎት ————————— YouTube | Telegram | Facebook | Instagram
ወዮላቸው! ============================ 📖“ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” — ኢሳይያስ 5፥20 መልካም መሆን ለራስ ነው። መልካምነት የሚያስከፍለው ዋጋ ንፁህ ልብን ብቻ ነው። መልካም ለመሆን ሀብታም፣ የተማርን፣ ዝነኛ ወይም ባለስልጣን መሆን አይጠበቅብንም። አሁን ላይ ሰዎች መልካምነትን ከውስጣቸው አውጥተው የጣሉ በሚያስብል ሁኔታ የሚታየው ነገር እጅግ ያሳዝናል። እምነት በክህደት፣ ፍቅር በጥላቻ፣ ይቅርታ በቂም ሲለወጥ አይተናል። ያጎረሱ እጆች ሲነከሱ፣ ያሳረፉ ቤቶች ሲፈርሱ ታዝበናል። መፅሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ አይነት ሰዎችን "ወዮላችሁ!" ይላቸዋል። “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” (ኢሳ 5፥20) ዛሬ ከዚህ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። ዘውትር ለእውነት እንቁም። የመልካምነት መፍሰሻ ስፍራ እንሁን። ከጨለማ ስራ ጋር አንተባበር። ከብርሃን ጋር ብቻ እንጣበቅ። ህይወታችን ጣፍጭ የሆነን ፍሬ ያፍራ። ይህን ስናደርግ በእውነት እግዚአብሔር በእኛ እጅግ ደስ ይሰኛል። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ እኔ በዘመኔ ከመልካምነትህ ውጪ ከቶ አላየሁምና እኔም ለሌሎች መልካም መሆን እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
ስካርን ለመከተል ============================ 📖“ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው!” — ኢሳይያስ 5፥11 መጠጥ፣ አዕምሮን ማዛባት የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን በውጥጡ ይዟል። በአዘቦት ጊዜ እንኳን ልናደርጋቸው ልናስባቸው ራሱ የማንችላቸውን ነገሮች በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተን ለመፈፀም ማን ከልካይ ኖሮን። ግና ነገሩ ካለፈ በኃላ የጥፋተኝነት ስሜት ውስጣችንን ያስጨንቀዋል። እንደ ክርስቲያን ከዚህ ልንርቅ ያስፈልጋል። መጠጥ ደስታን ምን አልባት ለጊዜው ሊሰጠን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ዘላቂነት ያለውን እርካታ ከቶ ሊሰጠን አይችልም። እዚህ ጋር ጤናን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ እንደ 'ሚችል ልታሰብበትም ይገባል። “ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን?” (ምሳ 23፥29-30) በማለት በግልፅ መፅሐፍ ቅዱስ የመጠጥን ዳፋ ያስቀምጣል። “ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው!” (ኢሳ 5፥11) በሚል ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያም ጭምር ቀርቦ እንመለከታለን። ስለዚህ ራሳችንን መግዛት እንማር። ለስሜቶቻችን ከቶ ተገዢዎች አንሁን። ከስካር ጋር አብሮ ሆኖ መለወጥ የለምና ምን አልባት እንደዚህ አይነት ነገር በህይወታችን የሚታይ ከሆነ አሁሁ ፀጋውን ታምነን ለማቆም ውሳኔን እናድርግ። እርሱም ይረዳናል። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ውስጤ የአንተ ማደሪያ ቅዱስ ስፍራ ነውና በስካር ተጠምጄ እንዳላረክሰው በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።
ለወይኔ ያላደረግሁለት ምን አለ? ============================ 📖“ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?” — ኢሳይያስ 5፥4 ጎበዝ ገበሬ የተሻለ ምርትን ለማግኘት ጠንክሮ ይሰራል። ማልዶ በመነሳት ዘር የሚዘራበትን መሬት ያርሳል፤ ያለሰልስማል። ለዘሩ ዕድገት አላስፈላጊ ነገሮች ናቸው ብሎ ያሰባቸውን ሁሉ ከስፍራው ላይ ያነሳቸዋል። ከዚያም በኃላ ምርጥ የተባለውን ዘር በተዘጋጀው መሬት ላይ ይዘራል። ከዚያም በኃላ ጎተራው በምርት ይሞላ ዘንድ ተስፋ በማድረግ ይጠባበቃል። በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ አምስት አንድ ዝነኛ የሆነ ታሪክ ቀርቦ እንመለከታለን። በዚህ ክፍል ላይ “አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው።” (ኢሳ 5፥1) በማለት የተጠቀሰው ስለ ወይን ቦታ የተነገረን ቅኔ በውስጡ ይዟል። ከመጀመሪያው ቁጥር ላይ መረዳት እንደ 'ምንችለው የወይኑ ቦታ የነበረበት ስፍራ ፍሬያማ ኮረብታ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የወይኑ ባለቤት አስፈላጊ የተባሉ ነገሮች ሁሉ ለወይኑ ተክል አደረገለት። “በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ...” (ቁ 2) ይህም ሆኖ ግን መጨረሻው ያማረና የተጠበቀው አልነበረም። “...ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ።” (ቁ 2) ይህ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው። ወርቅ ተጠብቆ መዳብ ሲገኝ ልብን ያደማል። ጠንክረው የሰሩ እጆች ያለ ምንም ውጤት ሲቀሩ ሁሉም ነገር ጭልምልም ይላል። አትክልተኛው እንዲህ አለ፦ “ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?” (ቁ 4) ይህ ቅኔ የእስራኤልን ቤት የሚያሳይ ሆኖ ዝቅ ብለን ስናነብ እናገኘዋለን። “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፥ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ።” (ቁ 7) የታሪኩ ግልባጭ ይሁዳ የሚል ነበር። እነዚህ ህዝቦች ሁሉ በሁሉ ከሆነው አምላክ ሁሉም ነገር ተደርጎላቸው ምንም ማፍራት የተሳናቸው አሳዛኝ ፍጥረቶች ሆኑ። ዛሬስ እኛ በምን አይነት ቁመና ላይ እንገኝ ይሆን? እግዚአብሔር ያላደረገልን፣ ያልሰጠን ነገር ከቶ ምን አለ? "ይህ ቀረብኝ?" ብለን እንኳን እርሱን ልናማ ምን አፍ አለን። ወገኖቼ፣ የተደረገልንን ነገር እናስብ። በመስቀል ላይ የተሰራልንን ታላቅ ስራ እንመልከት። ለመረዳት እንኳን በሚከብድ ሁኔታ የዳንበትን ልክ እናስታውስ። እነዚህ ነገሮች አቅም ሆነውን መልካም የሆነን ፍሬ እናፈራ ዘንድ ናፍቆቴ ነው። 🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ልጅህን በመስጠት ለእኔ ያለህን ድንቅ ፍቅር ስላሳየኝ ከልቤ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ይህ ሁሉ ተደርጎልኝ ደግሞ ሆምጣጣ ፍሬ እንዳላፈራ በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።