ማዕደ ፡ ጥበብ | Banquet of Wisdom
Статистика“ለንባብ ክብርን ስጥ። ራስኽን ለንባብ አስገድድ። ከቻልኽ ፥ ከምትጸልየው አስበልጠኽ አንብብ። የጥሩ ጸሎት ምንጩ ንባብ ነውና" (አቡነ ቄርሎስ ፮ኛ)
- Последний пост
- 14 авг.
- Последнее чтение
- 13 авг.
- Постов за неделю
- 6
- Всего постов
- 23
- Тип
- открытый
- Язык
- ti
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- 124
- 1/48двое суток
- 142
- 1/72трое суток
- 153
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
ተአምር ፭ ❝ ስምስ ይሉኻል ይኼ ነው! ❞ ልመናዋ ክብሯ የልጇ የወዳጇም ቸርነት በኹላችን ላይ ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይኽ ነው፦ በአንድ ወቅት ፊደል ያልቈጠረ መነኲሴ እንደነበረ ተነገረ። ታዲያ ከአባቶች አንዱ ወደርሱ ጠጋ ብለው “ሌሎችን ጸሎታት መጸለይ ስለማትችል ፥ ይኼን ጸሎት ጸልይ” ብለው “በሠላመ ገብርኤልን” ያሰተምሯቸዋል። መነኲሴም ፥ “እርሱንም ቢኾን መጸለይ አልችልም” ሲል ይመልሳል። “እሺ! ችግር የለውም! ‘ቅድስት ማርያም ሆይ!’ እያልኽ ብቻ ጸልይ” ሲሉ አዛውንቱ ያሳስቧቸዋል። መነኲሴውም መልሶ ፦ “እርሱንስ ማድረግ እችላለኹ! እስኪ ልሞክር” ብሎ ጸሎቱን ይጀምራል። መነኲሴው “ቅድስት ማርያም ሆይ!” የሚለውን ቃል ብቻ እየደጋገመ እየጸለየ ይመሻል ይነጋል። በዚኽ አኳዃን ቀናት ተቈጠሩ። ታዲያ አንድ ቀን ሰይጣን መጥቶ ምን ቢለው ጥሩ ነው? “ወደ አንተ መቅረብ አልቻልኹምና ይኽን ስም መጥራት አቁም!” ብሎት ዕ‘ርፍ! ታዲያ መነኲሴው ሊሰማ ነው? ይባስ ብሎ ጸሎቱን ብርትቶ ቀጠለበት እንጂ! “ዙሮ ዙሮ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት ከመሬት” ነውና ቀኑ ደርሶ መነኲሴው ያርፋል። ከጊዜያት በኋላ መቃብሩ ላይ ታዲያ ምን ተአምር ቢፈጠር ጥሩ ነው? መቃብሩ ላይ አበባ አብቦ ቁጭ! መነኰሳቱ መቃብሩን ቢከፍቱት የአበባው ሥር ያልፈረሰው ያልበሰበሰው የመነኲሴው ልብ ላይ ተተክሎ ኑሯል ለካ! ምን ይኼ ብቻ! “ቅድስት ማርያም ሆይ!” የሚለው ስም በወርቅ ቀለም በመነኲሴው ልብ ላይ ተጽፎ ይታይ ነበር። መነኲሴው በታሪክ መዝገብ ላይ “ቅድስት ማርያም ሆይ!” እየተባለ ሲታወስ ይኖራል። ❝ ድንግል ማርያምን የሚያመሰግናት እርሱ የከበረ ነው! እርሷን ባመሰገናት ቍጥርም ከፍ ከፍ ይላል!❞ ትርጒም፦ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን።
ተአምር ፬ ልመናዋ ክብሯ በእኛ ለዘላለም በእውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ - ሥጋ በድንጋሌ - ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን የሶርያ ዕፃ በምትኾን በጸደንያ ከተማ ያደረገችውን ተአምር የወንጌል ልጆች ሆይ ስሙ፡፡ ጊዜው በሶርያ ሀገር የእርስበርስ ጦርነት የነገሰበት ጊዜ ነበር፡፡ ይኽ የምነግራችሁም ተአምር የተከሰተው በከተማዋ በሚገኝ በአንድ ገዳም ላይ ከእርስበርስ ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሮኬት ጥቃት በደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ በገደሙ ውስጥ የነበሩ መነኮሳት የሮኬቱ ፍንዳታ ያስከተለውን ከባድ ንውጽውጽታ በሰሙ ጊዜ ጥቃቱ ለእነርሱም ኾነ ለገዳሙ እንደሚተርፍ እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እንዳሰቡት ሳይከሰት በመቅረቱ ሮኬቱ የገጠመውን ቢያውቁ ወደዱ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሀገሪቱ ሠራዊት ከጦር ጄኔራሎች አንዱ በሀገሪቱ ይከበር የነበረውን አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለገዳሙ መነኮሳት ሰላምታ ሊያቀርብ ወድዶ ወደዚህ ገዳም ጎራ አለ፡፡ ... በንግግራቸው መካከል ጄኔራሉ ሰሞኑን በአካባቢያቸው ያልተለመደ ክስተት ተከስቶ እንደኾነ ይጠይቃል፡፡ የገዳሙ መነኮሳትም የሮኬቱን ፍንዳታ እንደሰሙ በእነርሱ ላይ ግን አንዳች እንዳልደረሰባቸው ይነግሩታል፡፡ ጄኔራሉም ተመሳሳይ ነገር ከእነርሱ በመስማቱ እየተደነቀ ሮኬቱ ወደ ገዳሙ ሲወረወር እንደተመለከተ ነገር ግን በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች ጋር አንድ ያልተለመደ ክስተት እንዳስተዋሉ ይነግራቸዋል፡፡ ይኸውም፦ ሮኬቱ ገዳሙ ላይ ጥቃት ሊያደርስ በነበረበት ወቅት በድንገት በሰማያዊ ቀሚስ የተዋበች አንዲት ሴት ከሰማይ ወርዳ ሮኬቱን በእጇ ይዛ ከገዳሙ አርቃ ትወረውረዋለች፡፡ ይኽንን ይመለከቱ የነበሩ ሰዎችም ፈጽመው አደነቁ፡፡ ጄኔራሉ ሰማያዊ ቀሚስ የለበሰች ፣ ድንቅ የኾነ ግርማ ሞገስን የተጎናጸፈች ይኽቺ ሴት ማን እንደኾነች ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም ከወላዲተ -አምላክ ከአምላክ እናት ከቅድስት ድንግል ማርያም በቀር ሌላ ልትኾን እንደማትችል አስተዋሉ፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇ የወዳጇም ቸርነት ከኹላችን ጋር ይኹን! ለዘላለሙ አሜን! Source: Orthodox christian.com, Miracle of Holy Theotokos In the Christian Town Of Saidnaya, ትርጉም፦ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን
ተአምር ፫ « እኔ እናት እኾንኻለሁ » ውልደቱ በአውስትራሊያ ሀገር ነበር። የምንኲስና ኑሮው ደግሞ የቅዱስ እንጦንስ ገዳምን ጨምሮ በሌሎች ገደማት። “አባ አልዓዛር” ይባላል። በ‘እግዚአብሔር የለም’ እምነት ውስጥ ለአርባ ዓመታት የኖረ አባት ነበር። የእናቱን ሞት ተከትሎ ለዓመት ያኽል ውስጡ ሠላምን አጥቶ አለመረጋጋትን ተመልቶ ከባድ ጊዜያትን አሳልፏል። ወደ ምንኲስና ሕይወት ከመግባቱ በፊት በአንድ ወቅት ‘ቅዱስ ሳቫ’ ተብሎ በሚታወቅ አውስትራልያ ሀገር ውስጥ በሚገኝ አንድ የሰርቪያ ኦርቶዶክስ ገዳም ውስጥ የገጠመውን እንዲኽ ይተርክልናል፦ ‘ወደ ቤተ - ክርስቲያኑ ስገባ እኔ የመጨረሻው ነበርኹ። ቀድመው የገቡ ኹሉ ፊት ለፊታችን በምትገኝ ለየት ባለ ትልቅ ፍሬም የተቀመጠች ግድግዳው ላይ ተስቅላ ፊት ለፊቷም ላይ መቅረዝ ይበራባት በነበረች በአንዲት የእመቤታችን ስዕለ አድኅኖ ፊት እየተሳለሙ ሦስቴ እየሰገዱ ሲያልፉ እመለከታለኹ። የሚያደርጉትን ተግባር ምን እያሰቡ ይሰግዱም እንደነበር አልተረዳኹትም ነበርና ተግባራቸውን በአትኩሮት እመለከት ጀመር። ኹሉም ተሳልመው ከጨረሱ በኋላ ተራዬ ደረሰና ወደ ስዕሏ ተጠጋኹ። “እኔ በዚኽ ቦታ ጎብኚ ነኝና ሌሎች እንዳደረጉት ማድረግ ይገባኛል” ስል አሰብኹ። ምንም ለኔ ዐዲስና እንግዳ ነገር ቢኾንብኝም በጉልበቴ ተንበረከክኹ። ወደ ቤተ - ክርስቲያኑ ስገባ ስዕሏ የ “ወላዲተ - አምላክ” ወይም “የእመ - አምላክ” ስዕል እንደኾነች ሰዎች ነግረውኝ ነበር። በጉልበቴ እንደተንበረከክኹ “እመ - አምላክ - የአምላክ እናት” ስለሚለው ስም ማሰብ ጀመርኹ። “እኔ በዚኽ ሰዓት እናት የለኝም። እግዚአብሔር ደግሞ አ‘ለው። እግዚአብሔር ስለምን እናት ኖረው? እኔስ ስለምን አልኖረኝም?” የሚል ሓሳብ ውስጥ ገባኹ። ያለ እናቴ ምን ያኽል ብቸኝነት እንደወረሰኝ እያሰብኹ ዕንባዬ በጉንጮቼ ላይ ይፈስስ ጀመር። በዝግታ ተነሥኹና ኹለተኛውን ስግደቴን ለመስገድ ተዘጋጀኹ። እንደ ቀድሞው ተንበረከክኹና ግንባሬን መሬት አስነክቼ ተመሳሳይ ቃላትን ደጋግሜ እናገር ጀመር። ከዚያም ፥ ለስለስ ያለ ፣ ጥርት ያለ እና እጅግ መሳጭ ድምጽ “እኔ እናት እኾንኻለኹ” ብሎ ሲናገኝ ተሰማኝ። ምናልባት ከሰርቪያውያን ሴቶች አንዷ ከኋላዬ ደርሳ ልታጽናናኝ የተናገረችው መስሎኝ ቀኝና ግራዬን ዘወር ዘወር ብዬ ቃኘኹ። ነገር ግን ማንም አልነበረም። ሦስተኛውን ስግደቴን ለመስገድ ቀጥ ብዬ ቆምኹ። በዚኽ ጊዜ ደጋግሜ ስጠራቸው የነበሩትን ቃላት ሙቀት ልምላሜ በተዋሕደው ጸሎት እጠራቸው ጀመር። እኔ ግን አልታወቀኝም ነበር። ታዲያ በዚኽም ጊዜ ቀድሞ የሰማኹትን ድምጽ “እኔ እናት እኾንኻለኹ” ሲል ደግሜ ሰማኹት። ማን እንደሚናገረኝ ለማወቅ ጓጓቼ ጣሪያ ጣሪያውን አስስ ጀመር። ምንም የለም። ነገር ግን በድንገት ስዕሏ ወደ እኔ አዘነበለች። ስዕለ አድኅኖው በቦታው እንዳለ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከስዕሏ ወጥታ በፊቴ ቆመች። ፍቅርን በተመሉ ዓይኖቿም ፈገግ ብላ ትመለከተኝ ጀመር። ከዚያም ቃሏን ደገመችው ፦ 'እኔ እናት እኾንኻለኹ!' ውስጤ ታላቅ የኾነን መጽናናትን አገኘ። ሕመሜና ሐዘኔ ጓዘቸውን ጠቅልለው ውልቅ አሉ። ውስጤ ቀምሼው በማላውቅ አንዳች ደስታ ተጥለቀለቀ። ሌላ እናት እንዳገኹ አወቅኹ። እመቤቴ አኹንም ዘንበል ብላ እየተመለከተችኝ ነው።እኔም ልጇን እጅግ በጥንቃቄ እንደምትንከባከብ እናት ኾና በብሩህ ገጽ እያየኋት ነው። ጭንቀቴ ኹሉ ጥሎኝ ጠፋ። ከእርሷ የሚወጣው የብርሃኑን ነጸብራቅ መቋቋም ስላቃተኝ ፥ ራሴን ዘንበል አደረግኹ። እርሷም ወደ ስዕሉ ተመልሳ ገባች። ቆም ብዬ አካባቢውን ቃኘኹ። ቤተ - ክርስቲያኑ እንደ ቀድሞው ጸጥታ እንደሰፈነበት ነበር። ማንም ኾነ ማን ምንም ምን አላየም ነበር። (አባ አልዓዛር ከዚኽ በኋላ እመቤታችን ባደረግችላቸው ነገር ልባቸው ተነክቶ በብሐትውና ኑሮ በሕይወት እየኖሩ የሚገኙ አባት ናቸው።) ትርጒም፦ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን።
ተአምር ፪ ~ ምልጃ ይሉኻል እንደዚኽ ነው! ~ ልመናዋ ክብሯ የልጇ የወዳጇም ቸርነት በኹላችን ላይ ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይኽ ነው፦ የሳሮቩ አባ ሴራፊም (St.Seraphim of sarov) አንድ ቀን በጠዋት "ቅዱስ አባት ሆይ እርዳኝ! ቅዱስ አባት ሆይ እርዳኝ!" እያለ ወደርሱ የሚጮኽ ሰው ድምጽ ይሰማል። ይኽም ቅዱስ አባት ከሚኖርባት አነስተኛ በኣት ወጥቶ ወደ ሚጮኸው ሰው ድምጽ ይመጣል። ሰውዬውም በዕንባ ታጅቦ መለመኑን ተያያዘው፦ "ቅዱስ አባት ሆይ! ልጄ እየሞተብኝ ነው። ዶ/ሩ ምንም ማድረግ አልቻለም። ቅዱሱ ሆይ! እባክኽ ስለልጄ ጸልይልኝ ገና ስምንት ዓመቱ ነውና።" አባ ሴራፊም ውስጡ ይረበሻል። በእርሱ ባደረበት መንፈስቅዱስ እግዚአብሔር የልጁን ነፍስ ይወስድ ዘንድ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉን ዐሳቡንም እንደማይቀር አውቋልና። ከዛም መለሰ ፦ "ልጄ ሆይ! ምንም ማድረግ አልችልም! እግዚአብሔር አምላክ የልጁን ነፍስ ይወስድ ዘንድ ቁርጥ ውሳኔን አድርጓልና" አለው። ሰውዬው ግን አኹንም አኹንም በዕንባ ይለምን ነበር። ቅዱስ ሴራፊምም መለሰ ፦ "እሺ ትንሽ ጠብቀኝ መጣኹ" ብሎት ወደ በኣቱ ይመለሳል። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ተመልሶ መጥቶ "ልጄ ሆይ! ለቅሶኽን ተወው። ልጅኽም በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም" ይለዋል። ሰውዬውም ለቅሶውን ትቶ በአግራሞት ይጠይቃል፦ "ቅዱሱ ሆይ! እንዴት የእግዚአብሔር ቁርጥ ውሳኔ ልታስቀይር ቻልኽ?" ይለዋል። ቅዱስ ሴራፊምም መለሰ ፥ እንዲኽም አለ፦ "ልጄ ሆይ! እኔ ውሳኔውን አላስቀየርኹም። እመ - አምላክ ውሳኔውን አስቀየረችው እንጂ!" ሲል መለሰለት። አባ ሕርያቆስ "ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር - ስምሽ በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠነ ነው!" ያለው ይኽንንም አይደል? ይቆየን! (ለጊዜው ምንጩን ካረሳኹት ከአንድ የውጭ ምንጭ የተተረጎመ) ትርጒም፦ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን
ተአምር ፩ (እንደተለመደው በፍልሠታ ጾም አንዳንድ የእመቤታችንን ተአምራት የማስታውሳችሁ ይኾናል) - እንጀምር፦ «ከእኔና ከእርሷ ማን ያምራል? » ተአምረ ማርያም ላይ ከሰፈሩት ተአምራት መኻል የሚደንቀኝ አንዱ ተአምር እነሆ፦ አንዱ በአንዷ ፍቅር እ’ብድ ብሎ የሚያደርገው ቢያጣ አንድ አባት ጋር ይኼዳል፦ አባ! አቤት! አንዲት ሴት ወድጄ ነበር። እሺ። እንዲያው እንዴት አድርጌ እጄ ውስጥ እንደማስገባት መላው ቸገረኝ። ይኼ ‘ኮ ቀላል ነው። ማለት? ኼደኽ የእመቤታችን ስዕለ አድኅኖ ፊት በየቀኑ 150 እየሰገድህ ጠይቃት። ትሰጥኻለች! የምሮትን ነው አባ? አዎ! ልጁ በሞራል ስግደቱን ጀመረ። በየቀኑ 150 እየሰገደ እመቤታችንን ልጅቷን ትሰጠው ዘንድ መለመን ጀመረ። በየቀኑ 150 እየሰገደ ዓመት ሞላው። ታዲያ ከዚኽ በኋላ አንድ ቀን የተለመደውን ስግደቱን ሊሰግድ ወደ ስዕለ አድኅኖዋ ያቀናል። የወደዳትን ልጅ ውበት እያደነቀ መስገድ ጀመረ። አቤት ዐይኗ! አቤት ጥርሷ!... ይሰግዳል። አቤት ጸጒሯ! ይሰግዳል። አቤት ቁመና!... ይሰግዳል። ለልጅቷ መልክዕ መድረስ ነው የቀረው። ስግደቱ ለእመቤታችን ሳይኾን ለልጅቱ ነበር የሚመስለው። ታዲያ በዚኽ መኻል እመቤታችን ትገልጸታለች። ታላቅ ድንጋጤን ደነገጠ! ከዚያም እመቤታችን ከዚኽ በፊት ምናልባት ከአንድም ቅዱስ ተሰምቶ የማይታወቅ አንድ ታሪካዊ ጥያቄን ጠየቀችው፦ ‘ከእኔና ከእርሷ ማን ያምራል?’ የሚል ጥያቄ! ወንድማለም የልጅቱን ውበት ወዲያው ረሳው! በእመቤታችን ውበት ፊት ምንም ኾናበታለችና! ሻማ በፀሓይ ፊት ምንድን ነው?! ምንም! ልጁም የገጠመው ይኼው ነው። እርሱም መለሰ፦ ‘አንቺ ታምሪያለሽ!’ እመቤታችንም መልሳ ‘ስለዚኽ እኔን ለምን አታገለግለኝም?’ እርሱም ወዲያው ተስማማ። ከዚኽ በኋላ የምናገረው ቃል ለማመን ሊከብድኽ ይችላል፦ መ ነ ኮ ሰ! ማን? እንደዚያ በሴት ልጅ ፍቅር አብዶ የነበረው ወጣት በእመቤታችን ፍቅር ተነክቶ ወዲያው ለመመንኮስ ወሰነ። መነኮሰም! ግሩም ድንቅ! ✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን። (መልዕክቱ ጠቅሞኛል ብለው ካመኑበት ለሌሎች በማጋራት አገልግሎቱን ይደግፉ) @Tibebsenayit
« Trade your time for eternity! » ክረምት እንደመኾኑ ሕፃናቱ የክረምት ጨዋታዎችን ተያይዘውታል። ብይ ፣ ቆርኪ ፣…። ታዲያ እኔ በእነርሱ ዕድሜ ስለጨዋታዎቹ ይሰማኝ የነበረውን ስሜት አስታወሰኝ። በጊዜው እንደማንኛውም ሕፃን ዓለሜ ነበሩ። ከጓደኛዬ ጋር ከሰዓት ላለብኝ ግጥሚያ ጠዋት ወጥቼ እለማመዳለኹ። ታዲያ ግጥሚያው ደርሶ ‘ብይ’ መበላት ሞቴ ነበር። በጣም ነበር ምበሽቀው። ነገር ዓለሙ ኹሉ የጨለመብኝ ነው የሚመስለኝ። ሕይወት ከዚያ በኋላ ትርጒም የሌለው ኹሉ ሊመስለኝ ይዳዳኛል። በዚያኑ ቀን ሌሊት ሳልም የማድረው ‘በቀጣዩ ቀን ተነስቼ በምን ዐይነት ብልሃት ተጋጣሚዬን እንደምረታ ፣ ብዬቹ ተደርድረው ቀስቷን ስመታ ፣ ብዙ ብዬች ሰብስቤ በሰፈሩ የብይ ከበርቴ ስኾን ፣…’ ዐይነት ሕልም ነው። ለቆርኪውም ቢኾን እንዲኹ። ከተደረደሩት ቆርኪዎች ቀስት ቀስቷን ብዬ ፥ የሰፈሩ ሕዝብ ሲያጨበጭብልኝ ፣ ያገር ቆርኪ ሰብስቤ ፥ ‘ቆርኪ በኬሻ ሙሉ ያለው ከበርቴ’ ኾኜ ፣ ቆርኪዎቼን ቀጥቅጬ ዋንጫ ስሠራ ፣… ምናምን ነበር የማልመው። የምር እንደዚያ ነበር የሚሰማኝ በነገራችን ላይ። የኔ ብቻ ሳይኾን በዚያ ዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረ ኹሉ ስሜቱን ይጋራዋል። በጊዜው አንድ ሰው መጥቶ «ሕልምኽ ምንድር ነው? » ብሎ ቢጠይቀኝ ‘በሰፈሩ የብይ እና የቆርኪ ከበርቴ መኾን’ ብዬ ልመልስ ኹሉ እችላለሁ። በዚያ ወቅት አንድ ሰው ሊያደርግልኝ የሚችለው ‘ትልቅ ውለታ’ ብዙ ብዮች እና ቆርኪዎች ገዝቶ ቢሰጠኝ ነበር። ታዲያ ያ ኹሉ ጊዜ አልፎ አኹን ላይ አለኹ። አኹን ላይ ኾኜ ያኔ የነበረው እኔ ‘ብይና ቆርኪ ዓለሙ እንደነበር’ ሳስበው ከት ብዬ እስቅበታለኹ። ጉድጓድ ውስጥ ያለች እንቊራሪት ‘አንቺ እንቊራሪት ሆይ! ሰማይ ምን ያህላል?’ ብላ ተጠየቀች አሉ። ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው? ‘የጉድጓዱን አፍ ያህላል’ ብላ መለሰች አሉ። ሰማይን ያየችው በጉድጓዱ አፍ ያህል ነበር። እኔም በዚያ ዕድሜዬ ዓለምን የማየው በብይና በቆርኪ ስኬት ዐይን ነበር። አኹን ላይ ላለው እኔ ብይና ቆርኪ ምኑ ነው? ምኑም!! ይኽን ኹሉ ሳወጣ ሳወርድ ‘ግን እኮን ለቅዱሳኑ ዓለም እንደዚኽ ናት’ የሚል ሐሳብ ድንገት ብልጭ አለብኝ። ለቅዱሳኑ ብቻ ሳይኾን ልቡን በሰማይ ላይ ላኖረ በዓለም ያሉት ውጣ ውረዶችን ከት ብሎ ነው የሚስቅባቸው። የአኹኑ እኔ በብይና በቆርኪ የተነሣ ከጓደኞቹ ጋር ሊጋደል የሚዳዳውን ያን ሕፃኑን እኔን ከት ብሎ እንደሚስቅበት ፥ በዓለም ጣጣዎች የተነሣ የሚጋደሉ ሰዎችም ልባቸውን በሰማይ ላይ ያኖሩ ሰዎች እንዲኽ ነው የሚስቁባቸው። ብይና ቆርኪ ከንቱ መኾኑ የገባኽ ካደግህ በኋላ እንደኾነ ፣ ሰው በዚኽ ምድር ላሉ ነገሮች ሰው መጨነቅ የሚያቆመው በመንፈሳዊነት ሲጎለምስ ነው። በጊዜው ብይና ቆርኪ አዝናንተውኝ ነበር። ሕይወቴ ላይ የሚጨምሩበት ግን አንዳች ነገር አልነበረም! በጊዜው ግን የሚጨምሩልን ነገር ያለን ይመስለን ነበር! አባ ጳውሊ ይኼ ስለገባው ነበር ከወንድሙ ጋር በንብረት ይገባኛል ጥያቄ የተካሰሰውን ክስ ጥሎ በረሓ የገባው። "Trade your time for eternity! - በሚያልፍ ጊዜያችሁ የማያልፍ ዘላለማዊ ሕይወትን ሸምቱበት!" እመቤታችን በዕረፍቷ ፍጻሜ ላይ የተናገረችው ኃይለ ቃል ነበር። ይቆየን! ✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን።
"እግዚአብሔር ምንም ነገር ሲያደርግ በምክንያት ነው" የምንለው ለዚህ ነው!
እነሆ የቅዱስ ገብርኤል ተአምር፦ ጸሎትና በረከቱ በእኛ በሕዝበ ክርስቲያን ላይ ይኹንና መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ያደረገው ተአምር ይኽ ነው፦ ባለትዳር ናቸው። መስሊምም ናቸው። ለዓመታት ልጅ መውለድ ተስኗቸው ብዙ ቦታ ደከሙ። አልቻሉም። ችግራቸውን የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች "ለቅዱስ ገብርኤል እኮን ብትሳሉ ልጅ ይሰጣችኋል" ቢሏቸው ፥ አምነው ይሳላሉ፦ "ቅዱስ ገብርኤል ሆይ! ልጅ ብትሰጠን ክርስቲያን እንኾናለን" ብለው! ከዘጠኝ ወራት በኋላ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ! ይኼኔ ዲያብሎስ መጥቶ ሹክ አላቸው። እነርሱም ክርስቲያን የመኾን ሓሳባቸውን ተዉ። ስእለታቸውን አጠፉ። "ምነው?" ቢባሉ ፥ "ያው ዘመድ አዝማዳችን ጠቅላላ ሙስሊም ነው። ሃይማኖት ብንቀይር መከራው ብዙ ነው። ማግለልና መድሎው ጭንቅ ነው" ብለው። ቅዱስ ገብርኤል ይኼን ሲሰማ "አቤት! ምን አላችኹ??" ያለ ኹሉ ይመስለኛል። የተወሰኑ ጊዜያት ነጎዱ። ሠላም ነበር። ሠላሙ ግን አልቀጠለም። ቅዱስ ገብርኤል "ልጄን መልሱልኝ" ሲል ተጣራ። ልጁም ጥሪውን ሰማ። በተኛበት ጸጥ አለ። ነፍሱን ለቅዱስ ገብርኤል አሳልፎ ሰጠ። ልጁ ሲወለድ የነበረው ፍሥሐ ወሐሴት ከልጁ ነፍስ ጋር ወደ መጣበት ተመለሰ። ዋይታና ልቅሶ ቤቱን መላው። አፋፍሰው ቢወስዱት "የሞተ ልጅ ነፍስ ዝሩበት ነው ወይ የምትሉን?" አሏቸው። ይኼኔ እናቱ ወደ ልቧ ተመለሰች። ደግነቱ አልዘገየችም። በቅዱስ ገብርኤል ዘንድ መዘግየት አልነበረም። ሐዘኗ በፊቱ ደርሷ አንኳኳ። ፈጥና ኺዳ ልጇን ወስዳ መቅደሱ በር ላይ ጣለችው። ልጁም 'አለሁ!' አለ። ለመኖሩ ምልክትም ሽንቱን ሸና። በጨለማ የሚኖሩ ባለትዳሮች ታላቅ ብርሃን በራላቸው። ታላቅ ደስታ ኾነ። አኹን ግን ስእለታቸውን ሊያጥፉ አልደፈሩም። ክርስትናን ተቀበሉ! እግዚአብሔር ይመስገን! ~ መምህር ተስፋዬ ሞሲሳ በአንድ ስብከታቸው ሲመሰክሩ እንደሰማኹት (ነገር ግን በጸሓፊው አገላለጽ የቀረበ) እንኳን አደረሳችኹ!
በቅዱስ ሚካኤል ስም ከተዘመሩ መዝሙሮች በጣም የወደድሁት አንዱ መዝሙር ነው። ተጋበዙልኝ እስኪ፦ እንኳን አደረሳችኹ! https://youtu.be/WecrDoAaop4?si=vbOTvYujUswccyGb
እንኳን ለቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ የሰማዕትነት በዓል በሠላም አደረሳችኹ! በስማቸው የተዘመሩ ጣፋጭ መዝሙራት እነሆ! https://youtu.be/oGFsEOaHRMk?si=-7OfjimCoVqKn5mL
« ከክርስቲያን ቤት ውስጥ የዓይጥ ወጥወድ ባገኝ ውርደት ነው! » እያሉ ነው አባ ገብረ ኪዳን ... በዚህ ዓይነት አብዛኞቻችን ሌባ ነን ማለት ነው? ምን ታስባላችሁ?🤔 እስኪ ስሙት ምን ሰርቀን እንደኾነ ከጠፋብን ምናልባት የሰረቅነው 'ዐሥራት' ይኾን?🤔 @Tibebsenayit
ያዳምጡት! ያተርፉበታል! https://vm.tiktok.com/ZSCBLayV1/ « በዓላትን እንደ አይሁድ በመጠንቀቅ አታክብሩ! » >> ግመልን የምትውጡ ትንኝን የምታጠሩ!
« በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ » (፪ኛ ነገ. ፬ ፥ ፪) ድርሳነ ሚካኤል ላይ በተጻፈ ፣ በአንድ ወቅትም ሲነበብ ሰምቼው ውስጤ በቀረ ታሪክ ልጀምር ወደድኹ። ነገርዬው እንዲኽ ነው፦ አንድ ችግረኛ ሰው ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ - ክርስቲያን ማልዶ እየኼደ በስዕሉ ፊት በመቆም ቅዱስ ሚካኤልን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ይሰጠው ዘንድ ከልቡ ይለምናል። ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጥቶ እንዲኽ ይለዋል፦ (በድርሳኑ ላይ "ቃል በቃል" የተጻፈውን እንዳለ አቅርቤዋለኹ) “አንተ ሰነፍ! ሰውነትኽ መሥራት ከሚችለው ሥራ አንዳችም አልሠራኽም! ነገር ግን በሥራ ፈትነት ተቀምጠኽ ምን ትዘበዝበኛለኽ? ለመሥራትም ክንድኽን አላነሣኽም። እርሻ አርሰኽ ምድር በምትሰጠው ጥቅም አልተጠቀምክም! አታክልት አልተከልክም። ዘር አልዘራኽም። ይኽን ማድረግ እንኳን ባይቻልኽ ንግድ አትነግድምን? የሥራ ፍሬኽን አበዛልኽና እባርክልኽ ዘንድ። እንግዲኽ ፣ ረዳት እኾንኽ ዘንድ በማናቸውም የሥራ መስክ ያልተሠማራኽና ዕድልኽንም ያልሞከርኽ ስለኾነ ፣ ከሰው ኹሉ በታች ኾነኽ ተዋረድኽ። በስንፍናኽና በታካችነትኽ ከልጆችኽና ከሚስትኽም ጋር በችግር አለንጋ ስትገረፉ ትገኛላችኹ። አኹንም ወደ ቤተ-ክርስቲያን ኺድና ትነግድበት ዘንድ ከቤተ-ክርስቲያኑ ገቢ ገንዘብ እንዲሰጥኽ ለኤጲስቆጶሱ ንገረው። እኔም በትርፉ ቤተሰቦችኽን ታስተዳድርበት ዘንድ እንዲባርክልኽ ከወጣኽበትም በሠላም መልሶ ከቤትኽ እንዲያገባኽ እግዚአብሔርን እለምነዋለኹ አለው።” ይለናል በድርሳኑ ላይ የተጻፈው ታሪክ።¹ ከዚኽ በኋላ ይኽ ችግረኛ ገንዘቡን ተበድሮ ነግዶ አትርፎ ፣ ብድሩንም በጊዜው መልሶ የልቡ መሻት እንደተፈጸመለት ድርሳኑ ይነግረናል። ዝርዝሩን ለአንባቢ ልተወውና ወደ ርእሰ ጉዳይዬ ልመለስ። ይኽ ችግረኛ ሰው በእጁ ላይ ያለውን ሳይጠቀም እንዲኹ መለመኑ ከቅዱስ ሚካኤል ዘንድ የደረሰበትን ተግሣጽ ሰምተናል። አንተም እንዲኹ ታደርግ ዘንድ ከወደድኽ እንዲኽ ያለውን ተግሣጽ ታስተናግዳለኽ። "አንተ ሰነፍ! ሰውነትኽ መሥራት ከሚችለው ሥራ አንዳችም አልሠራኽም!" የሚለውን ተግሣጽ አንተም ትሰማለኽ! እግዚአብሔር እጁን ያሳይኽ ዘንድ ከወደድኽ እጅኽን አሳየው! በቤትኽ ያለውን ንገረው! በእጅኽ ባለው በጥቂቱ ታመን! እጅኽን አጣጥፈኽ ከተቀመጥኽ ግን እግዚአብሔርም እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል። ስለዚኽ ውጣ ውረድ ጣር ድከም! ድካምኽ በእርሱ ዘንድ ያማረ የተወደደ መስዋዕት ነውና። ድካምኽ በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር ትለምን ዘንድ መተማመንን ይሰጥኻልና! በእጅኽ ያለውን መጀመሪያ ተጠቀም! ኤልሳዕ እመበለቲቱን ሴት "በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ" እንዳላት አንተንም እግዚአብሔር "በቤትኽ ያለውን ንገረኝ! በእጅኽ ያለውን አሳየኝ" ይልኻል። ከዛም የእግዚአብሔር እጁን ታያለኽ። ይቆየን! እንኳን ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሠላም አደረሳችሁ! ስለዘገየሁ ይቅርታ ይደረግልኝ! ✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን። -------------- ¹ድርሳነ ሚካኤል ዘጥቅምት ከገጽ 313 - 314
እየሰገድህ ዝሙት ካልጠፋልህ... © አባ ገብረ ኪዳን
አንድ << ቻሌንጅ >> ብንጀምን ምን ይመስላችኋል? ከኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወንድምና እኅቶቻችን ጋር ያለን የ "Hi- Hi" ሠላምታ ወደ "ክርስቶስ ተንሥአ - በአማን ተንሥአ" ላንዴ እስከ ወዲያኛው ብንቀይረው ምን ይመስላችኋል? "ክርስቶስ ተንሥአ" የሚለው ቃል የቅዱስ ኤፍሬው የዘወትር ሠላምታው እንደነበረ ይነገራል! በአካል ለ አካልም ኾነ በሞባይል የንግግርም ጊዜ በጽሑፍ መልዕክትም ጊዜ እኛስ የዘወትር ሠላምታችን እንዳናደርገው ምን ይከለክለናል? ሠላምታ ሰጪው "ክርስቶስ ተንሥአ" (ክርስቶስ ተነሥቷል!) ብሎ ነገሩን ይጀምራል። ሠላምታ ተቀባዩ "በአማን ተንሥአ!" (በእውነት ተነሥቷል!) ብሎ ይመልሳል። ከግላችን ጀምረን ወዳጅ ዘመዶቻቸን ሠላምታውን ልምድ እንዲያደርጉት በማድረግ ብንቀጥል ምን ታስባላችሁ? የተስማማችሁ አሁኑኑ መጀመር ይቻላል! ✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን
« ሦስት ሺሕ ነፍስ » ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን ከሐዋርያት ጋር ተቀብሎ ገና ማስተማር ከመጀመሩ የተፈጠረ ክስተት ነበር - በአንድ ቃል ስብከት ሦስት ሺሕ ሰዎች ወደ ክርስትናው የተጨመሩበት ታላቅ ክስተት! የተጨመሩትን ሰዎች ግን መጽሐፉ “ነፍስ” ሲል ይገልጻቸዋል። ‘ሥጋ የሌላቸው ነፍስ ብቻ ለማለት ነው?’ አይደለም! የሰውን ልጅ “ሥጋ” ወይም “ነፍስ” እያሉ መጥራት የመጽሐፍ ልማድ ስለኾነ መጽሐፍ እንዲያ ሲል ገለጻቸው እንጂ። እዚኹ ላይ ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው ነጥብ ፥ 'ሦስት ሺሕ' ብሎ “ነፍሳት” ማለት ሲገባው “ነፍስ” ብሎ በነጠላ አንቀጽ የጠራው ለምንድን ነው? 'ሦስት ሺሕ' ብሎ 'ነፍስ' ማለት እንዴት ያ'ለ ነገር ነው? 'ሦስት ሺሕ' በነጠላ ቍጥር መጠራት ጀመረ እንዴ? "ምነው ቅዱስ ሉቃስ ሰዋሰው (Grammar) አልተማረም እንዴ?" ያሰኛል። ሦስት ሺሕ አንድ ሲኾን ያየነው በሐዋርያት ጊዜ ነው። ይኽ እንዴት ኾነ? እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ ኾነው 'በኅብረት እንጀራንም በመቁረስ' (ሥጋወደሙን በመቀበል) ይኖሩ ስለነበሩ ስለዚኽም ከክርስቶስ ጋር 'አንድ አካል' ኾነው በመቅደስ እየተጉ ይኖሩ ስለነበር እርሱን ለመግለጽ ነበር። ተጨማሪ አንድምታ ካለው ሉቃስ ያውቃል! ቅዱስ ሉቃስ "እንዲኽ ያለ አንድነት እንደምን ያለ አንድነት ነው? ሦስት ሺሕ ነፍሳት እንዴት አንድ ነፍስ ይኾናሉ?" እያለ አንድነታቸው ሳይደንቀው አልቀረም። "በአንድ ልብ ኾነው ሳለ..." የሚለውን አገላለጽ ምዕራፉን ሲጀምርም ሲጨርስም ይጠቅሰዋልና። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው ስብከት መጀመራቸውን ያስተዋለ መቼም «ሐዋርያት ግን ከመቼው ጾመው ነው ወዲያው ስብከት የጀመሩት? የሐዋርያት ጾም ወዴት አለ?» የሚል ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል። እንዲኽ ብለው ለሚጠይቁ እንዲኽ ብለን እንመልስላቸዋለን ፦ ሐዋርያት ከኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ሌሎች ዐለማት ከመውጣታቸው በፊት ‘ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም’ እንዲል ለዓመት ያኽል በኢየሩሳሌም ቆይተዋል። የሐዋርያትን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ስብከት ከመጀመራቸው በፊት ጾመዋል ብለን ሳይኾን በሌሎች ዓለማት ዕጣ ተከፋፍለው ስብከት ከመጀመራቸው በፊት ጾመዋልና ብለን ነው። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ፥ የቅዱስ ጴጥሮስን የስብከቱን ነገር እንመርምረው፦ “በአንዲት ቃል ብቻ እንዴት ሦስት ሺሕ ሰዎች ልታሳምን ቻልኽ? አማኞቹስ ‘ምንተ ንግበር - ምን እናድርግ?’ ባሉኽ ጊዜ ምን ተሰማኽ? ‘የካድኩትን ጌታ ካስሁት!’ የሚል ድምጽ በውስጥኽ አላቃጨለምን?” እንኳን የሦስት ሺሕ ሰው ልብ የአንድን ሰው ልብ ቢኾን እንኳን መንፈስ ቅዱስ ካልሠራ መለወጥ አይቻልም። እኛ እኮን በአንድ ቃል ሦስት ሺሕ ነፍስ መግዛት ቀርቶ በሦስት ሺሕ ስብከት አንድ ሰው መለወጥ አቅቶናል። ይኽ ለምን ኾነ? መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ዐድሮ ኀይሉን ይገልጥ ዘንድ ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት የተመችን አይደለንም ማለት እኮን ነው። በነገራችን ላይ በቅድስና የበቁ ሰዎች ችግር አለባቸው። በተናገሩ ቁጥር መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው ነገር አለ። ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲኹ በሌላ ቦታ ቆርኔሌዎስን ሊሰብክ ኼዶ ከእርሱ ጋር ለተሰበሱት በተናገረ ጊዜ ‘ቃሉን በሰሙት ኹሉ ላይ’ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ነበር። (ሐዋ.፲ ፥ ፵፬) ቅድስት ኤልሳቤጥም እንዲኹ የእመቤታችንን የሠላምታ ቃል በሰማች ጊዜ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባት” ተብሎ ተጽፏል። ቅዱስ ባስልዮስም እንዲኹ ከብቃት የተነሣ በሚያስተምርበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ቃሉን የሚሰሙትን ምዕመናን ይዋሐዳቸው ነበር። ጸጋው ሞልቶ ሲፈስስ እንዲኽ ነው። አፍኽን በከፈተኽ ቍጥር መንፈስ ቅዱስ ሰማያትን ከፍቶ ይወርዳል። ስለዚኽ ሰው ሌላውን ለመስበክ የሚተጋው ትጋት ፍሬ እንዲያፈራ ራሱ ላይ መጀመሪያ በደንብ መሥራት አለበት ማለት ነው። ይቆየን! እነሆ የቤተ - ክርስቲያን ልደት! እንኳን አደረሳችሁ! ✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን።
ይቅር በሉኝ! ዛሬም የእንግሊዝኛ መዝሙር ልጋብዛችሁ ነው! ይህን መዝሙር "ማዳመጥ ማቆም ለቻለ" እሸልማለሁ! https://youtube.com/watch?v=3D_7BsDhMdk&si=LTmEXxDGQ1hzuZ56
እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል በሠላም አደረሳችኹ!