Fresenbet G.Y Adhanom
Статистика- Последний пост
- 1 авг.
- Последнее чтение
- 15 авг.
- Постов за неделю
- 0
- Всего постов
- 21
- Тип
- открытый
- Язык
- und
- Категория
- Книги (по похожим)
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- 2 223
- 1/48двое суток
- 2 547
- 1/72трое суток
- 2 747
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
+ አለመቁረብ ምን ያጎድላል? + የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ አዲስ አበባ መጥተው በቀደሱበት ጊዜ ሕዝቡ ጥቅጥቅ ብሎ ቅዳሴ መሳተፉን አይተው ተደስተው ሳያበቁ፥ የሚቆርበው ምዕመን ቁጥር እጅግ ትንሽ መሆኑን ተመልክተው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ “ሕዝቡን እየቀለዳችሁበት ነው፤ ሕዝቡም እናንተ ላይ እየቀለደባችሁ ነው” እንዳሏቸው ይነገራል። አቡኑ እውነታቸውን ነው። ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ መቁረብ ካለመፈለግ በላይ፥ ካህን ሆኖም አስተምሮ ካለማቁረብ በላይ ቀልድ ማግኘት ይከብዳል። በጥንት ዘመን አባቶች ሰላምታ ሲለዋወጡ ‘የጸሎት ሕይወትህ እንዴት ነው?’ ይባባሉ እንደነበረ ይነገራል። ከሰላምታው ጀርባ ያለው እሳቤ፥ አንድ ሰው የጸሎት ሕይወቱ ደህና ከሆነ፥ እርሱም ደህና እንደሆነ የሚያጠይቅ ነው። ይህ መለኪያ በአሁኑም ዘመን የሚሠራ ሆኖ ሳለ፥ የመንፈሳዊ ሕይወት ጤንነትን አመላካች ከሆኑ ነገሮች አንዱ የቅዱስ ቁርባን ሕይወታችን መሆኑን ማስታወስ መልካም ነው። ከቅዱስ ቁርባኑ የተለየ ክርስቲያን ከምን እንደጎደለ ለማወቅ፥ በአንጻሩ ቅዱስ ቁርባን የሚያስገኘውን ጥቅም ማስተዋል ጥሩ አማራጭ ነው። ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ በጻፉት “አኮቴተ ቁርባን፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ መሠረት፥ ታሪካዊ እድገት እና ይዘት” በተሰኘ መጽሐፋቸው (ገጽ 42) ላይ እንዲህ በማለት ይዘረዝሩታል፦ ለኃጢአታችን ይቅርታ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል የምንኖር ከሆነ፦ - የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን አባልነታችን ይረጋገጣል። - በተፈጠርንበት የእግዚአብሔር አርአያና አምሳል እናድጋለን። - የጌታን ሕማምና ሞት እያሰብን በምናደርገው የቅዳሴ አገልግሎት ምክንያት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን በዝቶ ይፈስልናል። (ሮሜ 5፡5) - “ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ - የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ላክልን” እያልን በቅዳሴው አገልግሎት ዘወትር ስንለምን፥ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በየጊዜው እንቀበላለን። - በሥጋውና በደሙ የምንቀበለው መድኃኒታችን ክርስቶስ በውስጣችን ህልው ስለሚሆን፥ ወደተፈጠርንበት ዓላማ፥ ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ ኅብረት ወደ ማግኘት እናድጋለን። - እንደ እና ቅዱስ ቁርባንን ከሚቀበሉ አማንያን ጋር ኅብረት ይኖረናል። - በጥምቀት የተቀበልነውን የልጅነት ጸጋ ጠብቅን እንድንኖር ያደርገናል። - ሥርየተ ኃጢአትን (የኃጢአት ይቅርታን) እናገኛለን (1 ዮሐ 1፡7)፤ እንዲሁም ለኃጢአት ሞተን ድል አድራጊ ሕይወትን እንጎናጸፋለን። (ሮሜ 6፡11) - ክርስቶስን የመምሰል ወይም ክርስቶስን የተሸከምን (ጸዋርያነ ክርስቶስ) እንሆናለን። - በክርስቶስ የተሰጠን ዘላለማዊ ሕይወት እውን ይሆንልናል። - የመንፈሳዊ ሕይወታችን መገለጫ ይሆንልናል፤ ይህን ሰማያዊ ማዕድ ሳንቀበል በፍጹም መኖር አንችልም። ስለሆነም በቅዱስ ቁርባን የምንቀበለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ሕይወታችን ይሆናል። ይህ በቅዱስ ቁርባን የከበረ ሕይወት መለኮታዊ ጸጋን አልብሶ፥ የእግዚአብሔርን አርአያ እና አምሳል በሕይወታችን ወደምናሳይበት መንፈሳዊ ደረጃ ያሳድገናል። ከቅዱስ ቁርባን ራስን ማግለል ማለት ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ሁሉ በራስ እጅ መግፋት ማለት ነው። ከዚህ ሁሉ ጎድለን ክርስትናችንን እንዳናጣ፥ የመዳን ቀን ዛሬ መሆኑን በማስታወስ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ከሕይወት ማዕድ እንቀበል። 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
видео или голосовое, без подписи
+ የደካማው ጸሎት + ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን በመሃል እጅህ ይዘህ ሳለ ለእኛ ሕይወት ታስባለህ። ከሞቃቷ ፀሐይ ይልቅ ሙቀቷ የሚያቃኝለው ደካማ ፍጥረት፥ ከመሬቱ ይልቅ ወደ መሬት ገብቶ ከአፈር የሚዋሐደው የሰው ልጅ ጉዳይ ትኩረትህ መሆኑን ማሰብ እጅን በአፍ ያስጭናል። በዚህ አድካሚ ዓለም ስንኖር፥ አንተ እንደምትወደን ከማሰብ በላይ የሚያጽናና ነገር የለም። ለክብር ተፈጥረን በመዋረድ፥ ለንጽሕና ተፈጥረን በማደፍ ሕይወታችን እንዳይደመደም በጸጋህ ጠብቀን። ሰውን ወዳጅ እና ይቅር ባይ የሆንክ አምላካችን ሆይ፥ የዓለም ጨው መሆን እንዳቃተን አይተህ፥ ድንጋይ ናቸው ብለህ አትጣለን፥ ታገሰን እንጂ። የዓለም ብርሃን መሆን እንዳልቻልን አይተህ፥ ከዕንቅብ በታች አታስቀምጠን፥ እስክናበራ ጠብቀን እንጂ። 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
+ ዓይንህ ማንን ያያል? + ክርስቶስ ከመረጣቸው አሥራ ሁለት ደቀ-መዛሙርት መካከል ሦስት ዓይነት ሰዎችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ዮሐንስ ነው። ዮሐንስ ከመጠራቱ አንስቶ እስከ መስቀል ድረስ ጌታችንን የተከተለ ደቀ መዝሙር ነው። ፍቅሩ ፍጹም ነው። የተጠራበትን አገልግሎት የሕይወት ጥሪው አድርጎ በመውሰድ በጽናት እስከመጨረሻው ድረስ የተጓዘ ነው። ሁለተኛው ድግሞ ጴጥሮስ ነው። ጴጥሮስ እድሜው ገፋ ካለ በኋላ የተጠራ ደቀ መዝሙር ነው። ብዙ እድሜውን በዓለማዊ ነገር አሳልፏል። ብዙ ባክኗል፥ ብዙ አጥቷል፥ በመጠራቱ ደግሞ ብዙ አትርፏል። ጴጥሮስ ራሱን መልካም ደቀ መዝሙር አድርጎ ያስብ የነበረ፥ ክርስቶስን ‘አላውቀውም’ ለማለት ግን ትንሽ ነገር የበቃው ሰው ነው። የጴጥሮስ ታሪክ ግን መጨረሻው ያምራል። በፍጹም ንስሃ ተመልሶ የሐዋርያት አለቃ እስከመሆን የደረሰ፥ በሰማዕትነትም ጌታውን መስሎ ያረፈ ሰው ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ይሁዳ አለ። ይሁዳ ከከፋ ሕይወት የተጠራ፥ ሌባ ሆኖ ሳለ የገንዘብ ባለሟል ተደርጎ የተሾመ ነው። ይሁዳ ገንዘብ ያሰከረው፥ ጥቅም ያሳወረው፥ ክርስቶስን በመሳም አሳልፎ የሰጠ፥ ለክብር የጠራውንም ጌታ የካደ ነው። ጌታችን ክርስቶስ ጠርቷቸው ከዋለበት እየዋሉ፥ ካደረበት እያደሩ፥ የቃሉን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ተዓምራቱን ሳይቀር እየተመለከቱ ከተማሩ አሥራ ሁለት ሐዋርያት መካከል ዮሐንስ፥ ጴጥሮስ እና ይሁዳ ተገኝተዋል። ታዲያ በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል ይሁዳን ካገኘን፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ ይሁዳዎችን ስናገኝ የምንደነቀው ለምን ይሆን? ቤተክርስቲያን ሦስቱንም ዓይነት ደቀ መዛሙርት ይኖሯታል። ቤተክርስቲያን በጥሪያቸው ጸንተው እስከ መጨረሻው የሚኖሩ ዮሐንሶች ይኖሯታል። ቤተክርስቲያን ክርስቶስን ‘አላውቅህም’ ብለው በንስሃ ግን ፍጹም ሆነው የተመለሱ ጴጥሮሶችም አሏች። ቤተክርስቲያን ጌታቸውን በአላዋቂነት፥ በገንዘብ ፍቅር፥ በድንዛሬ ‘በመሳም’ አሳልፈው የሰጡ ይሁዳዎችም ይኖሯታል። ቤተክርስቲያንን ስታይ ዓይንህ ማንን ያያል? ቤተክርስቲያን ውስጥ ዮሐንሶች ብቻ ያሉ መስሎህ አለመሆኑን ስታውቅ አዝነህ ይሆን? በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ጴጥሮሶችን ጥፋታቸውን አይተህ ንስሃቸውን ሳትመለከት ተሰናክለህባቸው ይሆን? የቤተክርስቲያን ይሁዳዎችን ተመልክተህ 'አምላክ ለምን አይፈርድም!' ብለህ ከፈጣሪ ተሟግተህ ይሆን? እንግዲያውስ፥ አንተ የተጠራኸው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ልትሆን ነውና፥ ዓይንህን በጌታህን ላይ አድርግ። ደቀ መዛሙርቱን መመልከት ካለብህ ደግሞ የቤተክርስቲያን ዮሐንሶችን እየተመለከትክ በእምነት ምሰላቸው። የቤተክርስቲያንን ጴጥሮሶች እየተመለከትክም በፍጹም ንስሃቸው ምሰላቸው። ይሁዳዎቹን ግን ተዋቸው! 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
видео или голосовое, без подписи
+ የእኔ ቤት ይቀርባል + አንዲት እናት ቁጭ ብላ ለልጇ መጽሐፍ ቅዱስ ታነብላታለች። ይህ የዘወትር ተግባራቸው ነበር። እናት ካነበበች በኋላ ለልጇ ‘እስቲ አሁን የሰማሽውን በራስሽ አገላለጽ ንገሪኝ’ የማለት ልማድ ነበራት። ከእለታት በአንዱ ቀን ከኦሪት ዘፍጥረት እያነበበች እያለች የጻድቁ ሄኖክ ታሪክ ጋር ደረሰች። “ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ። ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።” (ዘፍ 5፡23-24) የሚለውን ካነበበች በኋላ ‘እስቲ ይህንን በራስሽ አገላለጽ ንገሪኝ’ ብላ እድሉን ለልጇ ሰጠቻት። ልጇም እንዲህ በማለት በራሷ መንገድ ገለጸችው። “የውልሽ እናቴ… ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር ኖረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይሄድ ነበር። በጣም ወዳጆች ነበሩ። አንዳቸው ለሌላቸው ምስጢራቸውን ይናገሩ ነበር። ለብዙ ዘመን ተነጋገሩ። ቀናት ወደ ወራት፥ ወራት ወደ ዓመታት ተቀየሩ። እንዲህ እያሉ ለሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት አብረው እየተጓዙ ተነጋገሩ። አንድ ቀን ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገረ እያለ፥ ቆም አለና፦ “የተወደድክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ቀኑ በጣም ገፋ፥ እየመሸ ነው። እስቲ ወደ እኔ ቤት ጎራ እንበልና በዚያ እንቀመጥ።” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “ልጄ ሄኖክ ሆይ፥ ለሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመታት ተነጋግረናል፤ አብረንም ተጉዘናል። አሁን ከአንተ ቤት ይልቅ ለእኔ ቤት ቀርበናልና፤ ለምን ከእኔ ጋር አብረኸኝ አትመጣም? ወዳጄ ሄኖክ ሆይ፥ ወደ እኔ ቤት ና። መላእክቱ ሳይቀር ሊያዩህ እጅግ ጓጉተዋልና።” አለው። ሄኖክም ከእግዚአብሔር ጋር ተስማማ፥ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፥ እግዚአብሔር ወስዶታልና።” (ዘፍ 5፡24) የአይሁድ ሊቃውንት የዳዊትን መዝሙር ሲተረጉሙ የሰው ልጅ ንቁ እንቅስቃሴ በመቆም፥ በመቀመጥ፥ በመራመድ መጠቃለል ይችላል ይላሉ። ቅዱስ ዳዊትም በመጀመሪያ መዝሙሩ ሦስቱንም ጠቅሶ 'በክፉቸች ምክር አትሂዱ'፥ 'በኃጢአተኞች መንገድ አትቁሙ'፥ 'በዋዘኞች መንገድ አትቀመጡ' እያለ ይመክረናል። የሚያስመሰግነውን መንገድም ‘በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል’ (መዝ 1፡2) የሚባልለት ሰው መሆን እንደሆነ ይነግረናል። በእግዚአብሔር ሕግ ደስ መሰኘት ከእግዚአብሔር ጋር መሄድ ነው። ሕጉን ቀንና ሌሊት ማሰብና ማሰላሰል ከእግአዚብሔር ጋር መጓዝ ነው። አካሄድ እለት እለት መሆኑን፥ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ፥ ወድደን ፈቅደን የምንተገብረው መሆኑን ማሰብም ብልህነት ነው። ለመሆኑ የእኛስ አካሄድ ከማን ጋር ይሆን? የሕይወት ዘመናችን ሲገፋ፥ ዓመታቶቻችንም ሲነጉዱ፥ ለማን ቤት እየቀረብን ይሆን? ለሰይጣን ወይስ ለእግዚአብሔር? 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
видео или голосовое, без подписи
+የአህያ መስዋእትነት + ለረዥም ጊዜ "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች አህያ" እየተባለ ሲተረት እናውቃለን። ተረቱ ለሌላው ካለማሰብ የሚመጣን ራስ ወዳድነት የሚያጎላ ተደርጎ ይነገራል። በእርግጥ አህያ ማኅበረሰቡን አገልጋይ ሆና ሳለ፥ ራስ ወዳድ ሆና መሣሏ የሚገርም ነው። ተረቱ ግን የሚያንጸባርቀው እውነት ከአባባሉ ተለምዷዊ ትርጉም እጅግ የራቀ ነው። በድሮ ዘመን በትልቅነቱ ከግራር እና ከዋርካ የሚተልቅ 'ሰርዶ' የሚባል ዛፍ ነበር ይባላል። ዛፉ ለብዙ አገልግሎት ስለሚውል ዝሆን እየገነደሰው፥ አህያ ደግሞ እየተሸከመች ታጓጉዘው እንደነበረ ይነገራል። ዘመን ሲገፋ ግን አህያም አቅሟ እየደከመ፥ ወገቧም እየተላጠ መጣ። ይህንን ያስተዋለው አንበሳ እንስሳቱን ሁሉ ስብሰባ ይጠራል። የስብሰባውም አጀንዳ አህያ ነበረች። እንስሳቱ ሁሉ ከተሰበሰቡ በኋላም አንበሳ ተነሳና "እንግዲህ እንደምትመለከቱት አህያ እየደከመች ነው። ወገቧም እየተላላጠ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ የሰርዶን ግንድ በመሸከም ስታገለግል ኖራለች። አሁን እርሷ ጡረታ ወጥታ ማረፍ ይገባታልና፥ በፈቃደኝነት ኃላፊነቷን ወስዶ የሚሠራ እንስሳ ያስፈልጋል" በማለት ተናገረ። የአህያን ከባድ ኃላፊነት በፈቃደኛነት ተቀብሎ መስራት የሚፈልግ ግን ሊገኝ አልቻለም። በዚህ ጊዜ አንበሳ "እንግዲህ በፈቃደኛነት ሰርዶን የመሸከም ኃላፊነት መውሰድ ካልፈለጋችሁ፥ የእንስሳት ሁሉ ንጉሥ እንደመሆኔ ኃላፊነቱን እኔ ራሴ ለምፈልገው እሰጣለሁ። በመሆኑም፥ ከዛሬ ጀምሮ ድመት ይህንን ኃላፊነት ወስዳ ትሠራለች" በማለት ተናገረ። በዚህ ጊዜ አህያ በመደናገጥ "ጌታዬ አንበሳ ሆይ፥ ድመት ደግሞ በምን አቅሟ ሰርዶን የሚያክል ግንድ ትሸከማለች? እርሷ ትንሽ ናት፤ ይህንን ኃላፊነት ተሸክማ መሥራት አትችልም" በማለት አሳቧን ሰጠች። ሌሎቹም እንስሳት በመስማማት አንገታቸውን በአዎንታ ነቀነቁ። አንበሳም አህያ ስለተከራከረችው በቁጣ "እና ማን ይሸከመው ነው የምትይው?" በማለት ጠየቀ። አህያም "ጌታዬ አንበሳ ሆይ፥ አቅሜ ቢደክምም ድመት በሰርዶ ግንድ ተደፍጥጣ ከምትሞት እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እሸከመዋለሁ" በማለት ተናገረች። አንበሳ ግን የአህያ የተቃውሞ አካሄድ አላማረውም። ዛሬ እርሷ ስትከራከረኝ ያዩ፥ ነገ ደግሞ ይከራከሩኛል በማለት ፈራ። በመሆኑም አህያን በእብሪተኛነት በመክሰስ የሞት ፍርድን ፈረደባት። አህያ የሞት ፍርዱ ሊፈጸምባት ሲል "መጨረሻ የምትይው ነገር አለ?" ተብላ ተጠየቀች። አህያም "አዎ፥ የአንበሳ ፍርድ ፍትሐዊ አይደለም። ድመት ሰርዶን መሸከም አትችልም። አንበሳ ሊሰማኝ አልቻለም፤ እኔስ ይህንን ኢፍትሐዊነት ከማይ መሞት እመርጣለሁ። አምላኬ ከሰማኝ፥ እንዲያውም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" አለች ይባላል። ተረቱ "አህያን በሸክም መበደላችን ሳይቀር፥ ለካ በተረቱም ስንበድላት ነበር እንዴ?" ያስብላል። 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
видео или голосовое, без подписи
ክርስቶስ ተነስቷል! አዎ! ለዘመናት ሕዝብን ከአሕዛብ ሳይለይ የገዛውን ሞት ድል አድርጎታል! ድንጋዩን የሚያንከባልል ሳይፈልግ መቃብሩን ባዶ ትቶት ሄዷል! እኛም ከሞቱ ጋር የምንተባበር፥ ከትንሣኤውም ጋር እንተባበራለንና፥ እጅግ ደስ ይለናል! ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል! ደስ ይበላችሁ! ደስ ይበለን! እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!
+ በዐቢይ ጾም የነቢያቱን ቋንቋ ይማሩ! + መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት ጥንታዊ ቋንቋዎች ተጽፏል። ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ እና በአረማይክ፥ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ ነው። እነዚህ ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እናት ቋንቋዎች ተብለው ይጠራሉ። ከእነዚህም ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የበዛውን ክፍል የሚይዘው የዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። ዕብራይስጥ ታላቁ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕግ የተቀበለበት ቋንቋ ነው። ዕብራይስጥ በኦሪት ድንኳን አምልኮ የተፈጸመበት ቋንቋ ነው። ዕብራይስጥ ዳዊት ድንቅ የሆነውን መዝሙሩን የዘመረበት፥ ልጁ ሰለሞንም ምሳሌዎቹን የከተበበት ቋንቋ ነው። የዕብራይስጥ ቋንቋ ስለ ክርስቶስ ትንቢት የተናገሩ ነቢያት ትንቢታቸውን ያሰሙበትም ቋንቋ ነው። በመጀመሪያው ዙር የዕብራይስጥ 1 የትምህርት ቆይታ እጅግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፈናል። በቤተክርስቲያናችን ስመ ጥር የሆኑ ታላላቅ ሊቃውንት ሳይቀር የተሳተፉበትንም ነበር። የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ዙር ትምህርታቸው - ዕብራይስጥ 2 - ሲቀጥሉ፥ እነሆ የዕብራይስጥ 1 ትምህርት ደግሞ እንደገና ተከፍቷል። ይህንን የዐቢይ ጾም ጊዜ ብሉይ ኪዳን የተጻፈበትን የጥንታዊ ዕብራይስጥ ቋንቋ ከቤትዎ ሆነው ከሥር ከመሠረቱ 'አሌፍ' ብለው ይማሩ ዘንድ ይህ እድል ተመቻችቷል። ለዝርዝሩ የሚከተለው የምዝገባ ቅጽ ላይ ያለውን መረጃ ይመልከቱ። በክፍያው እና በትምህርቱ ሰዓት ከተስማሙ ምዝገባውን በቅጹ ላይ መፈጸም ይችላሉ። https://docs.google.com/forms/d/e/1FAIpQLSfUK7gqKAC8C7V8uIdXApC3cX66A3Zg1uXCPqJ6aMymWCHGCw/viewform?usp=publish-editor
አግፕያ (Ϯⲁⲅⲡⲓⲁ) የቅብጥ ቃል ሲሆን፥ የሰዓታት ጸሎት የሚል ትርጉም አለው። የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በዋነኛነት የሚጠቀሙት የጸሎት መጽሐፍ ነው። ከጠንካራዎቹ የግብጽ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት ጀርባ አግፕያ አለ ብንል ውሸት አይሆንብንም። መጽሐፉ የሰባቱን ዐበይት ሰዓታት ጸሎቶችን በማካተቱ፤ አንድ ክርስቲያን በቀን ሰባት ጊዜ ጸሎት ማድረስ አለበት የሚለውን መታዘዝ ለሚፈልግ ሁነኛ መጽሐፍ ነው። በየአንዳንዱ ሰዓት የመግቢያ ጸሎቶችን፥ ከመዝሙረ ዳዊት የሚደገሙ መዝሙራትን፥ የወንጌል ንባብ፥ ሊጦን እና የመሳሰሉትን ይዟል። ጸሎታችሁን ቅርጽ አስይዞ ለማስቀጠል ጥሩ መርጃ ነው። ዶ/ር ሥርግው ገላው የጀርመንኛውን ቅጂ ወደ አማርኛ ጥሩ አድርገው ተርጉመውታል። አራት ኪሎ አካባቢ ታገኙታላችሁ። ሸምታችሁ ብትመለከቱት በብዙ እንደምታተርፉ አልጠራጠርም።
+ ውሻ ተሸክመህ ትሄዳለህ? + አንድ ቀን አንድ አባወራ ለበዓል በግ ሊሸምት ወደ ገበያ ይወጣል። ጥሩ የሚለውን በግ መርጦ ከገዛ በኋላም ተሸክሞ ወደ ቤቱ ጉዞውን ይጀምራል። ይህንን ሁኔታ ሲከታተሉ የነበሩ ሦስት ሌቦች፥ በምን አይነት መንገድ ሊሰርቁት እንደሚችሉ ተነጋግረው በመንገዱ ላይ ፈቀቅ ፈቀቅ ብለው ይዘጋጃሉ። አንዱ ሌባ በመንገድ ላይ በግ ተሸክሞ ሲሄድ የነበረውን አባወራ አስቆመውና "ሰውዬ፥ ምን ኾነህ ነው ውሻ ተሸክመህ የምትሄደው?" ብሎ ይጠይቀዋል። አባወራውም በስጨት ብሎ "በግ መኾኑን እያየህ ውሻ ነው ትለኛለህ እንዴ? ምን ይላል ይሄ!" ብሎ መንገዱን ይቀጥላል። ጥቂት እንደተጓዘም ሁለተኛው ሌባ ያስቆመውና "ምን ኾነህ ነው ውሻ ተሸክመህ የምትሄደው ጃል?" ይለዋል። አባወራውም "ዛሬ ሰው ምን ነክቶታል? በጉን ውሻ ትለኛለህ እንዴ?" ብሎ አልፎት ይጓዛል። ውስጡን ግን ጥርጣሬ ይገባው ጀመር። ጥቂት ፈቀቅ እንዳለም ሦስተኛው ሌባ "በጠራራ ፀሐይ ውሻ ተሸክመህ ትሄዳለህ? ምን ኾነሃል?" ይለዋል። ሰውየውም በመጨረሻ "ይህ ሁሉ ሰው ውሻ መስሎ ከታየውማ በግ ብዬ የገዛሁት ውሻ ነው" ብሎ ጥሎት ሄደ። ሌቦቹም የፈለጉትን በግ ከእጃቸው አስገብተው ሄዱ። ውሸት ሲደጋገም በእርግጥም እውነት ይመስላል። ብዙዎች ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ያልኾነው ተነግሯቸው ተሸውደዋል፥ የውሸት አርበኞች ያልተባለውን ተባለ ብለዋቸው ተሳስተዋል። በዚህ መልኩ እንቁዋቸውን 'ድንጋይ' ብለው የጣሉ፥ ብኩርናቸውን ለምስር ወጥ አሳልፈው የሰጡ እልፍ ናቸው። አንዳንዴ በሕይወታችን ዋጋ ያለቸውን ነገሮች ሰዎች ሲያራክሱብን "ሊያስጥሉን ይኾን?" ብሎ ማሰላሰሉ፥ ረጋ ብሎ ሁኔታዎችን መመዘኑ ይበጃል። ይህ አካሄድ እርግጥም ከብዙ ኪሣራ ያድነናል። 🖋 Fresenbet G.Y Adhanom ---------- የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom
видео или голосовое, без подписи
+ ነገርን ከሥሩ ለመረዳት... + በኦርቶዶክሳዊያን ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እለቱን ተቦክቶ እለቱን የተጋገረ አይደለም። ለረዥም ዘመን የታቀደ እና የተሠራበት ነው። በብዙ አሥርት ዓመታት ውስጥ ቤተክርስቲያን ከሚናዋ እንድትሸራተት፥ በብዙዎች ዘንድ 'የለውጥ ጎታች' ተደርጋ እንድትሳል፥ ሕዝቡ በራሱ ጉዳይ በንቃት እንዳይሳተፍ፥ ከላይ እስከታች "እኔን ካልነካኝ፥ ምን አገባኝ?" በሚል አዚም ውስጥ እንድንቀረቀር፥ አጀንዳ ተቀባይ ብቻ እንድንሆን በእቅድ ተሠርቷል። በእኛ በኩል ደግሞ ከሃይማኖት ይልቅ ጥቅም ተኮር መኾን፥ በረባው ባልረባው መከፋፈል፥ ኦርቶዶክሳዊ ርዕዮተ-ዓለም መፍጠር አለመቻል ለሌሎች አመቺ ዒላማ አድርጎናል። ይህንን አውቀን የእርምት እርምጃ መውሰድ ካልቻልን፥ ከዛሬ ይልቅ ነገ የከፋ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ታዲያስ ምን እናድርግ? የተወሰኑ አሳቦችን እነሆ፦ 1) ይህ ሁሉ ችግር እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም። የራሱ ምንጭ እና አባባሽ ምክንያቶች አሉት። ችግርን ማወቅ የመፍትሔው ግማሻ አካል ስለኾነ፥ ለዚህ አሳዛኝ ምስቅልቅል የዳረጉንን ምክንያቶች በደንብ አጥርተን ማወቅ ይገባናል። ችግሩን በየደረጃው አጥርተን ካልተረዳን፥ ለመፍትሔው ልንሠራ አንችልም። ግንዛቤው የተወሰኑ ሰዎች ጋር ቢኖርም፥ እንደ ሕዝብ ንቃተ ሕሊና መፍጠር ካልተቻለ ግን በፍጹም ውጤት ልናይ አንችልም። የጸረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ቤተክርስቲያን ያሳየችውን ትጋት በዚህ ጉዳይ ላይም ማሳየት አለባት። 2) ብዙ ሰው ከሃይማኖታዊ ዕውቀት ርቆ፥ ከመንፈሳዊነት ጎድሎ፥ ከምስጠራት ራሱን አግልሎ ኦርቶዶክሳዊነትን ባሕሉ ብቻ አድርጎ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ይህንን ሕዝብ በእውቀት የማጎልበት፥ በመንፈሳዊነት የማጠናከር፥ በቤተክርስቲያን ጥላ ውስጥ የመሰብሰብ ሥራ ካልተሠራ በስተቀር፥ ስለ ቤተክርስቲያን እንዲገድደው ማድረግ አይቻልም። ሰዎች ወንጌል ስትሰብክ የማይገኙባትን፥ የማያስቀድሱባትን፥ ንስሃ የማይገቡባትን፥ የማይቆርቡባትን ቤተክርስቲያን ደርሰን 'ተቆርቆሩላት' ብንል የማይኾን ነው። 3) 'ልማት' የሚለው አሳብ ላይ ያለን መረዳት መለወጥ አለበት። ሕንጻ ቤተክርስቲያን መሥራት መልካም ቢኾንም፥ የሰው ልማት (Human Development) ላይ መሥራት ካልጀመርን ትርጉም የለውም። የውጤታማነታችን ዋና መለኪያ ያለውን ማጽናት፥ የጠፋውን መሰብሰብ መኾን አለበት። ይህ ካልኾነ በስተቀር ጉዟችን ሁሉ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እንደኾነ ይቀጥላል። ነገ ላይ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ የሚረከበው አጥቶ ባዶ እንዳይቀር ዛሬ መስራት ይኖርብናል። በነገራችን ላይ፦ 'ምን ታመጣላችሁ?' በሚመስል መልኩ በምስራቅ አርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ አንጎደቼ፥ ጉሬ፥ ወሸባ፥ ተሬ አሚኛ ቀበሌዎች የኦርቶዶክሳዊያን አፈና እና ግድያ ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ የእኛም መፍዘዝ እንደዚያው! በዚህ አካሄድ ገና ብዙ ብዙ ዋጋ እንከፍላለን። ሰውን ወዳጅ መድኃኔዓለም ሆይ፥ ስቃያችንን ተመልከት!
видео или голосовое, без подписи
ለልጆቻችን የምናወርሰው ምንድር ነው? የኦርቶዶክሳዊያን ስቃይ አሁንም አይሎ ቀጥሏል። የክርስቲያኖች ደም የጠማቸው ተረፈ ዲዮቅልጢያኖሳዊያን አረመኔዎች ዛሬም ዘጠኝ ኦርቶዶክሳዊያንን ገድለዋል። ከጥንት ጀምሮ ሰማዕትነት ያልተለያት ቤተክርስቲያን፥ እነሆ ዛሬም "ሰማዕታት የምታፈራ ቤተክርስቲያን" መሆኗ በተግባር እየታየ ነው። በዚህኛው በኩል ደግሞ፥ የተቋማቶቻችን ዝምታ የሞትን ሳይኾን የገደልን እስኪመስል አጀብ ያሰኛል። ይህ ወቅት 'ለልጆቻችን የምናወርሰው ምን አይነት ሀገር ነው?' ብለን የምንጠይቅበት ወሳኝ ጊዜ ነው። እህቴ ሆይ፥ ለልጆችሽ በአንገታቸው ያለውን መስቀል የሚደብቁበት፥ ኦርቶዶክስ ለመባል የሚያፍሩበት ሀገር ማስረከብ ትፈልጊያለሽ? ወንድሜ ሆይ፥ ለልጆችህ ነጠላ በአደባባይ ለመልበስ የሚሸማቀቁበት፥ ኮሽ ባለው ሁሉ የሚደነግጡበትን ሀገር ልታስረክባቸው ትፈልጋለህን? ይህ እንዳይሆን የምንፈልግ ከሆነ ከአሁኑ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል። አምስት እና አሥር ሳይሆን፥ ሃምሳ እና መቶ ዓመት አሻግረን በማቀድ የምንንቀሳቀስበት ጊዜ አሁን ነው! ሰውን ወዳጅ መድኃኔዓለም ሆይ፥ ስቃያችንን ተመልከት!
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи