አብርሃም ሠጠኝ
Статистикаከሐዋሳ ዩ.ቲ በBiomedical Eng Bsc፣ ከጅማ ዩ.ቲ ደግሞ በProject Mag’t & finance MA ምሩቅ ስሆን በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ህብረት (ኢቫሱ) ስር ከ2015-2017 በጅማና አካባቢው፣ ከ2018 ጀምሮ በአዲስ አበባና ዙርያው በሚገኙ የዩኒቨርስቲና ኮሌጅ ክርስቲያን ተማሪ ህብረቶችን በማገልገል ላይ እገኛለሁ። በዚህ ቻናል መንፈሳዊ መልእክቶችን ያገኛሉ።
- Последний пост
- 11 авг.
- Последнее чтение
- 13 авг.
- Постов за неделю
- 1
- Всего постов
- 21
- Тип
- открытый
- Язык
- ti
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- 102
- 1/48двое суток
- 116
- 1/72трое суток
- 126
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
አቤቱ፤ ግፍን አታሳየኝ 🥺 ከእለት ወደ ተእለት ለማየት ቀርቶ ለመስማት እንኳን የሚዘገንኑ ወንጀሎች፣ ነውሮች፣ የአደባባይ ግፎች፣ ስልታዊ ጭቆናዎች የተንሰራፋባት አለም ላይ አለን። አይነቱ ሊለያይ፣ ምክንያቱም ምንም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የጨቋኝና ተጨቋኝ ዜና በየዘመናቱ፣ በየስልጣኔው፣ በየቦታው አለ። ከዚህም የተነሳ የትም አገር ብንሄድ፣ ልንሸሸው የማንችለው እውነት ነው። በነብዩ ዕንባቆም ዘመንም ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሯል፤ ስለዚህም ፍትሕን ፍለጋ ተንከራቷል፣ ጮዃል፣ አጉረምርሟል፣ አልቅሷል። 📖 በአንድ ቦታ እንዲህ ሲልም ጸልዮኣል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቷል።” - (ዕን 1:2-3) ወደ በአገራችን የመጣን እንደሆነም ትራንስፖርት ላይ፣ ስራ ቦታ፣ በትምህርት መስክ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ እድር ስብሰባ፣ በማህበራዊ አውታር (Social media)፣ ወዘተረፈ የሰዎች መሰባሰቢያዎች አካባቢ የምንሰማው ነገር ቢኖር የፍትሕ እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ አለመረጋጋት፣ የፖለቲካ ሽኩቻ ወዘተ ከሆነ ሰነባብቷል። እንደ የእምነታችንንም እኛም ሆንን ሌሎች ለነዚህ ጉዳዮች የተለያዩ መፍትሔዎች እንሰጣለን። አንዳንዶች አላይም አልሰማም እያሉ እውነታን ሲክዱ (ፖለቲከኞች ላይ ይጎላል)፣ አንዳንዶች ለስደት ሲነሳሱና መንገዶችን ሲያስሱ፣ ሌሎች ደግሞ በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ሲጎዱ፣ ቀሪዎቹ ሕልማቸውን ለመኖር መፍትሔ ፍለጋ ሲኳትኑ እንታዘባለን። ወንድሜ ከየትኛው ነህ? አንቺስ እህቴ ከየትኛው ነሽ? የእንባቆምን ጨምሮ በየዘመናቱ ለሚጮኸው የሲቃ ጩኸት እግዚአብሔር ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አያውቅም (ኢሳ 33፥2:5)፤ ይልቁን አብሮነቱን ያሳያል እንጂ። ከሁሉ በላቀ ሁኔታ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው በሆነው በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በአንድያ ልጁ በኩል ደግሞ ግፍን አይቷል፣ ተቀብሏልም። ኢየሱስ ንጹህ ሲሆን የሰዎች ኀጢአት ውጤት ውላጅ የሆነውን ሰቆቃ ተካፍሏል። በልጅነቱ ከወላጆቹ ጋር ሞትን ሽሽት ተሰዷል (ማቴ 2፥13)፣ በወዳጁ ተከድቷል (ዮሐ 18፥2-3)፣ ያለ ጥፋቱ በደቦ ፍርድ በአደባባይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል (ሉቃ 23፥13-18)። ከመከራችን ራሱን ባለማራቁም የምናልፍበትን የሚረዳ ሆኖ ተገኘ(ዕብ 4፥15)። አላዋቂዎች እንደሚሉት ግን አብሮን የሚያለቅስ ምስኪን ሳይሆን አመፅን በጽድቁ እየቀጣ፣ ንሰሀ ገቢዎቹን የሚምር፣ ፍትሕን እስኪያወጣም ስራውንም በትዕግስት የሚፈፅም ብርቱ አዳኝ ነው (ኢሳ 42፥1-4)። ዕንባቆም በሚያፍበት ሁኔታ ጉልበተኛች ሲሳካላቸው፣ በተቃኒው ፃዲቃን ሲደኸዩ ሲያይ፣ ጌታን ፍረድ እንጂ ለምን ዝም ትላለህ? እስከ መቼስ ትታገሳለህ? ይለው ነበር። ቅዱሱም ጌታ የራሱን ምልከታ ለባርያው ዕንባቆም ባሳየ ጊዜ ነብዩ ደነገጠ። ንስሀ ለመግባት እልኸኛ የሆኑትን ለማጥፋት የእግዚአብሔር ሰይፍ ተስሎአልና። በዚህም መነሾ የሚደርሰውን ጥፋት ራዕይ ተገልጦለት ሲረዳ፣ ክርክሩ ወደ ልመና፣ ወቀሳውም ወደ ወዮታ፣ ውትወታውም ወደ ምስጋና ጸሎት ተለወጠ (ዕን 3፥14-19)። ሐዋርያው ዻውሎስም ምድር በኢፍትሀዊነት መጥለቅለቃን ሲያይ፣ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሠማይና ምድር “ተስፋ” አድርጎ የሰጠውን ጌታ በማሰብ እንዲህ አለ፦ “በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም።”(2 ቆሮ 5:4)። አዎ የኀጢአታችን ውጤት የሆኑት አመጽ፣ ስቃይ፣ ሕመም፣ ጉስቁልና፣ ሞትና ሐዘን በሙሉ በኢየሱስ ዳግም ምፅአት ይወገዱና በእረፍት፣ በሰላም፣ በጽድቅ፣ በደስታ፣ በሕይወት ይለወጣሉ (ራዕ 21፥4-8፣ 22፥3-5)። እስከዚያው ማራናታ እያልን፣ በምናየውና በምንሰማው ግፍ ልባችን ሳይሻክር፣ የጌታ ምሕረት የምድርን ገጽ እንዲያድስ እየቃተትን እንኑር፤ ተስፋን የሰጠ እርሱ የታመነ ነውና። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ ጌትዬ አምላኬ፣ የማልፍበትን መንገድ ስለምታውቅ አመሰግንሃለሁ። አንተ እኮ እረኛ ለሌላቸው የምትራራ እንጂ ጨካኝ ባላባት (አስተዳዳሪ) አይደለህም። ደግሞም ከእኔ ርቀህ፣ ከምኖርባትም ምድር ራስህን አግልለህ የምትኖር፣ ቆሻሻ አልይ የምትል ስላልሆንክ እወድሃለሁ። ስለዚህ ጸሎትን ሰሚ ቸር ሆይ እንዲህ እለምንሃለሁ፦ እባክህ ለምስኪኖች ድረስላቸው፣ ለተበደሉ ፍረድ፣ በዳዮችንም ይቅር በል፣ ዳግም እድል ስጣቸው፣ እኔም በማየው ነገር እንዳልወሰድ ልቤን ደግፍልኝ። አሜን! #ግፍ #ፍትሕ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
የለሁኝም (I am No more) 📴 ስልክ ተደውሎ ትፈለጋለህ/ያለሽ ስንባል፣ የማንችል ከሆነ አልችልም የለሁኝም እንላለን። ለበጎ እንደሆነ ስናውቅ ግን ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ለመገናኘት እንደምንሞክር እንናገራለን። ልክ እንዲሁ በሕይወታችን የለሁም፣ አልችልም፣ አልገኝም የምንልባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስም የመልእክቱ መጀመርያ እንደሆነ በሚታመነው ለገላትያ ሰዎች በፃፈላቸው ደብዳቤ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ይላቸዋል። 📖 “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።” - ገላ 2:20 ሐዋርያው ለሁሉም ጥሪ ምላሽ አይሰጥም፤ ይልቁን የለሁም፣ አልችልም የሚላቸውና ሌሎችም እምቢ እንዲሉ የሚያሳስብበት አንዳንድ የጌታን ዓላማ የሚቃወሙ ጥሪዎች አሉ። እነዚህንም በገላትያ መፅሀፉ ውስጥ ዘርዝሯቸዋል። እነርሱም፦ የሰዎች ምክር (1፥16)፣ እኔነት (2፥20)፣ በመንፈስ ጀምሮ በስጋ እንዲጨርስ የሚያባብል ጥሪ (3፥3)፣ የኢ-አማንያን ጉትጎታ (4፥17)፣ የስጋ ፍሬ (5፥16-21፡ 24) እና ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት መጣር (6፥12) ጥቂቶቹ ናቸው። የተጠቃቀሱትን ነገሮች ጠቅለል አድርገን ያየን እንደሆነ ከጌታ ጥሪ ውጪ ለሆነ ጉዳይ ራሳችንን እንድንሰጥ የሚወተውቱ፣ የአንዴ ሳይሆን የዘወትር ትግሎች ናቸው። ለዚህ ዻውሎስ ያስቀመጠው መፍትሔ፦ “ከክርስቶስ ጋር ለአለምና መሻቱ እንደሞተ በመቁጠር፣ ለእግዚአብሔር ሐሳብ ለመኖር በክርስቶስ ማመንን ነው”። አዎ እኛ በክርስቶስ ያመንን ሁላችን በአለም ውስጥ የምንኖር ብንሆንም ለአለም ሞተናል። ነገር ግን አለም ለእኛ አልሞተችምና በየእለቱ ልትቆጣጠረን መረቧን ትዘረጋለች። በራሳችን አቅም ደግሞ ልናሸንፋት አለመቻላችን ተስፋ አስቆራጭም የእምነትም ምክንያት ሆኗል። ተስፋ ቢስነት ራሱንና አቅሙን ተረድቶ ወደ ክርስቶስ ግን ሳይመጣ ለቀረና በአለም ለተዋጠ ነው። የእምነት ሰበብ የሚሆነው ደግሞ ወደ ክርስቶስ ለመጣ ነው። ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው ያ ቅዱስ መንፈስም፣ ለሚታመኑበት አለምን የማሸነፍያ ብርታትን ይቸራል (ሮሜ 8፥1-11፤ 1ኛ ዮሐ 4፥4)። እንግዲህ የሐዋርያውን ምስክርነት ካየን ዘንድ፣ ለእኔነት እምቢ ብለን የተሻለውን እንድንሆን ለሚያስችለን የክርስቶስ ፈቃድ ብንታዘዝ እናተርፋለን። የክርስቶስ ሐሳብ ጨርሶ ለፈቃዳችን ግድ የማይለው፣ ከራስ ወዳድነቱ የመነጨና ጨቋኝ ሳይሆን ምሉእነትን የሚያላብሰን ከጥልቅ እሳቤው የወጣ የሰላም እቅድ ነው (ኤር 29፥11)። ምንም እንኳን ለጊዜው የማይመች ተግሳፅም ቢሆን ራሱ ለጥቅማችን ነው (ዕብ 12፥5-6)። ስለዚህ ለጌታ አለሁ፣ ለአለም ግን የለሁም ማለት ይሁንልን። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ የተፈራህና የተወደድክ እግዚአብሔር አባት ሆይ፤ ላንተ እንድኖር በልጅህ ደም ስለገዛኸኝ፣ በመንፈስህም ስለቀደስከኝ አመሰግንሃለሁ። እንግዲህ ስለ እኔ በሞተልኝና አሁንም በሰማይ በአንተ ዘንድ ዋስትና በሆነልኝ በክርስቶስ እያመንኩ፣ በቃሉና በጸጋው እየተደገፍኩ፣ የዳንኩበትን ዓላማ ይኸውም ላንተ መኖሬ እውን እንዲሆን ራሴን እንድሰጥህ አድርገኝ። ለራሴ ሞቼ፤ ላንተ እንድኖር፣ አንተም በእኔ እንድትኖር እርዳኝ። በምትወደው ልጅህ ስም ጸለይኩ። አሜን! #የለሁም #ከክርስቶስጋርተሰቅያለሁ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
እንቅፋት🪨 አንድ በእድሜ የገፉ አገልጋይ፣ “ለአገልጋይ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?” ተብለው ሲጠየቁ፣ አራት ነገሮችን ጠቀሱ። እውቅና፣ ስንፍና፣ ገንዘብ እና ወሲባዊ ፍላጎት አሉ። እኔም እነዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ እንድንጠነቀቅ የሚያሳስበን፣ የክርስቲያን የእድሜ ልክ ጠላቶች ሆነው ስላገኘዋቸው ላጋራችሁ ወደድኩ። (ታዋቂነትን መሻት ፊል 2፥3-4፤ ስንፍና ኤር 48፥10፣ 2ኛ ተሰ 3፥10፤ ገንዘብ መውደድ 1ኛ ጢሞ 6፥10፤ ዝሙት 1ኛ ቆሮ 6፥18-20)። 📖 “ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” 1 ቆሮንቶስ 10:12 ⚠️ ተጠንቀቁ፣ እንጠንቀቅ! ጸጋው ይብዛልን🤗 #እንቅፋት ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ራሱን ያለ ምስክር የማይተው እግዚአብሔር፣ በተማሪዎች አገልግሎት የሰራውን ድንቅ ስራ የከተበ የ50 አመታት የታሪክ መፅሀፍ። ኑ አብረን እንመርቅ 🤗 ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ያለ እግዚአብሔር ልብ፣ ሐሳቡን ማገልገል እንደምን ይቻላል? ይህ ጥያቄ፣ ሰሞኑን የትንቢተ ዮናስ መፅሀፍን በቡድን ስናጠና፣ አንድ ወንድማችን የጠየቀው ነበር። እኔም ይህንኑ ሐሳብ ከጥናቴ ውስጥ ያገኘሁትን ትምህርት ለማካፈል ጥሩ መነሻ ስለሆነልኝ ለዛሬ ንባባችን መርጬዋለሁ። 📖 የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቷልና።” ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ኰበለለ … (ዮናስ 1:1-3) ዮናስ ከዛብሎን ነገድ የሆነ ዕብራዊ፣ እግዚአብሔርን የሚያመልክ፣ እውነተኛ ነብይ ነው (2ኛ ነገ 14፥23-25)። የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ ማሰማት የለመደው ዮናስ፣ በአንድ ወቅት ወደ ነነዌ ሂድ የሚል ትእዛዝ መጣለት። የተልዕኮው ዓላማም የአሦር ዋና ከተማ የሆነችውና የመቶ ሀያ ሺህ ሕዝብ መኖርያ የነበረችው ታላቅ ከተማ በርኩሰት ስለተሞላች፣ በንሰሐ እንድትመለስ ለማስጠንቀቅ ነበር። ዮናስ ግን ምክንያቱ ባልተገለፀ ጉዳይ ታዞ ለመሄድ አሻፈረኝ አለ። ከተላከበት በተቃራኒ አቅጣጫ በመርከብ ለመሄድ ገንዘብ ከፍሎ ጉዞውን ቢጀመርም፣ እግዚአብሔር ግን ማዕበልና ወጀብ አስነስቶ ከመንገዱ ገታው። ከእርሱም ጋር የነበሩትም፣ ጸሎትን ጨምሮ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው ቢያቅታቸው፣ ጥፋተኛውን ለመለየት እጣ ተጣጣሉ። እጣውም ዮናስ ላይ ወጣ፤ ስለዚህም የማዕበሉን መምጣት ምክንያት እንዲያስረዳ ጠየቁት። ዮናስም ባህርንና የብስን የፈጠረውን አምላክ እንዲያመልክ ተናግሮ፣ ላለመታዘዝ እንደኮበለለና የማዕበሉም መምጣት ምክንያት ይህ ስለሆነ፣ ወደ ባህር ቢጥሉት፣ ሞገዱ ፀጥ እንደሚል ተናገረ። ወደ አማልእክቶቻቸው ተጣርተው ምላሽ ያጡት እነዚህ ምስኪኖች፣ ከብዙ ማንገራገር በኋላ ዮናስ እንዳላቸው ቢያደርጉ፣ ወጀቡ ፀጥ አለ። ስለዚህም የዮናስን አምላክ ፈሩ፣ አከበሩትም። ዮናስ ግን ከመታዘዝ ሞትን መረጠ። ወደ ባህር የተጣለውን ዮናስ፣ ተረት በሚመስል ተአምር እግዚአብሔር ትልቅ አሳ አዘጋጅቶ፣ በነፃ ትራንስፖርት ወደ የብስ እንዲመለስ አደረገው። ዮናስም ከአሳው ሆድ ከወጣ በኋላ ወደታዘዘው አገር ለመሄድ ተስማማ። ቦታውም ላይ እንደደረሰ፦ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ (ዮናስ 3፥4)። ድምፁን የሰሙት ሁሉ ከንጉሱ እስከ ተራው ዜጋ፣ ብሎም እንስሳት ሳይቀር እንዲፆሙ፣ ማቅ እንዲለብሱ ተደረገ። በዚህም ሁኔታ በታላቅ ሐዘን ራሳቸውን አዋረዱ። ቀድሞም ከክፋታቸው እንዲመለሱ እንጂ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነብይ ያልላከላቸው መሐሪው እግዚአብሔር፣ ሊያመጣባቸው ካሰበው ጥፋት ተመለሰ። ኦው የነነዌ ሕዝብ! ምን አይነት የንሰሐ ልብ አሳዩ፣ እግዚአብሔርም የርህራሄ ባለጠጋ መሆኑ ተገለጠ። በዚህ አኳኃን ሰዎቹም ሆኑ እንስሳቶቻቸው ከሞት አፋፍ ዳኑ። እግዚአብሔር ይመስገን! ንሰሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል ይላል ቃሉ (ሉቃ 15፥7፡10)። አለመታደል ሆኖ፤ ዮናስ ግን ሰዎቹ ይቅር ሲባሉ ሊደሰት አልቻለም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ስለማይጠቅመን አልተፃፈልንም። ይልቁንም በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ነገር ለመከታተል ከከተማ ወጥቶ ሲጠባበቅ ያሳየናል። ሲጠብቅም ፀሐይ እንዳይጎዳው፣ ለራሱ ዳስ አዘጋጀ። ዮናስ ሰዎቹ ምህረት ሲያገኙ ከማየት ሞቱን የመረጠ ቢሆንም፣ ጌታ ግን ቸር አይደል? ዮናስን በዚህ ሁኔታ ሊተወው አልፈለገም። ይልቁን ልክ እንዳልሆነ ለማሳየት ብዙ ደከመ። ሊያስተምረውም፣ የቅል ዛፍ አበቀለ፣ ጥላም ስላገኘ ዮናስ ተደሰተ። እግዜር ግን ቅሏን አደረቃት፣ ዮናስ እንዴት ሲል? በቁጣ ነደደ። ብሞት ይሻለኛል አለ። ጌታም አንተ ለቅል አዘንክ፣ እኔ ታድያ መቶ ሃያ ሺህ ሕዝብ ለሚኖርባት ከተማ አልራራምን? ሲል ሞገተው። የዮናስን ምላሽ ሳያስቀምጥልን ልባችንን እንዳንጠለጠለ፣ ታሪኩ እዚሁ ላይ ተቋጨ። ዮናስ አምላኩን ጠንቅቆ ያውቃል፣ ድምፁን ይሰማል፤ ይህም በጸሎቱና በንግግሩ በግልጥ ይታያል። ነገር ግን አንድ ድካም አለበት። እርሱን ደስ ካላሰኘው የጌታውን መልእክት ለሌላው ለማስተላለፍ ልግምተኛ ነው። ሊያስተላልፍ ከሄደም በአምላኩ ልብ ሳይሆን፣ ነገሮች እርሱ እንደሚፈልጋቸው እንዲሆኑ በመሻት ነው። መልእክቱ የጌታ፣ ልቡ ግን የራሱ። ስንቶቻችን እንሆን ይህ የሚያሰቃየን? በአቋም ተቃርነን፣ ግን ለማገልገል የምንጥር። የልቡን ሳይሆን የልባችን እንዲሆን የምንታዘዝ። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ ቸር እግዚአብሔር ሆይ፤ እልፍ ጊዜ ካንተ የኮበለልኩ ብሆንም፣ በምሕረትህ ዳግመኛ እድልን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። አባት ሆይ፤ ያንተን ሐሳብ በሚቃረን ልብ እንዳላገለገል ለውጠኝ። ደግሞ ሌሎችን ስትምር፣ ስትረዳ፣ ስትባርክ እንዳልመቀኝ እርዳኝ። ይልቁን ጠላቴን የምወድበት አቅም ስጠኝ። እንደምትሰማኝ አምኜ፣ በክርስቶስ ስም ጸለይኩ። አሜን! #የአገልጋዩ_ልብ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ያለኝ ይበቃኛል 😌 በአለም ላይ የማይለወጥ ብቸኛ ነገር ለውጥ ብቻ ነው የሚል ታዋቂ አባባል አለ። ለውጥ ባለበት ደግሞ ነገሮች በአውንታዊ አልያም በአሉታዊ አቅጣጫ ይቀየራሉ። የሰው ልጅም ይህን ተፈጥሮ ጠንሳሽ ወይም ሰው ሰራሽ ለውጥ ተከትሎ ራሱን ለማላመድ ስልቶችን ይቀይሳል። በባይሎጂውም “Survival of the fittest” ይባል የለ፤ ደካማው ሲሸነፍ፣ ብርቱው በድል ይቀጥላል። የሰው ልጅ የሚታገላቸው ትግሎችም ተዘርዝረው የሚያልቁ ባይሆንም፣ ዛሬ ኑሮን ስለ ማሸነፍ የምናደርገውን ትግል በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ እንድንቃኘው ወድጃለሁና አብራችሁኝ ቆዩ። 📖 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።“ - 1 ጢሞ 6፥6-10 ሐዋርያው ዻውሎስ የወንጌል አጋሩና በእምነት ልጁ ለሆነው ጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመርያ መልእክት መጨረሻ ክፍል ላይ፣ ባለው ነገር ስለመርካት ይመክረዋል። ባለው ነገር የረካ፣ መንፈሳዊነት ማትረፊያው ነው። ትርፉ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ ወይም የማህበራዊ ጥቅማጥቅም ሳይሆን ዘለቄታ ያለው የውስጥ እርካታ ማግኘት ነው። ባለው ነገር የማይረካ፣ መንፈሳዊ ነገርን የሚፈልገው ጊዜያዊ ድርጎ(ትርፍ) ለማግኘት ነው። ይህ ደግሞ ወደ ባሰ ጥፋት ይመራል ይለዋል። ስራ መስራት፣ ቁጠባ፣ ኑሮን ማዘመን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው (1ኛተሰ 4፥10-11፤ ምሳ 6፥6-8፣ 24፥3)። ሐዋርያው ራሱ በገዛ እጆቹ እየሰራ ያገለግል ነበር (ሐዋ 18፥1-5)። ይህ የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ትጉህን እንደሚያበረታታ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ባለው ነገር የሚኩራራና እግዚአብሔርንም የሚረሳን ይነቅፋል። ባለጠጋ የመሆን ምኞትን ከሁሉም ነገር አስቀድሞ የሚፈልግን ያስጠነቅቃል፤ የሰው ነፍስ በሀብቱ ብዛት የተመሰረተ አይደለምና (ሉቃ 12፥15-21፤ 1 ጢሞ 6፥17)። «ያለኝ ይበቃኛል» ማለት በእግዚአብሔር መግቦትና ጥበቃ ላይ ማረፍ ነው። እርሱ የሚያስፈልገኝን ይሰጠኛል የሚል ጽኑ መተማመንና በዚሁ ተመስርቶ መሰማራት ነው። ማድረግ ሲችሉም ሆነ ሳይችሉ ያለኝ ይበቃኛል ማለት ነው። ባለን ነገር በመርካት፣ በምስጋና መመላለስ ነው። ምቹ ሁኔታዎች ከሚሰጡት የደህንነት ዋስትና ይልቅ አምላካችንን መደግፍ ነው (ፊል 4፥10-13)። አዳዲስ ግኝቶች ይመጣሉ፣ ዘመን ይዘምናል፣ ዛሬ አዲስ የሆነው ነገ ያረጃል። የሚቻል ቢሆን ሁሉ የሞላበት አለም ውስጥ ብንኖር መልካም ነው። ነገር ግን ኃጢአት ያበላሸው ይህ ምድር፣ ምሉእ የሚባል ሁኔታ የለውም። አንዱን ሲሰጠን፣ ሌላውን ይነጥቀናል። ጌታ መጥቶ ሁሉንም ለክብሩ ሲጠቀልልና አመጽን ሲቀጣ፣ ያኔ ግን ዘላለማዊ ምቾት ባለው ኑሮ ውስጥ ገብተን ንጉሳችን እናመልከዋለን። እስከዛው ድረስ፣ ዻውሎስ እንደመከረን ደስታችንን በሁኔታዎች ሳይሆን በጌታ ማድረግ ነው (ፊል 4፥4)። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ አባት እግዚአብሔር ሆይ፤ ዘማሪው ስለ ሐሳብህና ስራህ ሲዘምር፦ “ልቍጠራቸው ብል፣ ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር።“ እንዳለ፣ በቃላት ልገልጸው ስለማልችለው እልፍ ውለታህ አመሰግንሃለሁ። ደግሞ አምላኬ ሆይ፤ ልቤ በስጦታህ ረክቶ እንዲኖር፣ ያለኝ ይበቃኛል የሚል፣ ለስራም የተጋ፣ ለውጥን ካንተ በኋላ ያደረገ፣ የእድገቱን መለኪያ ደስታህን ያደረገ ሰው አድርገኝ። የመጣውን ሁሉ ሳሳድድ፣ እባክህ ዘመኔ አይለቅ። ለክብርህ እኖር ዘንድ ጸለይኩ። አሜን! #ይበቃኛል #እርካታ #ለውጥ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
እዘምራለሁ 🎶 ዝማሬ መልእክትን በግጥምና ዜማ፣ ውብ ድምፅ ባለው የሙዚቃ መሳርያ አጅቦ ማቅረብ ነው። ሰው በደስታ ሆነ በሀዘን፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ለአምላኩ ያዜማል። የውዳሴ፣ የምስጋና እና የንሰሃ ዘውጎች ደግሞ ታዋቂዎቹ ናቸው። የሕይወታችን መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስም የዝማሬ መጽሐፍ ነው። ለዛሬም ከዳዊት መዝሙር ውስጥ አንዱን እንመለከታለን። 📖 “ስለ ምሕረትና ስለ ፍትሕ እዘምራለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአንተ በምስጋና እቀኛለሁ።” መዝሙር 101:1 ምሕረት ለጥፋተኛ የሚቸር ይቅርታ ነው። ንጉስ ዳዊት ደግሞ ለእግዚአብሔር ምሕረት ምስክር ነው። የሰው ሚስት ነጥቋል፣ ባልየውንም አስገድሏል፣ በትዕቢት ተነፍቶ ብዙም ነገር አድርጎ ያውቃል። የራሱ ፅድቅ፣ በሕይወት ሆነ በንግስና እንዲቀጥል እንዳላደረገው ያውቃል። ስለዚህም የንሰሃ እድል የሰጠውን፣ እንደ ኃጢያቱ ያልከፈለውን፣ እንደበደሉ መጠን ያልመለሰለትን እግዚአብሔርን ደጋግሞ ያመሰግናል (መዝ 103፥3-13)። የእግዚአብሔር ምህረት ለወደቁ ተስፋ፣ ለደካሞች ብርታት፣ ለከርታቶች እርካታ፣ ለሀብታሞች ዘላለማዊ ዋስትና፣ ለድሆች አለኝታ፣ ለታናሹ ከፍታ፣ ለታላቁ ሞገስ፣ ለጀግኖች መኩርያ፣ ስም ለሌላቸው ክብር ነው። ምሕረቱ የኃጢአተኞች መጽደቅያ ብቸኛ መንገድ ነው። ምሕረቱ ሰውን ወደ ራሱ የሚያስጠጋበት የፍቅሩ ገመድ ነው። እግዚአብሔር መሐሪ ባይሆን ፍጥረት በፊቱ ሊቆም አይችልም፤ ምክንያቱም ፍጥረት በፊቱ ይቆም ዘንድ ንፁህ አይደለምና። ሁሉንም ስንፍና ይከሳቸዋል (ሮሜ 3፥23)። እናም ምሕረቱ የአምልኳችን መነሻ፣ የሕይወታችን መደላድል፣ የመኖራችን ምክንያት ነው። እግዚአብሔር መሐሪ ነው። ምህረትም ስሙ ነው (ዘጸ 34፥6)። ደግሞ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ለበተደሉ ይፈርዳል፣ የተገፉትን ይክሳል፣ የተጣመመን ፍርድ ያቀናል፣ ፍትህን ያሰፍናል። እግዚአብሔር ባያይ፣ ባይሰማ፣ አመፅን ባይቀጣ፣ ትክክለኛን ባያበረታታ፣ ምድር የሌቦች፣ ነፍሰ-ገዳዮችና ግፈኞች ዋሻ በሆነች። ግን እርሱ ወንበዴው እንዲመለስ፣ እልከኛው ንሰሃ እንዲገባ፣ ስግብግቡ ነጣቂ አደብ እንዲገዛ፣ ደም አፍሳሹ እንዲድን ስለሚሻ ይታገሳል (2 ዼጥ 3፥9)። መቼም ቢሆን በችኮላ አይፈርድም፤ ቢሆንም ለፍትህ አይዘገይም (ሉቃ 18፥7-8፤ ራዕ 22፥11-12)። “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።” (መዝሙር 85፥10) እግዚአብሔር ምህረት ሲያደርግ ፍትህ ማያዛንፍ፣ ጽድቅን ሲያሰፍን ፍቅሩን የማይረሳ ድንቅ አምላክ ነው። ምሕረትንና እውነት በአንድ ላይ ጠምዶ ምድርን ማስተዳደር የሚችል ጌታ ነው (መዝ 89፥14፤ ሚክ 7፥20)። ለዚህ ነው ንጉስ ዳዊት ደጋግሞ ስለ እግዚአብሔር ምሕረትና ፍትህ የሚዘምረው (መዝ 101)። ከመዘመርም አልፎ ተግባራዊ እርምጃዎችን ይወስዳል። ዛሬም እኛ እየዘመርን፣ እየኖርን፣ በፀሎት ልንለምነው የሚገባ ቀዳሚው ነገር፣ ምህረቱና ፍትሁ ምድርን እንዲከድን ሊሆን ይገባል (ምሳ 3፥3)። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ ስለ ምሕረትህና እውነትህ ብዙዎች ያመሰገኑህ ቢሆንም፣ እኔም ዛሬ አመሰግንሃለሁ። ትውልድ ሁሉ በአዲስ ቅኔ ቢዘምርልህ፣ ከቶ ስራህን ሊገልጽ አይችልም። ስለዚህ እገረማለሁ፣ እደነቃለሁ። አባት ሆይ ደግሞ ያካፈልከኝን ፍቅርህና ፍትህህ የሚኖር ነውና፣ እንድኖረው ጸጋ ይርዳኝ። አሜን! #ዝማሬ #መዝሙር ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
видео или голосовое, без подписи
National_Mission_Summit NMS2026 በመላው ኢትዮዺያ ከሚገኙ የክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረት (ፌሎሺፕ) የመጡ መሪዎች ጋር ለአምስት ቀን ታላቁን ተልዕኮ ማዕከል ያደረገ ከ1ኛ ዼጥሮስ “የመንግስቱ ተስፋ” በሚል የትምህርት ጊዜ እንዲሁም ልዩ ልዩ ስልጠናዎች፣ የውይይት፣ የፀሎት፣ የስእል አውደ-ርእይ፣ Camfire ጊዜ ነበረን። ተማሪዎቹ ከወንጌል ስርጭት፣ ከሚድያ፣ ከርህራሄ እና የንኡስ ቡድን አገልግሎት የተውጣጡ ነበሩ። ያለፈውን አመት ገምግመን፣ ጌታ ቢፈቅድ ለቀጣይ እንዲህ እናደርጋለን ብለን ተለያየን። እግዚአብሔር ይመስገን!!!! "ኢቫሱ (EvaSUE)፦ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ኅብረት፤ 'ተማሪዎችን በማገልገል የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋት' ዓላማው አድርጎ የሚሠራ አገራዊ መንፈሳዊ ተቋም ነው።" #የመንግስቱ_ተስፋ #HOPE_OF_THE_KINGDOM #National_Mission_Summit #Seeing #Living #Witnessing ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
እጆቼን አንሥቻለሁ 🤲 አብራም ግን ለሰዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፦ ‘እጆቼን አንሥቻለሁ’። እጅ ማንሳት የመማረክ ምልክት ነው። ሰው ከአቅሙ በላይ የሆነ ጉዳይ ሲገጥመው ሊረዳኝ ይችላል ብሎ ያሰበው አካል ላይ አይኖቹን ጥሎ፣ አንዳች ለመቀበል በሚጠባበቅ ልብ እጁን ይዘረጋል። የእምነት አባታችን በሆነው አብራም (በኋላ አብርሃም ተብሏል) ሕይወትም የሆነው ይህ ነው። 📖 ታሪኩ በመጽሀፍ ቅዱስ እንዲህ ሰፍሯል፦ “የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ “ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው። አብራም ግን ለሰዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ወደ ልዑል አምላክ (ኤል-ኤልዮን) እጆቼን አንሥቻለሁ፤ ‘አብራምን አበለጸግሁት’ እንዳትል፣ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አንዳች አልፈልግም።” - ዘፍ 14፥21-23 የዚህ ትረካ ጅማሮ እግዚአብሔር አብራምን ከሚኖርበት ዑር ምድር አውጥቶ ወደ ከነዓን እንዲሄድ ሲነግረው ነበር (ዘፍ11፥26)። በወቅቱ ለአብራም የመጣው ድምፅ ከወላጅ ቤተሰቦቹን ተለይቶ እንዲወጣ ነበር፤ እርሱ ግን የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ ወጣ(ዘፍ 12፥1)። ከዛም የኋላ ኋላ ንብረቶቻቸው ሲበዛ የከብት እረኞቻቸው መጣላት ስለጀመሩ ተለያይተው ለመኖር ይወስናሉ (ዘፍ 13፥6)። ነገር ግን አንድ ቀን ዘራፊዎች ሎጥንና ንብረቱ እንዲሁም በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ላይ አደጋ በመጣል ማርከው ይወስዱዋቸዋል (ዘፍ 14፥12)። አብራም ይህን ሲሰማ በቤቱ ያሉ አገልጋዮችን አስተባብሮ ሎጥንና ምርኮውን ያስመልሳል። በዚህም ወቅት ንብረትና ሰው ተማርኮበት የነበረው ሌላ ንጉስም አብራም ከጉዳት እንዳስጣለለት ባየ ጊዜ ሰዎቼን ስጠኝና ንብረቶቹን ውሰድ ይለዋል (ዘፍ 14፥21)። የአብራም ምላሽ ግን አስደናቂ ነበር። የአብራም መልስ የእምነቱን ጥልቀት ያሳየ ነበር፦ “አበለጸግሁት እንዳትል አንዳች አልፈልግም ነበር ያለው”። ምክንያት አድርጎ ያቀረበውም እኔ እጆቼን ወደ ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ዘርግቻለሁ ነው (ዘፍ 14፥22-24)። እኛም እነዚህን የመሰሉ አንዳንድ ወቅቶች ያጋጥሙናል። ታድያ ምላሻችን ምን ነበር? እግዚአብሔርን መጠበቅ ወይስ የሰውን እጅ ማየት? እግዚአብሔር ለአብራም ቤተሰብህን ትተህ ውጣ ሲለው፣ በዋናነት በጣኦት አምልኮ ከተበከለው ማህበረሰብ እንዲለይ እና እርሱን ብቻ እንዲያመልከው ነበር። በተጨማሪም ዘሩን እንደምድር አሸዋ እንደሚያበዛ፣ በእርሱ ምክንያት አሕዛብ እንደሚባረኩ ነግሮት ነበር። ታድያ ይህን ታላቅ ተስፋ በልቡ የያዘው አብራም ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንኳን አይኖቹን ከአምላኩ ሊያነሳ አልወደደም። መፅሀፍ ቅዱስ በአስቸጋሪ ወቅት እግዚአብሔርን ስለጠበቁ ቅዱሳን ብዙ ይናገራል። መዝሙረኛው ዳዊት እግዚአብሔርን ስለመጠበቅ ዘምሯል፦ “ዐይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረድኤቴ ከወዴት ይመጣል? ረድኤቴ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል (መዝሙር 121:1-2)። እንባቆምም ኤርምያስም ያደረጉት ይህን የመሰለ ነበር (ዕንባ 2፥1፤ ሰቆ.ኤር 3፥24-26)። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ፤ አቅም እንኳ እያለው የአባቱን ፈቃድ እንዲፈፀም አስቀደም እንጂ ሰዋዊ የሆነ ከችግር ማምለጫ መንገድ አልፈለገም ( ማቴ 26:51-54)። እኛ የምንፈተነው፣ እግዚአብሔር የተናገረንን እያለ፣ በሰውኛ መንገድ ለማለፍ፣ ለመበልጸግ፣ ከችግር ለማምለጥ፣ ወዘተ ስንሞክር ነው። 🙏 አብረን እንፀጸልይ፦ አባት እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፣ እድል ፈንታዬ፣ ዋስትናዬ ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። ጌትዬ ፅኑ መታመኛዬ የሆንክ፣ ሐይልህ ብዙ ሆኖ ሳለ ጠላቶችህ ግን የዋሹትን ምክር ሰምቼ የተፍገመገምኩበትን ጊዜ ይቅር በል። በመጠበቂያዬ ያልተገኘሁባቸውን አሳዛኝ ወቅቶች በምሕረትህ አስብ፣ ለድካሜም አሳልፈህ አትስጠኝ። ይልቁን አባ፣ እንደ አብራም አንተን በብርቱ የሚደገፍ ማንነትን ስጠኝ። ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁሉ ለስምህ ክብር ይሁን። አሜን! እንዲህ እንዘምር፦ ባይገባኝም እንኳን እቅዱ አንተ መልካም ነህ ሰዎች ሁሉ ለምን ቢሉህ አንተ መልካም ነህ ልቤ ጨክኗል ሊያመልክህ ወስኗል ኮስተር ብሎ መልካም ነህ ብሎሃል (2x) ልቤ ጨክኗል ሊያመልክህ ወስኗል ኮስተር ብሎ መልካም ነህ ብሎሃል (2x) #እርዳታ #መፍትሔ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ተመልካች ወይስ ተጫዋች? በአለም ዋንጫ ጨዋታ የማን ደጋፊ ናችሁ? ጊዜው የአለም ዋንጫ እንደመሆኑ ኳስ የሚወድ ሁሉ የቻለ ስታድየም ገብቶ ያልቻለ ደግሞ ቲቪውን ከፍቶ ጨዋታዎችን ይመለከታል። ደጋፊዎች የፈለገ ኳስ ወዳድ ቢሆኑም ግን ከመደገፍ ወይም ከመንቀፍ ባለፈ ገብተው ለመጫወት ሕጉ አይፈቅድላቸውም። የቡድናቸውንም ውጤት መለወጥ የሚችሉት ተጫዋች ከሆኑ ብቻ ነው። ለመጫወት ደግሞ ልምምድን ጠንክሮ መስራትና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማሟላት ይጠይቃል። በዚህም ምክንያት ተመልካች መሆን ቀላል፣ መጫወት ግን መስዋዕት መክፈልን በይበልጥ የሚፈልግ ሆኗል። 📖 ኢየሱስ እየተከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አለ፦ “… ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። … ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ ‘እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ? በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም’።” - ሉቃስ 7:26-32 እነዚህ ሰዎች እየተፈጠሩ የነበሩትን ሁነቶች ከመመልከት ያለፈ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጡ አልነበሩም። በመጥመቁ ዮሐንስ ሆነ፣ በኢየሱስ የቀረበውን መልእክት ሲሰሙ ያደረጉት ነገር፣ ልክ በለቅሶ ስፍራ እንዳለ ነገር ግን ሙሾ ሲሰማ እንደማያለቅስ፣ እንዲሁም በሰርግ እንደታደመ ግን በዘፈኑ እንደማይጨፍር ሰው አይነት ነበር። ማለትም ለመጣው የእግዚአብሔር መልእክት ልባቸው የደንዘዘ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ በብርቱ ነቅፎኣቸዋል (ሉቃስ 7:24-35)። ዛሬም በቤት፣ በቤተክርስቲያን፣ በማህበረሰብ እና በአገር ደረጃ እንዲህ አይነት ሰዎች መኖራቸው የሚያሳዝን ነው። የተበላሸውን የሚያስተካክል፣ የፈረሰውን የሚሰራ፣ የጠመመውን የሚያቀና፣ የሳተውን የሚመልስ፣ የተሰበረውን የሚጠግን፣ ለጠፋው የሚማልድ ጥቂት ነው። አብዛኛው ግን ልክ እንደኳሱ ግጥሚያ ደጋፊ፣ ሀሳብ ብቻ እየወረወረ፣ ጨዋታው ሲያልቅ ወደየጉዳዩ የሚሄድ ነው። ወይም ኢየሱስ እንደነቀፋቸው አይነት ሰዎች ጨርሶ ምንም ምላሽ የማይሰጡ ናቸው። በእርግጥ “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምራል፣ ሲይዙት ያደናግራል” እንደሚባለው ሳይሰሩ መተቸት ቀላል ቢሆንም ማድረግ ግን ከፍተኛ ጥረትን ቢጠይቅም፣ ተፅዕኖው የጎላ ነው። እኛስ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ውስጥ ያለን ሚና ምንድን ነው? ተመልካች ወይስ ተጫዋች? እንደ ሰራተኛ ወይስ እንደ ተቺ? 🙏 አብረን እንጸልይ፦ ጌታ ሆይ፤ በየወቅቱ ለሚመጣው ድምፅህ ምላሽ የሚሰጥ፣ ልቡ የተከፈተ ታዛዥ ሰው አድርገኝ። ደግሞም በልጆችህ ስትሰራ፣ ድካማቸውን እያወጣ ነቃፊ ተቺ ብቻ እንዳልሆን ይልቁን አብሬ እንድሰራ እርዳኝ። ስለምትሰማኝ አመሰግንሃለሁ። አሜን! ተጨማሪ፦ ያዕ 1፥22-25፤ ማቴ 9:37-38 ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ራስን ማሰልጠን 🏋️♂️ በዚህ ክረምት ራሳችሁን ምን ልታሰለጥኑ አሰባችሁ? 📖 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ «እግዚአብሔርን ከማያከብር ርባና ቢስ አፈ ታሪክና ከአሮጊቶች ተረታ ተረት ራቅ፤ ይልቁንም ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን። የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማልና፤ ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስን ማሠልጠን ግን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁለቱም ይጠቅማል።» 1 ጢሞ 4፥7-8 ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቁት፣ ጳውሎስ ወደ ልስጥራና ደርቤ ለወንጌል ተልእኮ በሚሄድበት ጊዜ ነው። ጢሞቴዎስ ግማሽ ጎኑ አይሁዳዊ ሲሆን፣ በአባቱ በኩል ደግሞ ግሪካዊ ነው። አያቱ ሎይድ እናቱ ኤውንቄ ሲባሉ፤ እነሱ የእግዚአብሔርን ቃል አስተምረውታል። በኋላም ጳውሎስ ለወንጌል ተልእኮ አብሮት እንዲሄድ ባሰበ ጊዜ፣ ከአይሁዳዊ ወገን ተቀባይነት እንዲያገኝ በማሰብ ጢሞቴዎስን ገረዘው(ሐዋ. ሥራ 16)። ከዚህ በኋላ በብዙ ቦታ ወንጌልን አብረው ሰብከዋል። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈለት ስለ ወንጌል ታስሮ ከተፈታ በኃላ መቄዶንያ(ግሪክ ውስጥ ያለች ከተማ) በነበረበት በእድሜው አመሻሽ ወቅት ነበር። ረዥም ጊዜ አብሮት ላገለገለው የወንጌል አጋር የጻፈለት መልእክት ይዘቱ ምን ይሆን? የጢሞቴዎስ መልእክት መጽሐፍ በአጠቃላይ «አደራ» የተሰጠበት፣ የአደራ መልእክት ነው (ም 1፥3፣ 6፥20)። ዓላማውም በኤፌሶን እያገለገለ የነበረው ጢሞቴዎስ፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንዲያውቅ ነው(3፥14-15)። ጳውሎስ ስለ ራሱ ሕይወት፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ እረኞችና ዲያቆናት መስፈርት፣ ስለ መበለቶች፣ ስለ ሽማግሌዎች፣ ስለ ባሪያዎች ስለ ብዙ ነገር ያነሳል። ከዚህ መሃል ነው የዛሬውን ሐሳብ እንድናይ የፈለግኩት። እሱም«እግዚአብሔርን መምሰል» ወይም «ለእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት ራስን ማሰልጠን» የሚል ነው። አስቀድመን ራስን ማሰልጠን ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ራስን ማሰልጠን ማለት አንድ ነገር ላይ እውቀት ወይም የሙያ ችሎታ እንዲኖረን በማሰብ ማንበብ፣ መጣጣር፣ መጠየቅ፣ በተግባር መለማመድና በተለያዩ መንገዶች ራሳችንን ለማብቃት(Qualified) የምናደርገው ጥረት ነው። ከላይ ባየነው ክፍልም ጳውሎስ እግዚአብሔርን መምሰልን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር ያወዳድረውና ልህቀቱን ያሳየዋል። ሁለቱም ትጋትን፣ መሰጠትን፣ ድግግሞሽንና ዋጋ መክፈልን ቢጠይቁም የአካል ብቃት ክህሎት ለዚህ ምድር ብቻ ሲሆን እግዚአብሔርን መምሰል ግን ለዚህም ለወዲያኛውም ይጠቅማል በማለት ይደመድማል። እንግዲህ እግዚአብሔርን ለመምሰል እርሱን ከማያስከብር እርባና ቢስ አፈ ታሪክና ከአሮጊቶች ተረት ተረት መራቅ እንዳለበት የሚነግረው። ይልቁን ታላቅ የሆነውን «እግዚአብሔርን የመምሰል ሚስጥር» ቁልፍ 🗝️ ይሰጠዋል። እርሱም ክርስቶስ ነው(3፥16)። እርሱ “ በሥጋ ተገለጠ፤ በመንፈስ ጸደቀ፤ በመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ ዘንድ ተሰበከ፤ በዓለም ባሉት ታመነ፤ በክብር ዐረገ።” እናም ቁልፉን የተቀበለው ጢሞቴዎስ፣ ዻውሎስ ወደ እርሱ ቶሎ ቢመጣ ወይም ቢዘገይ በተሰጠው አደራ የእውነት አምድና መሰረት የሆነችውን የህያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሊያስተዳድር ይገባዋል። ብሉይ ሆነ አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ውልደት፣ እድገት፣ አገልግሎት፣ ስቃይ፣ ሞት፣ ትንሳኤ፣ እርገትና ዳግም ምፅአት ብዙ ተናግረዋል። ምክንያቱም እርሱ የእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት ምንጭ ስለሆነ ነው። ጳውሎስ ሮሜ ላይ እንደዚህ ይላል፦ «እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው (ሮሜ 8:29)። እንግዲህ እግዚአብሔርን መምሰል በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እንደሆነ ግልጽ ነው። ስብከታችንም፣ ዝማሬያችንም፣ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ወደ እርሱ ሊያደርሰን ይገባል፤ካልሆነ ግን ከንቱ ልፋት ብቻ ይሆንብናል። ስለሆነም ራሳችንን ለመንፈሳዊ ሕይወት ማሰልጠን ከፈለግን ክርስቶስን እንየው፣ እንወቀው፣ እንከተለው፣ እንምሰለው። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ አባት እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን እንዳውቅህ፣ ካንተ ህብረት እንዲኖረኝ፣ ደግሞ እንድመስልህ ልጅህን ኢየሱስ እውነት፣ ሕይወትና መንገድ አድርገህ ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። እርሱን ለማወቅ እንድተጋ፣ ራሴን እንድገዛ፣ በፈተናዎች እንድጸና አግዘኝ። የልጅህ መልክ በኔ እንዲታይም ዘወትር መንፈስህን ሙላኝ። ሁሉ ሲሆን ኢየሱስ ይታይ፣ ቅዱስ መንፈስህ ይክበር፣ አባት ሆይ ስምህ ይጠራ። አሜን! #እግዚአብሔርን_መምሰል ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
ቃሉ ወይስ አገልጋዩ፡ ማነው መዛኙ? ⚖️ “በቃሉ በቂነት ሳይሆን በሰው ብቃት ላይ ስንታመን ለርግማን እንሰጣለን!” እርግማን ከጌታ ውጪ በሆነ ቁጥጥር ስር እንድንሆን ታልፎ መሰጠት ነው። ዋናው ገዢያችን እግዚአብሔር መሆኑ ይቀራል። ምልክቶቹም የመንፈሳዊ ርሃብ መደብዘዝ፣ የአገልግሎትን ግለት ማጣት፣ ፍቅረ-ንዋይን ማስቀደም፣ የህይወት ግብን መሳት፣ ኃይል ማጣት፣ ኃጢአትን አቅልሎ ማየት፣ ራስን አለመግዛት፣ አምልኮተ-ሰብዓ መጨመር፣ በሽታ፣ ኪሳራና ልዩ ልዩ አጋንንታዊ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የመሳሰሉት ናቸው። ዋናው ምክንያት ደግሞ በእግዚአብሔርና ከአፉ በወጣው ቃል ላይ ያለን መታመን መቀነስ ነው። 📖 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ “በሰው የሚታመን፣ በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው። … ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።” - ኤርምያስ 17፥5፡ 7 ነቢዩ ኤርምያስ በነበረበት ዘመን፣ እውነትን ከመናገር ይልቅ የሕዝቡንና የነገሥታትን ጆሮ የሚያሳክክ ትንቢት የሚናገሩ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ። እግዚአብሔር ሳይናገር፣ በስሙ የሚነግዱም ነበሩ። እነዚህ ነብያት ሆዳቸውን የሚያገለግሉ፣ በሰዎች ቁስል የሚሳለቁ፣ ለነገስታት የሚያሸረግዱ፣ ባዶ ተስፋ የሚሰጡ፣ እግዚአብሔርን ለሚንቁ ክፉ አያገኛችሁም የሚሉ፣ ሰላም ሳይሆን “ሰላም፣ ሰላም ነው” በማለት የሚሰብኩ ናቸው (ኤርምያስ 23፥9-21)። እውነተኞቹ ነብያት እና ሐዋርያት እንዲሁም የእምነት አባቶቻችን ግን አኗኗራቸው ሆነ አገልግሎታቸው በተገለጠው የእግዚአብሔር መልእክት ላይ የተመሰረተ ነበር። ማሳያውም ለቃሉ ጥናት የሰጡት ትኩረት (ሐዋ 2፥44)፣ ከብዙ የአገልግሎት ፍሬ በኃላ እንኳን ለምክክር መሰባሰባቸው (ሐዋ 15፥1-2)፣ ሲያጠፉ በቀላሉ መገሰጻቸው (ገላ 2፥14)፣ ሌሎች ቅዱሳን እንዲፀልዩላቸው መጠየቃቸው (ኤፌ 6፥19)፣ ድካማቸውን ለሌሎች ማስተማርያነት በማቅረብ ራሳቸውን ዝቅ ማድረጋቸው (ኤር 20፥7)፣ በከሳሾቻቸው ፊት እግዚአብሔር እንዲሟገትላቸው መፍቀዳቸው (ዘኅ 12፥1)፣ ቃሉ የሚለውን ለመኖር የቆረጡ ነበሩ (ገላ 1፥7) እና የሌላውን ምክርና እገዛ ይቀበላሉ (ዘፀ 17፥12)። እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት በራሳቸው ብቃት ላይ ሳይሆን በፀጋው ቃል ላይ ያላቸውን መታመን ነው። እንግዲያስ ቀደምቶቻችን በቃሉ ታምነው ከኖሩ፣ ታድያ እኛ እንዴት ደካማውን ሰው እንታመን? እነርሱ ለመጣው የእግዚአብሔር ድምፅ ኖረው ታሪካቸው በመልካም ከሰፈረ፣ እኛ ለምን አዲስ መሰረት እንመሰርታለን? ቃሉ ከአገልጋዩ የሚበልጥ ከሆነ፣ እንዴት ቃሉን ችላ ብለን እንግዳ መገለጥ ፍለጋ እንከራተታለን? እንዲህ ያደረግን ጊዜ ከምን አይነት ክብር እንደምንወድቅ በተገነዘብን። እናም ወገኔ ሆይ፤ ለሁላችን የሚበጀን ቃሉን የሕይወት ጥራት፣ የኑሮ እቅድና የአገልግሎት ስኬት መለኪያ ማድረግ ነው። ምክንያቱም የተፃፈው ቃል በቂ፣ ብቁ፣ ግልጽና የማይለወጥ እውነት ስለሆነ ነው። ዋናው ጉዳይ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ፍፁም ሰው ሳይሆን ፍፁም ቃል እንዳለን አውቆ መኖር ነው። ሕይወት የሚመራው በአገልጋይ ሳይሆን በሕያው የእግዚአብሔር ቃል ነውና። 🙏 አብረን እንጸልይ፦ አባት እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰጠኸኝ ሕይወት የሚቀጥለው ካንተ በሚሆን መግቦት ስለሆነ አመሰግንሃለሁ። አይኔን ካንተ አንስቼ በስጋ ለባሽ ላይ በማድረግ ጎስቋላ ኑሮ እንዳልኖር እርዳኝ። ቃልህን በማስቀደም፣ መከተል ይሁንልኝ። አሜን! #ቃሉ ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn
አቋርጦ መውጣት ‘Incomplete’ ያሰጣል! በትምህርት አለም ውስጥ ፈተና ከበደኝ ተብሎ ተትቶ አይወጣም። አቋርጦ ለሚወጣ ግን መልሶ ያንን ትምህርት ለመማር ይገደዳል፤ ምክንያቱም በሴሚስተሩ መጨረሻ ላይ ውጤቱ ያልተሞላ ስለሚሆን (Incomplete) ነው። በመንፈሳዊው አለምም እንዲሁ ነው። 📖 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፦ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” - ያዕቆብ 1:12 ቅዱስ ያዕቆብ መልእክቱን መጻፍ የጀመረው ስለፈተና መልካም ጎን በማውራት ነው (ያዕ1፥2)። እምነታችሁ ሲፈተን ትዕግስትን ትማራላችሁ፤ ደግሞ ፍፁማን ትሆኑ ዘንድ ትሰራላችሁ ይላቸዋል። አስከትሎም በእምነቱ ምክንያት ሲፈተን የሚፀና የተባረከ ነው፤ እግዚአብሔርንም ለሚወዱ የተዘጋጀውን የሕይወትን አክሊል እንደሚያገኝ እያበሰረ ያበረታታቸዋል። ዛሬም ከእናንተ ጋር ለማየት የመረጥኩት ርእሰ-ጉዳይ ይህንን ነው። ክርስትና እንደስሙ የክርስቶስን ፈለግ መከተል ነው። ማለትም እያንዳንዱ ሰው የራሱን መስቀል ሊሸከም የግድ ነው(ሉቃ 9፥23)። በእርግጥ በዚህ ዘመን ስለ ፈተና መስበክ፣ መፃፍ ሆነ መልእክትን በልዩ ልዩ መንገድ ማስተላለፍ “ኃላ ቀር” አድርጎ ቢያስቆጥርም፤ መጽሐፋችን ግን ክርስትናን ከመስቀል አይለየውምና ስለዚህ መማር አስፈላጊ ነው። ዘመኑ ሊያዳምጥ የሚሻው መስቀል አልባ ኑሮን ቢሆንም የእምነት መፈተን በመንፈሳዊ ብስለት የማንለውጠው እውነታ ነው። ስለዚህ ቅዱሳት መጽሐፍት ስለ ፈተና ከሚሰጡን ብርቱ ተስፋዎች መካከል ጥቂቶቹን እንይ፦ • 🛡️ እግዚአብሔር ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም። 1 ቆሮ 10፥13 • 🔑 የምንፈተነው እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ መሆናችን እንዲረጋገጥ ነው። መዝ 105፥19 • 💝 እግዚአብሔር በክፉ ዓላማ(ሊጎዳን) አይፈትነንም። ያዕ 1፥13 • 🏆 በፈተና ውስጥ አልፎ ድል ለነሳ የተዘጋጀ ሽልማት አለ። ራዕ 7፥13-17፤ ዕብ 12፥1-4 • 💪 ከሁሉ በላይ ከኃጢአት በቀር፣ እንደኛ በነገር ሁሉ የተፈተነ ሊቀካህን ስላለን፤ በፈተናችን ወቅት ሊረዳን ይችላል። ዕብ 2፥18፣ 4፥14-16 እናም ይሄ ሁሉ ተስፋ እያለን ብናፈገፍግ፣ ጌታ በዚህ ደስ አይሰኝም (ዕብ 10፥38)። በተጨማሪም የተሰጠንን ፈተናም ካልጨረስን ሌላ ጊዜ በሌላ መልኩ እንድንወስድ እንገደዳለን፤ ይህ ደግሞ አድካሚና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነው። እስራኤላውያንም በምድረበዳ የእምነትን ፈተና ባለማለፋቸው የሆኑት እንዲህ ነበር፦ የቀናት መንገድ አርባ አመት ፈጀ (ዘዳ 8፥2)። ‼️ ስለዚህ ሁለት ነገር ልብ እንበል፦ አንደኛ፡ በምናልፍበት መንገድ ያጋጠመን መከራ ጽድቅን ከመምረጣችን የተነሳ የመጣ ወይስ በጥፋታችን? ሁለተኛ፡ ስለ እውነት የምንቀበለው መከራ በዚህ ምድር የሚገባንን ካሳ ላንቀበልለት ስለምንችል፣ ለላቀው ከክርስቶስ እጅ ለምናገኘው አክሊል እንጽና። 🙏 አብረን እንጸልይ እግዚአብሔር ሆይ፤ በእውነት አንተ ቅዱስና ሩህሩህ አባት ስለሆንክ በመታመን አመልክሃለሁ። ከቅድስናህ የተነሳ በሚያጋጥመኝ ፈተና፣ ተገቢውን ብድራት ስለምትሰጠኝ፣ ደግሞም ስለ ምህረትህ ስትል ከምችለው በላይ እንድፈተን ስለማትፈቅድ አመሰግንሃለሁ። በዚህ ጽኑ መሰረት ላይ ተደላድዬ እንድኖር ጸጋህን አብዛልኝ። በምትወደው ልጅህ በክርስቶስ ስም ጸለይኩ፣ አሜን! ለሌሎች ለማጋራት 👇👇👇👇 @AbrhamSetegn