Wazema Media / Radio
СтатистикаWazema is Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
- Последний пост
- 04:29
- Последнее чтение
- 14:45
- Постов за неделю
- 11
- Всего постов
- 49
- Тип
- открытый
- Язык
- английский
- Категория
- Новости и СМИ (по похожим)
- В каталоге с
- 13 авг.
- 1/24сутки в ленте
- 11 951
- 1/48двое суток
- 13 695
- 1/72трое суток
- 14 771
Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.
Посты
ምክክሩን በቶሎ የማጠናቀቅ ዕቅድ መኖሩ እየተነገረ ነው የኮሚሽኑ ምክር ቤት የምክክር ጉባኤውን ቶሎ ለማጠናቀቅ መወሰኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ በምክክር ስልቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነውን የ12 ቀናት ጊዜ እንደሚወስድ ታቅዶለት የነበረው የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲታጠፍ መደረጉን ገልጠዋል። የምክክሩ 34 ኛ ቀን ዘገባችንን ያንብቡት- https://cutt.ly/VydaSGPB
የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት እስከ 60 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል ተረድታለች። ዝርዝሩን ያንብቡት-- https://cutt.ly/CydaSvxj
#Newsalert አብን፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁለት ኮሚሽነሮች በምክክር ጉባኤው በተለይ በከተሞች አጀንዳ ውስጥ እጃቸውን በቀጥታ በማስገባት የተሳታፊዎችን ፍላጎት "ለማስቀየር" እና "ተጽዕኖ ለማሳደር" ሙከራ አድርገዋል በማለት ከሠሠ። ፓርቲው፣ ኮሚሽኑ መሠረታዊ ሥጋቶቹንና ቅሬታዎቹን "አቅጣጫ የሚያስቱ" እና "ተጨባጭ" እና "ተደጋጋሚ" አቤቱታዎቹን ከግንዛቤ ያላስገባ ምላሽ ዛሬ ሠጥቷል ሲል ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ወቅሷል። ፓርቲው፣ ኮሚሽኑ ያቀረብነውን ቅሬታ "አጠቃላይ የሂደት ክፍተት" አስመስሎ ለማቅረብ ሞክሯል በማለት ጭምር ተችቷል። ኮሚሽኑ የመደባቸው አንዳንድ ባለሙያዎች "አድሏዊ" እና "ተገቢ ያልሆኑ" ሀሳቦችን ሲያራምዱ ነበር ያለው አብን፣ የተወሰኑ አስተባባሪዎች ደሞ የፓርቲው ተወካዮችና ሌሎች ተሳታፊዎች መሠረታዊ አቋሞቻቸውንና ሀሳቦቻቸው እንዳያቀርቡ "በስልታዊ" መንገድ አፈና ሲፈጽሙ ነበር በማለት ከሷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ፣ ነሃሴ 11፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ከአማራ ክልል ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ተከስሰው በእስር ላይ የሚገኙ በርከት ያሉ ታሳሪዎች መንግሥት ያቀረበላቸውን በቅድመ ሁኔታ የታሠረ የይቅርታ መጠየቂያ ሠነድ መፈረማቸውን ዋዜማ ሠምታለች፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ክርሰቲያን ታደለን፣ ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይንን ጨምሮ በርካታ እስረኞች የይቅርታ መጠየቂያ ሠነዱን እንደሞሉ ምንጮች ነግረውናል። አምስት ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ጨምሮ 30 ያህል እስረኞች ግን ሠነዱን 'አንፈርምም' ማለታቸውን ተረድተናል። ሠነዱን አንፈርምም ካሉት መካከል፤ የአማራ ክልል ምክር አባሉ ዮሐንስ ቧያለው፤ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው፣ ዶ/ር ወንደወሠን አሠፋ፣ መስከረም አበራ እና ጎበዜ ሲሳይ ይገኙበታል ተብሏል። የይቅርታ ሠነዱን እንዲፈርሙ የቀረበላቸው እስረኞች 300 ገደማ እንደሚጠጉ ታውቋል፡፡ 2፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ አብን የምክክር ጉባኤው "አካታች" እና "አሳታፊ" አይደለም በማለት ያቀረበውን ትችት ውድቅ አደረገ። ኮሚሽኑ፣ አብን ባቀረባቸው ቅሬታዎች ላይ ምርመራ ማድረጉን ጠቅሷል። ከአብንም ኾነ ከሌሎች የተለያዩ አካላት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሠጠ እንደሚገኝ የጠቀሠው ኮሚሽኑ፣ አብንም ኾነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀሪው የምክክር ሂደት ላይ በንቃት እንዲሳተፉና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ እንዲተባበሩ ጠይቋል። ኾኖም አብን የምክክር ሂደቱ በገዥው መንግሥት ተጽዕኖ ሥር እንደወደቀና የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምጽ በአግባቡ ሳይወከል በከተማዋ ላይ ያንድ ወገን ፍላጎት ለማስፈጸም ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን ጨምሮ በምክክር ሂደቱ ዙሪያ ቅዳሜ'ለት ባወጣው መግለጫ በዝርዝር ላቀረባቸው በርካታ ቅሬታዎች ኮሚሽኑ ዝርዝር ምላሽ አልሠጠም። 3፤ የፌዴራሉ መርማሪ ፖሊስ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ባላቸው የኢሕአፓ አባላት ይስሐቅ ወልዳይ፣ አበበ አካሉ እና ጠበቃ አበራ ንጉስ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ዘይሴ ወረዳ ታጣቂዎችን አደራጅተዋል የሚል አዲስ ክስ አቀረበ። የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፣ ፖሊስ በቀድሞው የምርመራ መዝገቡ ያልተካተተ አዲስ ክስ ማቅረቡ ተቀባይነት የለውም በማለት ዛሬ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አስረድተዋል። መርማሪ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቴክኒክ መረጃዎች መቀበሉን፣ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤቶችን በደብዳቤ መጠየቁንና የአንድ ምስክር ቃል መቀበሉን ዛሬ ለችሎቱ ያስረዳ ሲሆን፣ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከመንግሥትና ከግል ባንኮች እንዲኹም ከመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ሠነዶችንና የቴክኒክ ማስረጃዎችን መቀበል እንደሚቀረው ገልጧል። ችሎቱም፣ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 12 ቀናት ፈቅዷል። 4፤ ትምህርት ሚንስቴር፣ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ፕሬዝዳንቶች ግልጽ፣ ፍትሐዊና ተወዳዳሪ በኾነ መንገድ በብቃት ላይ በተመሠረተ መስፈርት ለመምረጥ ያዘጋጀውን አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። ሚንስቴሩ፣ በመጀመሪያው ዙር፣ ለወልድያ፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሰላሌ፣ መቱ፣ ወልቂጤ፣ ድሬዳዋ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወራቤ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች የፕሬዝዳንትነት ቦታዎች በአዲሱ የውድድር መመሪያ መሠረት ከነሃሴ 15 ጀምሮ ለውድድር ክፍት መኾናቸውን ዛሬ አስታውቋል። ውድድሩን የማስፈጸም ኃላፊነት የየዩኒቨርሲቲዎቹ ቦርዶች ኃላፊነት መኾኑን የጠቀሠው ሚንስቴሩ፣ በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ፍላጎትና ብቃት ያላቸው ግለሰቦች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል። 5፤ ጎጎት ፓርቲ፣ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ሥር በዋሉ ሦስት ግለሰቦች ላይ በቅርቡ የፈጸሙት ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ። ፓርቲው፣ መንግሥት በጉራጌ ዞን ጸጥታ ኃይሎች ስነ ምግባር፣ ገለልተኛነትና ብቃት ላይ ግምገማ ሊያደርግ እንደሚገባም ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። በጉራጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የታጠቁ አካላት የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ለመከላከል መደበኛ የጸጥታ ኃይሎችን የሚያግዙ ወጣቶችን በማሠልጠን እንዲያስታጥቅም ፓርቲው ጥያቄ አቅርቧል። ፓርቲው፣ የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ባልቻሉ የፖለቲካ፣ ጸጥታ እና የደኅንነት አካላት ላይ ተጠያቂነት ሊሠፍን እንደሚገባ አሳስቧል። 6፤ የኢትዮጵያ አዋሳኝ የሆነችው የሳውዝ ዌስት ፌዴራል ግዛት የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲአዚዝ ላፍታግሪን ታማኝ ታጣቂዎች በባይደዋ ከተማ ላይ ዛሬ ጧት መጠነ ሠፊ ጥቃት ከፈቱ። በከተማዋ በታጣቂዎቹና በፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት እንደተካሄደና ሲቪሎችና የሁለቱ ወገኖች ተዋጊዎች እንደተገደሉ የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ታጣቂዎቹ ከተማዋን ከፌደራሉ መንግሥትና ከአጋሮቹ ኃይሎች አስለቅቀን ተቆጣጥረናል ማለታቸውን የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ ፌዴራል መንግሥቱ ግን ማስተባበሉን አመልክተዋል። የፌዴራል መንግሥቱ ኃይሎች ባለፈው መጋቢት ወር ባይደዋን በኃይል ተቆጣጥረው፣ ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ማባረራቸውና አዲስ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ማስሾማቸው አይዘነጋም። በቀድሞው የግዛቲቷ መንግሥት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ግጭት የተቀሠቀሠው፣ የግዛቲቱ ፕሬዝዳንት ፌደራል መንግሥቱ ያጸደቀውን የቀጥተኛ ምርጫ ሥርዓት ውድቅ በማድረግ ቀጥተኛ ባልኾነ የምርጫ ሥርዓት በድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎ ነበር። እንዲኹም፤ 1፤ የቡሄ በዓልን ምክንያት በማድረግ ነሃሴ 12 ቀን ከእንጦጦ እስከ ቀበና በነጻ የከተማ ጉብኝት ተዘጋጅቷል። 100 ተጓዦችን የሚያሳትፈው ጉብኝት፤ የእግር ጉዞን፣ ባሕልን፣ እደጥበብንና የከተማ ምኅዳርን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ በዕለቱ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ጀምሮ መነሻውን አራት ኪሎ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ያደርጋል ተብሏል። 2፤ "ጃዝ ቲዩስዴይ" የተሠኘ የጃዝ (ብሉዝ እና ፈንክ) ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ዝግጅት በየሳምንቱ ማክሰኞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ባዝራ ኮፊ (BazraCoffee) ይካሄዳል።[ዋዜማ]
#NewsAlert አብን፣ በምክክር ጉባኤው የታየው ግድፈት "ከተራ የአሠራር ግድፈት" ወይም "ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት" የዘለለ ነው አለ። ፓርቲው፣ የምክክሩን "ተዓማኒነት"፣ "አካታችነት"፣ "ገለልተኝነት" እና "ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ "ተደጋጋሚ" እና "የተደራጁ "ጥፋቶች ተፈጽመዋል በማለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ተችቷል። በምክክሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ድምጽና ፍላጎት ባግባቡ ሳይወከልና እንደ ዋና ባለቤት ሳይቆጠር መታለፉ "እጅግ አሳሳቢ" ነው ያለው ፓርቲው፣ የከተማዋ ተወካዮች የአንድን ወገን "ያልተገራ" እና "ድንበር የለሽ" ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ የነዋሪዎችን መብትና ጥቅም አሳልፈው ሠጥተዋል በማለት ወቅሷል። ፓርቲው በምክክሩ ላይ የታዩ ጥሠቶች ካልታረሙ፣ ለውጤቱ ፈጽሞ እውቅና እንደማይሠጥና እንደማይተባበር አስታውቋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ነሃሴ 9፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የደስተኛ ሕይወት ጣሪያ ላይ ለመድረስ በነፍስ ወከፍ የሚያስፈልገው አማካይ ገቢ ከ123 አገራት ዝቅተኛው መኾኑን አንድ ጥናት አመለከተ። ኢትዮጵያ ውስጥ ደስተኛ ሕይወት ለመኖር 10 ሺሕ 176 ዶላር ገቢ እንደሚያስፈልግ ሪሚትሊ የተባለ ዓለማቀፍ ኩባንያ ባደረገው ጥናት ገልጧል። ናይጄሪያና ሩዋንዳ ከ15 ሺሕ ዶላር በታች በኾነ ገቢ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል። ከአፍሪካ ከፍተኛው 59 ሺሕ 675 ዶላር ገቢ የተመዘገበባት ግብጽ ስትኾን፣ በጥናቱ የተካተቱት 32 የአፍሪካ አገራት አንዳቸውም ከ100 ሺሕ ዶላር ገቢ አልደረሱም። በአገራት መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዲታይ አስተዋጽዖ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ ዶላር መግዛት የሚችለው ምርትና የውጭ ምንዛሬ ተመን መለያየት ተጠቅሠዋል። 2፤ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ በንጹሃን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ላይ "አፋጣኝ"፣ "ገለልተኛ"፣ "ግልጽ" እና "አስተማማኝ" ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ። ሐምሌ 24 ቀን በጉራጌ ዞን፣ አበሽጌ ወረዳ፣ ናቻ ቁሊት ቀበሌ "ፋኖ ናችሁ" በሚል ሰበብ በሦስት ወጣቶች ላይ ተፈጸመ የተባለውን ግድያ ያወገዘው ትብብሩ፣ ሕዝቡ በመጪው ማክሰኞ የወጣቶቹን "የዘፈቀደ" ግድያና በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ተመሳሳይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች "የንጹሓን የግፍ ግድያ ይብቃ" በሚል መሪ ቃል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ እንዲያወግዝ ጠይቋል። ትብብሩ፣ የወጣቶቹን ግድያ አስፈጽመዋል ያላቸው አካላት "የማናለብኝነት" መግለጫ መስጠት ያቁሙ በማለት አሳስቧል። 3፤ በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ በሕገወጥ የሐዋላ ንግድና የሰዎች ዝውውር ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሕገወጥ ተግባራት በአስቸኳይ ይቆጠቡ ሲል አስጠነቀቀ። ኢምባሲው፣ ሕገወጥ ደላሎችና በሕጋዊ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ኤጀንቶች የሐሰት የሥራ እድል በመስጠትና ያልተገባ ክፍያ በመቀበል ዜጎችን ለአደጋ ዳርገዋል ብሏል። ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ የሚልኩ ግለሰቦች ሕጋዊ የባንክ የሐዋላ ብቻ እንዲጠቀሙና ሠራተኞችን በሕጋዊ መንገድ እንዲያስመጡ ያሳሰበው ኢምባሲው፣ ይህ ካልሆነ ግን የሁለቱ አገራት የሕግ አካላት በቅንጅት ርምጃ መውሠድ ይቀጥላሉ ሲል አስጠንቅቋል። ሁለቱ አገራት ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠትና የሕግ ትብብር ስምምነት አላቸው። 4፤ ኡጋንዳ ወታደሮቿ ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ ሶማሊያ ውስጥ እንደሚቆዩ የአገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር ኪርዮዋ ኪዋኑካ ተናገሩ። ኡጋንዳ ከኅብረቱ ተልዕኮ ውጪ ሶማሊያ ውስጥ በሁለትዮሽ ስምምነት የሠፈሩ ሁለት ሺሕ ወታደሮች እንዳሏት ከወታደራዊ ምንጮች መስማቱን ጠቅሶ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል። መከላከያ ሚንስትሩ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ግብጽም፣ በአውሮፓዊያኑ 2027 ወታደሮቻቸውን ሶማሊያ ውስጥ ማቆየት እንደሚፈልጉ እንደሚያውቁ ተናግረዋል ተብሏል። አሜሪካ ከቀጣዩ ዓመት አጋማሽ በኋላ የኅብረቱን ተልዕኮ በገንዘብ መደገፍ አቆማለሁ ማለቷን ተከትሎ፣ የተልዕኮው ዕጣ ፋንታ አጠያያቂ ኾኗል። 5፤ ኬንያ፣ በአጎዋ የቀረጥ ነጻ ዕድል ሽፋን የቻይና ምርቶችን መልሳ በማሸግ ወደ አሜሪካ ሳትልክ አትቀርም የሚል ጥርጣሬ እንዳላት አሜሪካ ገለጠች። የቻይና ኩባንያዎች የኬንያን ርካሽ ጉልበትና የወደብ አገልግሎት ለመጠቀም ሲሉ ምርታቸውን ወደ አገሪቱ ሳይዛውሩ እንዳልቀሩ ሰሞኑን የወጣ አንድ የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት አመልክቷል። ኬንያ በዚህ ድርጊት መሳተፏ ከተረጋገጠ፣ ማዕቀብና ታሪፍ ሊጣልባት ወይም ከአጎዋ ልትታገድ እንደምትችል አሜሪካ አስጠንቅቃለች። የአሜሪካ መንግሥት በቻይና ግብዓቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ ሶላር ፓነሎች በቻይና ምርቶች ላይ የተጣሉ ታሪፎችን በመተላለፍ ወደ አሜሪካ ይላካሉ በሚለው ውንጀላ ላይ ምርመራ ሊጀምር መኾኑን በቅርቡ መግለጡ አይዘነጋም። እንዲሁም:- 1."ደበብ ያለ ጨዋታ" የተሰኘ ጥበባዊ ዝግጅት ነገ እሑድ ነሐሴ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ጀምሮ በኢዩቤልዩ ቤተ-መንግሥት ግቢ (አዲስ የባህልና ጥበብ ተቋም) ውስጥ ይካሄዳል። 2.በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ የሚገኘው የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሠቢያ ቤተ-መጽሐፍት በዚህ ሳምንት የ60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ተከብሯል። በበዓሉ አከባበር የአሜሪካ ኤምባሲ ለቤተ-መጽሐፍቱ እድሳት የሚውል 235 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የእድሳት ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር ተገልጿል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ፣ ነሃሴ 8፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በምክክር ጉባኤው፣ ከስምንቱ የሥራ ቡድኖች የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫ መካሄዱን ዋዜማ ሠምታለች። ከአንድ የሥራ ቡድን 15 የማረጋገጫ ቡድን አባላት ከሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ከፌደራል መንግሥት መውጣጣት ቢኖርባቸውም፣ ከአንድ ቡድን እስከ አምስት የሚደርሱ ከአንድ ክልል የተወከሉ ተመካካሪዎች የተመረጡበት ሁኔታ መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል። የኮሚሽኑ ሃላፊዎች፣ ምክረ ሀሳቦችን በመመሪያው መሠረት በ75 በመቶ ድምጽ ማስወሠን ጉባኤውን ችግር ላይ ይጥለዋል የሚል አቋም እንዳላቸውና በአከራካሪ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ያልደረሱ የሥራ ቡድኖች መኖራቸውንም ምንጮች ነግረውናል። ስምምነት ያልተገኘባቸው ምክረ ሀሳቦች በምን አኳኋን መፍትሄ እንደሚያገኙ ኮሚሽኑ እስካሁን አልገለጠም። 2፤ ኢትዮጵያና ማላዊ፣ የሰዎች ፍልሠት ወንጀልን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። የመግባቢያ ስምምነቱ፣ ሁለቱ አገራት በፍልሠት አስተዳደርና በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በመከላከል፣ የሰው አዘዋዋሪዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግና ለሰው ዝውውር ሰለባዎች ጥበቃ በማድረግ ዙሪያ እንዲተባበሩ የሚያስችል ነው። ሁለቱ አገራት ለስምምነቱ ተግባራዊነት የጋራ ኮሚቴዎችን ለማቋቋምና መደበኛ ስምምነቶችን ለመፈራረም ንግግራቸውን እንደሚቀጥሉ ፍትሕ ሚንስቴር ገልጧል። ማላዊያን፣ በአዲስ አበባ በኩል በሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚጓዙ ከአገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። 3፤ በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ፣ በጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ በ"'ጽንፈኛ ፋኖ'" ታጣቂ ቡድን ላይ እርምጃ ወስጃለሁ አለ። ፖሊስ፣ ታጣቂ ቡድኑ የሠላማዊ ሰዎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ለማስተጓጐል ሙከራ ሲያደርግ ነበር ብሏል። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ባሰባሰበችው መረጃ፣ ታጣቂዎች ባለፈው ማክሰኞ በወረዳው መቀመጫ አንገር ጉቴ ዙሪያ በከባድ የጦር መሣሪያዎች በከፈቱት ተኩስ፣ ቢያንስ 20 ንጹሃን ሕይታቸው ማለፉን ሠምታለች። ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሠባቸው ተጎጂዎችም ወደ ሕክምና ተቋማት መወሠዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል። 4፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ)፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሽብር የተከሰሱ አምስት ጋዜጠኞች በይቅርታ ከእስር ለመውጣት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ቀውስና ለጠፋው የሰው ሕይወት "ይቅርታ" እንዲጠይቁና "ኃላፊነት" እንዲወስዱ ግፊት እያደረጉ ነው በማለት ወቀሠ። ቡድኑ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና ዓባይ ዘውዱ ራሳችን ጥፋተኛ አድርገን የይቅርታ ደብዳቤ አንጽፍም ማለታቸውን ከጠበቃቸው መስማቱን ጠቅሷል። ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት ውስጥ የካዱትን የወንጀል ክስ አሁን እንዲያምኑ ባለሥልጣናት እያስፈራሯቸው ነው ያሉት የቡድኑ የአፍሪካ ኃላፊ ሙቶኪ ሙሞ፣ ባለሥልጣናት ጋዜጠኞቹን ከማዋረድና እጃቸውን ከመጠምዘዝ እንዲቆጠቡ፣ ክሱን እንዲያነሱና ከእስር እንዲለቋቸው ጠይቀዋል። 5፤ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ላይ ይፈጽመዋል ያለውን ማዋከብ እንዲያቆም ጠየቀ። ተቋሙ፣ የጸጥታ አካላት ከጣቢያው ቢሮ የወሠዷቸውን ንብረቶች መንግሥት እንዲመልስም ጠይቋል። በተለይ በአማራና ትግራይ ግጭቶች ዙሪያ ለሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኀን ምኅዳሩ "በእጅጉ የተገደበ" ነው ያለው ተቋሙ፣ ለውጭ መገናኛ ብዙኀን የሚሠሩ ዘጋቢዎችም ፍቃድ ለማግኘት ከፍተኛ መሠናክሎች ይገጥሟቸዋል ብሏል። 6፤ የሳዑዲ ዓረቢያ ፖሊስ፣ በወንጀል ድርጊት ሲሳተፉ ያዝኳቸው ያላቸውን ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን አሠረ። ፖሊስ ኢትዮጵያዊያኑን ጃዛን ግዛት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ያዋለው፣ 200 ኪሎ ግራም ጫት ከውጭ ወደ አስገብተዋል በማለት መኾኑን የሳዑዲ ጋዜጦች ዘግበዋል። ሳዑዲ "አደንዛዥ እጽ" አስገብተዋል ወይም አዘዋውረዋል በሚል ክስ በቅርብ ወራት ብቻ ከ17 በላይ ኢትዮጵያዊያን በሞት የቀጣች ሲኾን፣ በርካቶች ደሞ እስር ላይ ይገኛሉ። እንዲኹም፤ 1፤ በ"ነገረ መጽሐፍት" ውይይት ላይ ሙሉጌታ አረጋዊ በእንግድነት ተጋብዟል። ለውይይት የተመረጠው፣ "ሀገረ ትግራይ" የተሠኘው የደራሲው መጽሐፍ ነው። ዝግጅቱ ነገ ነሐሴ 9 ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ አዳራሽ ይካሄዳል። 2፤ የክረምት አልባሳት ኤግዚቪሽን ተዘጋጅቷል። የሀገር ውስጥ አልባሳትና ምርቶችን የሚያስተዋውቅ "Threads of Addis" በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ ነገ ቅዳሜ ከረፋዱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በሀኑ ቤት ይካሄዳል። 3፤ የጉንጉን የባሕል ሙዚቃ ባንድ አባላት ዛሬ ዓርብ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከል የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ያቀርባሉ። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ፣ ነሃሴ 7፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በአገራዊ የምክክር ጉባኤው የአማራ ክልል ማኅበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተመካካሪዎች፤ ለምክክር ኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን ዋዜማ ሠምታለች። ቅሬታውን የተቀበሉት ኮሚሽነሮች፤ 'ተወያይተን መልስ እንሠጣለን' የሚል ምላሽ እንደሠጡ ምንጮች ነግረውናል። ተመካካሪዎቹ ያቀረቧቸው ቅሬታዎች፤ ሀሳብን ለመግለጽ የሚሠጡ ዕድሎች ፍትሃዊ እንዳልኾኑ፣ ማንነትንና ሀሳብን መሠረት ያደረገ ጫናና ሀሳብን ለማስቀየር በአካልና በጽሑፍ ግፊት እንደሚደረግ፣ የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና የምሁራን ፓናል አባላት ገለልተኛ እንዳልኾኑና የምክክር ሂደቱ ተዓማኒነት ችግር እንዳለበት የሚጠቅሱ ናቸው ተብሏል። Link- https://cutt.ly/NyaVwjrJ 2፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ከአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በተጻራሪ በሚቆሙ የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኀን ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ አቀርባለሁ አለ። የባለሥልጣኑ ሃላፊ ሐይማኖት ዘለቀ፣ ከእንግዲህ ሕገወጥ የበይነ መረብ ጣቢያዎች እንዲሠሩ አንፈቅድም በማለት ዛሬ ባለሥልጣኑ መከላከያ ሚንስቴርንና ፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ ከ11 የመንግሥት ተቋማት ጋር የትብብር መግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ተናግረዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው፣ በመገናኛ ብዙኀን ላይ የሚያካሂደውን ክትትልና ቁጥጥር ለማጠናከር፣ በዘርፉ ዲጂታልና የቴክኖሎጂ ትስስር በመፍጠር የፍቃድ፣ የምዝገባና የባለቤትነት አክሲዮን ዝውውር መረጃዎችን ለማስተሳሰር፣ የ"መሶብ" አገልግሎት ለመዘርጋትና የጥላቻ ንግግር ሥርጭትን በቅንጅት መከላከል መኾኑን ባለሥልጣኑ ገልጧል። 3፤ የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የመቀሌ ከተማ ፍርድ ቤት አንስት ዘውዱ ሃፍቱን ገድለዋል በሚል ቀደም ሲል የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸው የነበሩትን ተከሳሾች ባለፈው ሳምንት በነጻ ያሰናበተበት ውሳኔ ሕጋዊ አሠራሩን የተከተለ ነው አለ። ፍርድ ቤቱ አንዳንድ አካላት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት ለማሳጣት መሠረተ ቢስ መረጃ ያሠራጫሉ በማለት ወቅሷል። የመቀሌ ፍርድ ቤት ግለሰቦቹን በነጻ ያሰናበታቸው፣ የክልሉ ሠበር ሠሚ ችሎት በማስረጃ አያያዝ ዙሪያ ችግር በማግኘቱ የታች ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያየው ባዘዘው መሠረት መኾኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ገልጧል። ፍርድ ቤቱ፣ በዚህ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው አካል አሁንም ይግባኝ ማለት ይችላል ብሏል። 4፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የመንግሥትን የሠላም ጥሪ አንቀበልም ባሉና ''ሽፍቶች'' ሲል በጠራቸው አካላት ላይ እርምጃ መወሠዱን ገለጠ። ቢሮው፣ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ዋልጋ እና ዳርጌ በተባሉ አካባቢዎች "ፋኖ ነን" በማለት ጫካ በገቡ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብሏል። ኾኖም የክልሉን መልካም ገጽታ ለማጠልሸትና የሕዝቦችን አንድነት ለመሸረሽር አንዳንድ ''ኃላፊነት የጎደላቸው" አካላት' ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ላይ ናቸው ሲል ቢሮው ወቅሷል። ቡድኑ፣ 'በጉራጌኛ'፣ 'በኦሮሚኛ'፣ 'በከምባትኛ' እና በሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም ነበር በማለት ከሷል። ቢሮው ይህን ያለው፣ የጸጥታ አካላት በአበሽጌ ወረዳ፣ የፋኖ አባላት ናቸው ያላቸውን ተመስገን ጌታቸው፣ ይታገሱ አሰግደው እና ግዛው ግርማዬ የተባሉ ወጣቶችን ከመኪና አስወርደው ስለመረሸናቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተሠራጨ ማግስት ነው። 5፤ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለማቀፍ ቅርስ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ከዚህ ቀደም በማኅበረዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሠራጩት ተንቀሳቃሽ ምስል የገዳሙን ክብር ነክተዋል ያላቸውን ግለሰቦች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ቅር የተሠኙ አካላትን ይቅርታ ጠየቀ። ጽሕፈት ቤቱ፣ በወቅቱ ''አርቲስቶችና አዝማሪዎች'' የሚል ቃል በመጠቀሙ በርካታ አርቲስቶች ''በጅምላ ተሰደብን' በማለት ቅር እንደተሠኙ መረዳቱን ጠቅሷል። ጽሕፈት ቤቱ፣ የቀደመው መግለጫ ዒላማ አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው አርቲስቶችን ብቻ የሚመለከት ነው ብሏል። ጽሕፈት ቤቱ ካሁን ቀደም ወቀሳ ያቀረበው፣ ላሊበላን ከልመና ጋር አያይዘው በሐሰት የሚያጠለሹ "አርቲስቶች" እና "አዝማሪዎች" አሉ በማለት ነበር። 6፤ ኢትዮጵያዊያን ፍልሠተኞች ወደ የመን ለመሻገር ከጅቡቲ ይልቅ ፊታቸውን ወደ ሶማሊያዋ ቦሳሶ ወደብ እያዞሩ መኾኑን ዓለማቀፉ የፍልሠት ድርጅት ገለጠ። በዘንድሮው የአውሮፓዊያን ሩብ ዓመት በቦሳሶ በኩል ወደ የመን የተጓዙ ኢትዮጵያዊያን ፍልሠተኞች ብዛት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ189 በመቶ ብልጫ እንዳለው ድርጅቱ ጠቅሷል። ድርጅቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጅቡቲ መውጫ መስመር በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥርና ጅቡቲ ውስጥ እስርና በተለያዩ የሰው አዘዋዋሪ መረቦች መካከል ውጥረት መኖሩ፣ የፍልሠተኞች እንቅስቃሴ ውስን እንዲኾን ማድረጉንና ፍልሠተኞች ፊታቸውን ወደ ቦሳሶ እንዲያዞሩ ምክንያት መኾኑን ገልጧል። 7፤ የአሜሪካ ፍርድ ቤት፣ ከሰባት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሠከሠው ቦይንግ 737 ማክስ እውሮፕላን ሕይወታቸውን ላጡት ናወይዝ ሪያን የተባሉ አየርላንዳዊ መንገደኛ ቤተሰብ ቦይንግ ኩባንያ 29 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወሠነ። በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው ሪያን፣ የዓለም ምግብ ድርጅት ሠራተኛ ነበሩ። ባለፈው ግንቦትም፣ የቺካጎ ፍርድ ቤት ቦይንግ ሳሚያ ስቱሞ ለተባሉ ሟች መንገደኛ ቤተሰቦች 49 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል መወሠኑ አይዘነጋም። እንዲኹም፤ 1፤ የሙዚቀኛ ቴዎድሮስ አምዴ "ምስክር" የተሠኘ የኢትዮ ጃዝ ኢንስቱርመንታል የሙዚቃ አልበም ነገ ዓርብ ነሐሴ 8 በናሆም ሪከርድስ በኩል ለአድማጮች ይቀርባል። 2፤ የፎቶግራፈር ገረመው ጥጋቡ "Black, White and Memories" የተሠኘ የፎቶግራፍ ኤግዚቪሽን ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአርታዊ ጋለሪ ይከፈታል። ኤግዚቪሽኑ እስከ ጳጉሜ 1 ቀን ድረስ ይቆያል። [ዋዜማ]
ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፣ ልዩነቶች እየከረሩ ነው የአማራ ክልል የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች፤ ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል። ተመካካሪዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት የቅሬታ ደብዳቤ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በተገኙበት ነሐሴ 05 ቀን ለኮሚሽኑ ቀርቧል። የቅሬታ ደብዳቤውን እንዲሁም ተመካካሪዎች በቃል ያቀረቡትን ቅሬታ የተቀበሉት ኮሚሽነሮቹ፤ “ተወያይተን” መልስ እንሰጣለን ማለታቸውን ሰምተናል። የዋዜማን ዝርዝር ያንብቡ- https://cutt.ly/NyaVwjrJ
ለቸኮለ! ረቡዕ፣ ነሃሴ 6፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉን ክርስቲያን ታደለንና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ ዮሃንስ ቧያለውን ጨምሮ 30 የሽብር ተከሳሾች መንግሥት ያቀረበውን በቅድመ ሁኔታ የታሠረ ይቅርታ ውድቅ አደረጉ። ተከሳሾቹ፣ ወንጀለኞች መሆናቸውን አምነው ከፈረሙ ከእስር እፈታቸዋለሁ በማለት መንግሥት ያቀረበውን የይቅርታ ሠነድ 'አንፈርምም' ማለታቸውን ዋዜማ ተከሳሾቹ ከጻፉት ደብዳቤ ላይ ተመልክታለች። የይቅርታ ሠነዱ፣ ተከሳሾቹ ከእስር ለመፈታት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ፣ በቀውሱ ሕይወታቸውን ላጡና ለቆሰሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎችና ለወደመው በቢሊዮኖች የሚገመት ንብረት ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅ ነው። ኾኖም ተከሳሾቹ፣ በሕግ ነጻ ሆኖ የመታየትና ራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን አሳልፈው እንደማይሠጡ ገልጸዋል። 2፤ እናት ፓርቲ፣ የአገራዊ ምክክር ጉባዔው የገዢው ፓርቲን ፍላጎት ለማስፈጸም ያለመ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ነው በማለት ከሠሠ፡፡ ፓርቲው፣ ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት ሳይኾን ዋና ዋና መገለጫዎቿ ለድርድር የቀረበበት መድረክ ኾኗል በማለት ተቃውሟል። በምክክሩ ላይ አብላጫ ቁጥር የያዙት የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው ያለው ፓርቲው፤ ሂደቱ "ቀድሞ የተወሠነ ውሳኔን በአገራዊ ምክክር ስም ቅቡልነት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ነው" በማለት አጣጥሎታል፡፡ አብን በበኩሉ፣ በምክክር ጉባኤው በታዩ ግድፈቶች ላይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አፋጣኝ ማስተካከያ ካላደረገ ራሱን ከጉባኤው እንደሚያገል አስጠንቅቋል። አብን፣ ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ አዳዲስ ተመካካሪዎች ግልጽ ባልኾነ መንገድ መጨመራቸው፣ የገዥው ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ የሥራ ቡድኖችእየገቡ ጫና መፍጠራቸውና የአመካካሪ ባለሙያዎች ገለልተኝነት ማጣት ሂደቱን አደጋ ላይ ጥሎታል በማለት ስጋቱን መግለጡን ለኮሚሽኑ ከጻፈው ደብዳቤ ላይ ዋዜማ ተመልክታለች። ፓርቲው፣ የአዲስ አበባ አጀንዳ አዲስ አገራዊ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል በማለት ከምክክሩ እንዲሠረዝ፣ አዳዲስ ተሳታፊዎችን ማስገባት በአፋጣኝ እንዲቆም፣ በጉባኤው ሂደት ላይ ገለልተኛ ኦዲት እንዲደረግና ገለልተኛ የቅሬታ ሠሚ አካል እንዲቋቋም ጠይቋል። 3፤ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሠውን የሥራ ዘመን ላንድ ተጨማሪ ዓመት እንዳራዘመ ተሠማ። መስፍን የሥራ ቆይታቸው ላንድ ዓመት መራዘሙን እንዳረጋገጡለት ጠቅሶ ፎርቹን ዘግቧል። መስፍን የሥራ ዘመናቸው በመጠናቀቁ ጡረታ እንደሚወጡና ኾኖም በኃላፊነት ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ የሚወስነው መንግሥት መሆኑን በቅርቡ በሠጡት መግለጫ ላይ ተናግረው ነበር። 4፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፣ ኢትዮጵያዊያን ፍልሠተኞችን ጨምሮ ሕጋዊ ሠነድ የላቸውም ያላቸውን የበርካታ አገራት ዜጎች ለማባረር ያወጣውን ወጪ አገራቱ እንዲከፍሉት ጠየቀ። አገሪቱ የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ የውጭ ዜጎችን ወደ መሰባሰቢያ ማዕከላት ለማጓጓዝና ለሥራ ማስኬጃ 18 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቷን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። የአገሪቱ ጸረ-ፍልሠተኛ ቡድኖች ባደረሱት ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ጥቃት፣ ከ80 ሺሕ በላይ ፍልሠተኞችና ስደተኞች ካለፈው ወር ጀምሮ ወጥተዋል ተብሏል። እስካሁን ምን ያህል ኢትዮጵያዊያን እንደተባረሩ ወይም በፍቃዳቸው እንደወጡ ለጊዜው ማረጋገጥ አልተቻለም። ኾኖም በርካታ ኢትዮጵያዊያን እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገልጸዋል። 5፤ በኢትዮጵያ የወባ ትንኝ ተሕዋሲያን ላይ የሚታየው የዘረ መል ለውጥ በነባሮቹም ኾነ በአዲሶቹ የወባ መድሃኒቶች ውጤታማነት ላይ ስጋት መደቀኑን የለንደን የወባ በሽታ ተመራማሪዎች ገለጡ። ተመራማሪዎቹ በኢትዮጵያ ባካሄዱት ጥናት፣ የወባ በሽታ አማጭ ተኅዋሲያን በሥራ ላይ ያለውን አርቲሚሲኒን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶችን ከመቋቋም ጋር የተያያዘ የዘረ መል ለውጥ እንዳሳዩ ገልጸዋል። ቫይቫክስ እና ፋልሲፈረም ዝርያዎች በጣምራ በሚገኙባቸው በርካታ አካባቢዎች፣ ላንዱ የወባ ዝርያ የሚውለው መድሃኒት ሌላኛው ዝርያ መድሃኒት የመቋቋም አቅሙን እንዲያዳብር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጥናቱ አሳይቷል። የወባ መድሃኒቶችን የመቋቋም አቅም እንዴት እንደሚፈጠር ተከታታይ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ተመራማሪዎቹ አስምረውበታል። 6፤ ብሄራዊ ባንክ ዛሬ ለጨረታ ባቀረበው 125 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የባንኮች ፍላጎት ከ470 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደረሠ። ባንኩ በጨረታው አንድን ዶላር 161 ብር ከ80 ሳንቲም ገደማ እንደሸጠ ገልጧል። በሐምሌ አጋማሽ በተካሄደው ጨረታ፣ አንድ ዶላር በ157 ብር ነበር የተሸጠው። በዛሬው ጨረታ 28 ባንኮች የተሳተፉ ተሳትፈው፣ ዘጠኙ ብቻ የውጭ ምንዛሬ አግኝተዋል። ላንድ ዶላር የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ 163 ብር ከ99 ሳንቲም ገዳማ ሲኾን፣ ዝቅተኛው ዋጋ 159 ብር ከ97 ሳንቲም ኾኗል። እንዲሁም፤ 1፤ የገጣሚ ሰለሞን ሳህለ "ፍቅር እኮ ነው" በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍ፣ ነገ ሐሙስ ነሐሴ 7 ከምሽቱ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ በዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ ይመረቃል። ( ይህ ዝግጅት ፈቃድ በመከልከሉ መሰረዙን አዘጋጆቹ ነግረውናል) 2፤ አስሊ ኢትዮ-ጃዝ ባንድ በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ በየሳምንቱ ሐሙስ ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ የቀጥታ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርባል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ፣ ነሃሴ 5፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በምክክር ጉባኤው፣ 'አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትኹን' የሚል ድንጋጌ በሕገመንግሥቱ ላይ ይስፈር የሚል አማራጭ ምክረ ሀሳብ መካተቱ ተቃውሞ ማስነሳቱን ዋዜማ ሠምታለች። የምክረ ሀሳቡ ደጋፊዎች፣ 'ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም ይኖራታል' በሚለው የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ ምትክ፣ ይሄ ምክረ ሀሳብ እንዲካተት መጠየቃቸውን ምንጮች ነግረውናል። በመንግሥት አደረጃጀት አጀንዳ ላይ በሚመክረው ቡድን ደሞ፣ አራት ጉዳዮች ስምምነት አልተደረሠባቸውም ተብለው እንደተለዩ ምንጮች ገልጸዋል። የገዥው ፓርቲ ተመካካሪዎች፣ የመንግሥት ቅርጽ ፓርላሜንታዊ ሆኖ ፓርላማው የሥራ አስፈጻሚነት ሥልጣን ያለው ፕሬዝዳንት ይምረጥ የሚል ምክረ ሀሳብ በማራመድ ላይ እንደኾኑ ታውቋል። 2፤ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በኃይማኖት ጉዳዮች እና በሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ የቆዩ ሁለት የሥራ ቡድኖች በምክረ ሃሳቦች ላይ መግባባት ላይ ደርሠዋል አለ። ኾኖም ሁለቱ የሥራ ቡድኖች በየትኞቹ አጀንዳዎች ላይ ተመካክረው ከስምምነት ላይ እንደደረሱ ኮሚሽኑ አልጠቀሠም። ኾኖም በሰላም ግንባታ አጀንዳ ሥር ከተካተቱ ንዑስ አጀንዳዎች መካከል፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የምርጫ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የራስን እድል በራስ የመወሠን መብት፣ የፌደራል መንግሥት መቀመጫ፣ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በሕገመንግስቱ ያላቸው ቦታ፣ ማንነት እና ቋንቋ ይገኙባቸዋል። 500 አባላት ያሏቸው የምክክሩ ስምንት የሥራ ቡድኖች በተመደቡላቸው አንድ አንድ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ላይ መኾናቸውን ኮሚሽኑ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት ላይ አንድ የሥራ ቡድን ከስምምነት ላይ መድረሱንም ዘግየት ብሎ አስታውቋል። 3፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስቴር፣ የውጪ ዜጎችና ባለሀብቶች ዝቅተኛውን 150 ሺሕ ዶላር በመክፈል ቤት መግዛት እንዲኾኑ የሚፈቅድ ዝርዝር መመሪያ አወጣ። መመሪያው፣ የውጭ ዜጎች በአዲስ አበባና ሸገር ከተሞች መኖሪያ ቤት ለመግዛት ማቅረብ ያለባቸው አነስተኛው የውጭ ምንዛሬ 150 ሺሕ ዶላር እንዲኾን ያስቀመጠ ሲኾን፣ እንደ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ ባሕርዳር፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ ባሉ ከተሞች ደሞ አነስተኛውን 120 ሺሕ ዶላር አድርጎታል። በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ቤት ለመግዛት ደሞ፣ አንድ የውጭ ዜጋ ማቅረብ ያለበት አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ 100 ሺሕ ዶላር እንዲኾን ተወስኗል። መመሪያው፣ የውጪ ዜጎች፤ በመንግሥት ድጎማ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን፤ በመንግሥት ወይም ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ለትርፍ ላልሆነ ዓላማ የተገነቡ ቤቶችን፤ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወይም የሕዝብ ድርጅቶች ቤቶችንና በሕብረት ሥራ ማኅበራት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን መግዛት እንደማይችሉም ደንግጓል። 4፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ታጣቂዎች ዛሬ ማለዳ ላይ ግልገል በለስ ከተማን ለመቆጣጠር ተኩስ ከፍተው እንደነበር ዋዜማ ሠምታለች። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች የታጣቂዎችን ጥቃት ለመመከት ከባድ መሳሪያ ጭምር እንደተጠቀሙ ምንጮች ገልጸዋል። የዞኑ አስተዳደርም፣ ራሱን የጉሙዝ ኃይል ብለው የሚጠራ ቡድን ከ"ጽንፈኛ ፋኖ" ጋር በመተባበር ወደ ከተማዋ ጥሠው ለመግባትና ጉዳት ለማድረስ ሙከራ አድርገዋል በማለት ከሷል። አስተዳደሩ፣ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሙከራውን መመከታቸውንና በታጣቂዎቹ ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጧል። 5፤ በአላማጣ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የሰው ሕይወት መጥፋቱን በትግራይ በኃይል ሥልጣን የያዘው ሕወሃት-መራሹ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ አስተዳደሩ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በምዕራብ እና በደቡብ ትግራይ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ፈጽሟል በማለት ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ባሠራጨው መረጃ ከሷል፡፡ ትናንት በራያ አለማጣ ወረዳ "መረዋ" ቀበሌ በትግራይ ኃይል አባላት ላይ ተፈጽሟል ባለው የድሮን ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሠው አስተዳደሩ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡና አጋር አካላት ሁኔታው ወደባሰ ቀጠናዊ ቀውስ ሳይቀየር ባስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል። መረዋ ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት፣ አራት የክልሉ ተዋጊዎች እንደቆሠሉ መስማቱን ጠቅሶ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የዘገበ ሲሆን፣ ቢቢሲ በበኩሉ ሦስት ተዋጊዎች ተገድለው ሰባት መቁሠላቸውን ሠምቻለሁ ብሏል። 6፤ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ በአዲሱ ደመወዝ መሠረት ተሠልቶ እንዲከፈል መመሪያ ማስተላለፉን ዋዜማ ሠምታለች። የክልሉ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ካለፈው መስከረም ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የደምወዝ ጭማሪ መሠረት ተሠልቶ ሳይከፈል መቅረቱን ቢሮው ጠቅሷል። ይህ ሁኔታም፣ በጤና ባለሙያዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ቢሮው ለሁሉም የወረዳና የከተማ አሥተዳደር የጤና መዋቅሮች ከጻፈው ደብዳቤ ላይ ዋዜማ ትመለከታለች። 7፤ የተመድ የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ በኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተያዘው ክረምት የአገሪቱ 70 በመቶ የሰብል ምርት አምራች አካባቢዎች የድርቅ ስጋት ተደቅኖባቸዋል አለ። ድርጅቱ፣ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ በሌሎች አካባቢዎች ከባድ ጎርፍ ሊከሠት እንደሚችልም ገልጧል። ከ163 በላይ ወረዳዎች ለኢልኒኖ ስጋት ተጋላጭ መኾናቸውን የጠቀሠው ድርጅቱ፣ ሁኔታው ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር፣ የሰብዓዊ ተረጂነትና መፈናቀል ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። ድርጅቱ፣ ካለፈው ሰኔ እስከ ቀጣዩ ዓመት መጋቢት በተለይ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች በ114 ወረዳዎች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የኤልኒኖ ተጎጂዎችን ለመደገፍ 50 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል። እንዲሁም፤ 1፤ ዓለማቀፉን የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ መሰናዶ ነገ ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሪቲሽ ካውንስል ይካሄዳል። በመሠናዶው ተጋባዥ የፓናል ተወያዮች ልምዳቸውንና አዳዲስ ሀሳቦቻቸውን ያካፍላሉ ተብሏል። 2፤ በደራሲ ይፍቱሥራ ምትኩ ሁለት መጽሐፍት ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይትና የፊርማ ሥነሥርዓት ነገ ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2018 ዓ፣ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በዋልያ መጽሐፍ አዳራሽ ይካሄዳል። [ዋዜማ]
- ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ፓርላመንታዊ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ከፓርላማው ይመረጥ የሚል ምክረ ሀሳብ በብልፅግና ቀርቧል -ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5፤ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ስለሚኖራት “ልዩ ጥቅም” የሚደነግግ ሲሆን፤ በምክክሩ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ድንጋጌ እንዲቀር ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጡልን ምንጮች፤ በንዑስ አንቀጹ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ” ትሁን የሚል ድንጋጌ እንዲካተት መጠየቁን ነግረውናል። ዝርዝሩን ያንብቡት- https://cutt.ly/MyasBwLM
ለቸኮለ! ሰኞ፣ ነሃሴ 4፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የብሄራዊ የምክክር ጉባኤው ምክረ ሀሳብ አጠናቃሪ ቡድኖች የአዲስ አበባን ጉዳይ 500 አባላት ላሏቸው የሥራ ቡድኖች ማቅረብ ሳይችሉ ቀሩ። አጀንዳው ለሥራ ቡድኖች ያልቀረበው፣ ከተማዋ 'የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማና መቀመጫ ትሁን' የሚለው ጥያቄ ስምምነት ሊደረስበት ስላልቻለ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። ገዥው ፓርቲም፣ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መኾኗን ለተቃወሙ ተመካካሪ ተወካዮቹ ማስጠንቀቂያ ሠጥቷል ተብሏል። የማንነት እውቅናና የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ያሏቸው ፓርቲዎች ለጥያቄያቸው ከገዥው ፓርቲ ድጋፍ ማግኘት ከፈለጉ፣ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትኾን ድጋፍ እንዲሠጡ በተጓዳኝ በሚካሄዱ መድረኮች መደራደሪያ እንደቀረበላቸው ጭምር ምንጮች ጠቁመዋል። በሌላ በኩል፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ተመካካሪዎች ለተወከሉበት አካባቢ ጥያቄ ብቻ መልስ ለማስገኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ አገሪቱን ያማከለ ምክክር እንዲያደርጉ ጠየቁ። የምክክር ጉባኤው የመጨረሻ ምክረ ሀሳቦችን አቅራቢ እንጂ ውሳኔ ወሳኝ እንዳልኾነ ዋና ኮሚሽነሩ ዛሬ በሠጡት መግለጫ አጽንዖት ሠጥተዋል። ኮሚሽኑ፣ በምክክሩ ሂደት የተፈጠሩ ስሜቶችን ለማርገብ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር በተናጥል መምከሩንም ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ መግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል። Link- https://cutt.ly/ryp24cTb 2፤ በብሄራዊ ምክክር ጉባኤው፣ በአመዛኙ የክልሎች ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ይፍረስ የሚለው ምክረ ሀሳብ ሚዛን እንደደፋ ዋዜማ ሠምታለች። በክልል ልዩ ኃይሎች ፋንታ፣ ወጥ አደረጃጀት ያለውና ወርሃዊ ደመወዝ የሚከፈለው ብሄራዊ የሚሊሻ ሠራዊት እንዲቋቋም ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ተፎካካሪዎች እንዳሉ ምንጮች የገለጡ ሲሆን፣ ይኼው አጀንዳ 500 አባላት ላሏቸው የሥራ ቡድኖች መቅረቡን ዋዜማ ተረድታለች። በርካታ ተመካካሪዎች፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን አልበተኑም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል ተብሏል። 3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ በገዥው ብልጽግና ፓርቲ የሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የኦሮሞ ብሔር ተወካዮች ቁጥር ከሌሎች ብሔሮች ተወካዮች ቁጥር መብለጡ ተገቢ ነው በማለት ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናገሩ። ዐቢይ፣ ለብሄር እኩልነት ሲባል በፓርቲው ውስጥ እኩል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሊኖር አይገባም ብለዋል። የፓርቲው የሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቁጥር፣ በብሔረሰብ ቁጥር እንዲሁም ብሄረሰቡ ለአገር ግንባታ ባለው አስተዋጽዖና ተሳትፎ ልክ መሆን አለበት በማለት ዐቢይ አብራርተዋል። 4፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በዱቤ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስቀጥሉ ደንበኞች ላይ የሚጥለውን ወለድ ሙሉ በሙሉ አነሳ። የአዲስ ኤሌክትሪክ ማስቀጠያ የክፍያ ጊዜው እስከ 24 ወራት የሚደርስ ሲኾን፣ ከ6 ወራት በላይ ለሚቆይ ክፍያ ደንበኞች ከ3 እስከ 9 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይከፍሉ ነበር። የወለዱ መነሳት፣ አዲስ ኤሌክትሪክ መስመር በዱቤ ለማስገባት የሚፈልጉ አቅም የሌላቸውን ደንበኞች በይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተቋሙ ገልጧል። የዱቤ አሠራር በሥራ ላይ የዋለው ካለፈው ሰኔ ጀምሮ ነበር። 5፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ፣ በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ የሚሠጠውን የሠነድ ማረጋገጥና ማመሳከር አገልግሎት ከሐምሌ 20 ጀምሮ በክልል ደረጃ ብቻ ለመስጠት መወሠኑን ዋዜማ ተረድታለች። የሠነድ ማረጋገጥና ማመሳከር የአገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓቱ በተሻሻለው መመሪያ መሠረት ተፈጻሚ እንዲኾን እንደተደነገገ፣ ኤጀንሲው ለዞንና የልዩ ወረዳ መዋቅሮች ከጻፈው ደብዳቤ ላይ ተመልክተናል። 6፤ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች፣ የትግራይ ባለሥልጣናት በትግራይ ነጻነት ፓርቲ አመራሮች እና የመናገር መብታቸውን በሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ "የማዋከብ"፣ "የማስፈራራት"፣ "የዛቻ" እና "የዘፈቀደ እስር" እየፈጸሙ ነው በማለት ከሠሠ። ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ብቻ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ካህሱ ኪዳኔ እና እዝጋሚን ተክለ ብርሃን ታስረዋል ብሏል። በደቡባዊ ትግራይ ዞን በአላማጣ፣ በማዕከላዊ ዞን እና በሰሜን ምዕራብ ዞንም ሰባት ተጨማሪ "የዘፈቀደ እስሮች" በቅርብ ጊዜያት እንደተፈጸሙ ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ የትግራይ ባለሥልጣናት በተቃዋሚዎች፣ መምህራንና ጋዜጠኞች ላይ ይፈጽሙታል ያለውን "የዘፈቀደ እስር" እንዲያቆሙና ሀሳባቸውን በመግለጣቸው ብቻ ታስረዋል ያላቸውን ግለሰቦች እንዲለቁ ጠይቋል። 7፤ አምስት የትግራይ ሲቪል ማኅበራት፣ የመቀሌ ፍርድ ቤት አንስት ዘውዱ ኪሮስን ገድለዋል ብሎ የእድሜ ልክ እስራት የፈረደባቸው ያሬድ ገብረሥላሴ እና አንገሶም ኃይለማርያም ከቀናት በፊት በነጻ መሠናበታቸውን ተቃወሙ። ድርጅቶቹ፣ የብሄራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት በግለሰቦቹ ዙሪያ የያዘውን ኹነኛ የኤሌክትሮኒክ ማስረጃ አልተገኘም በሚል አሳማኝ ያልኾነ ምክንያት፣ ግለሰቦቹ በነጻ ተሠናብተዋል ብለዋል። ድርጅቶቹ፣ ፖሊስ ለምን የኤሌክትሮኒክ ማስረጃውን ለፍርድ ቤት እንዳላቀረበ ምርመራ እንዲደረግ፣ የአንደኛው "ፍርደኛ" ወላጅ አባት የኾኑት የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ኮሎኔል ገብረሥላሴ በላይ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ከሥራ ታግደው እንዲቆዩና የክልሉ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች፣ ዳኞችና ምስክሮች ደኅንነት የጽሁፍ ዋስትና እንዲሠጥ ጠይቀዋል። 8፤ ሳዑዲ ዓረቢያ ሰሞኑን ባንድ ሳምንት ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የአገሪቱን ድንበር ለማቋረጥ ከመሞከር ጋር በተያያዘ ወንጀል ከ950 በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን አሠረች። የሳዑዲ ዓረቢያ የድንበር ጸጥታ ኃይሎች ባንድ ሳምንት 1 ሺሕ 593 የውጭ ዜጎች የአገሪቱን ድንበር ለማቋረጥ ሙከራ ሲያደርጉ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የዘገቡት የአገሪቱ ጋዜጦች፣ ከእነዚህ ውስጥ 59 በመቶዎቹ ኢትዮጵያዊያን መኾናቸውን ጠቅሠዋል። እንዲኹም፥ 1፤ በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ በየሳምንቱ ሰኞ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ የኢትዮ-ጃዝ መስራች ሙላቱ አስታጥቄ እና አንጋፋው ድምጻዊ ግርማ በየነ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ ነው። 2፤ "ካይን-ላብ” የጃዝ ባንድ አባላት በየሳምንቱ ሰኞ ምሽት ሐያት ሪጀንሲ ሥር በሚገኘው ፈንድቃ የባሕል ማዕከል ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚዎች ያቀርባሉ። 3፤ "ባሎችና ሚስቶች" የተሠኘ ተውኔት በዓለም ሲኒማ ዘወትር ማክሰኞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመቅረብ ላይ ይገኛል። [ዋዜማ]
የአዲስ አበባ ጉዳይ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ የሚካሄደውን ምክክር ጥላ አጥሎበታል በምክክር አዳራሾች ከሚደረገው የምክክር ሂደት ውጭ፤ ትይዩ የሆኑ ድርድሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዋዜማ ሰምታለች። የማንነት እውቅና፣ የአስተዳደር መዋቅርና ሌሎች ጥያቄዎች ያሏቸው ፓርቲዎች፤ “ከብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ እንድታገኙ በአዲስ አበባ ጉዳይ አግዙን” የሚል መደራደሪያ እየቀረበላቸው መሆኑን ዋዜማ ጥያቄው ከቀረበላቸው የፓርቲ አመራሮች ሰምታለች። የዋዜማን ዝርዝር ዘገባ ያንብቡ- https://cutt.ly/ryp24cTb
የክልል ልዩ ኃይል ይፍረስ ፣ ሀገር አቀፍ ሚሊሻ ይደራጅ የሚሉ አጀንዳዎች ቀርበዋል የክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀት እንዲፈርስ የተወሰነ ቢሆንም፤ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች በተለያየ መልክና ስያሜ የልዩ ኃይል ሠራዊታቸውን ሳይበትኑ ማስቀጠላቸውን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ ውሳኔው በሁሉም ክልሎች በዕኩልነት ተግባራዊ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ሰምተናል። የዋዜማን ዝርዝር ዘገባ ያንብቡ- https://cutt.ly/Cyp24Kj8
ለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ነሃሴ 2፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ በብሄራዊ ምክክር ጉባኤው የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች 500 አባላት ላሏቸው የሥራ ቡድኖች መቅረብ ጀመሩ። ከእያንዳንዱ የባለ 500 አባላት የሥራ ቡድኖች የተመረጡ 30 አባላት ከስልታዊ ቡድኖች የቀረቡ የአጀንዳ ምክረ ሃሳቦችን አቀናጅተው 500 አባላት ላሏቸው ስምንት የሥራ ቡድኖች ማቅረብ መጀመራቸውን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማምሻውን ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ የሥራ ቡድኖች ባጠናቀሯቸው የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ምክክር የሚጀመረው በመጪው ሰኞ መኾኑን ጠቅሷል። 500 ተመካካሪዎችን የያዙ የሥራ ቡድኖች በሁሉም አጀንዳዎች ላይ የመጨረሻ ምክረ ሀሳቦችን አዘጋጅተው ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። 2፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን አስታወቀ። ለበጀት ዓመቱ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉት፣ ለጎረቤት አገራት የተሸጠው እና ሰባት ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች የገዙት ኤሌክትሪክ ኃይል መኾኑን ተቋሙ ገልጧል። ከኃይል ሽያጭ በዓመቱ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው ገቢ 75 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር እንደነበር የጠቀሠው ኩባንያው፣ ገቢው ግን 76 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሷል። የበጀት ዓመቱ ገቢ ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር፣ የ73 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል። ኩባንያው፣ በዓመቱ 205 የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረጉን ጭምር የገለጠ ሲኾን፣ ቀበሌዎቹ በክልል ደረጃ ያላቸው ሥርጭት ግን አልገለጠም። 3፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የሚፈጸመው ጫና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ነጻ መገናኛ ብዙኀንን ዝም ለማሠኘትና የትችት ዘገባዎችን ለማፈን የሚያደርጉት ዘመቻ አካል ነው በማለት ተቸ። ተቋሙ፣ መንግሥት የግንቦቱን ጠቅላላ ምርጫ ነጻ መገናኛ ብዙኀንን ለማገደብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚለው ስጋት አሁን እውን ኾኗል በማለት ወቅሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በነጻ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ዓለማቀፍ አጋሮች እንዲያወግዙ፣ ባለሥልጣናት የፕሬስ ነጻነትን እንዲያከብሩና ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስርንና ዛቻን ሳይፈሩ በነጻነት መዘገብ እንዲችሉ ግፊት እንዲያደርጉ ተቋሙ ጠይቋል። 4፤ ሁለት የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች፣ ለደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች የተሠጠውን ጊዜያዊ ከለላ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ማንሳት ይችላል በማለት ወሠኑ። አሜሪካ ውስጥ ጊዜያዊ ከለላ የተሠጣቸው 232 ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች ይኖራሉ። የጊዜያዊ ከለላ ፕሮግራሙ፣ በግጭት ከሚታመሱና የተፈጥሮ አደጋ ካጋጠማቸው አገራት የተሠደዱ ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ መቆየትና ሥራ መስራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው። የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር፣ በዚሁ ፕሮግራም የታቀፉ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከለላ ለማንሳት ከወራት በፊት የወሠነውን ውሳኔ፣ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ማገዱ ይታወሳል። 5፤ የአሜሪካ የአየር በረራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ ቦይንግ ኩባንያ በማክስ 737 አውሮፕላኖች ዋና አካል ላይ ስንጥቅ መኖር አለመኖሩን እንዲመረምር አዘዘ። መመሪያው፣ ቦይንግ 737-8፣ 737-9 እና 737-8200 የተባሉትን ማክስ አውሮፕላኖች እንደሚመለከት የአሜሪካ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በዓለም ዙሪያ በ1 ሺሕ 429 አውሮፕላኖች ላይ ከቀጣዩ ዓመት መስከረም ጀምሮ ምርመራ ይጀምራል ተብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 አውሮፕላኖች አሉት። በ737 ማክስ አውሮፕላኖች ዋና አካል ላይ እስካሁን ሥንጥቅ ባይገኝም፣ ተመሳሳይ ሥሪት ካላቸው ቦይንግ 737 'ኔክስት ጄነሬሽን' አውሮፕላኖች መውጫ በሮቻቸው አካባቢ ከአምስት ዓመት በፊት ሥንጥቅ ተገኝቶባቸው እንደነበር ይታወሳል። እንዲሁም:- 1. በደራሲ ታገል ሰይፉ የተዘጋጀው "የፕሬዝዳንቱ ልጅ" የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ልጅ ዶ/ር ትዕግሥት መንግስቱ የልጅነት ትውስታዎች ስብስብ ነው። 2.የመጽሐፍ ካርኒቫል እሁድ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ በአብርሆት ቤተመጽሐፍት ይካሄዳል። በካርኒቫሉ ላይ ዐውደ ጥናቶች ፣ የፓናል ውይይቶች፣ የመጽሐፍ ዳሰሳዎች እና ሌሎችም አዝናኝ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል። መግቢያ 300 ብር ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ፣ ነሃሴ 1፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ ሰሞኑን በስልታዊ ቡድን ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ቁመና ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው አገራዊ ምክክር የሀሳብ ልዩነት ማስተናገዱን ዋዜማ ሠምታለች። ከጥቃቅን ቡድኖች ደረጃ ጀምሮ ያልተነሱ ሀሳቦች በስልታዊ ቡድን ቃለ ጉባኤ ላይ እንዲካተቱ ጥያቄ መቅረቡ ሠፊ ልዩነት መፍጠሩን ምንጮች ገልጸዋል። በንዑስ ቡድኖች ደረጃ ያልተነሳው 'አዲስ አበባ የፌደራል ከተማና የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ትሁን' የሚለው ምክረ ሀሳብ፣ በቃለ ጉባኤ እንዲያዝ የቀረበው ጥያቄ ተቃውሞ እንደገጠመው ምንጮች ነግረውናል። በመጨረሻም ምክረ ሀሳቡ እንደ አማራጭ ተቀምጦ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ተወስኗል ተብሏል። 2፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ በኢሕአፓ አመራሮች ይስሐቅ ወልዳይ እና አበበ አካሉ እንዲሁም የቀድሞው የሰላም ሚንስትር ዴኤታ ታዬ ደንደኣ ጠበቃ አበራ ንጉሥ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ 12 ቀናት ፈቀደ። ፖሊስ፣ የተጠርጣሪዎቹን ለምርመራ አገኘሁት ያለውን የድምጽ ቅጂ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ተጠርጣሪዎቹ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ "ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭተዋል ወይስ አላሠራጩም" የሚለውን ጉዳይ ፖሊስ እንዱያጣራ ተሠጥቶ በነበረው ትዕዛዝ መሠረት፣ ችሎቱ መጠነኛ ጥርጣሬ አግኝቼበታለሁ ባለው የድምጽ ቅጂ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል በማለት ተጨማሪ ቀናት መፍቀዱን ገልጧል፡፡ ችሎቱ፣ ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 11 ቀጥሯል። 3፤ የኢትዮጵያ የሠነድ የሙዓለ ንዋይ ገበያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዮዲት ካሳን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾመ። ዮዲት የተሾሙት፣ ኩባንያውን ከጥንስሱ ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት ጥላሁን እስማኤል ከሃላፊነት መልቀቃቸውን ተከትሎ መኾኑን ኩባንያው አስታውቋል። ዮዲት፣ የሙዓለ ንዋይ ገበያው ዋና የቢዝነስ ኦፊሰር እና በኋላም ዋና ኦፐሬቲንግ ኦፊሰር ኾነው ማገልገላቸውን ኩባንያው ጠቅሷል። የዮዲት የሃላፊነት ዘመን፣ የውጭ ኩባንያዎችን መሠረት በማስፋት፣ በገበያው ውስጥ ተሳትፎን በማሳደግ፣ የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስፋት፣ አዳዲስ ዘርፎችንና የገበያ እድሎችን በማስተዋወቅና የካፒታል ገበያውን ለኢንቨስትመንት፣ ለፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማፋጠኛ እንዲሆን በማስቻል ላይ ያተኮረ ይኾናል ተብሏል። 4፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ፣ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስን ከሐምሌ 29 ጀምሮ ቋሚ ከአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስነት አገደ። በአገረ ስብከቱ ተስተውሏል ያለውን ሕገ-ቤተክርስቲያንና ሥራዎችን በበላይ አካል መመሪያ መሠረት ያለማስኬድ፣ የገንዘብ ብክነትና ከፍተኛ የተባሉ የአሠራር ግድፈቶችን ለማረም ሲባል፣ አቡኑን ማገድ እንዳስፈለገ መግለጡን ዋዜማ ቋሚ ሲኖዶሱ ለአቡነ ሕርያቆስ ከጻፈው የእግድ ደብዳቤ ላይ ተመልክታለች። ኾኖም ቋሚ ሲኖዶሱ አቡነ ሕርያቆስ ደርበው የሚያስተዳድሯቸውን የሐድያና ሥልጤ አኅጉረ ስብከቶች እንደያዙ እንዲቀጥሉ መፍቀዱን ገልጧል። አቡነ ሕርያቆስ በበኩላቸው፣ ተጠሪነታቸው ለምልዓተ ጉባኤ መሆኑን በመጥቀስ፣ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ከሕገ-ቤተክርስቲያን ውጪ ነው በማለት እገዳውን ውድቅ አድርገውታል። ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ቀርቦ በአካል ወይም በጽሑፍ ተገቢው ምላሽ ሳይሠጥበት እገዳ መጣል፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ማደናገር ነው ሲሉ አቡነ ሕርያቆስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ ኮንነዋል። 5፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አዲስ ስታንዳርድን ጨርሶ ለመዝጋት ያካሂዱታል ያለውን ዘመቻ እንዲያቆሙ ጠየቀ። የተቋሙ የአፍሪካ ሃላፊ ሙቶኪ ሙሞ፣ በአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ ነጻ መገናኛ ብዙኀን አንዱ የኾነውን የዜና አውታር ጨርሶ ለማጥፋት የተከፈተው ዘመቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታል በማለት ኮንነዋል። ተቋሙ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቀናት በፊት ከአዲስ ስታንዳርድ ቢሮ የተወሠዱ መሳሪያዎችን እንዲመልሱ፣ አዲስ ስታንዳርድ በግዳጅ ቢሮውን እንዲለቅ እንዳይገደድ፣ በመገናኛ ብዙኀኑ ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ተጨማሪ ጫናዎችን እንዲያስቆሙና ለዋና አዘጋጁ የ24 እስርና አካላዊ ጥቃት ተጠያቂ የኾኑ አካላትን በሕግ እንዲጠይቁ ጠይቋል። 6፤ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሲድሃርቶ ሱሪዮዲፑሮ፣ በጀኔቫ የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ የኾኑትን ሐብቶም ዘርዓይን የካውንስሉ ማኅበራዊ ፎረም ሊቀመንበር አድርገው ሾሙ። ሐብቶም የካውንስሉ ማኅበራዊ ፎረም ዋና ሊቀመንበር ኾነው የተሾሙት፣ የአፍሪካ አገራት በዕጩነት ካቀረቧቸው በኋላ መኾኑን ፕሬዝዳንቱ በጻፉት ደብዳቤ ገልጠዋል። የማኅበራዊ ፎረሙ ሊቀመንበርነት የካውንስሉ አባላት ለኾኑ ቀጠናዎች በየተራ የሚዳረስ ሹመት ነው። ማኅበራዊ ፎረሙ ስብሰባውን በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር እንደሚያካሂድና ትኩረቱም በዓለማቀፍ ትብብር እና አንድነት ላይ እንደሚኾን ካውንስሉ አስታውቋል። 7፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ (ሲፒጄ)፣ ለ20 ዓመታት እስር ላይ የሚገኙትን 16 የኤርትራ ጋዜጠኞች የዓመቱ "የዓለማቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት" ተሸላሚ አድርጎ መረጠ። ጋዜጠኞቹ እስካሁን ክስ እንዳልተመሠረተባቸው፣ ለፍርድ እንዳልቀረቡና ከቤተሰብ ወይም ጠበቃ ጋር እንዳልተገናኙ የጠቀሠው ሲፒጄ፣ የጤናቸው ሁኔታ ወይም በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ገልጧል። ከተሸላሚዎቹ መካከል፣ ዳዊት ይስሃቅ፣ አማኑኤል አስራት፣ ዳዊት ሃብተሚካኤል እና መድሃኔ ኃይሌ ይገኙበታል። በቀጣዩ ዓመት ሽልማቱን ከሚቀበሉት ሌሎች ጋዜጠኞች መካከል፣ የሊባኖስ፣ ኮሎምቢያ እና ማይናማር ጋዜጠኞች ይገኙበታል። እንዲሁም:- 1.በፍርድአወቀ ማሞ (ዶ/ር) "ቀይ ባሕር ሲቀላ" መጽሐፍ ዙሪያ የተዘጋጀው የመጽሐፍ ፊርማ ሥነሥርዓት ነገ ቅዳሜ ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 በጃፋር መጽሐፍ መደብር ይካሄዳል። 2.ደራሲ እመቤት አብዲሣ "በመሃል" በሚል ርዕስ ያዘጋጀችው አዲስ መጽሐፍ ቅዳሜ ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በከተማ ማዕከል ይመረቃል። [ዋዜማ]
“አዲስ አበባ ሕብረ ብሔራዊ ከተማ ናት እያልን ለአንድ ክልል ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ ውሳኔ አናስተላልፍም” ተመካካሪዎች - የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን የሚለውን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ተመካካሪዎች ደግሞ፤ ምክረ ሀሳቡ በሥራ ቡድን ደረጃ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ጠይቀዋል። የዋዜማን ዝርዝር ዘገባ ያንብቡት https://cutt.ly/TypeHvHz
ለቸኮለ! ሐሙስ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች 1፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሁለት ጊዜያት ተመካካሪዎች አድማ ማድረጋቸውን ለተመካካሪዎች በሠጠው ማብራሪያ ላይ መግለጡን ዋዜማ ሠምታለች። ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ፣ የምክክር ሂደቱ ሁሉም ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን የሚገልጡበት በመኾኑ አድማ መምታት አያስፈልግም በማለት መናገራቸውን ምንጮች ነግረውናል። የአድማ እንቅስቃሴ የታየው፣ በአገር ግንባታና በሁለቱ ከተሞች አጀንዳዎች ዙሪያ በተመካከሩ ስልታዊ ቡድኖች መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል። “ብሔራዊ ቋንቋ ይኑር ወይስ አይኑር?” የሚለው ጉዳይ እና የአዲስ አበባ ጉዳይ ተመካካሪዎች ምክክሩን አቋርጠው እንዲወጡ ያደረሱ ምክንያቶች እንደኾኑ ምንጮች ገልጠዋል። Link- https://cutt.ly/GyoXNxFt 2፤ አዲስ ስታንዳርድ የበየነ መረብ ሜዲያ፣ ባለፉት ቀናት ዋና አዘጋጁ ዮናስ ከድር ለ24 ሰዓታት ታግቶ ተወስዶ እንደነበር ገለጠ። የሜዲያው አሳታሚ ጃኪን ኩባንያ፣ ጸጥታ ኃይሎች ሐምሌ 26 ቀን የሜዲያውን ቢሮ መበርበራቸውንና ንብረቶችን መውሠዳቸውን እንዲሁም ለ16 ዓመታት ከተከራየው ቢሮ እንዲለቅ እየተገደደ መሆኑን ገልጧል። ጸጥታ ኃይሎች፣ የስቱዲዮ መገልገያዎችንና የቀረጻ መሳሪያዎችን መውሠዳቸውን እንዲሁም የተወሠኑ እቃዎችን መስበራቸውንም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አትቷል። ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሠድ መዘጋጀቱን የገለጠው ድርጅቱ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለሕግ ተገዢ እንዲኾኑ ጠይቋል። 3፤ መንግሥት፣ ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሽፋን ይሠጡ የነበሩ ሰባት የክሪፕቶ ካረንሲ መተግበሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማገዱን አስታወቀ። ምርት ልከው የውጭ ምንዛሬ ተመላሽ ያላደረጉ 29 ላኪ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ በሕግ ተጠያቂ መኾናቸውን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገልጧል። ወርቅ ከገበያ ውጭ በኮንትሮባንድ በማስወጣት ወንጀል የተሳተፉ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የጸጥታ አመራሮችን፣ አምራቾችንና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 183 ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸውን አገልግሎቱ ጠቅሷል። አገልግሎቱ፣ በሕገወጥ መንገድ የሽፋን ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት፣ ነዳጅ በመደበቅና አየር በአየር በመሸጥ ወንጀል የተሳተፉ 38 የመንግሥት አመራሮችም በሕግ ተጠይቀዋል ብሏል። ኾኖም ርምጃው ከመቼ እስከ መቼ እንደተወሠደ አገልግሎቱ አልጠቀሠም። 4፤ ማዕድን ሚንስቴር፣ በ2018 እና 2019 በጀት ዓመት አገሪቱ ከማዕድን ዘርፉ ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች አለ። ከኩባንያዎችና ከባሕላዊ ወርቅ አምራቾች 44 ቶን ወርቅ ተመርቶ ገቢው መገኘቱን የጠቀሠው ሚንስቴሩ፣ ዘርፉ ከ271 ሺሕ በላይ ለሚኾኑ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጧል። አገሪቱ በተያዘው በጀት ዓመት ከማዕድን ዘርፉ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዷን ሚንስቴሩ አመልክቷል። 5፤ ኢትዮጵያ በሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ከአፍሪካ አገራት አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የኢንተርፖል አዲስ ሪፖርት አመለከተ። በአሕጉሪቱ ውስጥ ከታዩ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ክስተቶች መካከል፣ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 3 በመቶ ድርሻ እንዳላት ሪፖርቱ ጠቅሷል። ሪፖርቱ፣ ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት የሳይበር ደኅንነት መከላከያዎችንና የተቋማትን ዝግጁነት ቀድመው መሄዳቸውን ገልጧል። አሕጉሪቱ በሳይበር ጥቃት ሳቢያ የሚገጥማት ኪሳራ 5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ያለው ድርጅቱ፣ አገራትና ድርጅቶች ለሳይበር ደኅንነት የሚያወጡት ወጪ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሻቀቡን አመልክቷል። በምሥራቅ አፍሪቃ አገራት ላይ ከሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች መካከል፣ የሞባይል ገንዘብ ማጭበርበር፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ጥቃቶች እና በመሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል። 6፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባሕርዳሩ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያስገነባውን አዲስ የመንገደኞች ተርሚናል አስመረቀ። የአውሮፕላን ማረፊያውን አዲስ ተርሚናል ዛሬ የመረቁት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ናቸው። አዲሱ ተርሚናል የተገነባው፣ በክልሉ በተከሠተው ግጭት በአውሮፕላን ማረፊያው መሠረት ልማት ላይ ውድመት በመድረሱ ነው በማለት ዐቢይ በተርሚናሉ የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል። አዲስ የተገነባው ተርሚናል የአውሮፕላን ማረፊያውን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚያሳድገውና አውሮፕላን ማረፊያው ለመንገደኞች የሚሠጠውን አገልግሎት እንደሚያሻሽለው አየር መንገዱ ባሠራጨው መረጃ ላይ ገልጧል። እንዲሁም:- 1.የደራሲ ሄኖክ በቀለ "ምናልባት አንድ ቀን" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በተለያዩ መጽሐፍት መደብሮች በኩል ለአንባቢያን ቀርቧል።ደራሲው አስቀድሞ "ሀገር ያጣ ሞት" እና "ይናፍቀኛል" የተሰኙ መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል። 2.ሳይንስ እና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ እንዲሁም ፊዚክስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ስላለው ተፅዕኖ የሚያነሳሳ ዝግጅት ቅዳሜ ነሐሴ 2 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በዋልያ መጽሐፍት ይካሄዳል። በዕለቱም ሽብሩ ተድላ (ፕ/ር) እና ተስፋዬ መኮንን ሀሳቦቻቸውን ያጋራሉ። [ዋዜማ]
አዲስ ስታንዳርድ የብየነ መረብ ሚዲያ ባለፉት ቀናት ዋና አዘጋጁ ታግቶ ተወሰዶ እንደነበር ፤ ቢሮው በፀጥታ ሀይሎች መበርበሩንና ንብረቶቹ መወሰዳቸውን እንዲሁም ለአስራ ስድስት ዓመታት ከተከራየው ቢሮ እንዲለቅ እየተገደደ መሆኑን አስታወቀ። ዝርዝሩን አንብቡት https://cutt.ly/Iyo1Ln60