tgindex
የሕይወት እምሻው አጫጭር ታሪኮች/ Hiwot Emishaw

የሕይወት እምሻው አጫጭር ታሪኮች/ Hiwot Emishaw

Статистика

ሕይወት እምሻው የተወዳጆቹ ባርቾ፣ ፍቅፋቂ፣ ማታ ማታ፣ ለእርቃን ሩብ ጉዳይ፣ የቡና ቁርስ እና ዥዋዥዌ መጽሐፍት ደራሲ ናት። በዚህ መድረክ ወጎችን እና ልብ ወለዶችን ታቀርባለች።

Последний пост
14 авг.
Последнее чтение
13 авг.
Постов за неделю
4
Всего постов
21
Тип
открытый
Язык
und
В каталоге с
13 авг.
Подписчики
7 232
+11 за 2 дн.
Сутки
0
0,00%
Неделя
 
Месяц
 
Просмотров на пост
3 203
21 постов
Вовлечённость
44,3%
к подписчикам
Постов в день
0,6
всего 21
Упоминаний
3
каналов
Охват размещения
оценка
1/24сутки в ленте
1 558
1/48двое суток
1 785
1/72трое суток
1 925

Оценка по просмотрам недавних постов: пост набирает почти всё за первые сутки.

Посты

  • 14 авг.1 6963313

    видео или голосовое, без подписи

  • 13 авг.2 1057611

    ‹‹ስለ እንትን አትጻፍ›› --- ወዳጄ ሰለሞን ሳህሌ ትላንት ልብ ሰባሪ የፌስቡክ መልእክት ለጥፎ ነበር፡፡  "ፍቅር እኮ ነው" የተሰኘውን መጽሐፉን ለአንባቢዎች ለማቅረብ ዝግጅቱን ጨርሶ ዛሬ ሊያስመርቅ ደፋ ቀና ሲል «ቁጥጥር ከሚያደርጉ» አካላት "መጽሐፉ አይመረቅም" የሚል የእገዳ መርዶ እንደደረሰው ነገረን። ውጥኑ፣ ገንዘቡ እና ህልሙ በአንዲት ውሳኔ እጁ ላይ ሟሙ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁና ማምሻውን በሶል ጉዳይ ተነስቼ ልል ስለምፈልገው ተለቅ ያለ ነገር እየተብሰለሰልኩ  ሰሞኑን ሁለንተናዬን ወደተቆጣጠረው ድንቅ መጽሐፍ ንባቤ ተመለስኩ፡፡ በረጅም ታሪኩ ውስጥ ካሉት መአት ሰዎች አንዱ ደራሲ በመሆን ዋዜማ ላይ ያለ ወጣት ገጸባህርይ ነው፡፡ የእሱን አንደኛ መደብ ትረካ ተመስጩ እያነበብኩ ነበር፡፡ የታሪኩ ‹‹መቼ›› በ1967 ዓ.ም መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ስለሶል ማሰቤን ሳላቆም እያነበብኩ እጩው ደራሲ የፓለቲካው መጋጋል ካሳሰባቸው እናቱ ጋር ያደረጋት ቁራጭ የስልክ ውይይት ፊት ለፊቴ መጣች፡፡ ‹‹ትጽፋለህ አሁን ድርሰት ምናምን?›› ይላሉ እናቱ፡፡ ‹‹አንዳንዴ›› ይመልሳል፡፡ እናቱ ያኔ ምን አሉ…? ‹‹በል ተጠንቀቅ፡፡ መንግሥት የሚነካ ነገር እንዳታደርግ፡፡ ወሽካታው በዝቷል፡፡ በጥርስህ ንጣት የቀና ያሳስርሃል መጥፎ ጻፈ ብሎ፡፡ ስለፍቅር ብቻ ጻፍ፡፡ ስለ ሌላ ሌላ ጻፍ፡፡ ስለወፎች ጻፍ፡፡ በቃ ብልጥ ሁን፡…..›› ግጥምጥሞሹ በጣም ገረመኝ፡፡ ቀድሞም በ2018  ዓ. ም ‹‹ይዘቱ ተገምግሞ››  የመጽሐፍ ምርቃት መከልከሉንም እንደሌላው ነገር ‹‹ወይ ጉድ›› ብሎ ማለፍ ያለፈለገው አንጎሌ ይህችን የድርሰት ብጣሽ ሲያይ ሃገሬ ዛሬም የኋሊት ጉዞ ላይ እንደሆነች አስታወሰኝ፡፡ የሳንሱር ሸምቀቆ ዛሬም ፈጠራን አንቄ ልግደል፣ ፈጣሪን አስቦክቼ ብእሩን ላንጥፍ ይላል፡፡  መርጠህ ጻፍ ብሎ ይዝታል፡፡ አስኳሉ ይሄ ነው ወዳጆቼ፡፡ ሌላውን ትተን ሃምሳውን አመት ብንቆጥር እንኳን ከመራመድ ይልቅ ባለንበት ተቸንክረናል፤ ሲብስም ወደኋላ ተንሸራተናል፡፡  በዚህ ላይ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መጽሐፍ ጽፎ ለህትመት ማብቃት፣ ብሎም ለአንባቢ ማድረስ በራሱ ተራራ መግፋት ነው፡፡ እልህ አስጨራሽ፣ ተስፋ አስቆራጭ እና እጅግ ፈታኝ ነው! መሰናክሉ መዓት፣ አሳሩ ብዙ ነው። የህትመት ዋጋ የምታውቁት ነው፡፡  አይቀመስም። እድል ሰምሮ አሳታሚ ቢገኝ እንኳን ከመጽሐፍ ሽያጭ ተቆራርጦ ደራሲው ኪስ በሚገባው ሳንቲም እንኳን ክብር ያለው ሕይወት ሊኖር የዕለት ጉርስን እንኳን መሸፈን አይቻልም። የምናደንቃቸው የኪነጥበብ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ‹‹ራበኝ›› እስከማለት የደረሱት ለዚህ ነው፡፡ ከገንዘብ ነክ ፈተናው ባሻገር ደግሞ ሌሎች ያፈጠጡ ችግሮች አሉ፤ ደራሲው ለሰው ከማይታዩ ጠላቶች ጋር በየጓዳው ይታገላል። "ማን ምን ይለኝ ይሆን?" በሚል ፍርሃት ተሸብቦ የራሱን ብዕር ይቆጣል፤ ወቀሳና ውንጀላን ለመሸሽ ራሱ ላይ ማዕቀብ (Self-censorship) ያደርጋል። ይህ ሁሉ ፈተና እንዳለ ሆኖ፣ ይባስ ብሎ ዛሬ በሶል እንዳየነው ያሉ መንግስታዊ እቀባዎች እና ግልጽ ጫናዎች ብቅ እያሉ የፈጠራ ነፃነትን ማነቅ ከጀመሩ ሰንብተዋል። የመንግሥት ተቋማት ዜጎች ምን ማንበብ፣ ምን ላይ መወያየት ወይም የትኛውን መጽሐፍ መመረቅ እንዳለባቸው ለመወሰን ጣልቃ ሲገቡ፣ የግለሰቦችን መጽሐፍትና ዝግጅቶች ብቻ ሳይሆን ነፃ አስተሳሰብን እያፈኑ መሆኑ ግልጽ ነው። ጉዳዩ ከአንድ ደራሲና ከአንድ መጽሐፍ የሰፋ ነው፡፡ መዘዙም ብዙ ነው፡፡ ይሄ አካሄድ ጨቋኝና አፋኝ ነው። የሚያስተላልፈው መልእክትም አደገኛ ነው፡፡  «ስለ እንትን ሳይሆን ስለ እንትን ጻፍ» የሚል አሰራር ጎታችና በዚህ ዘመን መኖሩ የሚያሳፍር አካሄድ ነው!

  • 12 авг.1 749705

    ተቃርኖ +++++ ሰዓቱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ቢልም ካፌው አሁንም በሰው ተሞልቷል። የሚያረገርግ ገላቸው እና ደክሞም የሚያምር ፊታቸው የሚጣራ ሴት አስተናጋጆች የተጠጣ እና የተበላባቸውን ዕቃዎች፣ ሊበሉ የተሰናዱ ምግቦችንና በተስተናጋጆች ፊት የሚከፈቱ መጠጦችን የተሸከሙ መለስተኛ ጠረጴዛ የሚያህሉ ትሪዎችን አየር ላይ በሰቀሏቸው እጆቻቸው ሚዛን አስይዘው፤ በተፋፈጉ ጠረጴዛዎች እና እየተንፏቀቁ በተጠጋጉ ወንበሮች መሃከል ሲሆንላቸው እየተሽሎከለኩ፣ ሲያቅታቸው ከገጠማቸው ጋር እየታከኩና እየተላተሙ ውር ውር ይላሉ፡፡  ዳሌና ደረታቸው ላይ የሚያንዣብቡና በዐይን የሚዳሯቸው ተባዕት ዓይኖች እንዲሁም ገላማጭና ፈራጅ እንስት ፊቶች እንቅስቃሴቸውን ያጅባሉ፡፡ በመሃል አንደኛዋ አስተናጋጅ እንደ አለቃ ተጀንኖ ወደ ቆመው ቦርጫም ሰውዬ ሄደችና - ‹‹ለይኩን መሄዴ ነው›› አለችው፡፡ እቃ ሊያመጡና ሊመልሱ የሄዱ ሁለት ሌሎች አስተናጋጆች-  ‹‹ሆ›› በሚል ተያዩና ከባልኮኒው ጀርባ ባለው ግማሽ በር ሾልከው ወደ ኪችኑ ገቡ፡፡ ‹‹ጭራሽ ለይስሙላ እንኳን አቶ ማለቱን ተወችው ማለት ነው?…እውነትም ማፈር ትተዋል›› አለች አንደኛዋ ቀድሟት ያመለጣትን ሳቅ ስቃ ስታበቃ፡፡ ‹‹እኛም የምንሰጠውን ሰጥተን በአራት ሰዓት  ሺፍት…ለዛውም እያለመጥን ሙሉ ደሞዝ ባገኘን›› አለች ሌላኛዋ በስጨት ብላ፡፡ የከተማዋ  መስተዳደር ከተማዋ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ በርታና ነቅታ እንድታመሽ ካዘዘ ወዲህ ካፌው እንደድሮው በአንድ ሰአት ተኩል አዛግቶ መዘጋቱ ቀረ ። ከሚበልጨለጨው ጎዳና ጋር ሲብለጨለጭ ያመሻል፡፡ ከካፌው ውጭ አንድ ቀጥታ መስመር የመሰለ ቀጭን ወጣት ብርሃን ካጥለቀለቀው አዲሱ ፏፏቴ አጠገብ የደረቁ ከንፈሮቹን በግርምት ከፍቶ ቆሟል።   በስስ ጥቁር ላስቲክ የያዛቸውንና ለቁርስ የገዛቸውን ሶስት ባለ አስራ አምስት ብር አንጀት ጠብ የማይሉ ዳቦዎች ወደደረቱ አስጠግቶ ይዟል፡፡ ውሃው አንዴ ከአረንጓዴ፣ ወዲያው ከቢጫ፣ ደግሞ ከቀይ ቀለም ጋር እየተዋሰበ ሲደንስ ሲያይ ደስ ቢለውም ፏፏቴው የሚረጨው ብርሃን ፌስታል መያዙን አጋልጦ  ለቅጣት እንዳይዳርገው በመሳቀቅ ፌስታሉን ይበልጥ ወደደረቱ ሳበ፡፡ በትርኢቱ ተመስጦ ሳለ ድንገት ሲመጣ ያላየው ሰው እጅ ከኋላ ማጅራቱን ሲነካው በርግጎ ፌስታሉን ወደ ውሃው ወረወረው፡፡ ከእሱ የሚቀጥንና ትከሻው ላይ የተቦተረፈ ቲሸርት ያደረገ ወጣት ስቅቅ ብሎ-  ‹‹ይቅርታ አስደነገጥኩህ እንዴ አባቱ? …ፎቶ አንሳኝ ልልህ ነበር›› ሲለው እሱን ትቶ ከፌስታሉ አምልጠውና የፏፏቴው ቂጥ ላይ ያለችው ሚጢጢ ኩሬ ገብተው ሻይ ውስጥ እንደተነከሩ በመራስ ላይ ያሉ  ዳቦዎቹን እያየ እንባ ተናነቀው፡፡ ማዶ ካለው መንገድ ላይ አንዲት በቄንጥ የለበሰች ወጣት ሴት በብርሃን በተጥለቀለቀው ያማረ አስፋልት ላይ ሰልፊ ፎቶዎችን ትነሳለች። ትስቃለች፡፡ ከንፈርዋን ታሞጠሙጣለች፡፡ ደግሞ ኮስተር፣ ደግሞ ፈገግ ትላለች፡፡ ሲላት ምላሷን ታወጣለች፡፡ በሃሳብ እንደተመሰጠች ሁሉ አሻግራ ባዶ አየር ላይ ታፈጣለች፡፡ ደግሞ የማይታይ እጅ እንደጎነተላት ሁሉ እፍረት ውስጥ የተነከረ ሳቅ ትስቃለች፡፡  በመሃል ስልኳ ነዘራት። ታላቅ እህቷ ነበረች፡፡  "የት ነሽ አንቺ አለሌ? ውሃ መቅዳት ተራሽ ሲሆን አውቀሽ ነው ምታመሺው አይደል?ደሞ ሰፈሩ በሙሉ መብራት ጠፍቷል። ፈጥነሽ ወደ ቤት ነይ። ማጅራትሽን እንዳይሉሽ " ብላት ዘጋችው፡፡ ከእሷ በተቃራኒ ከተዘጋ ሱቅ ስር፣ ሃያ አምስት አመት የማይሞላት እናት ከሁለት ትናንሽ ልጆቿ ጋር ተጠጋግታ መሬቱ ላይ ተዘርፍጣለች፡፡  ‹‹እማማ ዳቦ›› ይላል አፉ የተፈታው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በአይኑ ይሄንኑ ይላታል፡፡ አስር ሰአት ላይ ከመጣች ጀምሮ ካፌው በር ላይ ቆማ ትራፊ ስትለምን አምሽታለች፡፡ ቦርጫሙ ስራ አስኪያጅ ግን መልሱ እንደሁሌው ነበር፡፡ ‹‹ዋቴ ነሽ እንዴ? ስንቴ ልንገርሽ? ትራፊ እንዳትሰጡ ተብለናል…ታስቀጪናለሽ ዞር በይ›› ባለ ሰልፊዋ ወጣት ከተነሳቻቸው ደርዘን በላይ ፎቶዎች አንዱን መርጣ አወጣች፡፡ ምናምኑን በቅልጥፍና ተጭና ትናንሽ ብጉሯን አጠፋች፡፡ ጠይምነቷን አቀላች፡፡ ጥርሶቿን አነጣች፡፡ ከዚያ እንዲህ ብላ ጻፈችና ፎቶውን በየዲጂታል ቤቷ ለጠፈች። ‹‹ቆንጆ ልጅ። ቆንጆ ከተማ።›› ይህ በሆነ ከደቂቃዎች በኋላ ፊልተር ያልነካው ፊቷን እና ሕይወቷን ይዛ ከቅድሙ የረዘመውን የታክሲ ሰልፍ ተቀላቀለች፡፡ 💠💠💠

  • 11 авг.1 76523

    አዲስ ታሪክ/ ነገ 🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋🦋

  • 8 авг.2 98413227

    ‹‹ዲክሺነሪዋ›› ---- ሁለት ዓመት ሊሞላው ሦስት ሳምንት የቀረው… ግን ሳይድህ የሮጠ፣ ሳይኮላተፍ ምላሱ የተሳለ፣ የጨቅላነት ወራትን በችኮላ ዘሎ በቀናት የጎለመሰ የፍቅር ታሪክ አለኝ። ውክቢያችን ጊዜን ለመቅደም ይመስል ነበር። ጊዜ ራሱ ነገረ ሥራችን እያደናገረው «ኧረ ቀስ» ብሎ እስኪያዝንልን ድረስ ለመፋቀር ተጣደፍን። ይሉኝታ እስካጣ ድረስ ስላፈቀርኩት፣ አብሮ አደግ ጓደኞቼና እህቶቼ «ይሄ ነገሩ ልክ አይደለም» ሲሉኝ ክፉውን ላለመስማት ጆሮዬን ደፈንኩ። ከየፖድካስቱ የለቃቀሙትንና «ሬድ ፍላግ» ብለው የሚያውለበልቡትን የ«ተይው» ማስጠንቀቂያ ባንዲራ ላለማየት አንገቴን አዞርኩ፤ ዓይኖቼን ስህተቱና እንከኑን ላለማየት ጨፈንኩ። የኋላ ኋላ ልቤን በእሱ ላይ ሳይሆን «ይሄ ሰው ይቅርብሽ ይጎዳሻል» ባሉኝ በእነሱ ላይ አደነደንኩ። ጭቅጭቅና ንትርካቸው ሲብስብኝ በእሱ ላይ ለሚያቀርቡልኝ ስሞታ ሁሉ መልስ አቀባብዬ መተኮስ ጀመርኩ። ይባስ ብዬ ከእሱ አንደበት የሚወጡ ቃላትን ሁሉ እንደ ልቤ መሻት እየተረጎምኩ ፍቅሬን ለመጠበቅ ነጋ መሸ ላይ ታች ማለት ተያያዝኩ። «አንቺማ እሱን በተመለከተ የራስሽ ዲክሽነሪ አለሽ… እኛ የምንሰማው ሌላ፣ አንቺ የሚገባሽ ሌላ» ብለው እስኪዘባበቱብኝ ድረስ ገፋሁበት። ክሳቸው ብዙ ቢሆንም ዲክሽነሪዋ ግን እውነትነት ነበራት። ከዓለም በተለየ ንግግርና ሁኔታውን፣ ጠባይና አኳሃኑን የምተረጉምባት በፍቅር ብራና በመውደድ ቀለም የጻፍኳት የራሴ ዲክሺነሪ አለችኝ፡፡ ላሳያችሁ…? እነሆ በሆነውና በእኔ መረዳት መሃከል ያለውን ልዩነት ቶሎ ትቀልቡ ዘንድ በሁለቱ አረፍተነገሮች መሃከል ‹‹/››ን አጋድሜላችኋለሁ፡፡ ++++ • ሥራ የለውም። ቤትም አልሠራ። ለሕይወቱ እቅድ አያወጣም። / እንደ ዘንድሮ ሰው ንዋይ ወዳድ አይደለም። ከገንዘብ ይልቅ ፍቅርን ያስቀድማል። • ሁልጊዜ «እስቲ አትድበልበይ ኪሎ ቀንሺ» ይለኛል። / ረጅም ጊዜ እንድኖርለት ስለ ጤናዬ ተጨንቆ ነው። • አብዛኛውን ጊዜውን የሚያጠፋው በቤቲንግ ነው። / እድል ቀንቶት አንዴ ደህና ብር ቢያሸንፍ ዘና ብለን እንኖራለን። • በየቀኑ ይጠጣል። / ከባድ ነገር መስሏችሁ ነው… ? ቢራ እኮ ነው። • ሁልጊዜ አዲስ የንግድ ሃሳብ ያመነጫል። / ውይ ጭንቅላቱ እኮ… ምጡቅ እኮ ነው። • ካመነጫቸው ሃሳቦች አንዱንም አልሞከረም። / ራዕይ ይኑረው እንጂ የሆነ ጊዜ ያደርገዋል… ዋናው ራዕይ ነው። • ሁልጊዜ ዞር ስልለት ስልኬን ይጎረጉራል። / ከልክ በላይ ስለሚወደኝ ነው። • ከጓደኞቼ ጋር እንድወጣ አይፈልግም። / የእኔ ጌታ! ብዙውን ጊዜዬን ከእሱ ጋር እንዳሳልፍ ስለሚፈልግ እኮ ነው። • ስልክ ደውሎ ወይ ቴክስት ልኮልኝ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ካልመለስኩ ይበሳጫል። / ሁልጊዜ እንደናፈቅኩት ነው። • ስልኩን ካላነሳሁ ሠላሳ ጊዜ ይደውላል። / የሆነ ነገር ሆና ይሆን ብሎ ስለሚጨነቅ እኮ ነው። • «ጓደኞችሽ በሙሉ ከእኔ ጋር ባለሽ ነገር ደስተኛ አይመስሉኝም… ይቀኑብሻል» ይለኛል። / ይሄንማ እውነቱን ነው… በጣም ያምራል እኮ… ለራሳቸው ባይመኙት ነበር የሚገርመኝ። • የምለብሰውን የሚመርጥልኝ እሱ ነው። / ፋሽን አዋቂ ስለሆነ ነው። • ጓደኞቼን የሚመርጥልኝም እሱ ነው። / ጥሩ ጥሩ ሰዎችን ያውቃል። • «ከተውሽኝ እራሴን አጠፋለሁ» አለኝ። / የእኔ ማር እስትንፋሱ እኮ ነኝ። • ሳናድደው ግድግዳውን በቦክስ ይለዋል ወይ እቃ ይወረውራል። / ቢያንስ ራሱን መቆጣጠር ይችላል… ቢያንስ እኔን አይመታኝም። • የሆነ ቀን የሆነ ሰውዬ ትኩር ብሎ ስላየኝ ብቻ ተናዶ በጠፊ አጮለው። / የእኔ የወንዶች ቁና… ደስ አይልም? አያኮራም? • ከጠጣ በኋላ ጠብ ይጀምራል። / እሱ ምን ያድርግ… አልኮሉ ነው ሌላ ሰው የሚያደርገው። • ብዙ ጊዜ ለቀናት የት እንዳለ ሳይነግረኝ እልም ብሎ ይጠፋብኛል። / ወንዶች እኮ እንደ እኛ እንደ ሴቶች አይደሉም። ስሜታቸውን የሚያስተናግዱበት መንገድ ከእኛ በጣም ይለያል። አንዳንድ ጊዜ ሰከን ለማለትና ለማሰብ የራሳቸው ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። • እሱ ፈልጎ ካልደወለ እኔ ስደውል ስልኩ ብዙ ጊዜ ዝግ ነው። / የባትሪ ችግር ነው። • የቀድሞ ፍቅረኞቹን በሙሉ እስኪንገሸገሽ ይጠላል፤ እያነሳ ያማርራቸዋል። / እውነቱን እኮ ነው… ለእሱ የሚገቡ ሴቶች አልነበሩም። • የቀድሞ ፍቅረኞቹን "Devil 1," "Devil 2," እና "Devil 3" ብሎ ነው ስልኩ ላይ ሴቭ ያደረጋቸው። / ድንገት ሳት ብሏቸውና ናፍቀውት ቢደውሉ እንዳያነሳ ብሎ እኮ ነው። • ብዙ ጊዜ እኔ ፊት ሌሎች ሴቶችን ያሽኮረምማል። / ተጫዋች ስለሆነ ነው። • ሴትና ወጣት አስተናጋጆች ሲገጥሙን ቅልስልስ እያለ «የኔ ቆንጆ» ይላቸዋል። / አቤት ትህትና! • ኢንስታግራም ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶችን ይከተላል። / አልጎሪዝሙ ነው፣ እሱ ምን ያድርግ? • ሁሉም ሴቶች ግማሽ እርቃን ፎቶ የሚለጥፉና በግብረ ሥጋ የተወለዱ ሳይሆን ተስለው ነፍስ የተዘራባቸው የመሰሉ ናቸው። / ሴቶችን በምንም ሁኔታ መደገፉ ደስ የሚያሰኝ ነው። • ከሌላ ሴት ጋር ወጣ። / የዚያ ሰሞን ራሴን ጣል አድርጌ፣ እሱንም ችላ ብዬው ነበር። ወንዶችም ፍቅር ይፈልጋሉ። • «ፍቅር ካልያዘኝ ሴክስ ባደርግ እኮ ቺቲንግ አይደለም» አለኝ። / ከእሱ አላውቅም። • ሁለት ስልክ ነበረው፤ አንዱን አያስነካኝም። / የማያስነካኝ ስልክ የሥራ ስልክ ስለሆነ ነው። • መአት ጊዜ ብለምነውም ሶሻል ሚዲያ ላይ ፎቶዬን መፖሰት እንቢ አለ። / የግል አደባባይ ማስጣት ስለማይፈልግ እኮ ነው… በዚህ ላይ የሶሻል ሚዲያ ፖስት እውነተኛ ሕይወት አይደለም። ዋናው ላቩ ነው። • ሁለት ዓመት ሙሉ አብረን መሆናችንን በእሱ በኩል ያለ ማንም ሰው እንዲያውቅ አልፈለገም። ከማንም አላስተዋወቀኝም። / ግንኙነታችንን ከሰው ዓይንና አፍ ለመጠበቅ ፈልጎ ነው። ቡዳ ያላየውን አይበላም። • በየቀኑ የምንነሳቸውን ፎቶዎችና ቪዲዮዎች በሙሉ ከስልኩ ማጥፋት ይወዳል። / እኔም እኮ አበዛዋለሁ… ሺህ ፎቶና ቪዲዮ እያነሳሁ የስልኩን ስቶሬጅ አጨናነቅኩበት። • «ጾመኛ ነኝ» ብሎኝ ሊስመኝ ሲጠጋ ግን አፉ ሥጋ ሥጋ ወይ ቅቤ ቅቤ ሽታ ይሸታል። / እግዚአብሔር የልቡን ያውቃል። ዋናው ልብ ነው። • በየወሩ ገንዘብ ከእኔ ይበደራል። / ልንረዳዳ መስሎኝ አብረን ያለነው። • አንድም ቀን የተበደረውን ብር መልሶልኝ አያውቅም። / የእኔ የሆነ ሁሉ የእሱ ነው። • የሆነ ጊዜ የሲቢኢ እና ቴሌብር ፒኖቼን ጠየቀኝ። / በፍቅር ውስጥ መደባበቅ አያስፈልግም… ደግሞ የሴትነት ክብሬን አሳልፌ ለሰጠሁት ሰው ፒን ቁጥሬን ልከልክለው? • ሳይነግረኝ ከወንድሜ ገንዘብ ተበደረ። / እሱ እኮ ቀድሞውኑ ከቤተሰቤ ተቀላቅሏል… ምስኪን አይደል? • ሁለቱንም ዓመት ደጋግሜ አስታውሼው እንኳን ልደቴን ረሳው። / ወንዶች ሁሉ እንዲህ ናቸው፤ ተፈጥሮ ሆኖበት ነው እኮ። • የቫላንታይንስ ዕለትን እንዳትረሳ ብዬ ስንቴ አስታውሼው ረሳው። / ይሄም የወንድ ልጅ ደንቡ ነው። • ብዙ ጊዜ ትዝ የምለው ከእኔ የሚፈልገው ነገር ሲኖር ነው። / ሰበቡ ምንም ይሁን ቢያንስ ትዝ እለዋለሁ። የትም ፍጪው… • አንድ ጊዜ ለሦስት ሳምንት ስልኩን አጥፍቶ ጠፍቶብኝ ሲመጣ አበባ ይዞልኝ መጣ። / በጣም ሮማንቲክ እኮ ነው። • ወደ ቤቴ የሚመጣው ማታ ማታ ብቻ ነው። / የመንገድ መጨናነቁ ጋብ የሚለው ያኔ ስለሆነ ነው። • ሳበሳጨው ብዙ ጊዜ «የሆንሽ ከርከሮ… ከእኔ ውጭ ማንም በእንጨት አይነካሽም» ብሎኛል። / የሆዱን ስለሚናገር ክፉ ይመስላል አይደል… ግልጽ ስለሆነ እኮ ነው። • ደጋግሞ «በእኔ መመረጥሽ መታደል ነው» ይለኛል። / በራስ መተማመኑን ስወድለት! • ብዙ ጊዜ ሲናደድ ይሰድበኛል። / ስሜታዊ ሆኖ እንጂ አስቦበት አይደለም። • አንድ ሁለቴ «በጣም የተማርሽ መሆንሽ አንአትራክቲቭ ያደርግሻል» አለኝ። / ሐቁን ነው የተናገረው… • ሥራሽን ብትለቂስ ብሎ መከረኝ። / እሱ ሊያስተዳድረኝ ፈልጎ ነው። የእኔ ወንዳወንድ… ውድድ! • ብዙ ጊዜ ስለማይረቡ ነገሮች ይዋሸኛል። / ሁሉም ሰው ይዋሻል። • ስለ ትልልቅ ነገሮችም ደጋግሞ ይዋሻል። / መልአክ መስሎ ቢፈጠርም የሰው ፍጹም የለም። • እንጋባለን አይደል ስለው «ጋብቻ እኮ ተራ የወሳኝ ኩነት ወረቀት ነው» አለኝ። / ልክ ነው… እኛ ከቀበሌ ወረቀት በላይ ነን። • ካንዴም ሁለት ሦስቴ «ሴቶች አንዴ ካገቡ በኋላ አሮጊት፣ ዱባ፣ አስጠሊታ፣ ነዝናዛና አሰልቺ ይሆናሉ» ብሎኛል። / ችግር የለም… ሲያገባኝ ሃሳቡን እቀይረዋለሁ። • ልጅስ ስለው «ልጅ መውለድ ማለት የራስን ሕይወት አከተመ ብሎ መፍረድ ነው» አለኝ። / ጊዜ እንስጠው። የወርቅ ፍልቃቂ እምቦቃቅላዎችን ሳስታቅፈው ገና ዛሬ መኖር ጀመርኩ ማለቱ አይቀሬ ነው። • ተው ግን እንጋባ ብዬ ስነተርከው «እግዚአብሔር ሲል አገባሻለሁ» አለኝ። / አሜን። • «እናቴ ግን የምትወድሽ አይመስለኝም» ብሎኛል። / ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ከእናቱ መዳፍ ፈልቅቄ አውጥቼ ከራሴ አጣብቀዋለሁ። • እናቱ አሁንም የሚለብስና የሚበላውን ትመርጥለታለች። / ሴቶችን በጣም በጣም ያከብራል። • አንድ ቀን መንገድ ላይ ያገኘችን እህቱ አምርራ ጠልታኛለች። / ለወንድሟ ተጨንቃ እኮ ነው። አብዛኞቹ እህቶች እንዲህ ናቸው። እኔም ለወንድሜ ሲሆን አራስ ነብር ነኝ። • እሱ እንዳለኝ የቀድሞ ፍቅረኞቹ በሙሉ የለየላቸው ቀውሶች ነበሩ። / ምስኪን የእኔ ጌታ! በመጨረሻ እኔን በማግኘቱ ምንኛ ታደለ። • እሱ እንዳለኝ ሕይወቱን በሙሉ የገጠሙት አለቆች ደደቦች ነበሩ። / ገና ለገና አቅሙን አይተው ቦታቸውን እንዳይቀማቸው መመቀኘታቸው እኮ ነው… አይ ሰው! • በተደጋጋሚ ከቤተሰብ አስተዋውቀኝ ስለው እምቢ አለ። / «ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም አለ ዘፋኙ»። • «ጋብቻ ፍቅራችንን ያበላሸዋል» አለኝ። / በእናቴና በአባቴ አይቼዋለሁ። • «ለማግባት 35 ዓመት እስኪሞላኝ እጠብቃለሁ» አለኝ። / የበሰለ ሰው ውሳኔ ነው። • እርግጥ ስንገናኝ ዕድሜው 38 ነበር። / አሁንም ቢሆን ወጣት ነው። ወንዶች በ80 ዓመታቸው እንኳ ልጅ መውለድ ይችላሉ። • በተዋወቅን በሳምንታችን የእውነት የማፈቅረው ከሆነ አብሬው እንድተኛ ጠየቀኝ። / በጣም ስለወደደኝ እኔም እንዳፈቀርኩት ማረጋገጫ ፈልጎ ነው። • በአንድ ወር ውስጥ አምስት ጊዜ «መለያየት አለብን» ብሎኝ ነበር። / ምን ያህል እንደሚያፈቅረኝ ሲያስብ ፍርሃት ውስጥ ገብቶ ሲርበተበት ያደረገው ነው። • ባለቀስኩ ቁጥር «ነገር ማጋነን እና ድራማ ትወጃለሽ» ይለኛል። / እውነቱን ነው፤ ስሜታዊነቴን መቀነስ አለብኝ። • ሁሌም «በትንሹም በታላቁም ለማልቀስ ሰበብ የምትፈልጊ ሕፃን ስለሆንሽ ካስከፋሁሽ ይቅርታ» ብሎ ይቅርታ ነው የሚጠይቀኝ። / ቢያንስ ይቅርታ እየጠየቀ ነው። • «ሴቶች በሙሉ አንድ ናቸው» ይለኛል። / ከእኔ ውጭ ማለቱ ነው። • «እንደሌሎቹ ሴቶች አይደለሽም» አለኝ። / ልዩ እንደሆንኩ ተሰማኝ። • «ካላመንሽኝ አብረን መቀጠል አንችልም» ብሎ ስለዚህ ጉዳይ ማለቃቀስ እንዳቆም ነገረኝ። / ለወደፊት ትዳራችን ልቤን ከፍቼ እንዳምነውና እንድታመነው እያሰለጠነኝ ነው። • «ጠንካራ ሴት ችግሮችን ትችላለች» አለኝ። / ነፃ የትዳር ሥልጠና እየሰጠኝ ነው። አልታደልኩም? • «ያለ እኔ ምንም አይደለሽም» አለኝ። / እሱ ሲጠፋብኝ ራሴን ማጥፋት ስለምፈልግ የዚህን አባባል እውነተኛነት በራሴ አረጋግጫለሁ። • «በዚህ ዕድሜሽ ማንም አያገባሽም» አለኝ። / በጣም ልክ ነው፤ በሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካሉት የኢንስታግራም ሴቶች ጋር ለመወዳደር በጣም አርጅቻለሁ። • «ችግሮቻችንን ለቤተሰብሽ አታወሪ» አለኝ። / ልክ ነው፤ ለወደፊት ጥሩ ልምምድ ነው። በትዳር ውስጥ ቤተሰብ ጣልቃ ማስገባት ትርፉ ጣጣ ነው። • «ፍቅርማ ትንሽ ማሳመም አለበት» ይለኛል ጎድቶኝ ሳለቅስ። / ይህንን ገና ድሮ ከአስቴር አወቀ ዘፈኖች ነው የተማርኩት። • «ብትወጂኝ ኖሮ ስህተቴን አታይም ነበር» አለኝ። / ልክ ነው፤ እውነተኛ ፍቅር ነውር እና ጉድፍን አያይም። ለማንኛውም ሁለት ዓመታችን ሊደርስ ነው ስለው አሁንም ስለ ትዳር ለመወሰን ዝግጁ እንዳልሆነ ተናገረ።  ልጅ መውለዴ ለውሳኔ ያበቃዋል ብዬ ወሰንኩና ሴት የምታደርገውን አደረግኩ። እና አሁን የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ነኝ። ፍቅሬን ካየሁትና ድምፁን ከሰማሁ ሦስት ወራት አለፉ። ክፉ እንዳላገኘው ተስፋ አደርጋለሁ። ጭንቅ አይችልም እኮ! 📏📏📏📏

  • 7 авг.2 655413

    ‹‹ዲክሺነሪዋ›› ---- «...ሁለት ዓመት ሊሞላው ሦስት ሳምንት የቀረው… ግን ሳይድህ የሮጠ፣ ሳይኮላተፍ ምላሱ የተሳለ፣ የጨቅላነት ወራትን በችኮላ ዘሎ በቀናት የጎለመሰ የፍቅር ታሪክ አለኝ። ውክቢያችን ጊዜን ለመቅደም ይመስል ነበር። ጊዜ ራሱ ነገረ ሥራችን እያደናገረው «ኧረ ቀስ» ብሎ እስኪያዝንልን ድረስ ለመፋቀር ተጣደፍን። ይሉኝታ እስካጣ ድረስ ስላፈቀርኩት፣ አብሮ አደግ ጓደኞቼና እህቶቼ «ይሄ ነገሩ ልክ አይደለም» ሲሉኝ ክፉውን ላለመስማት ጆሮዬን ደፈንኩ። ከየፖድካስቱ የለቃቀሙትንና «ሬድ ፍላግ» ብለው የሚያውለበልቡትን የ«ተይው» ማስጠንቀቂያ ባንዲራ ላለማየት አንገቴን አዞርኩ፤ ዓይኖቼን ስህተቱና እንከኑን ላለማየት ጨፈንኩ። የኋላ ኋላ ልቤን በእሱ ላይ ሳይሆን «ይሄ ሰው ይቅርብሽ ይጎዳሻል» ባሉኝ በእነሱ ላይ አደነደንኩ። ጭቅጭቅና ንትርካቸው ሲብስብኝ በእሱ ላይ ለሚያቀርቡልኝ ስሞታ ሁሉ መልስ አቀባብዬ መተኮስ ጀመርኩ። ይባስ ብዬ ከእሱ አንደበት የሚወጡ ቃላትን ሁሉ እንደ ልቤ መሻት እየተረጎምኩ ፍቅሬን ለመጠበቅ ነጋ መሸ ላይ ታች ማለት ተያያዝኩ። «አንቺማ እሱን በተመለከተ የራስሽ ዲክሽነሪ አለሽ… እኛ የምንሰማው ሌላ፣ አንቺ የሚገባሽ ሌላ» ብለው እስኪዘባበቱብኝ ድረስ ገፋሁበት። ክሳቸው ብዙ ቢሆንም ዲክሽነሪዋ ግን እውነትነት ነበራት።.....» 💖💖💖💖ሙሉ ታሪኩን ነገ ያንብቡ💖💖💖💖

  • 4 авг.3 4391086

    ‹‹የነተበ ዩኒፎርም›› ------- «አንቺ እኮ እንኳን ዛሬ ገና ትንሽ ልጅ ሳለሽ... አምስተኛ ነው አራተኛ ክፍል ሆነሽ ሰው ፊት ቆመሽ መናገር አትፈሪም ነበር... በተለይ ባመንሽበት ነገር ላይ ሳትፈሪ በስንት ሰው ፊት መናገር ታውቂበት ነበር» አለኝ አባባ። «ለምሳሌ ስለ ምን?» ጠየቅኩት። «ያን ጊዜ ትምህርት ቤት ውስጥ የምታደርጓቸው ክርክሮች አንዳቸውም ትዝ አይሉሽም እንዴ?» «እ... እነሱማ ትዝ ይሉኛል አባባ» «እኮ ብትረሺው ነበር የሚደንቀኝ... በተለይ ደግሞ በየዓመቱ የምታደርጉት አንድ ክርክር ነበር... ታስታውሺዋለሽ አይደል እሱን?» «አዎ አባባ... ልርሳውም ብል አታስረሳኝም አንተ... ሁሌ አይደል የምታነሳው... አጋጣሚ እየፈለግክ» «ግርም የሚለኝ እኮ ሁሌም የምትከራከሪው ለዕውቀት መሆኑ ነው... ጎበዝ ተሟጋች ስለሆነች ገንዘብን ደግፋ ትከራከርና እንያት ብትባይም የእኔ ልጅ ግን ወይ ፍንክች...» «ህእ..አዎ...» «ሁሌም የምትወግኚው ለዕውቀት ነበር» «ነገሩማ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ተማሪዎች ከገንዘብ ዕውቀት ይሻላል ነበር የምንለው እኮ አባባ» «ሌሎቹ እንኳን ለአፋቸው ይበሉት እንጂ እንዳንቺ ነጥብ ይዘው አይሟገቱለትም ነበር...» አለኝ። «አይ... ነገሩስ ሁሉም ተማሪ ዕውቀት ይበልጣል ባይ ነበር» አልኩት። « ለምን ሲባሉ ግን እንዳንቺ አጥጋቢ መልስ ነበራቸው?» አለ። «አጥጋቢ መልስ ኖራቸውም አልኖራቸውም ትምህርት ቤት ሆነው ‘ከዕውቀት ገንዘብ ይበልጣል’ ማለት የሚያሳፍር ስለሆነ ለዕውቀት ማገዛቸው የማይቀር ነው» አልኩት። ከሁለት ክፍሏ የቀበሌ ቤታችን ደጃፍ ተቀምጠን ነበር የምናወራው። አባባ የተቀመጠበት አሮጌ የእንጨት ወንበር በተንቀሳቀሰ ቁጥር ያቃስታል። እሱ በወጣትነቱ፣ እኔ በጨቅላነቴ እዚሁ ወንበር ላይ ተቀምጦ በእግሩ ላይ አሳፍሮኝ ቼ ፈረሴ ሲያጫውተኝ የነበረን ትዝታ ዛሬም ውል ይለኛል፡፡ ከወንበሩ እና ከእሱ የትኛው ቀድሞ እንዳረጀ ባላውቅም ሁለቱም ግን የማላውቀውን የድካም ድምጽ ማውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሁለት ቤት ዘሎ የሚገኘው ሌላ የቀበሌ ቤት የምትኖረው ጎረቤታችን ተሊሌ የአራጣ አበዳሪው ቀኝ እጅ ነው ከሚባለው አላምረው ጋር በውሉ የማይሰማኝ ነገር እየተሸቆጠቆጠች ስታወራ ይታየኛል፡፡ አሁንም አሁንም ጎንበስ እያለች ደጋግማ «እሺ... እሺ አልኩዎት እኮ... ሰማሁ» ስትል ግን ጆሮዬ ገባ፡፡ አላምረው በዚያ ግዝፈቱ ቁልቁል ሲያያት ቆይቶ፣ «እሺ እሺ አትበይኝ አንቺ ሴት... ስትወስዱ ተቅለስልሳችሁ መልሱ ስትባሉ ልባችሁ ያብጣል... ያስያዛችሁትን አምጡ ስትባሉ ደግሞ መሽቆጥቆጥ... የዛሬ ሳምንት ከነወለዱ ካልመለስሽ የሚመጣውን ቻይው... ውርድ ከራሴ» ብሎ ዝቶባት ሄደ፡፡ አባቴ ቀጠለ፡፡ «እዚያ ክርክርሽ ላይ በየዓመቱ ደጋግመሽ ስትይ የነበረው ነገር ትዝ ይልሻል?» ሐሳቤን ከተሊሌ እና አላምረው ንትርክ ነጠቅኩና ወደ አባቴ መልሼ፣ «እንጃ... ምን ነበር የምለው አባባ?» አልኩት፡፡ «‘ለአንድ ሰው ዛሬ ገንዘብ ብትሰጠው ነገ ያልቅበታል፤ ዕውቀት ብትሰጠው ግን—’» ንግግሩን አቋርጦ አየኝ። «‘—ለዘላለም አብሮት ይኖራል’» አልኩት። ፈገግ አለ። «አዎ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ አብሮት ይኖራል።» «ሌላ ደግሞ ምን ትዪ ነበረ መሰለሽ... ‘ዕውቀት አይሰረቅም፤ ገንዘብ ግን በሌባ ይሰረቃል’» «እህ... አዎ፣ ብያለሁ» አልኩት። «ይህንን ሁሉ ነገር እኮ ሸምድጄ ነበር የምቀርበው አባባ» ብዬ አከልኩ፡፡ «‘ዕውቀት ብል አይበላውም፤ ዕውቀት አይነቅዝም’ የሚለውንስ... አጥንተሽው ነው?» «ታዲያስ አባባ» «ይሄኛውስ ከእነዚያ የምትወጃቸው መጻሕፍት ከአንዱ የቀሰምሽው መሰለኝ» «አዎ፣ የጋሽ ከበደ ሚካኤል መጽሐፍ ይመስለኛል» አልኩት። «እኮ የአዋቂ መጽሐፍ» አለኝ። «እህምም...» አልኩ። ይህን ጊዜ ሌላው ጎረቤታችን ገብሬ ከርካሳ ላዳውን ከእኛ በጥቂት እርምጃዎች ርቀት አስጓርቶ ካቆመ በኋላ፣ በጥድፊያ ወርዶ በከፊል የዛገ የሹፌሩን በር በእርግጫ መታው። ክፉኛ የተበሳጨ ይመስላል፡፡ ፊቱንና ሁኔታውን አየሁና «ምነው ገብርዬ... ደህና አይደለህም እንዴ?» አልኩት ጮክ ብዬ። «ምን ደህንነት አለ?... ለአሳር የፈጠረን ሰዎች... ይሄ እርጉም መንግሥት... ነዳጅ ድጋሚ ጨመረ፤ አልሰማችሁም እንዴ?» አለኝ ከቅድሙ ትንሽ ሰከን ባለ ሁኔታ፡፡ አለመስማቴን ጭንቅላቴን በመነቅነቅ እንደነገርኩት ወደ ቤቱ የምታስገባውን ሁለት ሰው ጎን ለጎን የማታሳልፈውን ቀጭን መንገድ ይዞ ተሰወረብኝ፡፡ የተቀመጥኩበት ድንጋይ ላይ ለመመቻቸት ሞከርኩ፡፡ አባቴ ምንም እንዳልተፈጠረ ጨዋታችንን ቀጠለ፡፡ «ከልጅነትሽ ጀምሮ መጻሕፍትን ትወጂ ነበር። እናትሽ ይሄን መብራት ሌሊቱን ሙሉ እያነደደች ልታሳብደኝ ነው ብላ ስታጠፋብሽ እንኳን እያለቀስሽ ነበር ከመጻሕፍትሽ የምትለያዪው...» አለ። «መጽሐፍት ወደሚወስዱኝ ቦታ መሄድ ደስ ይለኝ ስለነበር እኮ ነው አባባ... በነጻ ጉዞ በለው... እኛማ ነጭ ደሃ አይደለን… ከጎረቤት ቤት ውጪ የት ሄደን እናውቃለን?...» አልኩት። «ታዲያ አሁንስ?» አለኝ። «አሁን... አሁንም አንዳንዶቹ መጽሕፍት ደስ ወደሚል ስፍራ ይወስዱኛል። ግን አደግኩ አይደል…እንደ ልጅነቴ በመጽሐፍት በኩል ከእውነተኛው ዓለም ማምለጥ አልችልም» አልኩት ትካዜ በተጫነው ድምጽ። ፈገግ አለ። «ታዲያ አሁን ስታደጊ ዕውቀት ከገንዘብ ይበልጣል ማለትሽ ስህተት ሆኖ ታየሽ እንዴ ልጄ?» «እንደሱ ማለቴ አይደለም አባባ፤ ግን...» አልኩት ዓይኖቼን ወደ ትንሽዋ የሸምሱ ሱቅ ወርውሬ፡፡ መምህሯ ትርንጎ ሰሞኑን ለመጣው ሱቁን የያዘ አሥራ ሁለት ዓመት ለማይሞላው ልጅ የተጣጠፉ ብዙ ብሮች ስትሰጠው አየሁ፡፡ ትርንጎ በእጇ የሰጠችውን ገንዘብ በዓይኖችዋ መልሳ ልትቀማው የፈለገች ይመስል እጅ እጁን ስታይ ልጁ ዘመኑን ሙሉ ብር ሲቆጥር እንደኖረ ሰው በፍጥነት ይቆጥራል። የተጠራቀመ ዱቤ እየከፈለች መሰለኝ፡፡ ወደ አባቴ ተመለስኩ፡፡ «አየህ አባባ፣ ትምህርት ቤት ሆነን ዕውቀት ከገንዘብ ይበልጣል ስንል ገንዘብ በዕውቀት ይገዛል የሚል እምነት ስለነበረን ነው። እናንተም ያስተማራችሁን ያንን ነው... ‘የተማረ ወድቆ አይወድቅም’ እያላችሁ... ትምህርት ጨርሰን ሥራ ስንፈልግ ግን ዘመን ተቀይሮ ጠበቀን፡፡ ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ሳታውቅ ገንዘብ ማከማቸት በዕውቀት የሚገኝ ገንዘብን ሲቀድመው ደረስን... ‘ከአሥር ዲግሪ አንድ ግሮሰሪ’ ይሉት አባባል ጋር ተዋወቅን» አባቴ ዝም አለ፡፡ «ከዕውቀት የሚቀድሙና የሚበልጡ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ኑሮ አስተማረን አባባ» አልኩት። «እንደ ምን ያሉ ነገሮች?» አለኝ። «እንደ ሆድ፤ እንደ የቤት ኪራይ፤ እንደ ታክሲና ባስ ሰልፍ... እኔማ ከፍ ስል ብዙ ነገር ገባኝ አባባ... ሴት ልጇ ትምህርት ቤት «ገንዘብ ምንም አያደርግም፣ ዋናው ዕውቀት ነው» ብላ ደረቷን ነፍታ እንድትከራከር ስትል የጋብቻ ቀለበቷን ሸጣ ደህና ትምህርት ቤት ያስገባቻት እናት እንደነበረችኝም ሳድግ አወቅኩ...» አባባ ለዚህ መልስ አልመለሰልኝም። «እስቲ ሬዲዮዬን አምጪልኝ» አለኝ፡፡ ተነስቼ ወደ ቤት ገባሁና ይዤለት መጣሁ፡፡ ዜናው የነዳጅ ዋጋ እንደገና መከለሱን እያወጀ ነበር። «ሰማኸው አባባ? ለካ ገብሬ እውነቱን ነው... ነዳጅ ድጋሚ ሊጨምር ነው» አልኩት። «አዬ፣ እሱ ጨመረ ማለት ደግሞ የሁሉም ነገር ዋጋ ይተኮሳል ማለት ነው» አለኝ ተከዝ ብሎ። ለጥቂት ጊዜ የቀለብላባውን ዜና አንባቢ ድምጽ እየሰማን በዝምታ ተቀመጥን። «ያልሽውን በደንብ አስቤበታለሁ ልጄ... ግን ዛሬም ቢሆን ዕውቀት ካለሽ ገንዘብ ማግኘት ትችያለሽ» አለኝ። «አዎ... እሱማ እችላለሁ፤ ግን—» አልኩት። «ምን ግን አለው? ... ይሄው ስንት ዘመን ያስጨበጨበልሽን የክርክር ችሎታሽን እኔ በስተርጅና አፈረስኩብሽ አየሽ... ድሮ ነበር ልክ የሆንሽው... ዕውቀት ከሁሉም ይቀድማል» አለኝ። «አይ አባባ ረሃብ ግን ከሁሉም ነገር ይቀድማል» አልኩት። ዞር ብሎ በቅሬታ አየኝ፡፡ የተናገርኩት ነገር አላስደሰተውም። የቤት ውስጥ ነጠላ ጫማውን ማስተካከል ባያስፈልገውም፣ ዝቅ ብሎ አስተካከለው። «ሰማያዊ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሜ ትዝ ይልሃል አባባ?» አልኩት። «እማማ አበሳዋን አይታ የግል ትምህርት ቤት እንዳስገባችኝ የተሰፋልኝ?» «በደንብ ነዋ!» አለኝ። «እንደሌሎቹ ልጆች ቅያሪ ስላልነበረኝ ኮሌታውና እጁ ላይ በሃይል ነትቦ ነበር። ሌሎች ሁለት፣ እንዲያውም ሦስት ዩኒፎርም ነበራቸው። ስለ ዕውቀት ከገንዘብ መብለጥ ለመናገር ክፍል ተማሪ ፊት ስቆም ስለሚያሳቅቀኝ መቀደዱን እንዳያዩብኝ አጣጥፈውና በእጄ እሸፍነው ነበር» አልኩት። ምንም አላለም። «የዚያን ቀን በደንብ ተከራክሬ ክፍሉን ሁሉ ስላሳመንኩ ቲቸር ራሱ በጣም ነበር ያጨበጨበልኝ» ብዬ ጨመርኩ። «ግን በዚያው ቀን ምሳ ሰዓት ላይ ጓደኞቼ በሙሉ ላዛኛ፣ በርገር፣ ፓስታ አልፎርኖ ይዘው መጥተው የቱን እንብላ ሲሉ፣ እኔ የምሳ ዕቃዬ ውስጥ ያለውን ሽሮ ከፍቼ ማሳየት ስላፈርኩ ‘አልራበኝም’ ብዬ ወደ ሽንት ቤት ሄጄ አልቅሼ ነበር» ረጅም ዝምታ ሰፈነ፡፡ ሬዲዮው ላይ ዜናው አብቅቶ የመሐሙድ አሕመድ ትዝታ ዘፈን ይጫወታል፡፡ የሸምሱ ሱቅ በዱቤ ጠያቂዎች ተወሯል፡፡ አባቴ ጉሮሮውን ጠረገና፣ «ግን እኮ ልጄ እነዚህ ትንንሽ ነገሮች ናቸው...» አለኝ። «ትንንሽ ነገሮች አይደሉም አባባ» አልኩት እንባ እያነቀኝ። «ወቸው ጉድ! አየሽ እንዴት እንዴት አድርገሽ ነገሩን እንዳሰካካሽው... አይ የእኔ ልጅ... ልጄ ሳትሆኚ የክፍል ጓደኛዬ ብትሆኚና አሁን የተከራከርሽውን ክርክር ብሰማ በእርግጠኝነት አጨበጭብልሽ ነበር» አለኝ ፈገግ ለማለት እየታገለ፡፡ ሳቅ ከማለቴ ተሊሌ ሻንጣ ሙሉ ልብስና ልጇን አንጠልጥላ በችኮላ መሪውን እየቀጠቀጠ ወደሚጠብቃት ገብሬ ሄዳ ላዳ ታክሲው ውስጥ ስትገባ አየሁ፡፡ 📏📏📏📏

  • 3 авг.3 107541

    አባቴ ምንም እንዳልተፈጠረ ጨዋታችንን ቀጠለ፡፡ «ከልጅነትሽ ጀምሮ መጻሕፍትን ትወጂ ነበር። እናትሽ ይሄን መብራት ሌሊቱን ሙሉ እያነደደች ልታሳብደኝ ነው ብላ ስታጠፋብሽ እንኳን እያለቀስሽ ነበር ከመጻሕፍትሽ የምትለያዪው...» አለ። «መጽሐፍት ወደሚወስዱኝ ቦታ መሄድ ደስ ይለኝ ስለነበር እኮ ነው አባባ... በነጻ ጉዞ በለው... እኛማ ነጭ ደሃ አይደለን… ከጎረቤት ቤት ውጪ የት ሄደን እናውቃለን?...» አልኩት። «ታዲያ አሁንስ?» አለኝ። «አሁን... አሁንም አንዳንዶቹ መጽሕፍት ደስ ወደሚል ስፍራ ይወስዱኛል። ግን አደግኩ አይደል…እንደ ልጅነቴ በመጽሐፍት በኩል ከእውነተኛው ዓለም ማምለጥ አልችልም» አልኩት ትካዜ በተጫነው ድምጽ። ፈገግ አለ። 📏📏📏 ሙሉ ታሪኩን ነገ ይጠብቁ።

  • 31 июл.3 974661

    የተወደዳችሁ! የምታዩዋቸው ስምንት ዥዋዥዌዎች ለንባብ ለሕይወት ካመጣሁዋቸው የሁለተኛ እትም የመጨረሻዎቹ ቅጂዎች ናቸው። ዕድሜ ለእናንተ ፈጥነን ያዘዝነው ሶስተኛ እትም አሁን እጄ ገብቷል። ኑ! ሸምቱ! ተጫወቱ! ለዓመታት ለለገሳችሁኝ ድጋፍና ፍቅራችሁ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ! 😘😘😘

  • 30 июл.3 7548

    видео или голосовое, без подписи

  • 30 июл.3 883488

    የተወደዳችሁ ንባብ ለሕይወት ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 23 ተጀምሯል። እኔም  ባለቤቴም መጽሐፎቻችንን ይዘን ተሰይመናል። ገና ወደ አዳራሹ ስትገቡ ፊት ለፊት ዱቅ ብለን ታገኙናላችሁ። ነገ ዓርብ ሐምሌ 24 ከቀኑ 10 ሰዓት ብትመጡ ደግሞ ዋልያ መጽሐፍት ባዘጋጀው ያማረ ስፍራ የፊርማ ስነስርዓት ይኖረናል። 🫶🫶🫶🫶

  • 29 июл.3 77216715

    ሩት፣ ናቲ እና የወር አበባ ( የመጨረሻው ክፍል) ++++++ ከሁለት ቀን በኋላ ናቲ ደወለልኝ። ከዚህ በፊት ያወራነው በሩት ስልክ ስለነበረ የእኔን ስልክ ቁጥር እንዴት እንዳገኘ አላውቅም። «ፂዮንዬ» አለኝ። ዬ? ግራ ተጋብቼ፣ «ሃይ ናትናኤል ደህና ነህ?» አልኩት። በእኔ ቤት ስሙን ባለማቆላመጥ እየቀጣሁት ነበር። ‹‹ደህና ነኝ ፂዮኔ›› ኔ? ዝም ስለው ‹‹እንዴት ነሽ?›› አለኝ። «ምን እንዴት ነሽ አለው… ተጨንቄአለሁ» አልኩ ቆጣ ብዬ። መልስ አልሰጠኝም። «ለምን ደወልክልኝ?» «እ… ሩት እንዴት ናት ብዬ ልጠይቅሽ ነው…።» «ታዲያ እሱን ራሷን ሩትን መጠየቅ ትችል የለ እንዴ?» «አይ… ስልኬን አትመልስም…» ጭጭ አልኩ። ረጅም ትንፋሽ ወሰደ። በዝምታዬ ጸናሁ። «ሩትን በተመለከተ በጣም መአት ስህተቶችን እንደሠራሁ አውቃለሁ» አለ ድምጹን ከማውቀው አለስልሶ። «ግን የሆነው አንዴ ስለሆነ በምችለው ሁሉ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ። ደግሞ ማን ያውቃል… ይሄ ነገር የተፈጠረው እግዚአብሔር አብረን እንድንሆን ስለፈለገ… ሊያጣምረን ፈቃዱ ሆኖ ሊሆን ይችላል።» እግዚአብሔር ደግሞ እዚህ ውስጥ ምን አገባው? ልለው እየፈለግኩ «እና ታዲያ ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው?» ስል ጠየቅኩት። «አብሬያት… ከጎኗ መሆን ነዋ። ኃላፊነቴን መወጣት። አስፈላጊ ከሆነ መጋባትም እንችላለን።» አስፈላጊ ከሆነ መጋባትም እንችላለን ሲል የድምጹ ስሜት ‹‹እንግዲህ ቀዶ ጥገና ያስፈልግሃል ካላችሁኝ ምን አደርጋለሁ… ቅደዱኝ›› የሚል ሰው ይመስላል። አማራጭ አጥቶ የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ሰው። ሩት ጸነሰችም አልጸነሰችም ለምን ከእሱ ጋር ሕይወት መመስረት እንዳልፈለገች አሁን ፍንትው ብሎ ታየኝ። «እሷ ግን አንተን ማገባት የምትፈልግ አይመስለኝም» አልኩት ጨከን ብዬ። «ያም ሆነ ይህ…» አለ ከጥቂት ዝምታ በኋላ፣ «አሁን ዋናው ጉዳያችን እሱ አይመስለኝም… ከዚያ የሚቀድም ነገር አለ አይደል?» በዚህ አባባሉ ተስማማሁ። +++ ከዚያ በኋላ የሩት የወር አበባ መቅረት የቡድን ፕሮጀክት ሆነ። እንደ እናት ሆና ላሳደገቻት ታላቅ እኅቷ ስትነግራትማ ነገሩ ተባባሰ። በወንድ የተማረሩ ሴት ማህበርተኞችዋን ምክር ተጣረሱ ወይ ተጣለዙ ሳትል ቃል በቃል እያመጣች ትግታት ጀመር፦ «ቀረፋ ጠጪ።» «ቀረፋ የሚባል እንዳትጠጪ።» «እስቲ ዞር ዞር በይ፤ አትጎለቺ።» «ምንድነው እንዲህ መቅበዝበዝ… እስቲ አረፍ በይ።» «ገላሽን በሙቅ ውሃ እንዳትታጠቢ።» «ቀዝቃዛ ሻወር አትውሰጂ።» «ምን ማድረግ እንዳለብሽ ካሁኑ አስቢበት።» «አትጨነቂ።» በተለይ የመጨረሻው ምክር ምንም የማይጠቅም ነበር። በዚያ ሰሞን ሩት በቦርሳዋ ውስጥ ሞደስ ይዛ መዞር ጀመረች። ይህንን የምታደርገው ተስፋ ሰንቃ ይሆን ተስፋ መቁረጥ አላውቅም። በሦስተኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነገሩ አስቂኝ ባህርይ መያዝ ጀመረ። ‹‹ፔሬድ ትመጣለች አትመጣም›› በሚል ሚጢጢ የገንዘብ ቁማር አደራን። ሽንት ቤት በገባች ቁጥር ‹‹መጣች›› ‹‹አልመጣችም›› የሚል የውርርድ ጨዋታ ጀመርን። አንድ ቅዳሜ ቤቷ እያለሁ ናቲ ግዙፍ የአበባ እቅፍ ላከ። «አልቀበልም» ብላ ኮስታራውን ዘበኛ «ውስደው» አለችው። ‹‹ብሩ ነበር እንጂ ይሄ ነገ አፈር የሚሆን ቅጠል ምን ያደርግልኛል›› ብሎ እያጎረመረመ ሄደ። በሌላ ቀን ደግሞ ምግብና አይስክሬም እንደላከላት ነገረችኝ። እሱንም ለዘበኛው ሰጠችው። ያኔ አላጉረመረመም። በቀን አስር ጊዜ በሚልካቸው ቴክስቶቹ «ማንኛውም ነገር ቢከሰት ለዘልአለም ከጎንሽ ነኝ» ብሎ አተተ። «እኔስ ታዲያ የምፈራው እሱን አይደል… ? ካንተ ጋር ለዘልአለም መሆን» ብላ መለሰችለት። በሚቀጥለው ሳምንት አርብ ምሽት ቤቴ ተመቻችቼ በተቀመጥኩበት ደወለችልኝ። «አሁኑኑ ነይ» አለችኝ። ስሮጥ ቤቷ ደረስኩ። ገርበብ ብሎ የተከፈተ በሯን ገፍቼ ወደ ውስጥ ስገባ መታጠቢያ ቤቷ ወለል ላይ ሙሉ ቱታ ለብሳ ዝርፍጥ ብላ፣ ትከሻዋ ላይ ፎጣ ጣል አድርጋ አገኘኋት። የምትለኝን ለመስማት ፈራሁ፤ ግን ከመጠየቅ ውጪ ምርጫ አልነበረኝምና «ሩትዬ… ምነው መሬት ላይ… ምን ሆንሽ?» አልኳት። አንገቷን ቀና አድርጋ ድካም ያረበበበት ፊቷን እያሳየችኝ «መጣች እኮ» አለችኝ። ለአፍታ ያለችኝን ነገር መረዳት አቅቶኝ ነበር። ከዚያ ግን ገባኝ። «ፔሬድሽ?» አልኳት በድንጋጤ የደረቀ ጉሮሮዬን ጠርጌ። «አዎ…» «መቼ?» «ልክ ስደውልልሽ ፂዬ» የመታጠቢያ በሩን ፍሬም ተደግፌ የእፎይታ ሳቅ ሳቅኩኝ። ሩት አብራኝ አልሳቀችም። ወለሉ ላይ እንደተቀመጠች በዝምታ አቀረቀረች። «እንኳን ደስ አለሽ ሩትዬ» አልኳት። «ከማይሆን ሰው አላረገዝሽም።» «ተይ አትቀልጂ ፂ» አለችኝ። «እየቀለድኩ አይደለም። ይሄ እኮ ኡፎይ የሚያስብል ዜና ነው… አይደል እንዴ?» ዝም ብላ በተቀመጠችበት ጀርባዋን ግድግዳው ላይ አስደግፋ ዓይኖቿን ጨፈነች። ግራ ገባኝ። «እፎይታው ነው ያስጠላኝ ፂ» አለች በለሆሳስ። «እ… እንዴት… ለምን?» «ምክንያቱም ከደህና ሰው ባረግዝ ኖሮ ወልዶ መሳሚያዬ ነበራ… ማለቴ… ሠላሳ ሊሞላኝ ሁለት ወር እኮ ነው የቀረኝ… እንኳን ያላረገዝኩ የምልበት የአፍላነት እድሜ ላይ አይደለሁም።» ምንም አላልኩም። የመታጠቢያ ቤቱ ፍሎረሰንትና ነጭ መብራት አጥበረበረኝ። የተዘጋው የሽንት ቤት መቀመጫ ላይ ተከፍቶ የተተወው የሞደስ ፓኬት፣ መሬት ላይ አጠገቧ የተቀመጡት ስልኳ፣ ግማሽ ባዶ የውሃ ብርጭቆ እና አፈ ክፍቱን የቆሻሻ መጣያ በተራ በተራ አየሁ። የቤት ውስጥ እርግዝና መመርመሪያን ይዘው የነበሩትን ሳጥኖች ቃኘት አደረግኩ። የመጨረሻውን መመርመሪያ መቼ እንደተጠቀመችና በእሱና አሁን በከፈተችው የሞደስ ፓኬት መሃከል የምን ያህል ጊዜና ስሜት ርቀት እንዳለ ለማስላት ፈለግኩ። ሙሉ በሙሉ በተከፈተችው ትንሿ የመታጠቢያ ቤቷ መስኮት በኩል በሚያባባ ሁኔታ የሚያለቅስ ህጻን ልጅ ድምፅ አፍልኮ ገባ። ሩት ዓይኖቿን ከፈተች። «ከዚህ ሁሉ የጭንቅ ጊዜ በጣም ደባሪው ነገር ምን እንደነበር ታውቂያለሽ?» ሳታየኝ ጠየቀችኝ። «እ… አላውቅም።» ‹‹እንደዚያ ያስፈራኝ ማርገዜ አልነበረም… ቢሆንማ ኖሮ አሁን ደስ ይለኝ ነበር… የፈራሁት ሕይወት በሲምፕል ስህተት በስንት አበሳ ካመለጥሽው ወንድ እግር ስር እንዴት በቀላሉ ልታነጥፍሽ እንደምትችል ስላየሁ ነው…» ምንም ማለት አላስፈለገኝም። እሷ ሻወር ስትወስድ እኔ ወደ ኩሽና ሄጄ ሻይ አፈላሁ። በፎጣ ታሽጋ ስትወጣ ወደማውቃት ሩት የተመለሰች ያህል ቅልል ብላ ታየችኝ። የቀይ ዳማ ፊቷ እንደ ድሮው ያበራል። ልብስ ለብሳ ወደ ሳሎን እንደተመለሰች ያቀረብኩትን ሻይ በዝግታ መጠጣት ጀመረች። «እና አሁን ለናቲ ምን ልትነግሪው አሰብሽ?» ስል ጠየቅኳት። «እውነቱን።» «እውነቱ ምንድን ነው?» «እርጉዝ እንዳልሆንኩ ነዋ።» «ሌላኛውስ እውነት?» መልሱ እዚያ ያለ ይመስል ወደ ሲኒዋ ውስጥ ተመለከተች። «ደም ስጥ እንደተባለ ሰው አገባሻለሁ ሲለኝ ለእኔ ምንም ፍቅር እንደሌለው እንዳወቅኩና እንደቆረጠልኝ… ሜይቢ…» አለች። ጭንቅላቴን በስምምነት ነቀነቅኩ። «አስቢበትና ነገ አውሪው» ስላት አሻፈረኝ ብላ እኔ እዚያ እያለሁ ቴክስት ልትልክለት ስልኳን አነሳች። ከመላኳ በፊት ድምፅ አውጥታ ስላነበበችልኝ የላከችለትን መልእክት አውቃለሁ፦ «ሃይ ናቲ… እርጉዝ አይደለሁም። ደግሞም እባክህን እኔን ማጋባት ትልቅ መስዋዕትነት መክፈል እንደሆነ አድርገህ ማውራትህን አቁም። ደስ አይልም። መልካም አዳር - መልካም ኑሮ።» ከላከችው በኋላ ለጥቂት ጊዜ የስልኳን ስክሪን በዝምታ ተመለከተች። «ትንሽ አበዛሁት እንዴ?» አለችኝ። «ሲያንሰው ነው ባክሽ…» አልኳት። ከአሥር ደቂቃ በኋላ መለስ ሰጣት፦ «ሩትዬ ደህና በመሆንሽ ደስ ብሎኛል። ነገሩን አባብሼው ከሆነ በጣም ይቅርታ።» ካነበበችልኝ በኋላ ስልኩን ባፍጢሙ ጠረጴዛው ላይ ደፍታ፦ «ይሄኔ ለጥቂት ተረፍኩ ብሎ እየጠጣ ነው… በእሱ ቤት አለሁልሽ ብሎ ወንድ ወንድ ተጫውቷል» አለች። «ያው መቼስ?» «ምንም ያው መቼስ የለውም» አለች። «ሲፈልግ ታንቆ ይሙት።» +++ ከሳምንት በኋላ ሩት ፀጉሯን ተሰራች፤ ናቲን ሁሉም ቦታ ብሎክ አደረገችው። +++ ሩት አሁን ደህና ትመስላለች። ምናልባት ከደህናም በላይ ሳትሆን አትቀርም። ነገር ግን አልፎ አልፎ፣ ሻይ እየጠጣን ሳለ ጨዋታው ወደ የቀድሞ ፍቅረኞች፣ ወደ ልጅ መውለድና እናት መሆን የሄደ እንደሆነ ያንን ከባድ ወር ታነሳዋለች። «ማህፀኔ ከናቲ ጋር ለዘልአለም ሊያጣብቀኝ የሞከረበት ጊዜ ትዝ ይልሻል?» ብላ ትስቃለች። «አዎ» ብዬ በሳቅ አጅባታለሁ። «ዘግተሽ የወጣሽውን በር አስከፍቶ ከውስጥ ሊዘጋብሽ ነበር» ብዬ እጨምራለሁ። የሆነው ሆኖ ሩት የናፈቀችውን የወር አበባዋን ተቀብላ የጠላችውን ናቲን ከሕይወቷ እስከወዲያኛው ያስወጣችው እንዲህ ነበር። 📏📏📏📏

  • 28 июл.3 3341228

    (ከላይ የቀጠለ) ----- በቀጣዮቹ ቀናት ሩት ከእንቅልፍ ርቃ ሌሊቱን ሙሉ እርግዝናን አስመልክቶ ያለ እረፍት ጉግል የምታደርግ ሰው ሆና አረፈችው። እያንዳንዱ የማርገዝ ምልክት የታየባት ይመስላታል። መጠነኛ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ፣ ራስ ምታት፣ የጡት ሕመም፣ ሌላም ሌላም… እንደ ኢንተርኔት ከሆነ ሁሉም በእርግጠኝነት የእርግዝና ምልክት ነው። ኤአይማ አቅሏን ሊያስታት ደረሰ። «ያረገዝኩ ይመስልሃል?» ስትለው «አዎ»፣ «ያላረገዝኩ ይመስልሃል?» ስትለውም «አዎ» እያለ ውዥንብር ውስጥ ከተታት። ከሥራ በኋላ ማታ ማታ ሰው ዳቦ እንደሚገዛው ፋርማሲ እየቀያየረች የእርግዝና ምርመራ ገዝቶ ወደ ቤት መግባት አመሏ ሆነ። ውጤቱ ግን አንድና ተመሳሳይ ነበር፦ ኔጋቲቭ። «ምናልባት እኔ ለየት ካሉት ሴቶች የምመደብ እሆን?» አለችኝ አንድ እሁድ ማታ በስልክ። ድምጿ ቅዝዝ ብሏል። «ምን ዓይነት ሴቶች?» «ዘጠኝ ወር ሙሉ በምስጢር እርጉዝ ሆነው የሚቆዩ ሴቶች አሉ ይባላል…» «ሳያውቁት ማለትሽ ነው?» «ኖ… ቴስት ሁሉ የማያየው እርግዝና የሚከሰትባቸው… ሜዲካል ሚራክል ነው የሚል ነገር አንብቤ ነበር።» «ሩት፣ አንቺ እንደዚያ አትመስይኝም።» «ግን ብሆንስ?» ----- ጊዜው ሲገፋ «ካደረግነው ሁሉ የተለየ ነገር ማድረግ አለብን» ብዬ ወተወትኳትና ፊጋ አካባቢ ከሚገኝ የማህፀን ሐኪም ጋር ቀጠሮ ያዘች። አብሬያት ሄድኩ። የሴት ጓደኝነት በብዙ ነገር ይፈተናል። አንደኛው በአንድ እጃቸው ያበጠ ሆዳቸውን ደገፍ አድርገው በሌላኛው ደግሞ የባላቸውን እጅ ይዘው ወዲህ ወዲያ በሚሉ ነፍሰ ጡር ሴቶች መሃከል «አርግዤ ባልሆነ» ብላ ጸሎት ቢጤ ከምታጉተመትም ጓደኛ ጎን ተቀምጦ «አርግዛ ባልሆነ» ማለት ነው። በዝግታ እንዳታብድ «አለሁልሽ» ማለት ነው። ሐኪሟ ከጠበቅነው በላይ ወጣት ነበረች፤ ትሁት ብትሆንም ተመሳሳይ መረጃን ከመደጋገም የመጣ የሚመስል መታከት ይታይባት ነበር። ሩት አብሬያት እንድሆን እንደምትፈልግ በአጽንኦት ካስረዳቻትና ከተቀመጥን በኋላ፣ መኖርና መማር ሁሉንም ነገር አቃሎ እንዲያይ ባደረገው ሰው ስሜት ውስጥ ሆና ገለልተኝነት በተሞላበት ድምፅ ተከታታይ ጥያቄዎችን ጠየቀቻት፦ • የወር አበባሽ ስንት ቀን ዘገየ? • ከዚህ በፊት የወር አበባሽ አመጣጡ የተስተካከለ ነው? • ሕመም ይሰማሻል? የቱ ጋር? • ደም መፍሰስ አለ? • ለመጨረሻ ጊዜ ያለ መከላከያ የወሲብ ግንኙነት ያደረግሽው መቼ ነበር? • ከዚህ ቀደም እርግዝና ተከሰቶብሽ ያውቃል? ሩት ፍርድ ቤት መሃላ ፈጽሞ ቃል እንደሚሰጥ ምስክር በታማኝነት መለሰች። ሐኪሟ የአልትራሳውንድ ምርመራ ካደረገችላት በኋላ ወደ ቦታዋ ተመልሳ የደም ምርመራ እያዘዘች፦ «እርግዝና ያለ አይመስልም» አለች። ሩት ወደ ቀደመ ቦታዋ ሳትቀመጥ በቁሟ፦ «'አይምስልም' ማለት ምን ማለት ነው ዶክተር?» አለች። «እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ከምርመራው በኋላ ቢሆንም…» «ቢሆንም ምን…?» «ግዴለም፣ ውጤቱ ይምጣና ያኔ እንነጋገራለን… ይሄን ላብራቶሪ ይዛችሁ ሂዱና—» ሐኪሟ በትህትና ፈገግ አለችና መረጃ አቀብላን ስትጨርስ ማውራት አቆመች። እኔ ተነስቼ የሩትን እጅ ይዤ ለመውጣት ስሰናዳ ግን ያልተፈታውን የሩት ፊት ስታይ ሃዘኔታ ቢጤ ተሰማት መሰለኝ፦ «ክፉኛ መጨነቅም የወር አበባን ሊያዘገይ ይችላል» አለች። «የወር አበባን ሊያዘገዩ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የሆርሞን መዛባትም ሊሆን ይችላል። የሴት ሰውነት ኮምፕሊኬትድ ነው…» ብላ ጨመረች። «በሠሩት ሥራ መሸማቀቅስ የወር አበባን ሊያዘገይ ይችላል?» ስትል ሩት ጠየቀች። እኔም ሐኪሟም ደንገጥ አልን። አጣድፌ ይዣት ወጣሁ። ሐኪሟ በስተመጨረሻ ያለቻቸው ነገሮች ውጤቷ እስኪደርስ አበረታቷት። የደም ምርመራው ውጤትም ኔጋቲቭ ሆኖ ተገኘ፤ ሩት ግን እፎይ ከማለት ይልቅ ተናደደች። «ተይው፣ ድሮም አውቄው ነበር» አለችኝ ቤቷ ደርሰን ከመግባታችን። «ምኑን ነው አውቀሽ የነበረው?» «ገላዬ ነው እየቀጣኝ ያለው… የገዛ ሰውነቴ!» «ማለት?» «ያንን ሁሉ ላደረገኝ ከንቱ ሰው ዳግመኛ አሳልፌ ስለሰጠሁት አዝኖብኝ ነዋ… ድጋሚ ስላረከስኩት…» ሁኔታዋ ስላስፈራኝ እሷ ቤት አደርኩ። ----- ይሄ ሁሉ ሲሆን የወር አበባዋ ከተጠበቀችው በሁለት ሳምንት ዘግይታ ነበር። ናቲ ወደ ሩት ታሪክ የተመለሰውም ይሄኔ ነው። ለካስ ሩት ስለተፈጠረው ነገር ነግራው ነበር። ለምን እንደዚህ እንዳደረገች አላውቅም። ምናልባት እውነትም ፅንስ ይዛ ከሆነ አባት ነውና የማወቅ መብት ስላለው ይሆናል። ምናልባት «ሁለታችንም በሠራነው ሥራ እሱ ተደስቶ ሲያበቃ፣ እኔ ለብቻዬ አበሳዬን የማየው ለምንድነው? ነግሬው እሱም ይጨነቅ» ብላም ይሆናል። «ምን አለሽ?» ስል ጠየቅኳት። አንድ እጇን ዓይኖቿ ላይ ጭና ሶፋዬ ላይ ተኝታለች። «ፔን ኪለር የማይበግረው ራስ ምታት አሰቃየኝ» ስትል ሳምንት አለፋት። «'ማንኛውም ነገር ቢሆን አብረን እንወጣዋለን' አለኝ።» «ተዪ እንጂ… ይሄማ ጥሩ ነው… እየበሰለ ነው ማለት ነው…» «ባክሽ ፂ ደግሞ! እያወቅሽው እንደማታውቂ አትሁኚ! ናቲ ነው የሚበስለው? ጥሬ ሆኖ የበሰበሰ…» «ተዪ… ሰው መቼም እያደረ ይቀየራል።» «እሱን ተዪው ይልቅ ግን ባዶ እጁን አለመምጣቱ ገረመኝ።» «ምን ይዞልሽ መጣ?» «ሁለት ኪሎ ሙዝ! ሰላም ሳይሆን ፖታሺየም የሚያስፈልገኝ ይመስል!» ሳቅኩኝ። «ደግሞ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?» ሩት ቀጠለች፦ «'እርጉዝ ከሆንሽ አገባሻለሁ።'» ጋደም ካልኩበት ቀና ብዬ ተቀመጥኩ። «እውነት እንደዚያ አለሽ?» «አዎ።» «እናስ?» «እናስ ምን…» «ምን ተሰማሽ?» «ሊያስመልሰኝ ነበር።» ፈገግ አልኩ። «ቋቅ ነው ያለኝ። እሱ ባለው ነገር ይሁን የእውነት እርጉዝ ስለሆንኩ እንጃ ግን አቅለሸለሸኝ…» «እና ምን አልሽው አንቺ?» «ምን እለዋለሁ… 'እውነት ግን የሚያስብ አንጎል አለህ?' አልኩት! ያን ሁሉ ነገር አድርጎኝ ገና ለገና ተሳስቼ ስላረገዝኩ ሃጢያቱ ሁሉ በልጅ የሚሰረይለት ነው የሚመስለው…?» «ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እየሞከረ መሰለኝ ሩትዬ…» «እዚያው ባለበት ያድርገው… ሆ! ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ጊዜማ ረፈደ፤ ድሮ ነበር ትክክል መሆን…» ሩት በንዴት ስትንጨረጨር የችግሩን እውነተኛ ምንነት ያየሁት በዚች ቅጽበት ነበር። ጓደኛዬ በሠራችው ስህተት እፍረትና መሸማቀቅ የተሰማት «አርግዣለሁ» ብላ ስላሰበች ብቻ አልነበረም። ሩት አርግዞ መውለድን፣ ወልዶ ማሳደግን በብቸኝነት ልትወጣው የሚያስችል አቋም ያላት ሰው ናት። «ሳታገባ ወለደች» የሚሉ ሃሜተኛ ምላሶች ሰብረው የሚጥሏት ልፍስፍስ ሴት አይደለችም። ልትቋቋመው ያልቻለችውና እንዲህ ለሳምንታት ያቃወሳት ጉዳይ ማርገዟ ሳይሆን ከናቲ ማርገዟና በዚህም ሰበብ ከእሱ ጋር ለዘለዓለም በልጅ ገመድ መታሰሯ ነበር። «እና ደግሞ ቀኑን ሙሉ ቴክስት ይልክልኛል» አለች ትንሽ ቆይታ። «ምን ዓይነት ቴክስት?» «'በላሽ?' 'እረፍት ለማድረግ ሞክሪ።' 'ከፈለግሽኝ አለሁ።' 'ቡና እንዳትጠጪ።' 'ከባድ ነገር አትሸከሚ።'» ፊቷን አኮሰተች። «ከተሸከምኩት በላይ የሚከብድ ነገር እንዳለ 'ከባድ ነገር አትሸከሚ' ይለኛል… ወገኛ! ደግሞ ገስ ዋት…?» «ዋት?» አልኩ። «የሚቀጥለውን ቀጠሮዬን 'አብሬሽ ልምጣ' አላለም?» «እንዲመጣ ትፈልጊያለሽ?» «ፂ ደግሞ! መንታ ፍየሎች አምጬ ብወልድ ይሻለኛል!» ከት ብዬ ሳቅኩ። እየሳቀች ትራስ ወረወረችብኝ። ሳቋ ናፍቆኝ ነበር… (ክፍል ሦስት ነገ ይቀጥላል) 🌱🌱🌱

  • 28 июл.2 9184810

    ሩት፣ ናቲ እና የወር አበባ (ክፍል ሁለት) «ኮንዶምም አልተጠቀማችሁም?» ስል ጠየቅኳት። «ኮንዶም ብንጠቀም እዚህ አዘቅት ውስጥ እገባ ነበር?» በሚል አስተያየት ገረመመችኝ። «አይ፣ እንደው በመሃል ሌላ ነገር ተከስቶ እንዳይሆን ብዬ ነው እንጂ እሱማ ገብቶኛል…» አልኳት። «አልተጠቀምንም!» ረገጥ አድርጋ ተናገረች። የጓጓሁለት ረጅምና ልብ አንጠልጣይ ድራማ «ተጠቀማችኋል?» በሚል ጥያቄ እና «አልተጠቀምንም» በሚል አጭር መልስ በአጭሩ ተቀጨ። ወደ ሳሎን ተመለስን። ሻዩን ቀዳች። ሰፈሯ ካለው ስመጥር ዳቦና ኬክ ቤት የገዛችውንና አብዝቼ የምወደውን ቸኮሌት ንክር ቦምቦሊኖ አቀረበችልኝ። ቦምቦሊኖው እጅ መንሻ እንደሆነ ተሰማኝ። «ከዚያ የማትወጂውና እንደማይመጥነኝ ደጋግመሽ የነገርሽኝ ከንቱ የቀድሞ ፍቅረኛዬ ጋር በንዝህላልነት ተኝቼ ሳላረግዝ ስላልቀረሁ ይቅር በይኝ፤ እነሆ የምትወጂውን ቦምቦሊኖ ብዪና ቁጣውን ትተሽ 'አለሁልሽ' በዪኝ» እንደማለት። ሲኒያችንን ይዘን ተቀመጥን፤ ግን ሁለታችንም ሻያችንን አንዴም ፉት አላልንም። «በዪ እንግዲህ፣ እንዲህ ካስጨነቀሽ ቴስቱን ውሰጂና ቁርጡን እንወቅ» አልኳት ቆየት ብዬ። «አይ…» አለች። «አይ?» «አሁን ደግሞ ማድረጉን ፈራሁ።» «ምን ማለትሽ ነው? ቴስት ማድረግ ካልፈለግሽ ለምንድነው እንደዚያ አዋክበሽ 'ገዝተሽ ነይ' ያልሽኝ?» «የሆነ ስቱፒድ ሃሳብ መጥቶልኝ ነው።» «ምን ዓይነት ስቱፒድ ሃሳብ?» «ቴስቱን ወስጄ እርጉዝ መሆኔን እስካላወቅኩ ድረስ አሁንም ነፃ ሴት ነኝ የሚል… ካላወቅኩ እርጉዝ አይደለሁም ዓይነት ነገር…» ሳይንስ ከዚህ ሃሳቧ ጋር እንደሚቃረን ነገርኳት። «አንቺ ደግሞ ያልቸገረሽን… ለሳይንሱ ካንቺ እኔ አልቀርብም፤ ቢጨንቀኝ እንጂ…» አለች። መውጫ ቀዳዳ ያሳጣት ጭንቀቷ አጃጃላት እንጂ እውነቷን ነው፣ ለሳይንሱ እሷ ትቀርባለች። አባብዬና አሳምኛት በመጨረሻ ምርመራውን ለማድረግ ወደ መታጠቢያ ቤቷ ስትገባ ሰዓቱ ወደ እኩለ ሌሊት ተጠግቶ ነበር። ውጤቱ «አዎ አርግዘሻል» ከሆነ ንዴታችንን ለማብረድ ወይን ጠጅ እየጠጣሁና መፍትሔ ሳፈላለግ አነጋለሁ። «አይ» ከሆነ ደግሞ ደስታዋን ለመጋራትና ናቲን በምላሳችን ለመቦጫጨቅ አብሬያት ጽዋ አነሳለሁ። ምንም ተፈጠረ ምን እዚሁ እንደማድር አውቃለሁና ሶፋው ላይ ተመቻችቼ ተቀመጥኩ። እየተቁነጠነጥኩ ሶፋው ላይ በተቀመጥኩበት፣ ከመታጠቢያ ቤት ቧንቧ ከፍታ ውሃ ስታፈስ እና ከዋናው መንገድ ሕንፃው ላይ እየነጠረ የሚመጣውን የመኪናዎች ጥሩምባ አዳምጣለሁ። ሶፋዎቹ መሃል ተንሰራፍቶ የሚገኘው አራት ማዕዘኑ የእንጨት ጠረጴዛዋ ላይ ለውዝ የያዘ ሚጢጢ ጎድጓዳ ሳህን፣ «ምጥቀት በቅኔ አክናፍ» የሚል ርዕስ ያለው ግማሽ የተነበበና በአፍጢሙ የተደፋ ረጅምና ወፍራም መጽሐፍ፣ አነስተኛ የጥፍር ቀለም ማስለቀቂያ የያዘ ሮዝ የፕላስቲክ ጠርሙስ፣ ተጨምድደው የተጣሉ ቁርጥራጭ ሶፍቶች፣ ሻይ የጠጣንባቸው ሲኒዎችና አንዴ ገምጬ የተውኩትን ዶናት የያዘ ዝርግ ሰሃን አለ። ሁሉም ተራና የመደበኛ ሕይወት አጃቢ ነገሮች ሆኑብኝ። በዚያችው ቅጽበት በሦስት ወይም አራት እርምጃ ርቀት በሚገኘው መታጠቢያ ቤት ውስጥ ሁሉንም ነገር ድብልቅልቁን ሊያወጣ የሚችል ክስተት እየተከናወነ ስለመሆኑ የማያሳብቁ ተራ ኮተቶች… ሩት ነጩን የፕላስቲክ ዘንግ ጫፍ ይዛ ወደ ሳሎን ስትወጣ፣ የሞት ፍርዷ እስኪፈጸም በመጨረሻ ሰዓቷ ላይ የምትጠባበቅ ፍርደኛ ትመስል ነበር። «ሦስት ደቂቃ ጠብቁ ይላል» አለችኝ ሶፋው ላይ ቁጭ እያለች። «እንግዲያው እንጠብቅ» አልኩ። ጠረጴዛው ላይ አስቀምጣው ካሁን አሁን ገነፈለ ተብሎ እንደሚጠበቅ ድስት ሙሉ ወተት አፈጠጥንበት። «ውይ ሴት መሆን ግን ሲያስጠላ!» አለች በመሃል። «ሴት መሆን ምኑ ነው የሚያስጠላው? በትንሽ ነገር ትልቅ ድምዳሜ ላይማ አትድረሺ» መለስኩላት። «እንግዲያው ባዮሎጂ… ባዮሎጂ ነው የሚያስጠላው፤ በተለይ የሴት ባዮሎጂ!» «እሱ ያስኬዳል። ግን ለምን?» «ሁሉ ነገር ዳገት የሚሆንብን ለምንድነው? ለምንድነው እኛም እንደ ወንዶች በገላችን እንዳሻን አዘንበትንና ተደስተንበት 'ይሄ ይመጣል' ብለን ሳንሳቀቅ መኖር የማንችለው? ኢት ኢዝ ኖት ፌር…» «ታዲያ 'ይሄ ይመጣል' የሚለውን ሰቀቀን ለመቀነስማ መፍትሔዎች ነበሩ አይደል…?» አልኳት፣ ዞር ብዬ እያየኋት። በስጨት ብላ፦ «ፂ ደግሞ… ምንም አልፈርድብሽም አላልሽም ነበር?» ስትል ዘንጉ አዲስ መልክ አወጣ። አንድ መስመር ብቻ አሳየ። አላረገዘችም። ---- ሩት ረጅም የእፎይታ ትንፋሽ ወስዳ ሶፋው ላይ ተደገፈችና ዓይኖቿን ጨፈነች። «ተመስገን ተገላገልሽ» ብዬ ፈታ ከማለቴ ግን ፍንጥር ብላ ተነስታ፦ «ግን ፂ… እውነተኛውን ውጤት ለማወቅ ገና ቢሆንስ?» አለች። «ፔሬዴ ስምንት ቀን ሆኗታል አላልሽም?» «ቅድም ብዙ ሳነብ ነበር።» «ወይ ይሄ ንባብ… ሌላውን ተይው ግን ለዚህ ስትዪ ማንበብ ማቆም አለብሽ።» እንድትስቅና ዘና እንድትል ነበር እንዲህ ማለቴ። እሷ ግን ፊቷን አኮማትራ፦ «እንዴት አላነብም? ይሄ ዋይፋይ ካልተቆረጠማ ማበዴ ነው… እንቅልፍ የለኝም እኮ» አለችኝ። የመጀመሪያው ሳምንት እንዲህ አለፈ። ምርመራው ሁሉ «አላረገዝሽም» ይላል፤ የወር አበባዋ ግን የውሃ ሽታ ሆነች። ሰላም አጣች። 👇👇👇👇

  • 27 июл.3 3617920

    ሩት፣ ናቲ እና የወር አበባ ------- ጓደኛዬ ሩት ከማትፈልገው ወንድ ያረገዘች መስሏት ተሸብራለች። የተፈጠረውን ስታስረዳኝ የተጠቀመችው አገላለጽ ይሄ ነበር፦ «ሳላረግዝ አልቀርም» አላለችም። «የወር አበባዬ ዘገየ» አላለችም። «ትልቅ ስህተት ሠራሁ መሰለኝ» እንኳን አላለችም።   አንድ ረቡዕ ከሰዓት በቢሮ ሥራ እየተዋከብኩ ደወለችልኝና፦ «በናትሽ ከማይሆን ሰው ቀብ ሳላደርግ አልቀርም..ተረባብሻለሁ» አለችኝ።   እንዲህ ስትለኝ አለቃዬን ጨምሮ ከሰባት ሰዎች ጋር የምጋራው፣ ምንም ግድግዳ በሌለበት ልቅ ቢሮ ውስጥ ስለነበርኩ ለወሬዋ የሚመጥን ምላሽ ልሰጣት አልቻልኩም።    ዙሪያ ገባዬን ቃኘት አደረግኩና በሹክሹክታ የት እንዳለች ጠየቅኳት።   «ስራ መስራት ስላቃተኝ አመመኝ ብዬ ቤት ነኝ» አለችኝና ሁኔታዬ ስለገባት፦ «ከሥራ ስትወጪ ቀጥታ ወደ እኔ ነይ። Pregnancy Test ከፋርማሲ ይዘሽ… አንድ አይደለም፣ ሁለት ሦስት…» ብላ ጨመረች። «ሌላስ?» ስላት፣ «ሌላ ደግሞ ለመፍረድ እንዳትቸኩዪ… በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ምክርም ሆነ አስተያየት እንዳትሰጪኝ» አለች። «ለምን ሲባል ነው አስተያየት የማልሰጥሽ?» «ምክንያቱም የምትይኝን ሁሉ አስቀድሜ ስለማውቀው… አሁን የሚያስፈልገኝ ይሄን ከባድ ጊዜ አብሮኝ የሚሆን ጓደኛ ብቻ ነው። ካንቺ በቀር ሌላ ሰው የለኝም፤ ፕሊስ አትምከሪኝ፣ አትፍረጂብኝ…» «ኦኬ… አሁን ማውራት አልችልም፤ ስደርስ እንነጋገራለን» አልኳት ነገሩ ሳይዋጥልኝ። --   ከሥራ እንደወጣሁ መገናኛ አካባቢ ካለ መድኃኒት ቤት ጎራ ብዬ ሁለት የቤት ውስጥ የእርግዝና መመርመሪያዎችን ገዛሁ። ሁለቱም ማሸጊያዎች ላይ ነፍሰ ጡር በመሆናቸው የተደሰቱ የሚመስሉ ሴቶች ምስሎች ነበሩባቸው። በደስታ የሚያበራ ፊታቸው ከሩት ሁኔታ ጋር አልሄድ ብሎኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ ሳያስቡት አርግዘው፣ ካልፈለጉት ጸንሰው የፈሩ ወይም የደነገጡ ሴቶች ምስል ያለበት ይኖር ይሆን?   ሩት የምትኖረው ፍየል ቤት አካባቢ ባለ አንድ መኝታ ቤት አፓርትመንት ውስጥ፣ አራተኛ ፎቅ ላይ ነበር። የሕንፃው ሊፍት አንድም ቀን ሲሠራ አይቼው አላውቅም፤  የሚገባና የሚወጣውን ሰው ሁሉ በጥርጣሬ የሚመለከት ጎልማሳ ዘበኛ አለው። ገና ስገባ ገላመጠኝ፡፡ ችላ ብዬው ደረጃዬን ጀመርኩ፡፡   እያለከለክኩ  ሩት ደጃፍ ላይ ደርሼ በሩን ስትከፍትልኝ፣ ሰውነቷን የዋጠ ሰፊና ረጅም ግራጫ ቲሸርት ለብሳ አገኘኋት። የቀይ ዳማ ፊቷ ከዚህ ቀደም አይቼው የማላውቀው ድካምና ጭንቀት ተጭኖታል።   ገና ከመቀመጤ፦ «እ… ሁለት ነው የገዛሽው?» አለችኝ። «አዎ።» «ኦኬ… ጨርሼ ከማበዴ በፊት ቢያንስ ሁለቴ ውጤቱን አይተን እናረጋግጥ ብዬ ነው።» «ቆይ ግን… ከዛ በፊት… ለመሆኑ ፔሬድሽ ስንት ቀን ነው የዘገየብሽ?» ስል ጠየቅኳት። «ስምንት ቀን» በቁሟ ቁልቁል እያየችኝ መለሰች። «ሳምንት? ይሄ ሁሉ ግርግር ለሳምንት? አንቺ ደግሞ… ሳምንት እኮ ረጅም አይደለም፤ ያን ያህል የሚያስደነግጥ አይደለም። ዝም ብለሽ ነው የተጨነቅሽው።» «ወይ ፂ…! ለእኔ በጣም ረጅም ነው! ታውቂያለሽ… የእኔ ከሃያ ስምንት ቀን ግማሽ ሰዓት እንኳን አታሳልፍም። አንድም ቀን ዝንፍ ብላ አታውቅም… ህእ! በጤናዬማ አይደለም… በዛ ላይ…»     ሁኔታዋን ስመለከት ለወትሮው ሩት ቀላሉን በማክበድና ቀጥታውን በማጠማዘዝ የምትታማ ሰው ስላልሆነች፣ ጭንቀቷ ከልብ የመነጨና መሠረት ያለው እንደሆነ ገባኝ።   የቀድሞ ፍቅረኛዋ ስም (እንደ አብዛኞቹ መርዝ ልውስ የቀድሞ ፍቅረኞች) ናቲ ይባላል። አንድ አራቴ በአካል፣ ሁለት ሦስቴ ደግሞ በስልክ አግኝቼዋለሁ።   በሰፊው ያገኘሁት ባለፈው ዓመት ለሩት ልደት ባዘጋጀሁት የእራት ግብዣ ላይ ነበር። ሰው ሊበላና ሊጠጣ ተሰብስቦ፣ ማንም ሳይጠይቀው ሃያ ደቂቃ ሙሉ ስለ ክሪፕቶከረንሲ ካላስረዳኋችሁ ብሎ ሲያሰለቸን አመሸ።   ከዚያ በኋላ አራት ኪሎ አዶርሲ ካፌ ከሩት ጋር ተቀምጠው አግኝቻቸው፣ እኔ ደግሞ ሌላ ሰው ቀጥሬ ስላረፈደብኝ አብሬያቸው ተቀመጥኩ።   በሥራ የጓጎለ ገላዬን ላፍታታ፣ የዛለ አእምሮዬን ላዝናና በሄድኩበት ካፌ አግቶኝ እንዴት አድርጎ እንዳስጀመረው ባልገባኝ ወሬ፦ «ጋብቻ ማለት የዘመናዊ ወንዶችንና ሴቶችን ፍላጎት የማያገናዝብ ያረጀ መዋቅር ነው» ብሎ እስኪያዛጋኝ ደሰኮረብኝ።   የቀጠርኩት ሰው መጥቶና ኡፎይ ብዬ ስሰናበታቸው ለጠጣሁት አይስ ላቴ እንድከፍል ጠየቀኝ። እኔም ሩትም ክው ስንል ሳቀና፦  «ግዴለም የዛሬውን እኔ እከፍልልሻለሁ፤ ግን በየቲክቶኩ እኩል ነን የምትሉትስ… ? እኩል ከሆናችሁ ቢል ሲመጣ ሽሽቱ ምንድን ነው?» ብሎ እየሳቀ የበለጠ አሳቀቀኝ።   ያን ዕለት አንጀቴ እርር ብሎ «ካልከፈልኩ እሞታለሁ» ብልም፣ በሁኔታው የተሸማቀቀችው ጓደኛዬ ልመና አሳዝኖኝ እየከፋኝ ሄድኩ።   ሩትና ናቲ አብረው በሆኑ በሦስት ወራቸው፣ ፍቅር ሠርተውና እርቃናቸውን ተቃቅፈው በተኙበት ፣ በዚያው ሰሞን አንድ ቢሮዋ ሲመላለስ ከወደዳት ልጅ ጋር «መሳሳቱን» ቀለል አድርጎ ነገራት።   ከእቅፉም ከአልጋውም ተስፈንጥራ ስትወጣና በንዴት ስትጨስ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ አይቷት፦ «መዋሸት ነበረብኝ? ቢያንስ ስህተቴን አውቄ እውነቱን መናገሬን እንኳን አታደንቂልኝም?» ብሎ እሷኑ ከሰሳት።   ስለዚህ ሩት «ከማይሆን ወንድ ሳላረግዝ አልቀርም» ስትል ከማን ማለቷ እንደሆነ ወዲያውኑ ገብቶኛል።   --- «ከናቲ ጋር እንደገና…?» ብዬ ጠየቅኳት። መልስ ሳትሰጠኝ ወደ ኩሽና ሄዳ የኤሌክትሪክ የሻይ ማፍያው ላይ ውሃ መሙላት ጀመረች። «ስሚ እንጂ… ከናቲ ጋር ተኛሽ?» ተከትልኳትና ጠየቅኳት። «እንደዚያ አትበዪው» «እንዴት ልበለው ታዲያ?»   ትከሻዋን ሰበቅ አድርጋ፦ «ለብዙ ዓመታት የምጸጸትበት አሳዛኝ ስህተት ሠራሁ በዪው» አለችኝ።   ሻዩን ጥዳ ሁለት ባለ ጆሮ የሻይ ሲኒዎችን ስታወጣ፣ ኩሽናው መግቢያ ላይ ባለው ባለጌ ወንበር መሰል ወንበሯ ላይ ሳይመቸኝ ተቀመጥኩ።     --- ነገሩ የተከሰተው ከሦስት ሳምንት በፊት እንደነበር ነገረችኝ። በዚያች ልጅ ምክንያት ተለያይተው ወር ካለፈ በኋላ፣ ከመሸ ወደ አፓርትመንቷ መጥቶ «በስርዓቱ እንድንነጋገር እፈልጋለሁ» አላት።   «ብታዪው ጭምትርትር ብሎ ነበር… አስኮናኝ… አሳዘነኝ…» አለችኝ፡፡   አብዛኛው ወንድን አስመልክቶ በሴቶች የሚፈጸም ከባድ ስህተት የሚጀምረው «አሳዘነኝ» በሚል ቀላል ቃል ነው።   «ልግባና እንነጋገር» አላት። ገባና ተነጋገሩ። እሷ እንዳለችኝ በጣም እየተቅለሰለሰ ይቅርታ ጠየቃት።  ብዙ ስህተቶችን እንደሠራ አመነ። «በየቦታው የምትገጥመውን ሴት ሁሉ ከእሷ ጋር እያነጻጸረ፣ እሷ ጫፍ ላይ መድረስ ሲያቅታት» በጸጸት እንደተንገበገበ ተናዘዘ።   ምን ያህል እንዳስቀየማት ቆይቶ እንደገባው ነገራት። ‹‹ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ነገር እንዴት ባንዴ ተገለጠልህ?›› ስትለው፣ አንዲት በጣም ቆንጅዬ ልጅ በእጮኛዋ ተክዳ ስታለቅስ የሚያሳይ ፖድካስት ካየ በኋላ እንደሆነ አጫወታት። «ደግሞ እኮ ስታምር… 'ሰው ከሰው እንዲህ አምሮ አይወጣም' አለ ቴዲ አፍሮ… በእሷ ላይ የሚደርብ ወንድ ግን ምን ገገማ ነው በናትሽ!» ብሎ ጨመረላት።   ከዚያም ዝናብ ጣለ። ዝናቡ በጣም ኃይለኛ ስለነበር «ውጣና ሂድ» ማለት ነውር መስሎ ተሰማት። ዝናቡ ጋብ እስኪል ድረስ እንዲቆይ ፈቀደችለት። እስከዚያ ብላ ሻይ አፈላች።  «ከቆየህ አይቀር» ብላ እራት አቀረበች።  «ወይ ይሄ ዝናብ እኝኝ አለ እኮ» ሲላት ወይን ቀዳች። ጠጡ። ወይኑና የተለማመዱና የተነፋፈቁ ገላዎቻቸው ተባብረው አልጋዋ ላይ ጣሏቸው።  ❤️❤️❤️❤️❤️❤️ (ክፍል ሁለት ነገ ይቀጥላል)

  • 26 июл.3 431341

    ‹‹….«ብታዪው ጭምትርትር ብሎ ነበር… አስኮናኝ… አሳዘነኝ…» አለችኝ፡፡ አብዛኛው ወንድን አስመልክቶ በሴቶች የሚፈጸም ከባድ ስህተት የሚጀምረው «አሳዘነኝ» በሚል ቀላል ቃል ነው። «ልግባና እንነጋገር» አላት። ገባና ተነጋገሩ። እሷ እንዳለችኝ በጣም እየተቅለሰለሰ ይቅርታ ጠየቃት። ብዙ ስህተቶችን እንደሠራ አመነ። «በየቦታው የምትገጥመውን ሴት ሁሉ ከእሷ ጋር እያነጻጸረ፣ እሷ ጫፍ ላይ መድረስ ሲያቅታት» በጸጸት እንደተንገበገበ ተናዘዘ። ምን ያህል እንዳስቀየማት ቆይቶ እንደገባው ነገራት። ‹‹ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ነገር እንዴት ባንዴ ተገለጠልህ?›› ስትለው፣ አንዲት በጣም ቆንጅዬ ልጅ በእጮኛዋ ተክዳ ስታለቅስ የሚያሳይ ፖድካስት ካየ በኋላ እንደሆነ አጫወታት። «ደግሞ እኮ ስታምር… 'ሰው ከሰው እንዲህ አምሮ አይወጣም' አለ ቴዲ አፍሮ… በእሷ ላይ የሚደርብ ወንድ ግን ምን ገገማ ነው በናትሽ!» ብሎ ጨመረላት። ከዚያም ዝናብ ጣለ። ዝናቡ በጣም ኃይለኛ ስለነበር «ውጣና ሂድ» ማለት ነውር መስሎ ተሰማት። ዝናቡ ጋብ እስኪል ድረስ እንዲቆይ ፈቀደችለት። እስከዚያ ብላ ሻይ አፈላች። «ከቆየህ አይቀር» ብላ እራት አቀረበች። «ወይ ይሄ ዝናብ እኝኝ አለ እኮ» ሲላት ወይን ቀዳች። ጠጡ።…›› 💕💕💕ክፍል አንድ ታሪክን ነገ ጠዋት ይጠብቁ፡፡💕💕💕💕

  • 24 июл.3 827552

    የተወደዳችሁ! እነሆ የቲክቶክን አብዮት ሰባት ዓመት አመንትቼና እጅግ ዘግይቼ በእንፉቅቅ ተቀላቅያለሁ፡፡ እዚህ የማልለቀውን ቪዲዮ እና ድምጽ ተኮር ይዘት ማየት ከፈለጋችሁ እዚያ ተከተሉኝ፡፡ የቲክቶክ መገኛዬ hiwot_emishaw ነው። https://vm.tiktok.com/ZSXGoRTAq/

  • 23 июл.4 47912012

    ሽንኩርትና ሹሩባ --- ከአሜሪካ ለጥቂት ሳምንታት ጉብኝት ወደ አዲሳባ የመጣችው ጓደኛዬ የቀጠርኳት ካፌ እጅግ አርፍዳ ስትመጣ ቦሆ ብሬድስ ተሰርታ ነበር።  ቦሆ ብሬድስ አሁን አሁን አዲስአባ ላይ ፋሽን የሆነና የተለመደውን የዊግ ቁጥርጥር ሹሩባን ከተዘናፋይ ዊግ ጋር አደባልቀው የሚሰሩት የሹሩባ አይነት ነው፡፡   ፈረንጅ ቅብ የሆነችውን ወዳጄን ያለ ጠባይዋ ያስረፈዳት ሰአታት የፈጀው ሹሩባዋ መሆኑን ቀድማ ስለነገረችኝ ብዙ አልተነጫነጭኩም፡፡   «ወደድሽው?» ስትል ጠየቀችኝ ስማኝ ከተቀመጠች በኋላም አይኔን ከእሱ ላይ መንቀል እንዳቃተኝ ስታይ። «አዎ… በጣም›› መለስኩ፡፡ «ያምርብኛል?» «በጣም በጣም ሄዶብሻል» «እሰይ! እኔም በጣም ነው የወደድኩት…አራት ሰአት መጎለቴ ቶታሊ ወርዝ ኢት አይደል?›› ‹‹አዎ…ብታረፍጂም ይገባዋል…›› ‹‹ ደሞ እኮ ክፍያውም አሪፍ ነው›› ‹‹ተይ ባክሽ?›› ‹‹እውነት…ስንት እንደከፈልኩ ታውቂያለሽ?» «እንጃ ግን ሲያዩት ውድ እንደሆነ ይናገራል »   ፈገግ አለች።   «የሚገርምሽ እኮ ውድ አለመሆኑ ነው… ኢትዮጵያን የምወዳት ለዚህ ነው፤ ይሄን ሁሉ ሰአት የፈጀ እንዲህ የሚያምር ሹሩባ በርካሽ ነው የተሰራሁት» «ተይንጂ… ስንት?» «ገምቺ» «ውይ ግምቱ እንኳን ይቅርብኝ…ኖርማል ቁጥርጥር ከተሰራሁ እንኳን ሁለት አመት አልፎኛል» «እኮ ቢሆንም ገምቺ» «ኤዲ ደሞ…አልገምትም አልኩሽ… ባለፈው ሳምንት የገዛሁት ሁለት ኪሎ ሽንኩርት ዛሬ ስንት እንደገባ እንኳን አላውቅም…ነገር ሁሉ በየቀኑ ነው ሰማይ የሚነካው…አንቺ እወዳታለሁ ያልሻት እኔ ደግሞ እንዳልጠላት እየታገልኩ ያለችው ኢትዮጵያ ይህቺ ናት…!»   ሳቀች።   «ዝም ብለሽ ገምቺ» ሰው እንዲህ ችክ ሲልብኝ አልወድም፡፡ ደሜ ይፈላል፡፡   ትእግስቴን አሰባሰብኩና ‹‹ኤዲ ትነግሪኝ እንደሆን ንገሪኝ…ካለዚያ ተይው…›› አልኳት፡፡ «የልጆቹን ቲፕ ጨምረሽ  ስምንት ሺህ ብር ብቻ ነው የከፍልኩት!»   ክው አልኩ፡፡   «ኤዲ ስምንት ሺ ለሹሩባ እኮ ርካሽ አይደለም» አልኳት ከድንጋጤዬ ሳላገግም፡፡ «ምን ሆነሻል? …በጣም ርካሽ ነው…» «አይደለም» «አንቺ እኮ አልገባሽም… ወደ ዶላር ስትቀይሪው እኮ ኢት ኢዝ አንደር ፊፍቲ ዳላርስ ። አሜሪካ ቢሆን እኮ በትንሹ ሶስት መቶ ዳላሬን ይቆነድዱኝ ነበር…ደግሞ ትረስት ሚ የዚህን ግማሽ አያምርም …!»   እኔም እሷም ከቆምንበት ስፍራ አንጻር እውነትን ይዘናል፡፡ መሸናነፍ የምንችልበት ክርክር ስላልሆነ ልገፋበት አልቻልኩም፡፡     ስለዚህ ፈገግ ብዬ አሜሪካኖ ቡናዬን ፉት አልኩና ጨዋታውን ቀየርኩ፡፡ --- ወደ ቤት እየተመለስኩ ከቀናት በፊት አረጋዊቷ ጎረቤቴ እትዬ ለታይ ሰፈር ያለው አትክልት ቤት  አግኝቼያቸው ያየሁት ትዝ አለኝ። መጀመሪያ ሁለት ኪሎ የሚሆን ሽንኩርት አንዱን ራስ እየጣሉ አንዱን እያነሱ ሲመርጡ ቆዩ፡፡ ከዚያ ልጁን ዋጋ ጠየቁ፡፡ ነገራቸው፡፡ እትዬ ለታይ ሊያስመዝኑ ያዘጋጁትን ፌስታል-መሰል-ማዳበሪያ ሙሉ ሽንኩርት መሬት ላይ አሳረፉና ግማሹን ወደ መደቡ መለሱ፡፡     ኤዲ ርካሽ ነው ብላ ስለተሰራችው ሹሩባ ሳስብ፣ እነዚያ ተመላሽ ሽንኩርቶች ለምን ትዝ እንዳሉኝ አላውቅም። ምናልባት እትዬ ለታይ በስምንት ሺህ ብር  ስንት ኪሎ ሽንኩርት መግዛት እንደሚችሉ እያሰላሰልኩ ይሆን? ወይስ ከዚያ የሚበልጡ ነገሮችን እያሰብኩ ? 🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱

  • 22 июл.4 057432

    ሽንኩርት እና ሹሩባ 📏📏📏 ነገ ይጠብቁ።

  • 22 июл.3 766655

    ሰሞኑን ከአራዳ ኤፍኤሟ ጎበዝና ወጣት ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ ሰይፉ ጋር በድርሰት ስራዎቼ ዙሪያ ቆንጆ ውይይት አድርገን ነበር።  ከረጅሙ ውይይታችን አልፎ አልፎ ቀንጨብ ቀንጨብ እያደረግኩ ባጋራችሁ ምን ይለኛል?

የሕይወት እምሻው አጫጭር ታሪኮች/ Hiwot Emishaw — tgindex